Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 17 March 2012 09:43

ለ‘ጠበል’ም ለ‘ኪኒን’ም የሚያስቸግር…

Written by 
Rate this item
(0 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

ይቺን ስሙኝማ… ሰወየው ሚስቱ ኃይለኛ ነች አሉ፡፡ እናላችሁ… እሷ አንዴ መናገር ከጀመረች ትንፍሽ አይላትም፡፡ ታዲያ… ብሶቱን ሲናገር ምን አለ መሰላችሁ… “እሷ አንዴ መናገር ከጀመረች ከንፈሮቼን ማላቀቅ የምችለው ሳዛጋ ብቻ ነው!”

ልጄ… እንዴት ዕድለኛ እንደሆነ አላወቀ! እኛ እኮ “ማዛጋት እንኳን ሊያቅተን ነው” እያልን ነው!

የምር…ምን ብናደርግ ነው የሆዳችንን ተናግረን ሰሚ የምናገኘው የሚያሰኝ ጊዜ እኮ ነው! አሀ…በእኛ ህይወት ሙሉ “ወኪል ነኝ” የሚል በዛብና!

ስሙኝማ… “እኔ ብቻ ነኝ የማውቅልህ” የሚል ‘ናሽናል ዲዚዝ’ ነገር ያለ አይመስላችሁም! (እግረ መንገዴን… ከ‘ናሽናል ዲዚዝ’ እነ ከ‘ናሽናል ዛር’ የትኛው ይብሳል?) እናማ… ጩኸታችን ለንፋስ እንኳን ሳይበቃ ወደ ውስጣችን እያስተጋባ ተቸግረናልማ!

አሪፍ ሀሳብ አለችን…ዲጄዎች ውሳኔ ሰጪነት ቦታ ላይ ይቀመጡልንማ! አሀ… ልክ ነዋ! የትኛውን ዘፈን ከየትኛው ቢደባልቁት ሰዉን እንደሚያስደስት የልብ አውቃ ናቸዋ! የሰው ስሜት ገብቷቸው የልቡን ይሞሉለታላ! የሰዉን ፍላጎት እያወቁ “ተወው እባክህ!” ብለው ቮድካ በኦሬንጅ ሊጠጡ አይሄዱማ!  የ‘ዳንሰኛውን’ የልብ ትርታ ማዳመጥ ይችላሏ!... እኛማ…ዳንሱና እስክስታው ቀርቶብን የልብ ትርታችንን የሚሰማልን ባገኘን እያልን ነው፡፡

እኔ የምለው፣ “ለአንተ የሚሆነውን ዘፈን እኔ ብቻ ነኝ የማውቅልህ…” ማለት…እንዴት ነው ነገሩ! እኛ እስከተመቸን ድረስ ለምን የ“መቃብር እጮኛዬ”  ከ“ትመቺኛለሽ” ጋር ‘ሪሚክስ’ አይደረግም! አለ አይደል… ይቺ “ልክ የሆነው በእኔ አንደበት የምናገርልህና በእኔ ጆሮ የምሰማልህ ብቻ ነው፣” አይነት ነገር ለጠበልም ለኪኒንም የምታስቸግር ‘ናሽናል ዲዚዝ’ እየሆነች ነው፡፡

ስሙኝማ… ለእኛ ‘የምናጣው ሰንሰለት’ እንኳን እየናፈቅን ላለነው ሰዎች…አለ አይደል… ከሚነገሩት ነገሮች አብዛኛዎቹ “ዋ ብቻ!” አይነት መሆናቸው ግርም አይላችሁም! ሀሳብ አለን… ‘ባለስልጣኖች’ (ወይም እንደዛ ነገር ‘የሚሰማቸው’ ሰዎች…) በምን ያህል መጠን እኛን “ዋ ብቻ!” ማለት እንደሚችሉ የሆነ ደረጃ ይውጣልንማ! አሀ… ከታች እስከ ላይ መሰደባችን ካልቀረልን “የዛሬውስ ሻል ይላል…” ማለት እንድንችል በባለስልጣኖች — በራስ ተነሳሽነት እንደ ‘ባለስልጣን’ የሚያደርጋቸውን ጨምሮ —  ‘ጆብ ዲስክሪፕሽን’ ላይ የ“ዋ ብቻ!”  ልክ ይገለጽልንማ!

