Saturday, 17 March 2012 09:49

የጥቃቅንና አነስተኛ ፓርቲዎች የመቋቋሚያ ብድር ይፈቀድ!

Written by  ኤሊያስ
Rate this item
(1 Vote)

የቀድሞው የየመን ፕሬዚዳንት ወዳጅነታቸው ለማን ነው?

“እውነተኛው ነፃነት የሚገኘው ከጠብመንጃ አፈሙዝ ውስጥ ነው” ሙጋቤ

ወደ ፖለቲካ ወጋችን ከመግባታችን በፊት የንባብ “አፕታይታችሁን” ለምን በቀልድ አንከፍተውም፡፡ ቀልዱን የነገረችኝ አንድ “የቀልድ ደንበኛዬ” ናት፡፡ እኔ ደግሞ ከጊዜው ጋር እንዲጣጣም መጠነኛ ማስተካከያ አድርጌበታለሁ፡፡ እንደመሰለኝ ቀልዱ የመነጨው ከገዢው ፓርቲ አካባቢ ነው፡፡ ራሱ ገዢው ፓርቲ ነው አልወጣኝም! (በራሱ ለመቀለድ  አልደረሰማ!) የቅርብ ሰዎች (ውስጥ አዋቂዎች እንደሚባለው) የፈጠሩት ሳይሆን አይቀርም፡፡ (በነገራችሁ ላይ ቀልዱ ባለቤት ስለሌለው የህዝብ ሃብት መሆኑ ይታወቅልኝ!) ለማንኛውም ቀልዱ እንዲህ ይላል፡- “እኛ አንድ እጃችንን ሶማሊያ፣ ሌላኛው እጃችንን ኤርትራ ዘርግተን የመንግስትና የግል ሌቦች ከደረት ኪሳችን ውስጥ ሞጨለፉን!!” (ቀልድ ነው መግለጫ?) ነገሩ ቢያሳዝንም የተሞጨለፈው ነገር (ምንም ይሁን ምንም) የኛ ነው (የህዝቡ!) እውነቱን ስለተናገሩ ግን ለአሁን ይቅርታ አድርገንላቸዋል (ተሞጨለፍን ባዮቹን!) ምክር ግን አለን፡፡ ለወደፊቱ ከስህተታችሁ ተምራችሁ በአንድ ጊዜ ሁለት እጃችሁን ከመዘርጋት ተቆጠቡ፡፡ ባይሆን ሥራ ሲበዛባችሁ እርዳታ ጠይቁ! (ተቃዋሚ ፓርቲዎችንም ቢሆን!)

እኔ የምለው… ምርጫ ደረሰ እንዴ? ፓርቲዎች መንጫጫት ጀመሩ ብዬ እኮ ነው! እውነቴን ነው የለመድናት የቅድመ - ምርጫ ውዝግብ ሸታኛለች፡፡ ኢህአዴግ ምርጫ ቦርድ ከሰጠው 7ሚ. ብር ላይ ቆንጥሮ፣ ለስድስት ተቃዋሚ ፓርቲዎች 1ሚ. ብር የመለገሱን የምስራች ገና አጣጥሜ ሳልጨርስ ንትርክ መስማቴ አስገርሞኛል፡፡ (የምን ልግስናን ማጠልሸት ነው?) አይገርምም…ከፊሉ፤ ኢህአዴግ በምን ስሌት 7ሚ. ብር ይደርሰዋል እያሉ ሲሟገቱ፤ ከፊሉ ደግሞ 1ሚ ብር ተሰጣቸው የተባሉት ተቃዋሚዎች “የይስሙላ ተቃዋሚዎች” ናቸው ሲሉ ይከራከራሉ (ያለ ማስረጃ!) እንዴ ምርጫ ቦርድ የሰጣቸው ሠርተፊኬትስ? (ተቃዋሚነት በደም ምርመራ ይታወቃል እንዴ?)

