Print this page
Saturday, 17 March 2012 09:37

የአበበች ጐበና አርቆ አሳቢነት የተመሰከረበት አውደርዕይ

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(0 votes)

“እጅግ በጣም አስፈሪው ድህነት፣ ብቸኝነትና በሌሎች ያለመፈለግ ስሜት ነው”   -ማዘር ቴሬ

ኑዛዜ በብዙ አገሮች የተለመደ ጥንታዊ ሥርዓትና ልማድ ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ በኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ 49 እና 50 ላይ ያዕቆብና ልጁ ዮሴፍ በሞቱ ጊዜ የትና እንዴት መቀበር እንዳለባቸው ወይም የአፅማቸው የመጨረሻው ማረፊያ የት መሆን እንዳለበት፣ በቁም ሳሉ አደራ ባሉት መሠረት ኑዛዜያቸው ተግባራዊ እንደሆነ ተጽፏል፡፡

ኃጢአትን ለንስሐ አባት ነግሮ ህሊናን እፎይ ለማሰኘት ወይም የማይቀረው ሞትን በሰላም ለመጠበቅ የሚናዘዙ አሉ፡፡ የሞቱ ዕለት ጽድቅና በረከት ይገኝበታል ተብሎ በሚታመን ቦታ እንዲቀበሩ አደራ ትተው የሚሞቱ ሰዎች እንዳሉም ይታወቃል፡፡ ኑዛዜው ከሀብትና ንብረት ጋር የተያያዘ ከሆነ ግን ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግበት ያሻል፡፡ ያለበለዚያ ብዙ ጉዳትና እንግልት የሚያስከትል ቀውስ ሊፈጥር ይችላል፡፡ በየፍርድ ቤቱ ከሚያጨቃጭቁ አያሌ ጉዳዮች ውስጥ ጥቂት የማይባሉት ከኑዛዜ ጋር የተያያዙ እንደሆኑ  ይታወቃል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የኑዛዜ አድራጊው አርቆ አሳቢነት፤ በወራሾች መሐል ሰላምና ፍቅር እንዲሰፍን፣ ፍርድ ቤቶችን የሚያጨናንቀው ማህበራዊ ቀውስ እንዲቀንስ፣ የተጀመሩ ሥራና ልማቶች እንዲቀጥሉ፣ የሀገር ሀብትና የዜጐች ዕውቀት እንዲጐለብት አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፡፡ ለዚህ ማሳያነት የሚጠቀሱ ሰዎችና ተቋማትም አሉ፡፡

የዳግማዊ አፄ ምኒልክ መታሰቢያ ድርጅት ከተለያዩ ግለሰቦችና ተቋማት ከተሰጠው መሬት፣ ቤትና ገንዘብ ውስጥ አንዳንዶቹ ለጋሾች በኑዛዜ መልክ የሰጡት እንደሆነ ሰነዶች ይጠቁማሉ፡፡ ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ ለመታሰቢያ ድርጅቱ፣ 71 ሺህ ሜትር ካሬ መሬትና ሁለት ቤቶችን በ1913 ዓ.ም ማውረሳቸው ይታወቃል፡፡

የአባታቸው የራስ መኮንንን መኖሪያ ቤት የወረሱትና ለብዙ ጊዜ የኖሩበትን ይዞታ፣ በ1954 ዓ.ም ለአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ያወረሱት አፄ ኃይለሥላሴ፤ ኑዛዜን በቁም ሳሉ በመፈፀም ብቻ ሳይሆን በዕውቀት፣ በብልሀትና አርቆ በማሰብ ተግባራዊ በማድረግም በመልካም አርአያነት ይጠቀሳሉ፡፡

ከየካቲት 29 እስከ መጋቢት 5 ቀን 2004 ዓ.ም በብሔራዊ ሙዚየም በቀረበውና “የሺዎች እናት” በሚል ርዕስ በተዘጋጀው አውደርዕይ ላይ ከኑዛዜ ጋር የተገናኘ አርአያነት በክብርት ዶ/ር አበበች ጐበና ታይቷል፡፡ በአውደ ትርዒቱ ከቀረቡት የቁሳቁስ፣ የፎቶግራፍና የጽሑፍ መረጃዎች መካከል፣ ዶክተር አበበች ጐበና ሰኔ 16 ቀን 2003 ዓ.ም በኢፌዲሪ የፍትሕ ሚኒስቴር የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽሕፈት ቤት ተገኝተው፣ ያስመዘገቡትና ሕጋዊ ዕውቅና ያሰጡት የቁም ኑዛዜያቸውን የያዘው ሰነድ ይገኝበታል፡፡

