Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Saturday, 17 March 2012 09:25

ከስፖርት ወደ ኢንቨስትመንት በበቆጂ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

አቶ ዳዊት ጌታቸው በፊት እግር ኳስ ተጨዋች ነበረ፡፡ ከኢትዮጵያ ከመውጣቱ በፊት ኢትዮ - ፎም በሚባል ቡድን ከመጫወቱም በላይ በዚያው ክለብ የኮሚቴ አባል ሆኖም ሠርቷል፡፡ ከ1986 ጀምሮ አሜሪካ ከሄደ በኋላ  ደግሞ አሁን ለሚኖርበት የቦስተን ከተማ ቡድን ለ4 ዓመት እንዲሁም  ለሎስ አንጀለስ ቡድን ተጨማሪ 4 ዓመት እንዲሁም ለአትላንታ  ቡድንም ለ1 ዓመት ተጫውቷል፡፡ በየዓመቱ በሰሜን አሜሪካ በሚካሄደው  የኢትዮጵያውያን የስፖርትና የባህል ፌስቲቫል ለሚሳተፉ ቡድኖች ከመጫወት ባሻገር በኢትዮጵያውያን ተጨዋቾችና ደጋፊዎች የበጐ አድራጐት ድርጅት ውስጥ በቦርድ አባልነት በመስራት  ላይ ይገኛል፡፡ በአሜሪካ ቦስተን ለ20 ዓመታት የኖረው አቶ ዳዊት፤ በአሁን ወቅት በትውልድ ስፍራው በቆጂ በእርሻ ልማት እና በሌሎች የኢንቨስትመንት መስኮች እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ ታላላቅ አትሌቶችን በማፍራት በምትታወቀው በቆጂ የተወለደው ዳዊት ጌታቸው፤ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ግሩም ሠይፉ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

ከበጐ አድራጐት ሥራዎቹ ሌላ ምን እየሠራህ ነው?

በኢንቨስትመንት ዘርፍ እሳተፋለሁ፡፡ በእርሻና በውጭ ንግድ የኢንቨስትመንት መስኮች በአገሬ እየሠራሁ ነው፡፡ በበቆጂ የእርሻ ልማት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ኢንቨስት ካደረጉ አምስት ባለሃብቶች አንዱ ነኝ፡፡ ዴቭ አሌክስ በሚል ስያሜ ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ የስጋ ምርቶችን የሚልክ ኩባንያም እየገነባሁ ነው፡፡  በበቆጂ ከሚገኝ ተራራ ላይ የሚፈልቅ የተፈጥሮ ምንጭ የውሃ ምርት እያሸጉ ለማቅረብ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክት ነድፌአለሁ፡፡

በቆጂ ላይ ኢንቨስትመንት ለማድረግ ያነሳሳህ የተለየ ምክንያት አለህ?

በቆጂ የትውልድ መንደሬ ናት፡፡ ያው በዓለም አቀፍ ደረጃ ዝነኛ አትሌቶች የወጡባት መሆኗ ይታወቃል ፡፡ ይህች ታሪካዊ መንደር እንዳላት ዓለምአቀፋዊ እውቅና በከፍተኛ ደረጃ ለማደግ አለመቻሏ ይቆጨኛል፡፡ ስለዚህም በተለይ በቆጂን እንደስሟ ሊያነሷትና ሊያስከብሩዋት በሚችሉ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ላይ መሳተፍ እፈልጋለሁ፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃም ለመስራት ዕቅድ ቢኖረኝም ቅድሚያውን ለትውልድ ስፍራዬ ለቆጂ ሰጥቻለሁ፡፡ ለእኔ ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ ያስተማረኝንና ያሳደገኝን ማህበረሰብ መደገፍ ሁሌም ሳስበው የነበረ ነው፡፡ በበቆጂ የእርሻ ልማት ኢንቨስትመንት ከጀመርኩ አራት ዓመት ሆኖኛል፡፡ በአጠቃላይ በኢንቨስትመንት ዘርፍ ምን መስራት እንደሚቻል ለማጥናት ከአሜሪካ መመላለስ ከጀመርኩ ግን 10 ዓመት ይሆነኛል፡፡

በበቆጂ ያለው የኢንቨስትመንት ዕድሎች ምን ይመስላሉ?

