Sunday, 22 January 2017 00:00

ለምጣዱ ሲባል አይጧ ትለፍ!

Written by 
Rate this item
(18 votes)

   ከዕለታት አንድ ቀን አንዲት ቆንጅዬ የገበሬ ልጅ፣ ወደ ላሚቱ ትሄድና ወተት ታልባለች፡፡ ወተቱን በጮጮ ጭንቅላቷ ላይ አድርጋ ወደ ቤቷ ስትመለስ፣ አንዳንድ ሀሳቦች ማውጣትና ማውረድ ትጀምራለች፡፡
“አሁን ይህን ወተት እንጥና ቅቤ አወጣለሁ፡፡ ያንን ቅቤ እወስድና ገበያ እሸጠዋለሁ፡፡ ይሄ የመጀመሪያ ሥራዬ ይሆናል፡፡ ከዚያ በማገኘው ገንዘብ ዕንቁላል እገዛለሁ፡፡ ያ ዕንቁላል ጫጩት ይፈለፍልልኛል፡፡ የተፈለፈሉትን ጫጩቶች አሳድጋቸዋለሁ፡፡ እነዚያን እወስድና ገበያ እቸበችባቸዋለሁ፡፡ ከዚያ ያገኘሁትን ብር ቀሚስ፣ ሸሚዝ፣ ሻሽና ጫማ እገዛበታለሁ። ‹ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ› ነውና፣ ያንን ቀሚስ እለብሳለሁ፡፡ ያንን ጫማ እጫማለሁ፡፡ ዝንጥ ብዬ የጥምቀተ - ባህሩ በዓል ዘንድ እሄዳለሁ፡፡
“ያኔ ወንድ ሁሉ እኔን ብቻ ነው የሚያየው፡፡ አንዱ ሲጠቅሰኝ፣ አንዱ “ሎሚ ጣሉባት በደረቷ” ሲል፤ እኔ ግን ምንቅንቅ ምንቅንቅ፣ አንገቴን ወዲህ ንቅንቅ፣ ወዲያ ንቅንቅ እያደረግሁ፣ ወንዱን ሁሉ ጭንቅንቅ አደርገዋለሁ” ስትል፤ ያ ራሱዋ ላይ አስቀምጣው የነበረው ጮጮ መሬት ላይ ወርዶ ይከሰከሳል፡፡ ያ ሁሉ ለብዙ ታቅዶ፣ ለብዙ ታልሞ የነበረው ወተት አካባቢው ላይ ፈሶ ቀረ!!
                                     *      *    *
ብዙ ባለምን፣ ብዙ ባቀድን ቁጥር አንዱንም ሳንተገብረው እንቀራለን፡፡ “ላም አለኝ በሰማይ፣ ወተቷንም አላይ!” የሚለው ተረት ሰለባ እንሆናለን፡፡ በሀገራችን በርካታ ዕቅዶች ይታቀዳሉ፡፡ በርካታ መመሪያዎች ይወጣሉ፡፡ በርካታ አዋጆችም ይታወጃሉ፡፡ በሥራ ላይ የሚውሉት ግን እጅግ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ አያሌ ግምገማዎች ይካሄዳሉ፡፡ ስህተቶችም ይታረሙ ዘንድ አስተያቶችና ሂሶች ይሰጣሉ፡፡ በውጤታቸው ሲታዩ ግን “ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ” ሆነው ይገኛሉ፡፡ ይህ የሚሆንበት ምክንያት አፋችን የሚናገራቸውን ልባችን ስለማይቀበለው ነው፡፡ “ጥልቅ ተሃድሶ” እንላለን እንጂ ወደ ውስጣችን ያልዘለቀ “የአንገት በላይ” ጉዞ ስምንጓዝ ነው! “ከዋሸህ ሽምጥጥ፣ ከመታህ ድርግም! ማድረግ ነው!” ይል ነበር ሟቹ ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህን፤ ነብሱን ይማረው፡፡ አባባሉ ግን ቋሚ ነው፡፡ ግምገማ የምናካሂደው ሰዎችን ለማልማት እንጂ ሰዎችን ለማንሳፈፍ መሆን የለበትም! መንቀዝን (Degeneration) ለመቋቋም እንጂ አወዳደቃችንን አሳምርልን (soft - landing) ለማለት መሆን የለበትም፡፡
በየትኛውም መልኩ አገር ቁልቁል እንድታድግ አንመኝም፡፡ ዛሬ፤ በተለይ በዋና ከተማችን በአዲስ አበባ፤ ሌላው ችግር ሳያንሰን ደግሞ አዲስ ችግር እያስተናገድን እንገኛለን - የሞተር ብስክሌተኞች አደጋ! ከችግር ወደ ችግር ጉዞ! “የበላችው ያቅራታል፣ በላይ በላዩ ያጎርሳታል!” ነው ነገሩ፡፡ “ለእግረኞች ቅድሚያ ባለመስጠት” ለሁሉም ችግር መፍትሄ አይሆንም!
