Saturday, 10 March 2012 12:19

ቡናና ጊዮርጊስ ከሰሜን አፍሪካ ክለቦች ይተናነቃሉ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግና በኮንፌደሬሽን ካፕ የመጀመርያ ዙር ማጣርያ ከሰሜን አፍሪካ ክለቦች የሚያደርጉትን ከባድ ፍጥጫ ከ2 ሳምንት በኋላ በሜዳቸው እንደሚጀምሩ ታወቀ፡፡  ከሳምንት በፊት በቅድመ ማጣርያ  የመልስ ጨዋታዎቻቸውን በሜዳቸው ያደረጉት ሁለቱ ክለቦች ተጋጣሚዎቻቸውን በሰፊ የግብ ልዩነት በማሸነፍ የማለፍ እድላቸውን ወስነዋል፡፡  በተያያዘ የግብፁ ክለብ አልሃሊ ምክትል አሰልጣኝ መሃመድ የሱፍ በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ የመጀመርያ ዙር  ተጋጣሚያቸው የሆነው ኢትዮጵያ ቡና ጥንካሬ እንዳሰጋቸው ሱፕር ስፖርት ዘግቧል፡፡ምክትል አሰልጣኙ  በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ  ቅድመ ማጣርያ ቡና የኮሞሮሱን ኪዮን ኖርድ 4ለ1 ያሸነፈበትን ጨዋታ በአዲስ አበባ ስታድዬም ተገኝተው ተከታትለዋል፡፡

ከጨዋታው በኋላ አልሃሊ  ባለፉት ሳምንታት ልምምድ ሲሰራ ወደቆየበት የዩናይትድ ኢምሬትስ ካምፕ የተመለሱት አሰልጣኙ በአዲስ አበባ ቆይታቸው ጎን ለጎን ተጨዋች ሲያፈላልጉ ነበር ተብሏል፡፡  ምክትል አሰልጣኙ የቡናን ጨዋታ በመታዘብ የቤትስራቸውን ለክለቡ ዋና አሰልጣኝ ማኑዌል ጆሴ ሪፖርት ማድረጋቸውን የገለጸው ሱፕር ስፖርት በተለይ በቡና ሶስት ምርጥ አጥቂዎች ብቃት የተሰማቸውን ስጋት እንዳሳወቁ ገልጿል፡፡ አልሃሊ በዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ ካምፑ ለ10 ቀናት ሲያደርግ የቆየውን ዝግጅት በነገው እለት አገባድዶ ወደ ግብፅ በመመለስ የአገሪቱን ሊግ ጅማሮ በከፍተኛ ዝግጅት እንደሚጠባበቅ ዘገባው አውስቷል፡፡ የግብፁ ክለብ አልሃሊ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ከሚያደርገው ወሳኝ ጨዋታ በፊት ቢያንስ ሶስት ኢንተርናሽናል የወዳጅነት ግጥሚያዎችን ለማድረግ በእንቅስቃሴ ላይ እንደሆነም ታውቋል፡፡ ኢትዮጵያ ቡና በሻምፒዮንስ ሊጉ ቅድመ ማጣርያ የመጀመርያ ጨዋታ ወደ ኮሞሮስ ተጉዞ 1ለ0 በመሸነፍ በመልሱ ጨዋታ 4ለ1 በመርታት በአጠቃላይ ውጤት 4ለ1 አሸንፎ ወደ ቀጣይ የማጣርያ ምእራፍ የመሸጋገር እድሉን ወስኗል፡፡ ከጨዋታው በኋላ በኮሞሮሱ ክለብ ኮየን ኖርድ ላይ ሁለት ጎሎችን ያገባው መድሃኔ ታደሰ ለካፍ ኦንላይን በሰጠው አስተያየት በተጋጣሚያቸው ሁለት ግቦች አስቆጥሮ ማለፋቸውን እንዲያረጋግጡ አስተዋፅኦ በማድረጉ መደሰቱን ገልፃል፡፡ የኮየን ኖርዱ አሰልጣኝ በደጋፊው ፊት የገጠሙትን ኢትዮጵያ ቡና ለመቋቋም እንደቸገራቸው መናገራቸውን የጠቀሰው ካፍኦንላይን የቡናው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ተጨዋቾቹ ያደረጉት ጥረት ስኬታማ አድርጎናል ማለታቸውን ዘግቧል፡፡

በሌላ በኩል በአፍሪካ ኮንፌደሬሽን ካፕ የመጀመርያ ዙር ማጣርያ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጋጣሚ የሆነው የቱኒዚያው ክለብ አፍሪካን ከፍተኛ ዝግጅት ማድረግ ጀምሯል፡፡ በቱኒዚያ የሚካሄደው የሊግ ውድድር ከብጥብጥ በተያያዘ  ያለፉትን ሳምንታት ስታድዬሞች በባዶ ጨዋታዎችን እንዲያስተናግዱ ተደርጎ ነበር፡፡ ፌደሬሽኑ የጣለውን እገዳ ከሳምንት በፊት እንዳነሳ የሊግ ውድድሩም በከፍተኛ መነቃቃት መጀመሩ የክለብ አፍሪካን ቅድመዝግጅት ያጠናክረዋል ተብሏል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በአዲስ አበባ የጋቦኑን ክለብ ማንጋ ስፖርት በመልስ ጨዋታ 4ለ0 በአጠቃላይ ውጤት 5ለ0 አሸንፎ ወደ ቀጣዩ ምአራፍ ተሸጋግሯል፡፡ የኮንፌደሬሽን ካፑን ኮከብ ግብ አግቢነት በ4 ጎሎች መቀናቀን የጀመረው የጊዮርጊሱ አዳነ ግርማ የቱኒዚያ ወኪል የሆነውን ቀጣዩ ተጋጣሚ ጥሎ ለማለፍ ከፍተኛ ዝግጅት እናደርጋለን ማለቱን ካፍ ኦን ላይን ዘግቦታል፡፡

 

 

Read 2082 times Last modified on Saturday, 10 March 2012 12:24