Saturday, 31 December 2016 11:25

‹‹ንስሓ ከኃጢአት፣ ውኃ ከእድፍ ያፀዳል!››

Written by 
Rate this item
(13 votes)

 ከዕለታት አንድ ቀን አንዲት ቀበሮ፣ በአንድ ገበሬ ግቢ እየመጣችና የሚያረባቸውን ዶሮዎች እየሰረቀች በጣም ታስቸግራለች፡፡
ገበሬው ለፍቶ ለፍቶ ለቀበሮ መቀለብ ሲሆንበት፣ ከሚስቱ ጋር ለመማከር ይወስንና፤
‹‹ሰማሽ ወይ ውዴ?››
‹‹አቤት ጌታዬ››
‹‹የዚችን የቀበሮ ነገር ምን ብናደርግ ይሻላል?››
‹እኔም ግራ- እየገባኝ ምን እናድርግ ልልህ ነበርኮ››
‹‹አንቺ ምን አሳብ አለሽ?››
‹‹እኔማ ሠፈሩን እንረብሻለን ብዬ ፈርቼ ነው እንጂ፤ መሳሪያ እያለህ አንድ ቀበሮ መግደል ምን ችግር ነበረው?››
‹‹አይ ያሉትን ይበሉ እንጂ ዕውነትም ጠመንጃዬን ወልውዬ አድፍጩ ብጠብቃት አታመልጠኝም›› አለ ፍርጥም ብሎ፡፡
‹‹ግን  እንዲህ ብናረግስ?››
‹‹ምን?››
‹‹ለሰፈሩ አለቃ ብናሳውቅ? ሰውም ጥይት ሲሰማ እንዳይሸበር፣ ለሊቀ መንበሩ ብንነግር?››
‹‹ደግ ሀሳብ አመጣሽ፡፡ አሁኑኑ እነግረዋለሁ፡፡›› አለና ወደ ሊቀ መንበሩ ቢሮ ሄደ፡፡
ሊቀመንበሩ ግን ሀሳቡን አልተቀበለውም፡፡ ይልቁንም፤
‹‹ለምን በወጥመድ አትይዛትም?›› ሲል ጠየቀው፤
‹‹ወጥመድ የለኝም››
‹‹እኔ እሰጥሃለሁ፡፡››
በዚሁ በወጥመዱ ሀሳብ ተስማሙና፣ በገብሬው ወጥመዱን ተረከበ፡፡
ማታም ቀበሮዋ መግቢያ ላይ ወጥመዱን አስቀመጠና መጠበቅ ጀመረ፡፡ ወጥመዱን ያልጠረጠረችው ቀበሮ ዘው ብላ ገባች፡፡ ተያዘች፡፡
ገበሬው በጣም ተደሰተ፡፡ በምን እንደሚቀጣ ያሰላሰለ ጀመር፡፡ በመጨረሻ…
‹‹እንዲያ ስትጫወትብኝ… እንደከረመች በፍፁም አልምራትም›› አለ፡፡
ከዚያም ጭራዋ ላይ ጭድ አሰረና እሳት ለቀቀባት፡፡ ከወጥመዱ አውጥቶም ወረወራት። ቀበሮም ቃጠሎው ሲበዛባት… በአቅራቢያው ወደሚገኘው የገበሬው የበቆሎ እርሻ ገባች፡፡ በቆሎው የደረሰ አዝመራ ነው፡፡ በእሳት ተያያዘ፡፡ ሙሉ በሙሉ ነደደ፡፡
*   *   *
ቂም በቀል የሁለት-ወገን-ስለት አለው፤ ይላሉ ፈረንጆች፡፡ ለሌላው የሳሉት ሰይፍ ወደ ራስ ሊመጣ እንደሚችል ማስተዋል ጥበበኝነት ነው፡፡ ክፋት ማቆሚያ የለውም፡፡ የጥፋተኝነት ስሜቱም አዕምሮን ከመነቆር አይገላገልም፡፡ ‹‹ዳባ ራሱን ስለት ድጉሡን›› ማለት ነው- በአማርኛ አገራዊ እነጋገር፡፡ በሀገራችን የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ዛሬ አንገብጋቢ እሳት ሆኗል- (Burning Issue እንዲሉ) በመልካም አስተዳደር ጉድለት፣ በሥልጣን መባለግ፣ የሀገርንና