Monday, 05 December 2016 08:58

የአዲሱ ካቢኔ ተስፋዎችና ፈተናዎች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(21 votes)

  “ምሁራን ብዙ መፍትሄዎች ሊያመጡ ይገባል”
                            አቶ አበባው መሃሪ (ፖለቲከኛ)

              ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በግንቦት 2009 ምርጫ ማግስት ራሳቸው ያቋቋሙትን የሚኒስትሮች ካቢኔ በመበተን፣ ከወትሮው በተለየ መንገድ በምሁራን የተዋቀረ አዲስ ካቢኔ መመስረታቸው አይዘነጋም፡፡ ሹመቱ የተከናወነው በዋናነት የትምህርት ዝግጅትና ብቃትን መሰረት አድርጎ መሆኑን የገለጹት ጠ/ሚኒስትሩ፤ አዳዲሶቹ ሚኒስትሮች የህዝብን ጥያቄ ለመመለስ አቅሙና ብቃቱ ያላቸው እንደሆኑ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ፖለቲከኞችና የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችስ ምን ይላሉ? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ በአዲሱ ካቢኔ ዙሪያ የአንጋፋ ፖለቲከኞችን አስተያየት እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡፡

        የህዝቡ ጥያቄ ሚኒስትሮች በደሉኝ የሚል አይመስለኝም፡፡ የህዝቡ ጥያቄ የሲስተምና የአስተዳደር ለውጥ ነው፡፡ ሰውን በሰው መተካት ብቻውን መፍትሄ አይሆንም፡፡ ምሁራን ከያሉበት ተለቅመው በካቢኔው መግባታቸው ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን ምሁራኑ ቢሮክራሲውን ያውቁታል ወይ? ጠ/ሚኒስትሩን ሊደግፉ ይችላሉ ወይ? በውስጥ ያለውን ብዙ ዓመት ሲጓተት የመጣ ችግር ሊፈቱት ይችላሉ ወይ? የሚሉ ጥያቄዎች ይነሳሉ፡፡ እንደኔ እነዚህ ሰዎች የቀለም ሰዎች ናቸው፤ ቢሮክራሲውን አያውቁትም፤ ቢሮክራሲውን ተሸክመው ገፍተው ይሄዳሉ የሚል እምነት የለኝም፡፡
የሚደረጉ ግምገማዎችስ ምን አይነት ናቸው? ግልፅ አይደሉም፡፡ እንደ ወትሮው ሁሉ  “ሙስናን እናጠፋለን፤ ህዝቡን በእውነተኛነት እናገለግላለን” የሚል ነው እየተነገረ ያለው፡፡ ይህ በአፍ ቀላል ነው፣ ይቻላል፤ ወደ ተግባር ለመለወጥ ግን እንደ አፍ አይቀልም፡፡ መንግስት የሚለውን ለውጥ ያመጣል ወይ የሚለው ለወደፊት የምናየው ይሆናል። ይሄም ቢሆን ግን ወደ ህዝቡ ጥያቄ ይቀርባል ማለት አይደለም፡፡ መንግስት በቅንነት ለሀገሪቱ የሚያስብ ከሆነ፣ ሁሉም ደስተኛ የሚሆንበት እርቀ ሰላም ያስፈልጋል፡፡ መቼም ሀገሩን የሚጠላ አይኖርም፤ሁሉም ሀገሩን ይወዳል፡፡ ሀገሩ ላይ ቀውስ እንዲመጣ የሚፈልግ ሰው ይኖራል ብዬ አላምንም፡፡ ሀገሬን እወድዳለሁ የሚል ሁሉ፣ሀገሩን ለማዳን ወደ እውነተኛው ውይይት መቅረብ አለበት፡፡ በተለይ ምሁራን ብዙ መፍትሄዎች ሊያመጡ ይገባል፡፡

----------------

                  “የምንጠብቀው የግምገማ ጋጋታ ሳይሆን ተግባር ነው”
                            አቶ አሥራት ጣሴ (ፖለቲከኛ)

