Print this page
Saturday, 17 March 2012 09:08

መምህራኑ የደመወዝ ጭማሪውን “ክብር የሚነካ” ነው አሉ

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(9 votes)

ሰሞኑን ከአፀደ ህፃናት እስከ መሰናዶ ትምህርት ት/ቤት ለሚያስተምሩ መምህራን የተደረገውን የደመወዝ ስኬል ማሻሻያ በተመለከተ፣ መንግስት ጭማሪው የመምህርነትን ሙያ ክብር የሚያስጠብቅ ነው ሲል መግለጫ መስጠቱን ተከትሎ መምህራን ተቃውሞአቸውን እየገለፁ ነው፡፡ የደመወዝ ጭማሪው “ክብር የሚነካ ነው ብለዋል - መምህራኑ፡የአገሪቱን የአኗኗር ሁኔታና የወቅቱን የኑሮ ውድነት መሠረት ያደረገ የደመወዝ ጥያቄ ማቅረባቸውን የገለፁ መምህራን፤ ሰሞኑን የተደረገው ጭማሪ ግን በመምህራኑ ላይ የተሰነዘረ የንቀትና የማላገጥ እርምጃ ነው ሲሉ ነቅፈውታል፡፡

ተቃውሞውን ተከትሎ በኢህአዴግ ተወካዮች ስብሰባ ተጠርተው አለመሄዳቸውን የጠቆሙ መምህራኑ በስብሰባው አለመገኘታቸውንና ት/ቤቶቹ በስራ ገበታቸው ላይ እንዲገኙ ማስጠንቀቂያ መለጠፋቸውን ተናግረዋል፡፡አንድ ስማቸው እንዳይገለፅ የፈለጉ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ የኮልፌ ኮምፕርሄንሲቭ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት መምህር፤ የደመወዝ ጭማሪ ጥያቄው ለረጅም ጊዜ ሲቀርብ የቆየ እንደነበር አስታውሰው፤ መምህራኑ በተደጋጋሚ ላቀረቡት የጭማሪ ጥያቄ የተሰጣቸው ምላሽ ግን እጅግ አሣዛኝ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ለበርካታ ጊዜያት ላቀረብነው የደመወዝ ስኬል ማሻሻያ ጥያቄ የዚህ ዓይነት ምላሽ እየሰጡ መምህሩ በትምህርት ጥራቱ ላይ ለውጥ እንዲያመጣ መጠበቁ ሞኝነት ነው ብለዋል - መምህሩ፡፡ በኮልፌ ኮምፕርሄንሲቭ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ውስጥ ያሉ መምህራንም በደመወዝ ጭማሪው ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ እንዳላቸው የተናገሩት እኒሁ መምህር፤ በተለያዩ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን የደመወዝ ጭማሪውን አስመልክቶ የተሰጠው መግለጫ የተሣሣተና ከእውነት የራቀ በመሆኑ በአስቸኳይ ማስተባበያ እንዲሰጥበት መጠየቃቸውን ገልፀውልናል፡፡

ተቃውሞአችንን ለክፍለ ከተማው ትምህርት ቢሮ አቅርበናል ያሉት መምህሩ፤ መንግስት ያደረገውን የደመወዝ ማሻሻያ በድጋሚ እንዲመለከተውም ጥያቄ ማቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡ ጥያቄው እስከ ፊታችን ሰኞ ምላሽ እንዲያገኝ አጥብቀው መጠየቃቸውን ጠቁመው፤ ይህ ሣይደረግ ቢቀር ግን ሥራቸውን ለማቆም እንደሚገደዱ መግለፃቸውን ገልፀዋል፡፡

የደመወዝ ማሻሻያው ከተደረገ በኋላ መንግስት በሰጠው መግለጫ፤ ጭማሪው ከመንግስት የመክፈል አቅምና ከአጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ ጋር በተገናዘበ መልኩ የተደረገ መሆኑን ያስታወቀ ሲሆን በደመወዝ ማሻሻያው መሰረትም ለዲፕሎማ ምሩቅ መምህር የስልሣ አንድ ብር፣ ለድግሪ ምሩቅ ደግም የሰባ ሶስት ብር ጭማሪ ተደርጓል፡፡ ቀደም ባለው የደመወዝ ስኬል፤ 1172 ብር ያገኝ የነበረው የዲፕሎማ ምሩቅ መምህር በአዲሱ ጭማሪ 1233 ብር ሲከፈለው፤ 1571 ብር ይከፈለው የነበረው የመጀመርያ ድግሪ ምሩቅ መምህር አሁን 1644 ብር እንደሚያገኝ ታውቋል፡፡

በአሁኑ ጭማሪ መምህሩ ከሌላው የሲቪል ሰርቪስ ሠራተኛ አንድ እርከን ተጨምሮለት ወደ ሰባት እርከን ከፍ እንዲል መደረጉ ቢነገርም፤ መምህራኑ ወደ ዘጠኝ እርከን ሊያድግልን ይገባል ይላሉ፡

ባለፈው ረቡዕ በተደረገው የደመወዝ ጭማሪ ላይ መምህራኑ ተቃውሞ ማንሣታቸውን ተከትሎ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የኢህአዴግ ባለስልጣናት መምህራኑን ለማወያየት በየትምህርት ቤቶቹ መገኘታቸውን የተናገሩ አንድ መምህር፤ በአብዛኛዎቹ ት/ቤቶች መምህራን ባለመገኘታቸው ውይይቱ ሳይካሄድ ቀርቷል ብለዋል፡፡ በኮልፌ ክፍለ ከተማ የሚገኘው የሚሊኒየም ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ውስጥ ካሉ ከ170 በላይ መምህራን ውስጥ በውይይቱ ላይ ለመሣተፍ የመጣ አንድም መምህር ባለመገኘቱ የማወያየት ጥረቱ ሳይሳካ እንደቀረ ምንጮች ተናግረዋል፡፡ መምህራኑ በስራ ገበታቸውም ላይ ባለመገኘታቸው ተማሪዎች ወደየቤታቸው መመለሳቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

መምህራኑ ወደ ስራ ገበታቸው እንዲመለሱና ጥያቄያቸውን በአግባቡ እንዲያቀርቡ ት/ቤቱ በማስታወቂያ የገለፀ ሲሆን በትላንትናው እለት አብዛኛዎቹ መምህራን ወደ ሥራ ገበታቸው ተመልሰው መደበኛ ትምህርት ሲሰጥ እንደዋለ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

በአየር ጤናና በመድሃኒያለም ት/ቤቶችም ተመሳሳይ ጥያቄዎች በመምህራኑ እንደተነሱና አብዛኛዎቹ መምህራን በተደረገው የደመወዝ ጭማሪ ማዘናቸውን በትምህርት ቤቶቹ ያነጋገርናቸው መምህራን ገልፀውልናል፡፡

የመምህራን ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ዮሐንስ በንቲ ስለጉዳዩ ማብራሪያ እንዲሰጡን በስልክ ብንጠይቃቸውም ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡ የማህበሩ ፀሐፊ አቶ መንግስቱ በበኩላቸው፣ በጉዳዩ ላይ ማበራሪያ መስጠት የሚችሉት ፕሬዚዳንቱ መሆናቸውን ጠቁመው እሳቸው ሳይወክሏቸው ለመናገር እንደሚቸገሩ ገልፀውልናል፡፡

 

 

Read 15705 times Last modified on Saturday, 17 March 2012 11:34