Monday, 12 December 2016 12:11

ከአንጋፋ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር ጋር የተደረገ ታሪካዊ ቃለ-ምልልስ!??

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(8 votes)

ጋዜጠኛው በአገሪቱ የተከሰተውን ፖለቲካዊ ቀውስ አስመልክቶ ለሚሰራበት የነጻ ፕሬስ ጋዜጣ ----- (በነጻነት ለማይንቀሳቀስ ፕሬስ “ነጻ ፕሬስ” ብሎ ስም? ግን እኮ  “ሆት ዶግ” ውስጥም “ዶግ” የለም፤ ከውሻ ሥጋ አይደለም የሚሰራው፡፡ ለነገሩ “ሃም በርገር” ውስጥም መቼ “ሃም” አለ? ከበሬ ስጋ እኮ ነው የሚሰራው” በራሴ ጊዜ ጥያቄዬን ተውኩት!!)
አዎ ጋዜጠኛው ሚዛናዊ ዘገባ ለመሥራት ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ለማነጋገር እየሞከረ ነው፡፡ (“ባለድርሻ አካላት” ለምን የእቃ ስም እንደሚመስለኝ አላውቅም! የእንግሊዝኛው ቃል “ስቴክሆልደር” ደግሞ “የአክስዮን ድርሻ”ይመስለኛል!) እናላችሁ ጋዜጠኛው ----- የሁሉንም ወገን ሰብስቦ የቀረው የአንድ አንጋፋ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ሃሳብ ብቻ ነው፡፡ (ኤዲተሩ ነው እኚህ ተቃዋሚ እንዲካተቱ የጎተጎተው!) ጋዜጠኛው የተቃዋሚ መሪውን አነጋግሯቸው ባያውቅም ቅሬታ አልተሰማውም ነበር፡፡ ችግሩ ግን ደጋግሞ ሊደውልላቸው ቢሞክርም ሰውየው ሞባይል ሥልካቸውን ጥርቅም አድርገው ዘግተውታል፡፡ “ለሚዲያ አክሰሰብል አለመሆን ያስቀጣል!” የምትል አዲስ ህግ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ብቻ ቢረቀቅ ብሎ አሰበ - መፍትሄ የመሰለውን፡፡ (እንኳን የተቃዋሚ፣ የገዢው ፓርቲ/የመንግስት ሹመኛስ መቼ “አክሰሰብል” ሆኖ ያውቃል?) እቺን ሃሳብ ትንሽ ሲያውጠነጥን በአንጋፋው የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ላይ ከማምረር ራሱን ገታ፡፡ “የባሰ አለ አገርህን አትልቀቅ” የሚለው የአበው ተረት ሳይጠቅመው አልቀረም፡፡ ወደ ተቃዋሚ መሪው የሞባይል ስልክ ለ10ኛ ጊዜ መታ። በልቡ ውስጥ ተስፋ ሲላወስ ተሰማው፡፡ ቢያንስ የተጠረቀመው ስልክ ተከፍቷል፤ግን ቢዚ ነው። (የተዘጋ ስልክ - switched off- እና “አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ” ለምን እንደተመሳሰሉበት ግራ ገባው!) አሰበ፡፡ ብዙ አሰበ። መመሳሰያቸው አልከሰትልህ አለው፡፡ ጋዜጣው ማተሚያ ቤት የሚገባበት ሰዓት እየተቃረበ መሆኑን የሞባይሉ ጊዜ መቁጠሪያ ጠቆመው፡፡ ሞባይሉን ከፍቶ ሪዳይል አደረገ - የአንጋፋ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪውን ስልክ ቄጥር፡፡ ተመልሶ ተጠርቅሟል - switched off!! ጆሮውን ማመን አቃተው፡፡ ንዴቴ ጣራ ነካ፡፡ (አገር ቀውስ ላይ ሆና አንጋፋ የተቃዋሚ መሪ እንዴት ሞባይሉን ዘግቶ ይቀመጣል?) ለነገሩ ህዝብ እዚህ በተቃውሞና በአመጽ አገር ሲያምስ፣ባህር ተሻግረው በአሜሪካና አውሮፓ ከዳያስፖራ ደጋፊዎቻቸው ጋር የሚወያዩ የተቃዋሚ መሪዎች ነበሩ፡፡ (ህዝቡን ጥለው የት ነው የሚሮጡት?)    