     አዲስ ከተሾሙት የካቢኔ አባላት መካከል በኔ እይታ አዲሶቹ ከአራት የሚበልጡ አይደሉም። ሌሎቹ በአንድም ሆነ በሌላ ከኢህአዴግ ጋር ቅርበት የነበራቸው ናቸው፡፡ እርግጥ ነው ምሁራን መሾማቸው ችግር የለውም፤ ቆንጆ ነው፡፡ ነገር ግን ካቢኔው የጥናትና ምርምር ተቋም ሳይሆን የፖለቲካ ተሿሚ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ነው፡፡ ስራው ደግሞ ሀገር ማስተዳደር ነው፡፡ ከዚህ አንፃር አዲሱ ሹመት በፖለቲካው ላይ የተሻለ ለውጥ ያመጣል ብዬ አላምንም፡፡ በህዝባዊ አመፁ ላይ የተነሱት ጥያቄዎች፣ “የሚኒስትሮችና የአመራር ችግር አለብን፤ ይነሱልን” የሚል አልነበረም፡፡ የኢህአዴግ መሰረታዊ ችግር የህዝብን ጥያቄ ማጣመምና ላልተጠየቀው ጥያቄ መልስ መስጠት ነው፡፡ ይህ አካሄድ ደግሞ ችግሮችን እያወሳሰበና መፍትሄውን እያከበደ ነው የሚሄደው፡፡ ህዝቡ ያነሳው ጥያቄ በቀጥታ መመለስ አለበት፡፡ አሁን በክልሎች የተደረገው መንግስትን የመተማመኛ ድምፅ የማሳጣት አይነት ነው። ለአጭር ጊዜም ቢሆን ኢህአዴግ ውስጥ ገብቼ ሰርቻለሁ፡፡ በጀርመን ሀገር የኢትዮጵያ ኤምባሲ ውስጥ በአማካሪነት ሰርቻለሁ፡፡ በተቃዋሚ ፓርቲ በነበረኝ ቆይታም ብዙ ፈትሸን አይተነዋል፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግን ጥሩ አድርጌ አውቀዋለሁ ብዬ አምናለሁ፡፡
እኔ እንዳየሁት አንዳንድ ሚኒስትሮች ጥሩ አድርገው ለመስራት ቢሞክሩም እንኳ የስርአቱ ባህሪ እንደዚያ እንዲሆኑ አይፈቅድላቸውም፡፡ እያንዳንዱ ተሿሚ ሙሉ ነፃነት የለውም፡፡ ስለዚህ የካቢኔ ለውጡ ትርጉም ያጣብኛል፡፡ ኢህአዴግ ግምገማ ከትጥቅ ትግሉ ጀምሮ ዋነኛው መሳሪያዬ ነበር ሲል እንሰማዋለን፡፡ ይሁን እንጂ ባለፉት 25 ዓመታት ግን ተመሳሳይ የግምገማ ጉዳይ ስንሰማ ከርመናል፡፡ ይሄ ግምገማ ሰርቷል ማለት ነው? ውጤት አምጥቷል? ኢህአዴግ ግምገማ የሚለውን የተሰለቸ አካሄዱን ትቶ፣ የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል ከሚሉ አካላት ጋር ሁሉ ግልፅ ውይይት ማድረግ ነው ያለበት፡፡
ሮዝ ፔሮት የተባለ የአሜሪካ ፖለቲከኛ በአንድ ወቅት “መናገር ቀላል ነው፤ ቃላቶችም የተትረፈረፉ ናቸው፤ ተግባር ግን ውድና ብርቅ ነው” ብሎ ነበር፡፡ እኛም አሁን የምንጠብቀው የግምገማ ጋጋታ ሳይሆን ተግባር ነው፡፡

--------------------

                          ‹‹ለኔ ተሃድሶው ግልፅ አይደለም››
                             ዳንኤል ብርሃነ (ጦማሪ)