ለምሳሌ ‘ሀ’ ላይ ያሉት…  “አገጭህን አውልቄ ከሉሲ አጽም ጎን እንዲቀመጥ ነው የማደርግልህ!” ማለት ሊፈቀድላቸው ይችላል፡

በ ‘ለ’ ላይ ያሉት ደግሞ “ዓይነ ስብህን በጥፊ አብርሬልህ መነጽር ፍለጋ ፒያሳ ለፒያሳ ስትደናበር እንዳትከርም!” ሊሉ ይችላሉ፡፡

‘ሐ’ ደግሞ  (እንግዲህ ‘ላይት ዌይት’ ነገር አይደሉ!)  “በቁንጥጫ እንዳልመለዝግህ!” ሊሉ ይችላሉ፡፡

ሌሎቹ ደግሞ… አለ አይደል… የዕቁብ ጸሀፊነት ስልጣን እንኳን ሳይኖራቸው ለወንበር ‘ሲቪያቸውን’ ለማደለብ መከራቸውን የሚያዩ ምን ሊሉ ይችላሉ መሰላችሁ… “እስከ ዶቃ ማሰሪያህ ልክ ልክህን እንዳልነግርህ!” (ይቺን እንኳን በሆዳችንም ቢሆን እኛም እንላታለን!) እናላችሁ… እንዲህ ነገርዬው ካልተከፋፈለልን የ‘ስልጣን መሰላል ጫፍ’ አካባቢ ያለውም… “መሰላሉን ተሸክመህ አምጣ” የተባለውም እኩል የ‘ኬጂ ህጻናት’ ነገር ሲያደርጉን ልክ አይመጣም፡፡

እኔ የምለው… እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ከላይ የጠቀስናቸውን አይነት “ነብር አየኝ በል…” አይነት ነገሮች ለምን አሁን፣ አሁን እየበዙ እንደሄዱ ግርም አይላችሁም! አሀ… ታዲያ ‘ዲሴንትራላይዜሽን’ ምናምን ለአስተዳደር እንዲመች ነው እንጂ እኛ ላይ ሥልጣን ያለውም፣ የሌለውም ትከሻውን እንዲያሳየን ነው እንዴ!

እናላችሁ…ብዙ ነገሮች ‘ናሽናል ዲዚዝ’ አይነት እየሆኑላችሁ ነው፡፡ አንዱ ‘ዲዚዝ’ ምን መሰላችሁ…መናናቅ! የምር…አገር በመናናቅና በ‘እኔ ብቻ ልክ’ እያለቀላችሁ ነው፡፡ ሁሉም ነገር ሰው ከመሆን በኋላ መምጣቱ እየተረሳላችሁ… ድፍን አገር በዓይን እንትን እየተያየ ነው፡፡ እናማ… ሥራ እንዴት ይሠራ! ሀሳብ አለን… ሰዉ እንዲናናቅ የሚያደርጉ ነገሮችን የሚያባብሱ ሰዎች በመዋጮ ትራንስፖርት ወደ ሸንኮራ ጠበል ይላኩልንማ! የእነሱ ችግር የዘመናዊ ህክምና ጉዳይ አይደለማ! ቂ…ቂ…ቂ…

ደግሞላችሁ… ሌላ ‘ክሮኒክ ናሽናል ዲዚዝ’ እየሆነ ያለ ነገር ምን መሰላችሁ…ለ‘ፈረንጅ’ የሚደረገው እጥፍ ዘርጋ!  (ይሄኔ ነበር… አለ አይደል… ታሪክ የሚያውቅ ሰው… “ቴዎድሮስ ሆይ፣ አንተ ‘ጫማችሁ ላይ ያለውን የአገሬን አፈር እጠቡ’ ያልካቸው ፈረንጆች አሁን ጫማቸው ሊሳምላቸው ምንም አልቀራቸው’ ማለት፡፡ ለነገሩ ምን ያደርጋል… የአገራችን ‘ስታንድ አፕ ኮሜዲ’ የሚመስሉ ነገሮች አያልቁም አይደል… ታሪካዊ ማብራሪያዎች መስጠት ከሙያነት ይልቅ ወደ ‘ጊዜ ማሳለፊያነት’ ሲለወጥ ቁጭ ብለን በዓይናችን እያየን ነው፡፡)