ከ10 ዓመት በፊት በበቆጂ የነበረው አስተዳደር፣ ኢንቨስተሮች በአካባቢው መዋዕለ ንዋያቸውን አፍሰው እንዲሰሩ የሚጋብዝ እንቅስቃሴ አያደርግም ነበር፡፡ አሁን ግን ብዙ መሻሻሎች እየተስተዋለ ነው፡፡ ታዋቂ አትሌቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ገብተው የትውልድ ስፍራቸውን ማልማት ጀምረዋል፡፡ በቆጂ አለም ያወቃት መንደር ሆና ብዙ ያልተሠራባት እንደመሆኗ መጠን ሰፊ እንቅስቃሴ በማድረግ ለውጥ ማምጣት ይገባል፡፡ አካባቢው በቀንድ ከብት፣ በእህልና በውሃ እንዲሁም በተፈጥሮ ሃብት እጅግ የበለፀገ ነው፡፡ ያን አቅም ተጠቅሞ መስራት ያስፈልጋል፡፡ በቆጂ በአትሌቶቿ የምትታወቀውን ያህል በኢንቨስትመንት እድገቷም ስሟን ለማስጠራት ከፍተኛ ፍላጎት አለኝ፡፡ ለከብቶች ግጦሽ ብቻ የሚውለው ሰፊ መሬት በመካናይዝድ ግብርና ሊለማ ይገባል፡፡ እኛም በአካባቢው የተፈጥሮ ሃብት ተጠቅመን ምርጥ እህልና ጥራጥሬ ለማምረት በማሰብ ነው የእርሻ ልማት ውስጥ የገባነው፡፡ በበቆጂ ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለብዙ ኢንቨስተሮች የሚበቃ መሬትና የተፈጥሮ ሃብት አለ ብዬ አምናለሁ፡፡ የእኛ የእርሻ ልማት ያተኮረው በምርጥ ዘር ላይ ነው፡፡ ወደፊት ደግሞ በአትክልትና የውጭ አገር እጽዋቶችን ወደ እዚህ አገር አምጥተን  በማልማት፣ ዓለም አቀፍ ገበያ ለማግኘት አቅደናል፡፡ የአካባቢው አርሶ አደሮች የሚታወቁት በድንች አምራችነታቸው ነው፡፡ ነገር ግን ምርታቸውን ለገበያ ለማቅረብ የመንገድ ችግር ነበረባቸው፡፡ ይሄን የመንገድ ችግር ለመፍታት የ6 ኪሎሜትር ጥርጊያ መንገድ አሠርተናል፡፡ አሁን በድንች ምርት አቅራቢነት በቆጂ እና በአቅራቢያው የምትገኘው የሊሙ ወረዳ፣ ከሻሸመኔ በመቀጠል ተጠቃሽ ሊሆኑ ችለዋል፡፡

በተፈጥሮ የምንጭ ውሃ ምርት ላይ ኢንቨስት የማድረግ ዕቅድ አለኝ ብለሃል?

የበቆጂ የተፈጥሮ ውሃ ላይ ኢንቨስት ለማድረግ የተነሳሁት፣ ከአትሌቶች ጋር አያይዤ በነደፍኩት የፕሮጀክት እቅድ ነው፡፡ ከዛሬ ሦስት ዓመት በፊት ከአንድ በቦስተን ከተማ ነዋሪ ከሆነች አሜሪካዊ ኢንቨስተር ጋር በመሆን በመስኩ ለመስራት ፈቃድ አውጥተናል፡፡ ከዚያ በኋላ ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ፈቃድ ለማግኘት እየጠበቅን በነበረበት ወቅት ያልታሰቡ ችግሮች አጋጠሙን፡

ምን አይነት ችግሮች?