ባለታሪኳ ከ1980 ዓ.ም ጀምሮ ሦስት ጊዜ በግላቸው፣ አንድ ጊዜ ውልና ማስረጃ መምሪያ ይባል በነበረው ተቋም ተገኝተው፣ ኑዛዜያቸውን ማኖራቸውን የሚያመለክተው ሰነድ፤ ኑዛዜያቸው ሕጋዊ ጥበቃና ከለላ እንዲኖረው በማሰብ በአዲስ መልክ ማስመዝገባቸውን ይጠቁማል፡፡

ታዛቢዎች ባሉበትና በመልካም ጤንነት ላይ ሳሉ፣ ኑዛዜ መፈፀማቸውን የገለፁት ክብርት ዶክተር አበበች ጐበና፤ በቀደሙትና በአሁኑ የአደራ ቃሌ ላይ የሃሳብ ልዩነት ካለ የመጨረሻው ኑዛዜዬ የፀና ይሆናል በማለት ቀዳዳዎችን ለመድፈን ሞክረዋል፡፡

በዶክተር አበበች ጐበና የኑዛዜ ሰነድ ላይ እንደተመለከተው፣ ከ1972 ዓ.ም ጀምሮ ወላጅ አልባ ልጆችን እየረዱ እንደቆዩ የተጠቆመ ሲሆን “የአበበች ጐበና ሕፃናት ክብካቤና ልማት ማህበር” ንብረቶች በሙሉ የማህበሩ ሀብት እንደሆኑ ተገልጿል፡፡

ዓለምን በሞት ሲሰናበቱ እንዲደረግላቸው የሚመኙትንም አበበች ጐበና በኑዛዜያቸው ላይ አስፍረዋል፡፡ ቀብራቸው በአዲስ አበባ ሆኖ የቤተክርስትያንና የቦታ ምርጫ ሳይደረግ ግብአተ መሬት ይፈፀምልኝ የሚሉት ዶክተር አበበች ጐበና፤ ሳጥንና ሐውልት እንደማይፈልጉ ገልፀዋል፡፡ ሰልስትና አርባም አስፈላጊ አይደለም ብለዋል፡፡ የግል ጌጣጌጦቻቸውና ልብሶቻቸው ተሸጠው ገንዘቡ ችግረኞች እንዲረዱበትም አበበች ጐበና አደራ ትተዋል፡፡

የኑዛዜ ሰነድን ጨምሮ ከዶክተር አበበች ጐበና የበጐ አድራጐት ሥራዎች ጋር የተያያዙ በርካታ መረጃዎች የቀረቡበት አውደርዕይ፤ የባለታሪኳን የ74 ዓመት የሕይወት ጉዞ የሚያስቃኝ ነበር፡፡

