Monday, 12 December 2016 11:59

‹‹ሹም ለሹም ይጎራረሳሉ፤ድሀ ለድሀ ይላቀሳሉ!››

Written by 
Rate this item
(11 votes)

‹‹የፍራየርስ ክለብ ኢንሳይክሎፒዲያ ኦፍ ጆክስ›› ካካተታቸው ቀልድ አከል ቁምነገሮች ውስጥ  የሚከተለው ይገኝበታል፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ሚስተር ሁበርት ሐምፍሬይ የተባሉ ምሁር ለአንድ የዩኒቨርስቲ ተማሪ የመጨረሻ የጥናት ወረቀት መካር (advisor) ሆነው ይቀጠራሉ፡፡ የመካርነቱን ሥራ በታላቅ ደስታ ነበር የተቀበሉት፡፡ እንዲህ ብለው፡-
‹‹በዕውነቱ ወጣት ምሁራን ለወግ ማዕረግ ይበቁ ዘንድ የመጨረሻ የጥናት ወረቀታቸውን ሲያቀርቡ ማገዝና ሙያዊ ክህሎታቸውን ማብቃት፣ ለእኔ ታላቅ ደስታና ዓይነተኛ ክብር ነው፡፡ በተቻለኝ አቅም ዕውቀቴን ላጋራው ፍቃደኛ መሆኔን እገልፃለሁ!›››
ሚስተር ሐምፍሬይ ተማሪውን መርዳት ቀጠሉ፡፡ ተማሪውም በትጋት መሥራቱን ቀጠለ፡፡
ወረቀቱን የማቅረቢያው ወቅት ሲደርስ ተማሪው በቆንጆ ሁኔታ የተጠረዘ ፅሑፉን ይዞ ሚስተር ሐምፍሬይ ዘንድ ከች አለ፡፡
‹‹ሚስተር ሐምፍሬይ፤ በወረቀቴ ላይ አስተያየትዎን ይሰጡኝ ዘንድ ይሄው መጥቻለሁ፡፡ ምን ይሉኝ ይሆን?››
ሚስተር ሐምፍሬይም፤
‹‹መልካም፡፡ አየውና መልስ እነግርሃለሁ›› አሉና አሰናበቱት፡፡ ተማሪው አመስግኖ ከቢሮአቸው ወጣ፡፡
ሁለት ወር አለፈ፡፡ ከሚስተር ሐምፍሬይ በኩል ምንም የተሰማ ነገር የለም፡፡ ስለዚህ ተማሪው ቢሮአቸው ሄደ፡፡
ከዚያም፤ ‹‹ሚስተር ሐምፍሬይ፤ ወረቀቴን እንዴት አገኙት?” ሲል ጠየቃቸው፡፡
ሚስተር ሐምፍሬይም፤
‹‹እርግጠኛ ነህ ይሄ የመጨረሻውና ያለቀለት ሥራህ ነው? ዕውቀትህ ይሄ ብቻ ነው?›› ሲሉ ትኩር ብለው እያዩት ጠየቁት፡፡
ተማሪው  ቅር ያላቸው ነገር እንዳለ በመገመት፤
‹‹አንዴ ወስጄ ልየው?›› አለ፡፡
‹‹ይሻላል›› አሉት፡፡
ተሜ፤ በድጋሚ መሥራቱ እየከፋው የወረቀቱን ጥራዝ ተቀብሎ ሄደ፡፡ ፕሮጄክቱን አንዴ ሊከልሰው ነው፡፡
ከሁለት ወራት በኋላ ተማሪው የከለሰውን ወረቀት አጠናቅሮ፣ ቀንብቦ፣ ለሚስተር ሐምፍሬይ አምጥቶ አስረከባቸው፡፡ ሁለት ወር አለፈ፡፡ ከሚስተር ሐምፍሬይ በኩል ምንም ወሬ የለም፡፡ ስለዚህ ‹‹ቢሮአቸው ብሄድ ይሻላል›› ብሎ ወደዚያው አመራ፡፡ እንደደረሰም፤
‹‹እንዴት ሆነልኝ፤ ሚስተር ሐምፍሬይ?›› ሲል ጠየቀ፡፡