ችግሩ ለእርሻ ልማት ከያዝነው መሬት ጋር የተያያዘ ነበር፡፡ የመንደሩ ገበሬዎች የይገባኛል ጥያቄ በማንሳታቸው የተፈጠረ የመሬት ክርክር ነው፡፡ ለእርሻ ልማት የተሰጠንን መሬት፣  ገበሬው የግጦሽ መሬት ነው በማለቱ ተነጠቅን፡፡ በዚህ የመሬት ጉዳይ ያለፈውን ሁለት ዓመት በፍ/ቤት ክርክር ስላሳለፍኩ፣ በውሃ ምርት ላይ የነደፍኩትን ፕሮጀክት በስራ ላይ ማዋል አልቻልኩም፡፡ የእርሻ ልማቱን የጀመርነው በ1000 ካሬ ሜትር ላይ ነበር፡፡ በኋላ 500 ካሬ ሜትር ተወሰደብን፡፡ በቅርቡ በወረዳው ከተፈጠረው የመልካም አስተዳደር ለውጥ ጋር በተያያዘ  መነቃቃት እየታየ ነው፡፡ በኢንቨስትመንት ዙሪያ ካሉ ችግሮች ውስጥ በወረዳ ደረጃ ያሉ አስተዳዳሪዎች ያለባቸው ድክመት ተጠቃሽ ነው፡፡ በተለያዩ ጊዜያት የተደረጉ የአስተዳደር ውሳኔዎች ባለድርሻ አካላትንና ኢንቨስተሮቹን ሳያማክሉ በመፈፀማቸው ለኢንቨስትመንት እንቅስቃሴው ዕንቅፋት ሆነዋል፡፡ ይህን በመቃወም አቤቱታ አስገብተን በአዲሱ አስተዳደር ውሳኔ ካገኘን በኋላ የተወሰደብንን መሬት አስመለስን በቅርቡ የእርሻ ልማቱን ቀጥለናል፡፡ ለሁለት ዓመት በውዝግብ የተነሳ የእርሻ ልማቱን አለመስራታችን ግን ጉዳት ነበረው፡፡ በተነጠቅነው 500 ካ.ሜ መሬት ላይ እስከ 10ሺ ኩንታል ምርት በየዓመቱ ልናገኝ እንችል ነበር፡፡ ልናመርት አቅደን የነበረው ለአገር ውስጥ ገበያ የሚቀርብ የስንዴ ምርጥ ዘር ነበር፡፡ በሞራል ደረጃ የደረሰብን ኪሣራም ቀላል አይደለም፡፡ አሁን ተመልሰን መስራት የጀመርነው በተደረገው  የአስተዳደር ለውጥ ተጠቃሚ እንሆናለን በሚል ተስፋ ነው፡፡

እስቲ ስለውሃ ምርት ፕሮጀክትህ በደንብ ንገረኝ …

ፕሮጀክት የነደፍኩት ከተራራ ስር በሚወጣ የውሃ ሃብት ላይ ነው፡፡ ከተራራው ስር የሚፈልቁ ምንጮች እጅግ በጣም ንፁህ የመጠጥ ውሃ ናቸው፡፡  ተራራው ጋላማ ይባላል፤ በበቆጂ ወረዳ ውስጥ ነው ያለው፡፡ የምንጭ ውሃ ለማልማት ያቀድኩት የትውልድ መንደሬን የተፈጥሮ ሃብት አቅም በቅርበት ስለማውቀው ነበር፡፡ እኔ መንቀሳቀስ በጀመርኩበት አካባቢ ብቻ እስከ አምስት የሚደርሱ የተራራ ስር ምንጮች አሉ፡፡

ስለውሃው እንዴት እርግጠኛ ሆንክ? ጥናት አስጠንተሃል…

ውሃውን ጠጥቼ ነው ያደግኩት፡፡ ከአትሌቶቹ ጋር ደግሞ የቀረበ ግንኙነት አለኝ፡፡ እነሱም የጥራት ደረጃውን መስክረውልኛል፡፡ አሁን ከጥሩነሽ ዲባባ ጋር በትውልድ አካባቢ ብቻ ሳይሆን እዚያ በአሜሪካ   ግዛት ቦስተን በሚደረጉ ውድድሮች በተደጋጋሚ እንገናኝ ነበር፡፡ ከደራርቱና ከሌሎቹ አትሌቶችም ጋር እቀራረባለሁ፡፡ ባንድ ወቅት ስለዚህ የተራራ ስር ውሃ ከአንዲት ታዋቂ አትሌት ጋር ስናወራ ያለችኝን አልረሳውም፡፡  “ለበቆጂ አትሌቶች ስኬት ምስጢሩ ወተቱ ይመስለኛል” ስላት አትሌቷ “በውሃው በበቀለ ሣር አይደል ከብቶች ወተት የሚሰጡት” በማለት ውሃውን ማስቀደሟን አስታውሳለሁ፡፡ በበቆጂ አትሌቶች ስኬታማነት ዙሪያ ብዙ ጥናቶች ይደረጋሉ፡፡ አትሌቶች በአካባቢው ውሃ  ተጠቃሚ መሆናቸው ከስኬታቸው ጋር ስላለው ግንኙነት ጥናት ለማካሄድ የሚጋብዝም ነው፡፡ በመሬት  ክርክሩ እና በሌሎች ውዝግቦች ስሟገት በነበርኩባቸው ጊዜያት እኔ የሰራሁት ፕሮጀክት በሌላ አካባቢ አምሳያ ፕሮጀክት ተሰርቶበታል፡፡