ፖለቲከኞች ብግን ሲያደርጉት የልብ የሚያደርስ ተረብ ወይም አሽሙር ምሱ ነው፡፡ ንዴቱን በረድ ያደርግለታል፡፡ (የ”ፓርታይም ፖለቲከኞች” ተጫወቱብን እኮ!!) ጋዜጠኛው ሌላው የሚጎዳው የአገር ፍቅሩ ነው፡፡ ልክ የለውም፡፡ አንዳንድ ወዳጆቹ እንደ “በሽታ” ይቆጥሩበታል፡፡ አርበኝነቱን ፋርነት የሚያደርጉበት አሉ፡፡   እሱ ግን በአገር ከመጡበት ወዲያ ወዲህ አያውቅም ለተቃዋሚም ለገዢውም አይመለስም፡፡ “የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች በስልጣን ተሻኮቱ፣ በማህተም ማስቀረጽ ተካሰሱ፣ ጠ/ሚኒስትሩ ጣልቃ ገብተው ያሸማግሉን አሉ፣ ሊ/ቀመንበሩ ጠ/ጉባኤ አልጠራም አለ-” ብግን የሚያደርጉት የዜና ዓይነቶች ናቸው፡፡ አንዳንዴ ከአቅም በላይ ሲሆንበት፣ ”የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ በእነዚህ ላይ ነበር!” ይልና ተንፈስ ይላል፡፡
ጋዜጠኛው የመጨረሻ ሙከራ ሊያደርግ ሞባይሉን አነሳ፡፡ ጋዜጣው ወደ ማተሚያ ቤት ሊላክ የቀረው  1 ሰዓት ብቻ ነው፡፡ የሚጠበቀው ደግሞ የሱ ዘገባ ነው፡፡ የአገሪቱን ፖለቲካዊ ቀውስ የሚመለከት ዘገባ!! (“የፖለቲካዊ ቀውስ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚሽን” መቋቋም አለበት!) ወደ አንጋፋው የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ  እየደወለ፣ ከአዕምሮው አንድ ጥግ ከፖለቲካ ቀውስ የተለየ ሽንቁር ሃሳብ ብቅ አለ። (“የግል ጋዜጦች እዛው ቢሮአቸው፣ዝግጅቱንም ህትመቱንም አጠናቀው ወደ ገበያ የማውጣት ወግ የሚደርሳቸው መቼ ይሆን?”) ሽንቁሩ ሃሳብ በአጭር ነው የተቀጨው። ጋዜጠኛው ልቡ ጆሮ ሆኖ፣ ከወዲያኛው የሞባይል መስመሩ ጫፍ ድምጽ እየጠበቀ ነው፡፡ በ20ኛው ሙከራ፣ ከ3 ሰዓት ተደጋጋሚ ሙከራ በኋላ የሰውየው ሞባይል መጥራት በመጀመሩ፣ ጉጉቱና እልሁ በእጅጉ ጨምሯል - የ”ነጻው ፕሬስ” ጋዜጠኛ። (እንደ “ነጻ ፕሬስ”፣ “ነጻ ተቃዋሚ ፓርቲ” ለምን የለም - ቢያንስ ስሙ ??)  
ጠርቶ ጠርቶ እንዳይዘጋ በልቡ ጸሎት ጀምሯል። ሳይጠበቅ ስልኩ ተነሳ፡፡
 “ሃሎ---ሃሎ----ጤና ይስጥልኝ------ከጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ነው ---”
ጋዜጠኛው ደስ ብሎታል፡፡ ጸሎቱም ስለቱም የሰመረለት ይመስላል፡፡  
“አቶ ደሳለኝ -----” የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው፣ ጋዜጠኛውን አቋረጡትና፤
“”የተከበሩ”----ለ5 ዓመት የፓርላማ አባል ነበርኩ” የአጠራር ማረሚያ አደረጉ፡፡
ይቅርታ የተከበሩ አቶ ደሳለኝ------” ሰውየው በድጋሚ አቋረጡት፡፡
“ዶክተር---- “
“ይቅርታ የተከበሩ ዶ/ር ደሳለኝ----” የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው፣በጋዜጠኛው አጠራር ተደስተዋል፡፡ ግን መረጃ ሊጨምሩለት ወደዱ፡፡
“እንደ ሌላው በአንድ መስክ ብቻ እንዳልመስልህ---- ዳይቨርሲፋይድ ነኝ------መጀመሪያ በገጠር ኤለመንታሪ ስኩል ሳይማር ያስተማረኝን ህዝብ አስተምሬአለሁ-----ለ10 ዓመት----ከዚያ በኮተቤ መምህራን ኮሌጅ 8 ዓመት አስተማርኩ----”
“በጣም ትልቅ ነገር ነው ዶ/ር-----” ጋዜጠኛው አደናንቆ ወደ ጉዳዩ ሊያስገባቸው ነበር ሃሳቡ፡፡   ግን ----
 “የተከበሩ---” የሚለውን ለማስታወሰ አናጠቡት፡፡
“በጣም ይቅርታ ቸኩዬ እኮ ነው--- የተከበሩ ዶ/ር ደሳለኝ----”
“ኤክሰለንት!---አየህ የመጀመሪያ ድግሪዬን በሶሻል ሳይንስ ነው ያገኘሁት---ሁለተኛ ድግሪዬን በፎረስትሪ----ዶክትሬቴን በፖለቲካል ሳይንስ----እኔ እንደሌላው በአንድ ዘርፍ ችክ አላልኩም----ዳይቨርሲፋይድ ነኝ!”