“ፓናሲያ” እንደሚሉት፣ ፈረንጆቹ፤ ‹አንድ መድሐኒት ለሁሉ በሽታ መድህን አይሆንም። በሽታን እየለዩ ማከም ነው የሚያድነን!›
እስቲ የሚከተሉትን አባባሎች አንድምታቸውን ልብ እንበል፡፡ ደጋግመን እንላቸዋለን እንጂ አልተማርንባቸውም! ዛሬም እንድገማቸው፡- ‹‹ሞተር ብስክሌት ስትገዛ፣ የሬሣ ሳጥን አብረህ ግዛ!››
አንድ ሰው፤ ‹‹ሞተር ብስክሌተኛ ማነው?›› ተብሎ ተጠየቀ፡፡
ሰውዬው እንዲህ ብሎ መለሰ ይባላል፡-
‹‹ሞተር ብስክሌተኛ ማለት፣ ወደሚቀጥለው ከተማ እሄዳለሁ ብሎ ወደሚቀጥለው ዓለም የሚሄድ ሰው ነው!››
ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ፣ በየተጨናነቀው የመኪና ትራፊክ መካከል ውር ውር፣ ብቅ-ጥልቅ የሚሉ፣ እየተጥመዝመዙ ቁልቁል ሽቅብ የሚበሩ፣ ድንገት ሹክክ እና ድንገት ፈትለክ የሚሉ፤ በርካታ የሞተር ብስክሌቶች አሉ፡፡ አገልግሎታቸው ፈጣንና ቀልጣፋ መሆኑ እያጠያይቅም፡፡ መልዕክቶችን ያደርሳሉ፡፡ ፓስታዎችን ያከፋፍሉ፡፡ የመኪና መለዋወጫ ዕቃዎችን ወደ ተፈለገው ቦታ ያቀብላሉ፡፡ ጫት ያደርሳሉ፡፡ ምግብ በሰዓቱ ይወስዳሉ ወዘተ… ይሄ ሁሉ ደጎናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ክፉ ጎናቸው ግን እየተከሰተ መሆኑ አሳሳቢ ሆኗል፡፡
በከተማችን አዲስ አበባ በሞተር ብስክሌተኞች አደጋ እየደረሰባቸው ያሉ ዜጎች እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡ ቄራ ቡልጋሪያ አካባቢ መንገድ ሲያቋርጡ በሞተረኛ ተገጭተው የሞቱ የልጆች እናት በጣም ያሳዝናሉ፡፡ በዚሁ ሰሞን በሞተረኛ ተገጭቶ እግሩ የተሰበረ አምራች ወጣት የአልጋ ቁራኛ ሆኗል፡፡ ወደ ትምህርት ቤት ሊማር ሲሮጥ የሞተረኛ ሰለባ የሆነ ታዳጊ ወጣት አለ፡፡ ሌላውን ቤቱ ይቁጠረው፡፡ መርካቶ፣ ጉለሌ፣ ኮተቤ፣ አራት ኪሎ ወዘተ… በርካታ የሞተር አደጋ ተሰምቷል፡፡ ኢትዮጵያ በትራፊክ አደጋ ከፍተኛውን ደረጃ ይዛለች መባሉ መቼም ፀሐይ የሞቀው ሀቅ ነው! በአብዛኛው የአሽከርካሪዎች ምን-ግዴነት ወይም ንዝህላልነት መሆኑ ተደጋግሞ ተነግሯል፡፡ ፈረንጆቹ Recklessness የሚሉት  መሆኑ ነው! አሁን አሁን እጅግ እየከፋ የመጣው ግን የሞተር አሽከርካሪዎች አደጋ ነው። አብዛኞቹ አሽከርካሪዎች ወጣቶች ናቸው፡፡ የእሳት-እራት ዘመናቸው ላይ ያሉ ናቸው። ጀብድ ወዳድ፣ (Adventurist) ናቸው፡፡ ተወዳዳሪ የለንም ብለው የሚያስቡ ናቸው። ዛሬ አንዴ ተጥመዝምዘውና አቆራርጠው በፍጥነት አደጋዎችን ማለፋቸውን እንጂ ነገ ምን እንደሚገጥማቸው ከቶም ቁብ የሚሰጡት ጉዳይ አይደለም፡፡ አንዲት ጉብል ከባንክ ገንዘብ አውጥታ ስትሄድ፤ ያስተዋለ ሞተረኛ ወጣት፣ ቦርሳዋን ከእጇ መንትፎ፣ በእግረኛ መንገድ ሲበር፣ ራሱ ተገልብጦ የአካል ጉዳት ደርሶበታል፡፡ ጎበዝ! የሞተረኞች ነገር አደጋው ፈርጀ- ብዙ ነው፡፡ የሚመለከተው የመንግሥት መሥሪያ ቤት ጉዳዬ ሊለው ይገባል! የሞተር ብስክሌተኞች መንጃ-ፈቃድ ሊተፈሽ ይገባዋል! እስከዛሬ ያሉን የአደጋዎች ዓይነት ሳያንሰን ደግሞ የጥቂት ሞተር - ሳይክሊስቶች አደጋ እንቅልፍ- ሊነሳን አይገባም! እናስብበት! ‹‹አደጋ የማይለያት አገር›› የሚል አገላለፅ  መለያ ስማችን ሊሆን አይገባም! ‹‹ለምጣዱ ሲባል አይጢቱ ትለፍ›› እያልን እስከ መቼ ችግሮቻችንን እያስታመምን እንዘልቃለን? ችግሮቻችንን አንድ በአንድ እንምታ!!

Read 6174 times