በፖለቲካው ንፍቀ ክበብ አንድ መጥራት የሚሻ “ውዥንብር” ያለ ይመስለኛል፡፡ ምን መሰላችሁ? ተቃዋሚ ለመባል የግድ በ97ቱ ምርጫ ቃሊቲ መታሰር ያስፈልጋል እንዴ? በነገራችን ላይ አንዳንድ ተቃዋሚዎች ቃሊቲ ያልገቡት እኮ ኢህአዴግ አላስርም ብሏቸው እንጂ እነሱ አንታሰርም ብለው አይደለም! ይልቅስ  ስድስቱም ተቃዋሚዎች በእልህ ወደ አጋር ድርጅትነት እንዳይቀየሩና የተቃዋሚዎች ድርቅ እንዳይመታን! (አያድርስ ነው!)

እኔ ግን የኢህአዴግን የ1ሚ. ብር ልግስና ስሰማ ምን ትዝ አለኝ መሰላችሁ? ከጥቂት ዓመታት በፊት ኢህአዴግ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ መፍጠር እፈልጋለሁ እያለ መወትወቱ! እውነቴን ነው የምላችሁ … ያኔ እኮ ሲፎግረን ነበር የመሰለኝ፡፡ ከዛ በኋላ ደግሞ ተቃዋሚዎች ዳግም እንዳያንሰራሩ ተግቶ እየሰራ ነው የሚል መረጃ ደረሰኝና ጭል ጭል ስትል የነበረች ተስፋዬ ድርግም ብላ ጠፋች፡፡ ይኸው ሰሞኑን ደግሞ የተዳፈነች ተስፋዬ እንደገና ጭል ጭል ማለት ጀመረች፡፡ ገዢው ፓርቲ ለ6 ተቃዋሚዎች 1ሚ. ብር ለገሰ የሚለውን “የምስራች” ስሰማ፣ ኢህአዴግ “ለቃሉ የሚታመን” ፓርቲ ነው የሚል እምነት በውስጤ አንሰራራ፡፡ (ኢህአዴግ ስህተቱን ያምናል እንጂ አይታረምም የተባለው ትዝ አለኝ) ከዚህ በኋላ ግን የማንንም የፈጠራ ወሬ አምኜ እንደማልቀበል ለኢህአዴግ ሳይሆን ለራሴ ቃል ገብቻለሁ፡፡

ይሄውላችሁ..ኢህአዴግ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ ለመፍጠር አሁንም እየተፍጨረጨረ መሆኑን 1ሚ. ብር መዥርጦ በመለገስ (ምጽዋት እኮ አይደለም!) በተግባር አሳይቷል፡፡  ይሄ የኢህአዴግ ጠንካራ ተቃዋሚ የመፍጠር ፅኑ ምኞት እንዳይከሽፍ፣ እኔ ደግሞ  አንዳንድ የመፍትሄ ሃሳቦች ሳዘጋጅ ነው የሰነበትኩት፡፡ (ለኢህአዴግ ብዬ እኮ አይደለም፡፡) የአገር ጉዳይ ስለሆነብኝ ብቻ ነው፡፡ እናም የተቃዋሚዎችን የገንዘብ አቅም ለማጠናከር “የቦንድ ግዢ ቢጀመርስ” የሚል ሃሳብ አለኝ - እንደ ህዳሴው ግድብ! ግዴለም ለስሙ አትጨነቁ - “የተቃዋሚዎች አቅም ግንባታ የቦንድ ግዢ” ልንለው እንችላለን፡፡ ምነው… እንደ ቢፒአር ስሙ ገመድ ሆነባችሁ እንዴ? (“መሰረታዊ የሥራ ሂደት ለውጥ” ነበር ያሉት?)

ግዴለም በሃሳቡ ላይ ከተስማማን፣ የአርትኦት ባለሙያዎች ቀጥረን ስሙን ኤዲት እናስደርገዋለን፡፡ አያችሁ… ዜጐች በህብረት ተነሳስተው የህዳሴውን ግድብ በገንዘባችን እንሰራዋለን እንዳሉት ሁሉ … የተቃዋሚ ፓርቲዎችን አቅምም በራሳችን ገንዘብ እንገነባዋለን ማለት ይገባቸዋል (ያኛው ለልማት፣ ይሄኛው ለነፃነት!)