ከወረዳው ውጭ በዲገሎና ጢጆ ወረዳዎች ውስጥ በበቆጂ ስም ውሃ ወጥቶ እየተሰራ ነው፡፡ ከተራራ ስር ሳይሆን ከሜዳማ ቦታ ላይ የሚወጣን ውሃ እኔ አስቀድሜ ፈቃድ ያወጣሁበትን   ስያሜ በመንጠቅ መሰራቱ ትክክል አይመስለኝም፡፡ በዚህ ላይ በውሃ ምርቱ በቆጂ ተጠቃሚ አለመሆኗ ያሳስበኛል፡፡የውሃውን ፕሮጀክት ከሰው በፊት ነው የጀመርኩት፡፡ ከ20-30 ሚሊዮን ብር በጀት መድቤ በሰፊ የፕሮጀክት ጥናት ለመስራት አቅጄ ነበር፡፡ የውሃ ምርቱን በሦስት ማሽኖች በቀን እስከ 50ሺ ሊትር ለማምረት ዕቅድ ነበረን፡፡ እኔ የተራራ ስር ምንጩን ውሃ ለማምረት የያዝኩት ቦታ እስካሁን እንደተዘጋ ነው፡፡ ቦታው ላይ የድሮ የአሜሪካ ሚሲዮኖች  የሰሩት ት/ቤትና ክሊኒክ አለ፡፡ ትምህርት ቤቱ አለ፡፡ ክሊኒኩም እየሠራ ነው፡፡ አሰላን ለማልማት በተቋቋመ ኮሚቴ ሳገለግል በነበረ ጊዜ በየአካባቢያችን እንድንሠራ ሃሳብ ስናቀርብ ነበር ቦታውን የሰጡኝ፡፡ የሚሲዮኖቹን ቤቶች እንደ አዲስ አሰርቼአቸዋለሁ፡፡ የውሃ መጠጥ ፕሮጀክቱን ጀምር ሲሉኝም ግንባታዬን በፕላኑ መሠረት አስቃኝቼ ሥራ ጀመርኩ፡፡ በኋላ ሙሉ ለሙሉ ቦታው ተወሰደ፡፡፡ ጉዳዩን እስከ ኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት በመውሰድ ስሟገት ቆይቻለሁ፡፡ አትሌቶች በቆጂን አስጠርተዋታል፡፡ እኛ ደግሞ የተፈጥሮ ሃብቷን እንድትጠቀምበትና ዓለምአቀፍ ገበያ እንዲኖራት አስበናል፡፡ ተስፋ አልቆረጥኩም፡፡ አሁንም ድረስ ቦታውን ለማስለቀቅ እየጣርኩ ነው፡፡ ቤተሰቦቼ ነዋሪነታቸው በቦስተን በመሆኑ ወደ አሜሪካ መመላለስ አለብኝ፡፡ ግን ተስፋ አልቆርጥም፡፡ በአገሬ እያከናወንኩ ባለሁት የኢንቨስትመንት ስራዎች ላይ ወደ ኋላ ማለት አልፈልግም፡፡ የምፈልገው ሁሉንም እንቅፋቶች  በማሸነፍ ዕቅዴን ማሳካት ነው፡፡

የኢትዮጵያውያን ተጨዋቾችና ደጋፊዎች የበጐ አድራጐት ድርጅት መቼና በምን ዓላማ ተቋቋመ? ምን በመስራት ላይ ናችሁ?