ሚስተር ሐምፍሬይ ግን፤
‹‹በቃ ይሄው ብቻ ነው ችሎታህ? እንደገና ቢሠራ ይሻላል›› አሉት፡፡
‹‹እሺ፤ የመጨረሻ ሙከራ ላድርግ›› አለና ተሜ፤ እየከፋው ወደ ቤቱ ሄደ፡፡ በጣም ቅር እያለው በነጋታው ጥናት ክፍሉ ገብቶ ለሶስተኛ ጊዜ ወረቀቱን ፃፈና፤
‹‹አሁንስ ‹አልቀበልም› ቢሉኝ፤ የራሳቸው ጉዳይ፤ እተወዋለሁ!›› እያለ ወደ ሚስተር ሐምፍሬይ ቢሮ ሄደና አስረከባቸው፡፡
ሚስተር ሐምፍሬይም፤
‹‹በቃ ይሄ ነው የመጨረሻ ሥራህ?›› አሉት፡፡
‹‹አዎ፤ ከዚህ በላይ ምንም የምጨምረው ነገር የለም›› አላቸው፤ ፍርጥም ብሎ፡፡
ቀጥሎም
‹‹አንዴ ብቻ ሳይሆን ሁለት ሶስቴ ተመራምሬበታለሁ፡፡ ሁለት ሶስት ዓይነት ትንተና ተንትኛለሁ፡፡ ደጋግሜም ፅፌዋለሁ፡፡ ይኸው ነው!››
ሚስተር ሐምፍሬይ ትኩር ብለው ካስተዋሉት በኋላ፤
‹‹ጥሩ! እንግዲያው ከሰጠኸኝ ወረቀቶች ሁሉ ለመጀመሪያ ጊዜ ይሄኛውን አነበዋለሁ!›› ብለው አሰናበቱት፡፡ ተሜ ወጣና፤
‹‹ወይኔ! እስከ ዛሬ አንዱንም ሳያነብቡ ነበር ለካ የሚያፈጉኝ!›› እያለ ሄደ፡፡
                                                          *    *    *
የሰውን ድካም ማቃለል የሚችሉ አመራሮችና ኃላፊዎች የየተቋማቱ ምሰሶዎች ናቸው፡፡ በአንፃሩ የሰው ድካም የማይሰማቸው ሰዎች፤ ሙሉ ልብ እንዳይኖራቸው የማያግዙ፣ የራሳቸውን መንገድ ብቻ የሚያሰላስሉና የመልካም አስተዳደር አካላት ያልሆኑ ግለሰቦች አሉ፡፡ ያልተገነዘቡት ነገር አለ፣ ለውጥ አሮጌውን ጥሎ አዲስ ይዞ እንደሚራመድ አዳዲስና ወጣት ኃይሎችን ያላቀፈ ዕድገት ወንዝ አይሻገርም፡፡ ከዚህም ጎን ለጎን የሲቪክ ማህበራትን ያላጠናከረና አዳዲስ እንዲፈጠሩ ያላገዘ የለውጥ ጉዞ፤ አገራዊ መግባባቶች፣ አገራዊ እርቆች፤ ቀና ውይይቶችና ሽምግልናዎች  የሚሰምሩት ሲቪል ማህበራት እንደ ልብ ሲንቀሳቀሱ ነው፡፡ አመራሮች ስለ ዕቅዳቸው የሚናገሩትና የሚገቡት ቃል የግብር-ይውጣ እንዳይደለ ማረጋገጥ ተገቢ ነው፡፡ የአመራር ለውጦች ሲደረጉ ከነበሩ ተጨባጭ የህዝብ ችግሮች ጋር በቅጡ የተሳሰሩና እነዚያን ችግሮች የሚፈቱ መሆን አለባቸው፡፡ አለበለዛ ‹‹ትሻልን ትቼ ትብስን አገባሁ›› የሚል ሥጋት ይፈጠራል፡፡ በተለይ ከሙስና ጋር ቁርኝነት ያላቸው የኃላፊነት ቦታዎች ብርቱ ጥንቃቄ ይጠይቃሉ። የቢሮክራሲና የደላሎች፣ የኤጀንሲዎች፣ የአስመጪና ላኪዎች ግንኙነት፣ ዛሬ ባገራችን ብዙ የተወራለት ስስ-ብልት ነው፡፡ ‹‹ዛር ልመና ሳይያዙ ገና›› ይሏል አበው፡፡ ከወዲሁ የነገሮችን አካሄድ ማጤንና መንቀሳቀስ ብልህነት ነው። ለትላንትና መልስ ለመስጠት፣ ዛሬም የቆምንበትን ሁኔታ አምርሮ መመርመር፣ የአዳዲስ ሹማምንት ሁሉ ብርቱ ኃላፊነት ነው፡፡
