Sunday, 12 February 2017 00:00

አገባሽ ያለሽ ላያገባሽ ከባልሽ ሆድ አትባባሽ

Written by 
Rate this item
(13 votes)

አንዳንድ ተረት ተደጋግሞ ይነገራል፡፡ ነገር ግን ወይ ስለማይገባ፣ አሊያም ቸል ስለሚባል እንደገና መደገሙ ግዴታ ይሆናል፡፡ የዛሬውም
ከዓመታት በፊት ያልነው ነው፡፡ (አንድ የፈረንጅ ጸሐፊ “As no one listens we should say it again…” ይላል፡፡ የሚሰማ ስለሌለ እንደገና
መናገር አለብን፤ ማለቱ ነው።)
እኛም እንድገመው፤ አሻሽለን፡-
ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ገበሬ የእርሻ ስራውን አጠናቆ ወደ ቤቱ እየመጣ ነበር፡፡
ጦጢት ደግሞ እንደ ልማዷ ዛፉ ላይ ሆና ገበሬው ሲመጣ ታየዋለች፡፡ ገበሬው ከዘር ዝሪ እንደሚመጣ ታውቋታል፡፡ ወቅቱ የዘር መዝሪያ ጊዜ
መሆኑን ተገንዝባለች፡፡ ስለሆነም የዘራው ዘር እሷ የምትበላው ዓይነት ከሆነ፣ ሄዳ እየፈለፈለች እያወጣች ልትበላ ነውና መረጃ ፈልጋለች፡፡
ስለዚህ ገበሬውን ለማወጣጣት በትህትና ትጠይቀዋለች፡፡
“ገበሬ ሆይ! እርሻ ምን መሳይ ነው?”
ገበሬ፤
“ሁሉ አማን፣ ሁሉ ሰላም ነው!”
ጦጢት፤
“ዛሬ የዘር ጊዜ ነው አይደል?”
ገበሬ፤
“አዎ የዘር ጊዜ ነው፡፡ በየዓይነቱ ዘር ይዘራል”
ጦጢት፤
“ዘንድሮ ምን ተዘራ?”
ገበሬ፤
“ምን ያልተዘራ አለ፡፡ በቆሎ፣ ጤፍ፣ ገብስ፣ ስንዴ፣ ሽምብራ፣ ባቄላ፣ ቦሎቄ፣ … ምኑ ቅጡ? ሁሉም የየአቅሙን ይዘራል፡፡ መሬቱ፤ መሬት ነውና