የበጐ አድራጐት ድርጅቱ ከሦስት ዓመት በፊት የተቋቋመ ነው፡፡ ዓላማውም በኢትዮጵያ ውስጥ ከዚህ በፊት በጨዋታ ላይ አሳልፈው መጨረሻ ላይ በሚታመሙበትና በሚጐዱበት ጊዜ በቂ ገቢ ስለሌላቸው ችግር ውስጥ የወደቁ ወገኖችን የሚታደግ ነው፡፡ ድርጅቱ መረዳት ያለባቸውን ወገኖች አፈላልጎ እና ያለባቸውን ችግር አረጋግጦ የህክምና እና የገንዘብ እርዳታ በመስጠት ድጋፍ የሚያደርግ ሲሆን ይህን ተግባር በተለያዩ የገቢ ማሰባሰብ መንገዶች በማጠናከር እየሰራ ነው፡፡ የበጎ አድራጎት ድርጅቱን የሚመራ የስራ አመራር ኮሚቴ አለ፡፡ በስራ አስኪያጅነት የሚመራው የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንና የመድን ክለብ ተጨዋች የነበረው አብዲ ሰይድ ሲሆን  ምክትሉ ደግሞ በሎስ አንጀለስ ከተማ የሚኖረውና የእርሻ ሰብልና የብሔራዊ ቡድን  የቀድሞ ተጨዋች የነበረው መንግስቱ ሁሴን ነው፡፡ በፀሃፊነት እየሰራ የሚገኘው የቀድሞው የቅዱስ ጊዮርጊስ ግብ ጠባቂ ታደሰ ተክለፃዲቅ ነው፡፡ ድርጅቱ ከተቋቋመ ሦስት ዓመት ቢሆንም ጥቂት የማይባሉ ተግባራትን አከናውኗል፡፡ የመጀመሪያው አንድ በኬንያ በችግርና በጉዳት ላይ የነበረ የብሔራዊ ቡድን ተጨዋች ወደ አሜሪካ ወስዶ ለማሳከምና ለማቋቋም መቻሉ ነው፡፡ በድሉ የሚባለውን የቀድሞ የምድር ጦር ተጨዋች ከታመመበት ጊዜ ጀምሮ፣ በየወሩ የህክምና እና የኑሮ ወጭዎችን በመደገፍ ከህመሙ  እንዲያገግግም እያደረግን ነው፡፡ በተጨማሪ ሌሎች ጉዳት ያለባቸው እና በአቅም ማነስ የተቸገሩ ስፖርተኞችን በየዓመት በዓሉ የገንዘብ እርዳታ  እየሰጠን እየደገፍን ነው፡፡ አሁን በቅርቡ ደግሞ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ተጨዋች የነበረችውን ብዙአየሁ ጀምበሩን እየደገፍናት ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት ለአንድ ተጨዋች ተመሳሳይ ድጋፍ እንዲሰጥ ተጠይቀን 10ሺ ብር ረድተናል፡፡  ኢትዮጵያውያን ስፖርተኞች ያለባቸውን ችግር ድሮ ተጨዋች ከነበርኩበት ጊዜ ጀምሮ አውቀዋለሁ፡፡ ተጨዋቾችና ስፖርተኞች በውድድሮች ሲሳተፉ ዋስትና አልነበራቸውም፡፡ ወደፊት ምን እንሆናለን ብለው የማሰቡን ነገርም አያውቁትም፡፡  እናም ከስፖርቱ ሲገለሉና በደረሰባቸው ጉዳት ከተወዳዳሪነት ወጥተው በስፖርተኛነታቸው የሚያገኙት ገቢ ሲቋረጥባቸው ለከፍተኛ ችግር ይጋለጣሉ፡፡ “ለወገን ደራሽ ወገን” ነው በሚል የቀድሞ ስፖርተኞች ሊገጥማቸው የሚችለውን ችግር በቅርብ ስለምናውቀው፣ የምንችለውን በመርዳት ልንታደጋቸው እንፈልጋለን፡፡  ኢትዮጵያ ውስጥ ባቋቋምነው ኮሚቴ፣ የበጐ አድራጐት ድርጅቱን እያጠናከርን ነው፡፡ መረዳት ያለባቸውን ስፖርተኞች ፈልገንና ያለባቸው ችግር አረጋግጠን ለመርዳት እንሞክራለን፡፡

የበጐ አድራጐት ድርጅቱ የገንዘብ ምንጭ ምንድነው?

በአሜሪካ የምንኖር የቀድሞ እግር ኳስ ተጨዋቾች፣ ስፖርተኞችና ደጋፊዎች በያለንበት ሆነን በመሰረትናቸው ማህበራት በየወሩ መዋጮ እንሰበስባለን፡፡ በየዓመቱ በሚዘጋጀው የስፖርትና የባህል ፌስቲቫል ላይም በተፈቀዱልን ቦታዎች ለድርጅታችን የተለያዩ የገቢ ማግኛ ስራዎችን እንሠራለን፡፡  ወደፊት ደግሞ ስፖርተኞቹ በዚህ ድርጅት በቋሚነት የሚረዱበትን ሁኔታ ለመፍጠር ድርጅቱን በፋውንዴሽን ደረጃ አሳድገን ለመስራት በስፋት እንቅስቃሴ ማድረግ ጀምረናል፡፡

 

 

Read 11485 times Last modified on Saturday, 17 March 2012 11:38

Latest from