 አንዳንድ ፀሐፍት ስለ አንዳንድ ቢሮክራቶች መመሪያ ይህን ይላሉ፡፡
 ‹‹ ሀ-ኃላፊ ስትሆን ጠያቂና ተመራማሪ ምሰል
   ለ- ችግር ሲፈጠር የበታችህን ወክል (delegate)
   ሐ- ስትጠራጠር የማይገባ ነገር አጉተምትም፤ አነብንብ
   መ- የቢሮክራትነት ዋና ጥበብ ይሄው ነው››
ከዚህ ይሰውረን! ስንት ቢሮክራቶች ይህን አባዜ ተሸክመው ይሆን? ብሎ መጠየቅ የአባት ነው፡፡
በሌላ ወገን ደግሞ ስለ ፕሮጄክት ልዩ ልዩ ደረጃዎች ሲፅፉ ፡- ‹‹ አንደኛው የፕሮጄክት ደረጃ ወይም ምዕራፍ/
           ስለ ፕሮጄክቱ ሥራ መጓተት ነው፡፡ ሁለተኛው/
           ከግራ-መጋባት ነፃ መሆን ነው፡፡ ሦስተኛው/
           መሸማቀቅና መጨናነቅ መጀመር ነው፡፡
አራተኛ/ ጥፋተኛውን ፍለጋ መግባት ነው፡፡ የማነው ጥፋቱ? መባባል ነው፡፡ አምስተኛው/ ምንም ያላጠፋውን የዋህ ሰው እንዲቀጣ ማድረግ ነው፡፡ ስድስተኛውና የመጨረሻው በፕሮጄክቱ ሥራ ምንም ያልተሳተፉ ሰዎችን ማሞገስና ክብር ሰጥቶ ማወደስ ነው፡፡››
ከላይ የተጠቀሱት ጉዳዮች እኛም ጋ አሉ የምንል እራሳችንን መፈተሽ ነው፡፡ ሹማምንቶቻችን አገርና ህዝብን ያስቀድማሉ ወይ? ካላስቀደሙስ? ከዚህም ይሰውረን እንበል፡፡ ምክንያቱም የተለያዩ እርስ በርስ የሚግባቡ፣ የሚሞዳሞዱ ወዳጅ አመራሮች፤ የሆድ ለሆድ መርህ ኔት-ወርክ፤ አላቸው፡፡ መደጋገፊያ መረብ ነው፡፡ በዚያም ክፉኛ ይጠቃቀማሉ፡፡ ሀቀኛና ምስኪን ሠራተኞች ግን ላባቸውን አፍስሰው ሥራዎች እንዲሳኩና አገራችን ከድህነት እንድትወጣ ዕለት-ሰርክ ደፋ-ቀና ይላሉ፡፡ ዛሬ ሁኔታችን ይሄን መሳይ ነው፡፡ ‹‹ሹም ለሹም ይጎራረሳሉ፤ ድሀ ለድሀ ይላቀሳሉ›› የሚባለው ለዚህ ነው! ሹመትና ሽረት የተለመደ ነው፡፡ ትልቁ ቁም-ነገር የተሾመው ሹም፤ ብቁና ከተሻረው ሹም ስህተትና ጥፋት ምን ተማረ፤ የሚለው ነው! ‹‹ትላንትና ማታ ቤትህ ስትገባ የመታህ የድንጋይ እንቅፋት፣ ዛሬ ማታም ከደገመህ፤ ድንጋዩ አንተ ነህ›› የሚለውን የቻይናዎች አባባል አለመርሳት ነው! ሹመት የብቃት ማረጋገጫ ይሁን!!

Read 5537 times