Monday, 30 January 2017 00:00

የምበላው ሳጣ ልጄ ጥርስ አወጣ

Written by 
Rate this item
(9 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን፣ አንድ በዓል ቀን፣ ባልና ሚስት አንድ እንግዳ ይመጣባቸዋል፡፡ የከበደ እንግዳ! ዶሮ ወጥ ተሰርቷል፡፡ በግ ታርዷል፡፡ ቤቱ በዓል በዓል ይሸታል፡፡ ስኒ ረከቦቱ ላይ ተደርድሯል፡፡ እጣኑ ቦለል ቦለል ይላል፡፡
እንግዳውና ቤተሰቡ ግብዣውን ለመብላት አኮብኩበዋል፡፡
ራቱ ተጀመረ፡፡ በመካከል “እ!እ!እ!” የሚል የትንሽ ልጅ የለቅሶ ድምፅ ይሰማል፡፡
እንግዳው፣
“ምንድን ነው ይሄ የሚሰማው ድምፅ?” ሲል ጠየቀ፡፡
አባት፤
“አይ፣ የእኛ ልጅ ነው ተወው” አለ፡፡
እንግዳውም፤
“እንዴት እተወዋለሁ? በዓመት በዓል እንዴት ከቤተሰቡ ይለያል? የት ነው ያለው አሳዩኝ” ብሎ ድርቅ አለ፡፡
እንግዳው፤
“እንዲያውም አልበላም” አለ፡፡
“ና ላሳይህ” ብሎ ወደ ጓዳ ወሰደው፡፡
ልጁ፤ ቆጡ ላይ ታስሯል፡፡
እንግዳው በጣም አዘነ፡፡
“ምን አድርጎ ነው እንዲህ ዓይነት ቅጣት የፈፀማችሁበት?”
አባት፤
“ምንም አላደረገም፣ ግን ከልምድ እንደምናውቀው፣ ከእንግዳ ጋር ገበታ ከቀረበ እጁ ባለጌ ነው!
ከእንግዳ ፊት ብድግ ያደርጋል፡፡ ብትቆጣውም አይሰማም” አለ፡፡
እንግዳው፣
“ኧረ በጣም ነውር ነው፡፡ ግዴለም፤ ይምጣ፣ ይምጣ፡፡ እናስተምረዋለን፤ ሥነ ስርዓት፡፡” አለና አግባባቸው፡፡
ልጁ ተፈቀደለትና ከእስር ተፈታ፡፡ ከቆጡ ወረደና ገበታ ቀረበ፡፡
የዶሮ ብልት በፈርጅ በፈርጁ ይቀርብ ጀመር፡፡
ልጁ ዕውነትም አደገኛ ኖሯል፡፡
እንግዳው ፊት የቀረበውን ሁለት የዶሮ እግር በተከታታይ እያነሳ ነጨ! ከዚያ የአባቱን የፈረሰኛ ብልት አነሳ! ይሄኔ ግራ የተጋባችው እናት በቁጣ፤
“ይሄን እንዲች ብለህ እንዳትነካ፤ ነግሬሃለሁ!” ብላ ለእንግዳው ሌላ ብልት ስታቀርብ፤ ልጁ ይሄ ሊመልሰው ነው? እጁን ሰደደ፡፡ ይሄኔ እንግዳው የልጁን እጅ ቀብ አድርጎ፣ ፈጥኖ አጠንክሮ ያዘና፤ ወደ ባለቤቶቹ ዞሮ፤ “እንግዲህ፣ ሸብ አድርጉልኝ ይሄን ልጅ!” አለ፡፡ ልጁም ከሶስት የዶሮ ብልት በኋላ፣ ሸብ ተደርጎ፣ ተመልሶ ቆጡ ላይ ሰፈረ!
*          *        *
ልማድ የልጅነት አባዜ አለው፤ አድጎ ተመንድጎም ራሳችን ላይ ፎቅ ሊሰራብን ይችላል። መላቀቅ ያለብን ብዙ ልማድ አለ! ይሄ ከባህላችን፣ ከማህበራዊ ኑሯችን፣ ከፖለቲካችንና ጋር በቅርብ የተሳሰረ ነው፡፡ ስነ ልቦናዊ ግንኙነቱም ከዚሁ የሚመነጭ ነው፡፡ ይሄን ወደ አገር ጉዳይ መንዝሮ ማየት ጉዳዩን በሚገባ መሰረት ያበጅለታል፡፡ እየተዘወተሩና እየተለመዱ የሚመጡ የአገራችን ጉዳዮች ውለው አድረው፣ ጎልበተው መታየታቸው አይቀሬ ነው፡፡ ትናንሽ ዕቅዶች ወደ ትላልቅ ፈቅዶች የሚያድጉት ትናንሾቹ በአግባቡ ሲፈፀሙ ነው፡፡ ለዚያ የጊዜ ስሌት፣ የዝርዝር አያያዝና የቁጥጥርና ግምገማ ሥርዓት በአግባቡ ማዘጋጀት ተገቢ ነው፡፡ ይህን ፈፃሚውና አስፈፃሚው አካል፣ የራሱ አቅልና ብስለት ያለው ሊሆን ይገባል፡፡ እዚህ ላይ ነው እንግዲህ የራስ አመለካከት ከአገር አመለካከት ጋር ይራራቅና ጣጣ የሚያመጣው፡፡ እያንዳንዱን ሰው ቀርፆ፣ ሰው ለማድረግ አዳጋች ነው፡፡ ይህን የሚሠሩ ተቋማት እጅግ ጥቂት ናቸው፡፡ ለዚህ ብሩህ አስተዋፅኦ የሚያደርጉ የሲቪል ማህበራት ቁጥርም፣ አቅምም በጣም ውስን ነው፡፡ ይህ የሆነው ፋይዳቸውን ከልቡ ያመነበት ወገን ባለመኖሩ ነው፡፡ ጊዜም ባይኖር ጊዜ ወስዶ፣ ለጥያቄው መልስ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ አማካዩ መንገድ ይሄው ነው፡፡ ከገዢው ፓርቲና ከተቃዋሚው ድርድር ባሻገር የህዝብን አስተሳሰብ የሚያሰባስብ፣ ወደ ተግባር እንዲያመራም የሚያግዝ ኃይል ያስፈልጋል፡፡
‹‹ከእናንተ ሌላ እኛም አለንኮ›› የሚል የህብረተሰብን ክፍል ማን ይታደገው ማለት አለብን፡፡ በጥቁርና በነጭ መካከል ያለውን ግራጫ መስመር፣ ስፋቱን ስለማንገነዘብ ጠቀሜታውም የዚያኑ ያህል ይሳሳብናል፡፡ ‹‹መካር የሌለው ንጉሥ፣ ለአንድ ዓመት አይነግሥ›› የሚለው አባባል፣ አበው ያለ ነገር አላሉትም፡፡ ለአመራሩ፣ ለገዢው ክፍል፣አማካሪ ያስፈልገዋል፡፡ በእርግጥ አማካሪ ሲባል በዕውቀት የረቀቀ፤ በልምድ የበለፀገና  ጊዜ ያስተማረው ሊሆን ይገባል! መንግሥት ሲቸኩል የሚያለዝበውም፣ ሲጠጥር የሚያልመው፤ ግትር ሲል የሚያላላው፣ አይዞህ ባይም፣ ገሳጭም፣ ነው የሚያሻው፡፡ የጥንት የጠዋቱ ገጣሚ ገሞራው፤ እንዳለው፡- ‹‹…ነገሩ አልሆን ብሎ፣ ሁኔታው ሲጠጥር
 ጠጣሩ እንዲላላ፣ የላላውን ወጥር…›› የሚሉ በሳሎች ያስፈልጋሉ፡፡ በመደራደር ብዙ መንገድ መሄድ ይቻላል፡፡ ነገር ግን አንድ ዕውነት መረሳት የለበትም፡፡ ማናቸውም ወገን ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ ገና ሶስተኛም ወገን ተጨምሮ አይበቃም ብሎ ማሰብ ብልህነት ነው። ጉዳዩን መሠረታዊ የሚያደርገው የሀገራችን ችግር ስፋት ነው፡፡ የፍትሕ መጓደል፣ የዲሞክራሲ አለመብሰል፣ የሀብት አለመደላደል፣ የተቋማት ሥርዓት አለመሻሻል፣ መልካም አስተዳደር አለመታደል፣ ያልተመለሱት ጥያቄዎች መልስ አጥተው መንሳፈፍ፣ ወዘተ ምኑ ቅጡ! ለዚህ ነው አገር ሙሉ ድርጅት ቢፈጠር እንኳ የአገር ቋት አይሞላም የምንለው!
እነዚህ ሁሉ በቅጡ ቢሰባሰቡና ኢኮኖሚውን ካቀረቀረበት ቢያቀኑት ድንገት ፎቀቅ እንል እንደሁ እንጂ ነገረ-ሥራችን እንኳ ከድጡ ወደ ማጡ እየሆነብን መቸገራችን የዕለት የሠርክ ሀቅ ነው፡፡ ስለዚህ ተራው ዜጋ ‹‹የምበላው ሳጣ፣ ልጄ ጥርስ አወጣ›› ቢል አይፈረድበትም! ኑሮው ከሥረ-መሠረቱ እናሻሽልለት! በዓል በመጣ ቁጥር የሚሰቀቀው አያሌ ነው! የእኛን መጥገብ ብቻ አንይ!! ይህንን ተደራዳሪዎቹ ወገኖች፣ እነሆ ወቅቱ መጥቷልና በምን መቀነቻ አጥብቀን እንያዘው ብለው ማሰብ ይገባቸዋል፡፡ ፀፀታችንን ሳይሆን ነገርአችንን እናስብ! የመሪዎችን ጉባኤ ስናስብም የአገራችንን መረጋጋት እንፈይድ!! 

Read 5816 times