በ1930 ዓ.ም በሰሜን ሸዋ የተወለዱባት ጐጆ ቤት፣ አባታቸው ከፋሽስት ጣሊያን ጋር ሲዋጉ የሞቱበት ቦታና ሌሎች መሰል ፎቶግራፎች የታዩበት አውደርዕይ፤ አበበች ጐበና በ1972 ዓ.ም የጀመሩት የበጐ አድራጐት ተግባር ከየት ተነስቶ የት እንደደረሰ አስቃኝቷል፡፡ በ1972 ዓ.ም ግሸን ማርያምን ለማንገስ ሄደው፣ በድርቅ በተጠቃ አንድ መንደር ውስጥ የሞተች እናቷን ጡት ለመጥባት የምትሞክር ሕፃን ያዩት ዶክተር አበበች፤ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የበጐ አድራጐት ሥራ ለማከናወን እንደተነሳሱ ይናገራሉ፡፡ ግሸን ማርያምን አንግሰው ብቻ ሳይሆን በቀጣዩ ህይወታቸው የሚኖሩለትን ዓላማ ይዘው ወደ አዲስ አበባ የተመለሱት አበበች ጐበና፤ ቤተሰቦቻቸው “ጤነኛ አይደለሽም? አሞሻል?” እንዳሏቸው ያስታውሳሉ፡፡   ከቤተሰባቸው ተቃውሞ ቢገጥማቸውም ቅሉ ከዓላማቸው ግን አልተገቱም፡፡ ለዶሮ ማርቢያ በተዘጋጀ የቀርከሐ ቤት ውስጥ ሕፃናትን ሰብስበው የእርዳታ ተግባራቸውን ማከናወን ጀመሩ፡፡ ዓላማቸውን ለማሳካት የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ ለማግኘት፣ የጉሊት ንግድ ላይ ሳይቀር የተሰማሩት አዛውንቷ፤ ከግሸን ሁለት ልጆችን ለማሳደግ ባመጡ በዓመቱ፣ ሰብስበው የሚረዷቸው ልጆች ቁጥር 21 ደረሰ፡፡ በቀርከሐ ሳጠራ ቤት የጀመሩት የበጐ አድራጐት ሥራ ወደ ተቋም ሲያድግ፣ “ብሩህ ተስፋ የሕፃናት መንደር” የሚል ስያሜ ተሰጠው፡፡

በመቀጠል ስሙን “የአበበች ጐበና ሕፃናት ክብካቤና ልማት ማህበር” ወደ ሚል የቀየረው ተቋም፤ የ30 ዓመት ዕድሜ ያስቆጠረ ሲሆን ዛሬ ከአገሪቱ ታላላቅ የበጐ አድራጐት ድርጅቶች አንዱ ለመሆን በቅቷል፡፡

አንዳንድ የሚዲያ ተቋማት የማዕከሉ መሥራች የሆኑትን ዶክተር አበበች ጐበና፣ ከበጐ አድራጊዋ ማዘር ቴሬዛ ጋር በማመሳሰል “አፍሪካዊቷ ማዘር ትሬዛ” ሲሉ ይጠሯቸዋል፡፡  በማዕከሉ የተለያየ እርዳታ ያገኙ ልጆች፣ ወጣቶች፣ ሴቶችና የኤችአይቪ ኤድስ ተጠቂዎች በተለያዩ ዘርፎች ስኬታማ በመሆን ከአገር አልፈው በዓለም አደባባይ ለመታወቅ በቅተዋል፡፡ በዶክትሬት ድግሪ ተመርቃ በሆላንድ በህክምና ባለሙያነት በማገልገል ላይ የምትገኘው ወጣት፣ ከማዕከሉ መኩሪያዎች መካከል በግንባር ቀደምትነት ትጠቀሳለች፡፡

244 ቋሚና 206 የበጐ ፈቃድ ሠራተኞች የሚያስተዳድረው ማዕከሉ፤ ለ12ሺህ ወጣቶችና 1.5 ሚሊዮን ለሚደርሱ የገጠርና የከተማ ነዋሪዎች እንዲሁም ለ1537 ሴቶች በተለያየ መልኩ እገዛ ማድረጉ ተገልጿል፡፡ በእነዚህም በጐ ተግባሮቹ ከተለያዩ የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ተቋማት በርካታ ሽልማቶችና የዕውቅና ሠርተፍኬቶች ተሰጥቶታል፡፡

“ሰውና እንጨት ተሰባሪ ነው” የሚሉት ዶክተር አበበች ጐበና፤ ከ30 ዓመት በፊት የመሰረቱትና አሁን ላለበት ደረጃ የደረሰው ተቋም፣ ቀጣይነቱ አስተማማኝ ይሆን ዘንድ ማዕከሉ የአገርና የሕዝብ ሀብት እንዲሆን በኑዛዜያቸው ላይ ገልፀዋል፡፡ ይህ በዚህ እንዳለ በኤግዚቢሽኑ ላይ ለእይታ የቀረበውና በቀራፂ ብዙነህ ተስፋ የተሰራው የዶክተር አበበች ጐበና ሐውልት፣ በብሔራዊ ሙዚየም በቋሚነት እንደሚቀመጥ ተነግሯል፡፡

 

 

Read 12095 times Last modified on Saturday, 17 March 2012 11:41