እናላችሁ… የሌለውን ትከሻ በአገሩ ልጅ ላይ የሚነሰንሰው ሁሉ ፈረንጅ ፊት ‘እንደ ስሙኒ መሀረብ ሲርገበገብ’ ስታዩት “ይህን ሰው፣ ሆድህን ለመሙላት ጭንቅላትህን ተከራይ እንዳጣ ቤት ወና ማድረግ ያሳፍራል የሚለው ይጥፋ!” ያሰኛችኋል! ኸረ ደስ አይልም!… እኛ ስንሆን ግንባሩ ላይ ሰባ ስድስት መስመር የሚያወጣው ሁሉ… ፈረንጅ ሲሆን ‘ተጨማሪዎቹን ሃያ ስድስት ጥርሶች’ ከየት እንደሚያመጣ አይገርማችሁም!

በየመዝናኛው ስትሄዱ… አለ አይደል… እናንተ አምስት ሆናችሁ ገብታችሁ አንድ አስተናጋጅ ከስንት ማጨብጨብ በኋላ ሲመጣላችሁ… ‘ፈረንጅ’ ሆዬ ብቻውን ገብቶ ገና እንትኑ ወንበሩን ሳይነካ አራት አስተናጋጆች ‘ጥርሳቸውን ሊለቅሙ’ እስኪደርሱ ሲሽቀዳደሙ  “ኸረ ፈረንጅ ሆዬ ራሱ ይታዘባል” የሚል እንደጠፋ ይገባችኋል፡፡ አይደለም አሳላፊዎቹ… ለስንት አቤቱታ ዱካው እንኳን የማይገኘው የቦታው ሥራ አስኪያጅ ከየት ‘ዱብ እንደሚል’ ግራ ነው የሚገባችሁ፡፡ ወይስ የመዝናኛ ቦታዎች ሥራ እኪያጆች ቢሮ ‘ፈረንጅን’ ነጥሎ የሚያሳይ… ‘ሲሲቲቪ’ ምናምን ነገር አለ!

እናላችሁ… የሆነ ‘ለፍተሻ ተባበሩን’ የሚል በትልቁ የተጻፈበት ተቋም በር ላይ እናንተ “ድንገት ጉንፋን ቢይዘኝ…” ብላችሁ ያጣጠፋችኋት መሀረብ ተገላብጣ እየተራገፈች ‘ስትፈተሽ’… ፈረንጅ ሆዬ የእህል በረንዳን መኪና ሊስተካከል ምንም የማይቀረው ‘ሸክም’ ይዞ ሲገባ በሰላምታ ሲሸኝ የፈረንጅ አምላኪነት ወደ ‘ናሽናል ዲዚዝነት’ እንዳይለወጥ ያስፈራችኋል፡፡

እናላችሁ…የ‘ናሽናል ዲዚዝ’ ምልክቶች እየበዙ ነው፡፡ ስንት የሚወራ ጉዳይ ባላት አገር፣ ስንትና ስንት ‘ያረሩባት’ ነገሮች ሞልተው በፈሰሱባት አገር… በየኤፍ.ኤሙ. የቢዮንሴ በሰላም መገላገልና የሪሃና ከሰውዬዋ ጋር እንደገና መታረቅ የአየር ሰዓቱን አብዛኛው ክፍል ሲይዝ… አለ አይደል… የምር ወደ ‘ናሽናል ዲዚዝነት’ እየተለወጡ ያሉ ነገሮች በአይነትና በመጠን መብዛት ሊያሳስበን ይገባል፡፡

ስሙኝማ…መቼም ጨዋታም አይደል፣ የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ… አንዳንድ የኤፍ.ኤም. ፕሮግራሞች ስሰማ ምን እላለሁ መሰላችሁ… “የእኔ ‘አይ ኪው’ ከአገሪቱ አማካይ ይሄን ያህል ወርዶ ተከስክሷል እንዴ!” ልክ ነዋ… ገና ሰላምታ ቀርቦ የመጀመሪያው ሙዚቃ ሠላሳ ሰከንድ እንደተሰማ… አለ አይደል… “በርካታ አድማጮቻችን እየደወሉ የዛሬው ፕሮግራማችሁ በጣም አሪፍ ነው እያሉን ነው…” ሲባል ለምን ‘ጦጣ’ አንሆን! ነው… ወይስ ፕሮግራሞቹ ቀድመው ዩ ቲዩብ ላይ በ‘ፔይ ፐር ቪው’ ምናምን ይለቀቃሉ! አሀ… በዚች፣ በዚች እንኳን ‘ማሰቢያ ኩላሊት’ እንዳለን ግንዛቤ ይግባልን እንጂ!