መቼም ለዚህች ብለን የIMF ወይም የዓለም ባንክን ደጅ አንጠናም (ምን በወጣን!) ከዳያስፖራም ጋር ፈፅሞ መነካካት አያስፈልግም (ከኢህአዴግ ጋር ያጋጨናላ!) ስለዚህ የተቃዋሚዎችን የፋይናንስ አቅም በቦንድ ግዢ በማጠናከር የዜግነት ግዴታችንን እንድንወጣ እማፀናለሁ (በአውራው ፓርቲ ስም!) የገንዘብ አቅም የሌላችሁ ደግሞ በፀሎት እንዳትረሱን አደራ እላለሁ፡፡ (ልማታዊ ሃይማኖት እኮ ይመቻል!)

አንድ ነገር ልንገራችሁ (ግን ምስጢር ነው!) የአገር ጉዳይ ሆኖብኝ ነው እንጂ እንዲህ ዓይነቱን የሚያሳማ ፕሮፖዛል ለመፃፍ እጄን (ብዕሬን) አላነሳም ነበር! አንዱ የጥንት ወዳጄ ስለ ፕሮፖዛሌ አጫውቼው ምን እንዳለኝ ታውቃላችሁ? “ገና ካሁኑ ማሊያ ልትቀይር ነው እንዴ?” (በእሱ ቤት እኮ ማሸሞሩ ነው!)

ማንም ያሻውን ቢልም ግን እኔ ያመንኩበትን ከማለት አላፈገፍግም! (ማንን ደስ ይበለው ብዬ?!) ስለዚህም ወደ ቀጣዩ ተያያዥ አጀንዳዬ ልግባ፡፡ ልብ አድርጉ! ተቃዋሚዎችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከፋይናንስ ፕሮብሌም ልገላግላቸው ቆርጬ ተነስቼአለሁ፡፡ እናም  ምን አሰብኩ መሰላችሁ? ጥቃቅንና አነስተኛ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በብድር መመስረት!! እንዴት አትሉም? መንግስት ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዲፈጠሩ ይመኛል አይደል?  ስለዚህ ብድር ያዘጋጃል ማለት ነው፡፡

(ምኞት ያለመስዋዕትነት አይሳካማ!) ከዛማ … ፍላጐቱና ዝንባሌው (የመቃወም ማለቴ ነው) ያላቸው ዜጐች 1ለ5 እየተደራጁ ተቃዋሚ ፓርቲ ለመመስረት ከመንግስት ብድር ይጠይቃሉ - ፕሮፖዛል ጽፈው በማስገባት፡፡ ከዚያስ? ብድሩን ያገኙ አመልካቾች ፓርቲ አቋቁመው ሰላማዊ ትግል ያካሂዳሉ፡፡ ትግል ማካሄድ ብቻ ግን አይደለም፡፡ እየታገሉ ብድራቸውን ይከፍላሉ፡፡ ብድራቸውን እየከፈሉ ይታገላሉ!!

አያችሁ…በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው ፓርቲ ካቋቋሙ በኋላ ኢህአዴግን አያስቸግሩትም፡፡ ኢህአዴግም የ1 ሚ.ብር ድጋፍ ለየትኛው ፓርቲ ልስጥ ብሎ ከመጨናነቅ ይገላገላል፡፡ ለምን ብትሉ… የገንዘብ አቅማቸው አስተማማኝ ይሆናላ! ይሄንን በማድረግም የቅድመ - ምርጫ ውዝግቦችን ሙሉ በሙሉ ማስቀረት ባንችል እንኳን በ70 በመቶ እንቀንሰዋለን!! (ውዝግብ የለሽ ፖለቲካዊ ከባቢ ተፈጠረ ማለት አይደል!)

ባለፈው ሳምንት የፓርላማ ጉባኤን በኢቴቪ ስከታተል ነበር፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና ም/ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተከበሩ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ የመስሪያ ቤታቸውን የአምስት ወር የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት ካቀረቡ በኋላ የተለያዩ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ተሰንዝረዋል - ከቤቱ፡፡ ትኩረቴን የሳበው ግን በፓርላማ ብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ አባል፣ የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ የሰነዘሩት በአስተያየት የተጠቀለለ ጥያቄ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ የሚበዛውን የውጭ ብድር (600 ሚ.ዶላር) ከቻይና መበደሯንና ከምዕራባውያን የተበደረችው ገንዘብ አነስተኛ መሆኑን የጠቆሙት የተከበሩ አቶ ግርማ፤ አገሪቱ ወደ ግራዘመም ርዕዮተ ዓለም ማዘንበሏን ያመለክታል ወይ ሲሉ ጠየቁ፡፡