ሁሉንም ይቀበላል”
ጦጢት፤
“እንደው ደፈርሺኝ አትበለኝና አንድ ጥያቄ እንድጠይቅህ ትፈቅድልኛለህ?”
ገበሬ፤
“እስካሁን የፈለግሺውን እንድትናገሪ ፈቅጄልሽ የለ?”
ጦጢት፤
“አይ ይሄኛው ወሳኝ ነው ብዬ ስለማምን ነው፡፡ ልጠይቅህ?”
ገበሬ፤
“ኧረ ጠይቂ፤ ምንም ችግር የለም”
ጦጢት፤
“አመሰግናለሁ፡፡ እንደው ዘንድሮ አንተ ምን ዘራህ?” አለችው
ገበሬ፤ ጦጢት ሄዳ እንደምትቦጠቡጠው ያውቃልና እሷ የማትፈለፍለውን እህል አስቦ መናገር አለበት፡፡ አሰላ አሰላና፤ በትህትና፡-
“ጦጢት ሆይ፤ እኔ ዘንድሮ የዘራሁት ተልባ ነው” አላት፡፡
(ጦጣ ለመፈርፈር በጣም የሚያስቸግራት ተልባ ነው)
ጦጢት፤
“በጣም ግሩም! በቃ ወርደን እናየዋለና! ወርደን እናየዋለን!” አለችው፡፡
*         *       *
ጦጢት የእኛ አገር ነገር የገባት ነው የምትመስለው፡፡ ከላይ የተነገረውን መሬት ወርዶ ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡
ዲሞክራሲ ሰፍኗል ተብለናል፡፡ መሬት ወርደን እናረጋግጥ! ፍትህ ሰፍኗል ተብለናል፡፡ መሬት ወርደን እናረጋግጥ! (Justice delayed Justice
denied የዘገየ ፍትህ እንደሌለ ይቆራል - ዕውነት ነው?)
የሕግ የበላይነት አለ ተብለናል፡፡ “ፍትህ የተዘጋጀ ዳቦ አይደለም” የሚለው አባባል ነው ተግባራዊ? ታች ወርደን እናረጋግጥ! ማንም የበላይ
የበታቹን እንዳሻው አይበድልም? እናጣራ!
“ዳሩ ዳኛ የለም ልተወው ግዴለም” እያልን አንዘልቀውም፡፡ ወርደን እንየው!
ትምህርት፤ በወላጅ፤ በመምህርና በተማሪ ሶስት - ማዕዘን (Triangular) ግንኙነት እያማረ ነው ተብለናል፡፡ እስቲ መሬት ወርደን እንየው፡፡
ጤና፤ በየጣቢያዎቹ ለህዝቡ በሚያመች ዘዴ ተሰልቶ ዝግጁ ሆኗል ተብለናል፡፡ መዳኒት አለ? የበቃ ህክምና አለ? ጤና ኬላ በቂ ነው? እስቲ
ጦጢት እንዳለችው፤ ይዋጥልን እንደሆን ወርደን እንየው! የመንገድ ሥራ ተሳክቶ ተጠናቋል፤ ተብለናል፡፡ ዘላቂ ናቸው አይደሉም? ወርደን
እናጣራ! አገራችን ሰላም ሆናለች፤ ተብለናል፡፡ ወደ ሰሜን፣ ወደ ምሥራቅ፣ ወደ ደቡብ ምዕራብ ወርደን እንታዘብ፡፡ መሬት የያዘውን አይለቅምና
ወርደን እንየው፡፡ በሀቅ እንዘግበው!
ሀብት፤ በፍትሐዊ መልክ ይከፋፈላል ተብለናል፡፡ እኩልነት ቤት - ደጁን ሞልቶታል ተብሏል፡፡ እስቲ ወርደን ኢወገናዊ መሬት መኖሩን አይተን
እንርካ! የትራፊክ አደጋ ቀንሷል እንባላለን፡፡ መሻሻል አለመሻሻሉን፣ ትራፊክ ሜዳው ላይ ወርደን እንየው! የመልካም አስተዳደር ችግር ነበር
ተብለናል፡፡ ዛሬስ? ወርደን ማየት ነው!
አገራችን የአሸባሪዎች ኮሪደር ናት ተብለናል፡፡ ዕውነት የሽብር ድልድይ ነን? ወርደን ማየት የአባት ነው! የአገራችን ፌደራሊዝም እና ክልላዊ
መስተዳድሮች አካሄድ የተቀናጀና የሰመረ ግንኙነት ያለው ነው ተብለናል፡፡ ወርደን እንየው! ባቄላ፣ በቆሎ ወይስ ተልባ? እናጣራ፡፡ እንናበባለን?
በፓርቲ አባላት መካከል ልባዊ መግባባት፣ ወቅታዊ መናበብ አለ? ተቃዋሚዎች ከአሉታዊ ፅንፍ ወጥተዋል ወይ? ወርደን እንየው!
መንግሥት በግል ሚዲያዎች ላይ ያለው ዕምነት ምን ይመስላል? ዛሬም “በሬ ወለደ ይላሉ” ነው? ዛሬም “የሌሎች አፍ ናቸው” ነው? ዛሬም
“ፀረ-መንግሥት” ናቸው ነው? ዛሬም መታሰራቸው ልክ ነው? ዛሬም የሚታኑና የማይታመኑ ሚዲያዎች አሉ? ወርደን እንያቸው!
በአገራችን ሙስና ጉዳይ የማንስማማበት ምክንያት ያለ አይመስልም፡፡ ይሰረቃል፡፡ ይዘረፋል፡፡ ችግሩ ግን የማይደፈሩ ሰራቂዎችና ዘራፊዎች አሉ
የሉም? ነው፡፡ ጥያቄው ግልፅ ነው!፡፡ ስለዚህ ወርደን እንየው!
ከሁሉም በላይ ደግሞ ከውጪ ያለውን አጋር ወይም ሐሳዊ ወዳጅ መንግስት የምናምነው ምን ያህል ነው? ሴትዮዋ ጓሮ ለሚጠብቃትና
እያስነጠሰ ምልክት ለሚሰጣት ውሽማዋ፣ የባሏን ቤት ውስጥ መኖር ለመንገር፣
“አንት የጓሮ ድመት፣ ምንም ብታነጥስ ዛሬ በዓል (ባል) ነውና፣ ቅጠልም አልበጥስ” እንዳለችው ያንን እየደጋገምን የምንጓዝበት ዲፕሎማሲ
ያስኬደናል ወይ?
ከገዛ ህዝባችን መግባባትና መስማማት እንጂ ከሌሎች በምናገኘው ገቢ (fund) ወይም ድጎማ መተማመን ብዙ አያራምደንም፡፡ የሚያዛልቀን
የህዝብ ሀብት ነው! መቼም ቢሆን ነባርም መፃኢም ህልውናችን የሚወሰነው በህዝባችን ፍቅር ነው!
“አገባሽ ያለ ላያገባሽ
ከባልሽ፣ ሆድ አትባባሽ”
የሚለውን ተረት ሳንታክት ማሰብ ለሀገር ልማትና ዕድገት መሰረት ይሆነናል! አንርሳው!

Read 5940 times