ሌላ ደግሞ… በተመሳሳይ ሰዓት በተለያዩ ኤፍ.ኤሞች ላይ የሚተላለፉ ፕሮግራሞች እንዲህ ዓረፍተ ነገሮቹ ቃል በቃል የሚመሳሰሉት እንዴት ነው ነገሩ! ነው ወይስ ልክ እንደ ስልኩ የኤፍ.ኤም. ፕሮግራሞች ‘ይጠላለፋሉ’! ቂ…ቂ…ቂ… (የምንስቅበት፣ ወይም ‘ልንስቅ የምንሞክርበት’ አታሳጣንማ!)እግረ መንገዴን… እነኚህ ከኢንተርኔት “እየተረጎማችሁ” የምታቀርቡልን ነገሮችን በተመለከተ የወዳጅነቴን ጣል ላድርግማ …. ኢንተርኔት ከፋች ብዙ ስላለ አንሸዋወድ! ወይም ዜናዎቹ ‘አዛማጅ ትርጉም’ ከሆኑ ይነገረና! (ስሙኝማ… የዜና ‘አዛማጅ ትርጉም’ አሪፍ ሀሳብ አይመስላችሁም!)እናላችሁ… “ራሴ የማወራውን እንጂ የሌላውን አላዳምጥም” የማለት ‘ናሽናል ዲዚዝ’፣ አይደለም ባንኮክና ደቡብ አፍሪካ ዋልድባ ገዳም ሰባት ዓመት ከሰባት ወር ቢከርሙ መዳኑ ያጠራጥራል፡፡ (ሀሳብ… አለን የሆነ ዓመት መርሀ ግብር ምናምን ‘ዕቅድና ስትራቴጂ’ ይውጣልንና ሁላችንም ለመንፈቅ፣ ለመንፈቅ  ሸንኮራ ጠበል እየተነከርን እንምጣማ! ምናልባት አንድዬ በዚህ ያዝንልን ከሆነ! ከየት እንደምንጀምር ደግሞ ሀሳብ ቢጤ አናጣም!)ደግሞላችሁ… ይሄንንም ‘ማጣጣል’፣ ያንንም ‘አፈር ድሜ ማስጋጥ’… አለ አይደል… ያለምንም አስተላላፊ በራሱ ከአንዳችን ወደ አንዳችን ዘሎ የሚሰፍር ‘ናሽናል ዲዚዝ’ እየሆነ ነው፡፡ “እሱ ብሎ ምሁር… ምን ያውቃልና ነው! ጂኑን ሲገለብጥ አይደል እንዴ የሚያመሸው!” (የምር ግን… እግረ መንገዴን… ጂንን ወደምሁር ሠፈር ያቀረባት የሆነ ማጂክ ኬሚካል አላት እንዴ!)

“እሱ ብሎ ፖለቲከኛ፣ አናውቀውምና ነው! ማኦና ማራዶናን መለየት የማይችል!” (በዚችስ እኛም አልፎ አልፎ ጥርጣሬ አለን… ቂ…ቂ…ቂ…) “እሱ ብሎ ደራሲ… ከፈረንጅ መጽሀፍ ቀዶ እየሰፋ አይደል እንዴ ጻፍኩ የሚለው…” (‘የተቀደደውን መስፋት’ እያቃተን እኮ ነው ነገሩ ሁሉ  የሆነ ቡቱቶ እየሆነብን የተቸገርነው፡፡)እናላችሁ… ወደ ‘ናሽናል ዲዚዝነት’ እየተለወጡ ያሉ ነገሮች እየበዙብን ግራ ገብቶናል፡፡ አንድዬ እያጣናቸው ያሉ ‘የሰውነት መገለጫ ባህሪያትን’ እንደገና የምንለማመድበት የሙከራ ጊዜ ይስጠንማ!

ነገሩ ሁሉ ለጠበልም ለኪኒንም የሚያስቸግር ሆነብና!

ደህና ሰንብቱልኝማ!

 

 

Read 4102 times Last modified on Saturday, 17 March 2012 12:04