“በጣም ግሩም ነው የተከበሩ ዶ/ር ደሳለኝ---እና በፖለቲካ ቀውሱ---”
 ጋዜጠኛው ትዕግስቱ ተሟጦ በማለቁ፣ስልኩን ጆሮአቸው ላይ ቢዘጋው ሁሉ በወደደ ነበር፡፡ ግን አላደረገውም፡፡ አንጋፋው ፖለቲከኛ ቀጠሉ፡-
“ይኸውልህ ጋዜጠኛ---የምነግርህን ሁሉ እንድትጽፍ እፈልጋለሁ---የትምህርት መስኮቼን ------የሰራሁባቸውን ----የገጠሯ ኤለመንታሪ ስኩል በተለይ መቅረት የለባትም----በአገር ሃብት ነው የተማርኩት -----በህዝብ ገንዘብ---ስለዚህ ህዝቡ ይወቀው”
“ችግር የለም ዶ/ር ---- አሁን ወደ ጥያቄው እንግባ-----”
“ስንቴ ልንገርህ--”የተከበሩ”--- ክብሩን ያገኘሁት እኮ ከሜዳ አይደለም---- ከህዝቡ ነው----ህዝቡ መርጦ ነው ፓርላማ ያስገባኝ---እኔን ማክበር የመረጠኝን ህዝብ ማክበር ነው”
“በትክክል!አሁን ወደ ጥያቄው እንግባ----ዴድላይን አለብኝ---ማተሚያ ቤት----”
“የዘመኑ ጋዜጠኞች ትገርሙኛላችሁ-----ያልተሟላ መረጃ ይዛችሁ መሮጥ ነው---ዶክትሬቱን ከየት አገኘው ብለህ ልትጽፈው ነው? ከምስራቅ ጀርመን ነው---ደሞ የጎልድ ሜዳልያ ተሸላሚ ነኝ----ከዚያ ስመጣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለ21 ዓመታት አስተምሬአለሁ----የመጨረሻዎቹን 10 ዓመታት የዲፓርትመንቱ ሄድ ነበርኩ---በሥራ መስክም ዳይቨርሲፋይድ ነኝ----”
“ይሄንማ ሁሉም ያውቃል----የተቃዋሚ ፓርቲም አመራር ነዎት-----”
ቀጠሉ ፖለቲከኛው፡፡
“በፖለቲካውም እኮ ዳይቨርሲፋይድ ነኝ----የተማሪዎች አብዮት መሪ ነበርኩ----የሰብአዊ መብት ተሟጋች------አክቲቪስት----የፓርላማ አባል----የተቃዋሚ ፓርቲ መስራችና መሪ----የፓን አፍሪካ ፓርላማ ቋሚ አባልም ነኝ ---- ነግሬሃለሁ ሁሉንም በዝርዝር እንድትጽፈው--- “
“እጽፈዋለሁ---እጽፈዋለሁ---ዶ/ር ----- ህዝቡ እንዲከበርለት ያነሳቸው ጥያቄዎች----ውይ-- የተከበሩ ዶ/ር-- መቅረጸ ድምጼ ባትሪው ሞቷል--”
ጋዜጠኛው ከአንጋፋው የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ጋር በከንቱ ያባከነው ጊዜ በጣም እያንገበገበው፡- “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ያልተጠየቁትን የሚዘባርቁ ፖለቲከኞችን የሚቀጣበት አንቀጽ የለውም እንዴ!?” አለ - ለራሱ፡፡

Read 2823 times