የህዝብን ጥቅም ለራስ ማዋል፣ ፖለቲካን የግል ንብረት በማድረግ ማስፈራሪያና ‹‹እኔ ብቻ ነኝ አድራጊ ፈጣሪ›› ማለት ወዘተ እጅግ ጎጂ ባህል ሆነው ከርመዋል፡፡ ያደረጉት ነገር በተጨባጭ ስህተት መሆኑ ታውቆ ለፍርድ ይቅረቡ የተባሉ አሉ፡፡ ይበል የተባለ እርምጃ መሆኑን የማይስማማ ያለ አይመስለንም፡፡ ሆኖም ዕውነቱን ፈልፍሎ የማውጣት ሥራ፣ ያለ ምንም ወገንተኝነት ህሊናዊ ንፅህናን የመጠበቁ ኃላፊነት እና የግብረ-አበሮችን ሰንሰለት መርምሮ፣ ፈለጉን የማግኘትን የመበጠስ ዕልህ - አስጨራሽ ጉዞ ሳያሰልሱ የመጓዝን ሂደት ከወዲሁ አስቦና አስልቶ መንቀሳቀስ ወሳኝ ነው። ጅምሮች በአጭር እንዳይቀጩ ከመርማሪ ፖሊስ እስከ ፍትህ አካላት የተባበረ ቅኝት ያስፈልጋቸዋል። ዲሞክራሲ ላጲስ አይደለም፤ ተጋጋዥ እንጂ ተጠፋፊ አይደሉም፡፡ ፖለቲካ የኢኮኖሚ ዕምቅ መገለጫ (Concentrated Expression) እንጂ ሌላ ላንቃ አይደለም፡፡ ሀቀኝነት ሳይኖር ፍትሃዊነት መጎናፀፍ አይቻልም፡፡ ለማኅበራዊ ምስቅልቅልነት መፍትሄው የመንግስትና ህዝብ ተቀራርቦ ሀገራዊ መተሳሰብን መፍጠር እንጂ ‹‹መንግስት ነኝና ልፈራ ይገባኛል›› የሚል አመለካከትና ጉልበታዊ ተግባር አይደለም፡፡ በመንግስት ውስጥ ያሉና ህዝብን በመበደል የሚኩራሩ ወገኖች ጊዜያዊ ድል እንጂ ዘላቂ ወንበር አይኖራቸውም፡፡ ያም ሆኖ እኒህንም አካላት ለፍርድ ሲቀርቡ ያለአድልዎ ዳኝነት የሚሰጥ አካል ሊኖር ይገባል። ህጋዊ ፍርድ በሀቅ ላይ የተመረኮዘ እስከሆነ ድረስ የመልካም አስተዳደር አለመጓደልን የሚያፈካ ብርሀን አለ ማለትን ማመን እንጀምራለን፡፡
የመልካም አስተዳደር ጉዳይ፣ በመልካም አስተዳደር ጉድለት እንዳይጨናገፍ ብርቱ ጥረት ያስፈልጋል፡፡ ሀገራችን የሰው አስተሳሰብ ልማት ያሻታል፡፡ ጠቃሚ የሆነ ነው የምንለውን የመዋቅር ለውጥ ለማምጣት፣ እስከ ቻርተር ማሻሻል ስንዘልቅ ዞሮ ዞሮ ወሳኙ ሁነኛ የሰው ኃይል መሆኑን አንርሳ! ተለውጧል ተሻሽሏል ማለት ብቻ ሳይሆን ከዕውነታው ያልራቀ መፍትሄ መሆኑን ማረጋገጥ ቁልፍ ነገር ነው!
በማናቸውም ግለሰብ ፣ በግል ኢንቬስተሮች፣ በቢሮክራሲ አባላት በንግዱ ማህበረሰብ፣ በሲቪክ ማህበረሰብ አባላት ወዘተ ላይ የምንሰነዝራቸውን ሂሶች፣ ውንጀላዎችና ፍረጃዎች ስናስብ፣ እኛስ ራሳችንን እንዴት እንገመግማለን? እንዴት እንፈርጃለን? እንዴትስ ስህተታችንን እናምናለን? የሚለውን ወሳኝ ጉዳይ ልብ - እንበል! ለዚህ የሚበጀን ዘዴ “ንስሓ ከኃጢአት፣ ውኃ ከእድፍ ያፀዳል!” የሚለውን ምሳሌ ለሊት ተቀን ማሰብ እና ስራ ላይ ማዋል ነው!

Read 6452 times