         የኢህአዴግ ም/ቤት ስብሰባን ጨርሰው “ጥልቅ ተሃድሶ እናደርጋለን” ብለው ሲለያዩ ተስፋችንን ዝም ብለው ሠቀሉት ወይም ሊያደርጉት እንደሚችሉ ፍንጭ ሰጡን እንጂ በኋላ ያገኘናቸውን መረጃዎች ስናይ የአመራር ለውጥ ለማድረግ አስበው አልነበረም የተለያዩት፤ ግምገማ አድርገን ችግሮችን ለይተን መፍትሄው ላይ እንድረስ ነው የተባባሉት፡፡ ብአዴንና ህውሓት አካባቢ የአመራር ለውጥ አያስፈልገንም የሚል አቋምም ነበራቸው፡፡
 እርግጥ ነው ሁሉም የአመራር ለውጥ ያስፈልናል ብለው አልነበረም ወደ የራሳቸው ግምገማዎች የተበታተኑት፡፡ ብዙ ሰው ግን እንደዚያ እንዲጠብቅ ተደርጓል፡፡ ኢህዴግ በራሱ ጊዜ ነው የአመራር ለውጥ ያደረገው፡፡ ዋናውን ግምገማ ሳይጨረሱ ነበር አመራር የቀየሩት፡፡ በብአዴንና ህውሓት በኩል ግን ቀውሱ ማንን ይመለከታል በሚለው ላይ ግልፅ አቋም የተያዘ አይመስልም፡፡ በህወሓት ዘንድ “እኛ ጋ ሰላም ነው፤ ምንም የተፈጠረ ችግር የለም” የሚል አመለካከት ይታያል፤በአንፃሩ ብአዴን ጋ ደግሞ “ችግር አለ፤ ችግሩ ግን የግለሰቦች ችግር ስላልሆነ እንደ ድርጅት ነው መታደስ ያለብን” የሚል መከራከሪያ አለ፡፡ ይሄ በንድፈ ሃሳብ ደረጃ ሊያስኬድ ይችላል፤ ነገር ግን ከአመራር ፅንሰ ሃሳብ አንፃር ብንመለከተው፣”እገሌ የሚባል አመራር እየመራው የተፈጠረን ቀውስ እስቲ እገሌ ደግሞ ይረከብና ይሞክረው” ይባላል፡፡ በሌላው አለምም የተለመደው ይሄ ሁኔታ ነው፡፡
ወደ ፌደራል ካቢኔ ሲመጣ ትልቅ የካቢኔ ለውጥ ተደረገ ተባለ እንጂ ለውጡን ካየነው የኦሮሚያ ነው፡፡ ከተቀየሩት የካቢኔ አባላት ውስጥ ግማሽ ያህሉ የኦህዴድ ሰዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ ይሄ ሲታይ የኦህዴድ ማዕበል ውጤት ነው ሊባል ይችላል፡፡ የአመራርና የአደረጃጀት ለውጥ ካልመጣ ተሃድሶ ምንድን ነው? የሚል ጥያቄም ይፈጠራል። ተሃድሶ የነበረውን አስተሳሰብ ፈትሾ ለአዲሱ ሃሳብ የሚመጥን አደረጃጀትና ሰዎችን መድቦ መንቀሳቀስ ነው ያለበት፡፡ አሁን “የሃሳብ ማስተካከያ ለውጥ ተደርጓል?” ብለን ከጠየቅን፣ አይመስልም። “ስልጣንን ለህዝብ ጥቅም አለማዋል” የሚለው በፊትም የነበረ አስተሳሰብ ነው፡፡ ተሃድሶው ውጤት እንዲያመጣ ከተፈለገ፣ ወይ የአስተሳሰብ አሊያም “አስተሳሰቡ መሻሻል አያስፈልገውም፤  ያለው ሃሳብ የጠራ ነው” ከተባለ ደግሞ ያን ሃሳብ የሚመጥን የሰው ሃይልና አደረጃጀት ማምጣት ነው የሚያስፈልገው፡፡ አሁን የፍልስፍና ማስተካከያ አደረግን ሲባል አልሰማንም፡፡ ይሄ ማለት ደግሞ “የነበረው ፍልስፍና የበቃ ነው” የሚል እምነት አለ ማለት ነው፡፡
እኔ የአመራርም ለውጥ አልተደረገም ብዬ ነው የማምነው፡፡ ምክንያቱም አሁን ባለው የመንግስት አወቃቀር ወሳኙ ኢህአዴግ እንደሆነ ይታወቃል። የካቢኔ ለውጡ ምናልባት ሰዎቹ የተማሩ ሊሆኑ ይችላሉ ነገር ግን ወደ ተሃድሶ ያመጣው ችግር የቴክኒክ እውቀት ችግር ነው ወይስ የአስተሳሰብ (ርዕዮተ አለም) ወይም ለስራው የመሰጠትና በኃላፊነት የመስራት ችግር ነው? የሚለውን ማየት ያስፈልጋል፡፡
ፓርቲው የፍልስፍና ለውጥ አድርጓል? የአደረጃጀት ለውጥስ አድርጓል? እነዚህን ካላደረገ ለኔ ተሃድሶው ግልጽ አይደለም፡፡ የመንግስት ካቢኔ መለወጡ ተሃድሶ ሊሆን ይችላል ወይ? ከተባለ፣ ሊሆን ይችላል፤ምናልባት ችግሩ የነበረው የቴክኒክ ችግር ከሆነ ማለት ነው፡፡

Read 3916 times