ም/ጠቅላይ ሚኒስትሩ መመለስ ጀመሩ (ተረጋግተው)ባሁኑ ጊዜ እንኳን እኛ እነ አሜሪካም  በቢሊዮን ዶላሮች የሚገመት ገንዘብ የሚበደሩት ከቻይና ነው ሲሉ ሳቅ የሚወደው ም/ቤቱ በሳቅ ተሞላ፡፡ (ምንም የሚያስቅ ባይኖርም!) በአሁኑ ጊዜ የምታበድረው Reserve ገንዘብ ያላት ቻይና ብቻ ነገርዬው መሆኗን የተናገሩት ሚኒስትሩ፤ በቅርቡ ለአውሮፓውያንም ላበድራችሁ ማለቷን አስታውሰው አገራችንም ከቻይና የተበደረችውአቅም ያላት እሷ ብቻ በመሆኗ እንጂ ዓለም ጉዳይ ጋር እንደማይያያዝ አስረድተዋል፡፡ ልብ በሉ! ይሄ ሁሉ ማብራሪያ ያለ አንዳች አሽሙርና ዘለፋ ነው፡፡ (ያስገመግማቸው ይሆን እንዴ?)

እኔ የምላችሁ… የየመኑ የቀድሞ ፕሬዚዳንት አብደላ ሳላህ ዕጣ ፈንታ ምን ሆነ? መጠጊያ አገኙ ወይስ አሁንም በአየር ላይ ናቸው? በነገራችሁ ላይ ፌስ ቡክ የተሰኘው አዲሱ የዘመናችን አብዮት ከመጣ ጀምሮ ስለአምባገነን መሪዎች አንድ ነገር ታዝቤላችኋለሁ፡፡ እናንተ፤ ለካስ አምባገነኖች ሲባሉ “ስማርት” አይደሉም፡፡ ስማርት ቢሆኑማ ኖሮ ከስልጣን ከመባረራቸው በፊት “የስደት አገር” ያዘጋጁ ነበር፡፡  አብደላ ሳላህ ቢያንስ ከስልጣን ከመውረዳቸው በፊት “ለፈፀምኩት ኢ-ሰብአዊ ተግባር ላልጠየቅ” ብለው ተደራድረዋል አሉ (የሚገርመው የአደራዳሪዎቹ ነው!) ግን እኮ ከሁሉም በፊት መቀመጫ ይቀድም ነበር፡፡ (መጀመሪያ የመቀመጫዬን አለች አሉ!)

አንዳንድ መረጃዎች፣ ግለሰቡ የአረብ አገራትን (ኦማንና ሳኡዲ አረቢያን) የፖለቲካ ጥገኝነት ጠይቀው ምላሽ ስላላገኙ ፊታቸውን ወደ ኢትዮጵያ አዙረዋል ቢሉም የውጭ ጉዳይ ሚ/ር ግን አስተባብሏል - “ኧረ በፍፁም!” በሚል፡፡ የየመን የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኢትዮጵያ ቆይተው መመለሳቸውን የጠቆመው የውጭ ጉዳይ ሚ/ር፤ ይሄ ደግሞ መብታቸው ነው ብሏል - “ወዳጅ እኮ ናቸው!” ከሚል ማሳሰቢያ ጋር፡፡ ወዳጅነታቸው ለማን ወይም ከማን ጋር እንደሆነ ግን አልተጠቆመም፡፡ በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው ግን ምን መሰላችሁ? ሰውየው የኢትዮጵያ ህዝብ ወዳጅ አለመሆናቸውን ነው፡፡ (ህዝብማ የአምባገነን ወዳጅ ሊሆን አይችልም!) ይሄ ማለት ግን የፖለቲካ ጥገኝነት ቢጠይቁም አይሰጣቸውም ማለት አይደለም፡፡

ስደተኛን መቀበልና የአምባገነን ወዳጅ መሆን ለየቅል እኮ ናቸው፡፡ የኢዴፓው ሊ/መንበር አቶ ሙሼ ሰሙ እንዳሉት፤ የግለሰቡ ወደ ኢትዮጵያ መሰደድ ለየመን ወዳጅ ህዝብ እስከጠቀመ ድረስ ጥገኝነት መስጠቱ ተቀባይነት አለው፡፡ ልብ በሉ! ኢትዮጵያውያን የህዝብ ወዳጅ እንጂ የአምባገነን መሪዎች ወዳጅ ሆነው አያውቁም!!

የአምባገነኖችን ጉዳይ ከጀመርን አይቀር… የአገራችን የቀድሞ አምባገነን መሪ ኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማርያም፤ የጥገኝነት አገር ወደሆነችው ዚምባቡዌ እንሻገር፡፡ ከቅኝ ግዛት ነፃነት አንስቶ አገሪቷን የሚያስተዳድሩት አዛውንቱ ሮበርት ሙጋቤ በአንድ ወቅት ያሉትን ሰምታችኋል? አንድ የውጭ ጋዜጠኛ “ህዝቡን ተሰናብተውታል?” ሲል ጠየቃቸው (ሥልጣን ይለቃሉ ወይ ማለቱ ነው) “ወንዱ” ሙጋቤ ምን ቢሉ ጥሩ ነው? “ወዴት ሊሄድ ነው?” አሉ (እሳቸው ሥልጣናቸውን ትተው ወዴትም እንደማይሰናበቱ ለመጠቆም)

የ82 ዓመቱ ሙጋቤ “ብርቱ” አምባገነን መሪ ናቸው አሉ (አሉ ነው!) እርጅናና በሽታ ከሥልጣኔ አይነቀንቀኝም ብለው የተፈጠሙ ቆራጥ መሪ፡፡

የአገሪቱ ጦር ሠራዊት (የራሳቸው ብትሉት ይሻላል) ደግሞ ሁሌም ከጐናቸው ነው፡፡ በቅርቡ በሚካሄደው አገራዊ ምርጫ ሊሸነፉ ይችላሉ በሚል ስጋት ማስፈራሪያና ማስጠንቀቂያ መሰንዘር ጀምሯል እየተባለ ነው፡፡ ጦራ ሰራዊቱ “ማንም አሸነፈ ማንም ሥልጣኑ የሙጋቤ ነው!” ማለቱም ተዘግቧል፡፡ (የቁርጥ ጊዜ ወዳጅ ይሏል ይሄ ነው!) የዚምባቡዌ ተቃዋሚዎች የሰጡት ምላሽ ግን አስገርሞኛል፤ “እኛ ጦርነት ለመግጠም ዝግጁ አይደለንም” ብለዋል (ይሞታል እንዴ!) ልብ በሉ! ሙጋቤ “እውነተኛው ነፃነት የሚገኘው ከጠብመንጃ አፈሙዝ ውስጥ ነው” ያሉ አምባገነን መሪ ናቸው!! (የፌስቡክ አብዮት ገና ባይጐበኛቸውም)

ይታያችሁ…እዚህ እኛ አገር አውራው ፓርቲ ኢህአዴግ፤ ጠንካራ ተቃዋሚዎች እንዲፈጠሩ ባለው ፅኑ ፍላጐት፣ ለተቃዋሚዎች 1 ሚ.ብር እየለገሰ በምርጫ እንዲወዳደሩ ይፍጨረጨራል (ምርጫና ሥልጣን ለየቅል ቢሆኑም!) የዚምባቡዌው ገዢ ፓርቲና ጦር ሰራዊቱ ደግሞ “ምርጫውን ብናሸንፍም ብታሸንፉም ሥልጣን የሙጋቤ ብቻ ነው” ይላሉ፡፡

አሁን ኢህአዴግም የዚምባቡዌው ፓርቲም (ZANu – PF) የተፈጠሩት ከአንድ አህጉር ይመስላል? (የእናት ሆድ ዥንጉርጉር አሉ!) በስተመጨረሻ የህዝብ አመፅ እስካሁን ያልበረደባት ሶሪያ፣ ፕሬዚዳንት የሆኑት በሽር አል-አሳድ  ክፉ ቀን ሳይመጣ ካሁኑ “የስደት አገራቸውን” ቢያፈላልጉ ሳይሻላቸው አይቀርም! (ፈርቼ እኮ ነው - እኛን ጥገኝነት እንዳይጠይቁ!)

 

 

Read 3579 times Last modified on Saturday, 17 March 2012 09:54