Monday, 28 November 2016 07:00

“ክፉ ቀን በሰጠኝ” የሚያስብል ጭንቀት አይድረስባችሁ

Written by 
Rate this item
(23 votes)

የሶማሌ ክልል ጉዞ - ከጉማራ ዙምራ

   ”እንዴት ነው ሶማሌ ክልል? አሁን ሰላም ነው አይደል?” ሁሌም ስጋት የማይለየው ሾፌር ጠየቀ፡፡
”አሁንማ ምን አለ? አገር ተረጋግቷል፡፡ ከአምስት ዓመት በፊት ምእራብ ጎዴ ስሰራ፣ በቀኝ በኩል ወታደር፣ በግራ በኩል ሽፍታ እያጀበኝ ነበር የሰራሁት፡፡”
“አሁንም ሽፍታ አለ እንዴ?”
”የለም አቦ፡፡ አቲፍራ፡፡ ወንድ ልጅ አይፈራም!!”
“እንደው ቤተሰብ ያለው ሰው ይጨነቃል ብዬ ነው” ሹፌሩ መለሰ፡፡
”ቆይ አንተ ስንት ልጆች አሉህ?”
“አንድ ልጅ ነው ያለኝ፡፡”
”ሀይ!! አንድ ልጅ ወልደህ ነው፣ ሃረካት የምታበዛው፡፡ አንድ ልጅ ብቻ ምን ያደርጋል! ጨምረህ ውለድ፡፡ ሚስትህን ውለጂ በላት፡፡ እምቢ ካለች ሌላ ሚስት አግባና ውለድ፡፡ ልጅ ኽይር ነው።”
ከአስራ ሁለቱ ወራት፣ እንደ መስከረም የሚሆንልኝ ተናፋቂ ወር የለም፡፡ ምን ያደርጋል? የዘንድሮውን የመስከረም ፀጋ፣ በቅጡ ሳላጣጥመው ነው፣ ወደ ሶማሌ ክልል ለመሄድ እንድዘጋጅ፣ ከመስሪያ ቤት ማሳሰቢያ የደረሰኝ፡፡ መስከረም 10 ቀን 2009 ዓ.ም፣ ጓዜን ሸክፌ ጉዞ ጀመርኩ፡፡ ምስጋና ለፈጣኑ የክፍያ መንገድ ይሁንና፣ አዳማ ላይ ቁርስ አድርሰን፣ ቡናም ጠጥተን፣ የማይቀሬውን ረጅሙን ጉዞ ተያያዝነው፡፡ እኔም መቋጫ የሌለው የጭንቀት ድር ውስጥ መብሰልሰል ተያያዝኩት፡፡
የሶማሌ ክልል ለረጅም ጊዜ ሰላም ርቆት የቆየ መሆኑ ብቻ አይደለም ያስጨነቀኝ፡፡ ጊዜው ጥሩ አልነበረም፡፡ አገሬው ሁሉ በግጭትና በረብሻ ወሬ ውጥረት ውስጥ የገባበት ጊዜ ነው፡፡ ሁከት እና ብጥብጥን እያሰላሰሉ መጓዝ አስቸጋሪ ነው፡፡
‹‹አሁን በዚህ ሰዓት፣ ሰው ቤቱ አርፎ ቁጭ ይላል እንጂ መንገድ ይወጣል? ‹ይሄኛው መንገድ ተዘጋ፤ እዚህ ከተማ መኪና ተቃጠለ› እየተባለ፣ ሰው ገንዘብ አገኛለሁ ብሎ ከከተማ ሊወጣ ይገባል? ኧረዲያ! ክልፍልፍ ሁኜ ነው እንጂ! … ለዚያውም የቤተሰብ ሃላፊ! …›› በጭንቀት መብሰልሰል፣ ጠብ የሚል ጥቅም እንደሌለው አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን ጭንቀትን አውልቆ መጣል አይቻልም፡፡ ለካ በክፉ ቀን ውስጥ ያላለፈ ሰው፣ ድንገት አስቸጋሪ ጊዜ በመጣ ወቅት፣ የሚይዘው የሚጨብጠውን አያውቅም፡፡ እኔም የክፉ ቀን ልምድ የለኝም፡፡ በዚህ የሀሳብ ወንዝ መቀጠል አልችልም፡፡ ልምድ ለማግኘት፣ “ ምነው ክፉ ቀን በሰጠኝ” ብዬ እንደመሳለቅ ይሆንባችኋል፡፡
የሶማሌ ክልል ደግሞ ጭንቀትን የሚያረጋጋ አልሆነልኝም፡፡ ለሩብ ምዕተ ዓመት መንግስት አልባ ሆና ከምትተራመሰው አገር ከሶማሊያ ጋር የተጎራበተ ክልል ነው፡፡ ከድንበር ባሻገር፣ በሞቃዲሾ፣ በባይዶዋና በመሳሰሉ የሶማሊያ ከተሞች፣ በአሸባሪዎች ጥቃት  ሰላማዊ ሰዎችና ወታደሮች መገደላቸው፣ … እንደ ዜና አይቆጠርም። የዘወትር ወሬ ነው፡፡ ግን ወሬው ብቻ አይደለም ድንበር ተሻግሮ ወደ ሶማሌ ክልል የሚዘልቀው፡፡ የሽብር ጥቃትና ግድያም፣ አልፎ አልፎ ወደ ሶማሌ ክልል ይሻገራል፡፡ እና አንዳንዶቹ ወረዳዎች ደግሞ የባሰባቸው ናቸው፡፡ “ክልሉ ውስጥ በሚገኙ አንዳንድ ወረዳዎች ውስጥ በእጀባ ልትገቡ ትችላላችሁ፡፡ እጀባ የማታገኙ ከሆነ ግን፣ አሳውቁንና እንዲቀየርላችሁ ይደረጋል” ተብሎ ተነግሮናል፡፡ … እጀባ፣ ወታደር፣ ክላሽ ፣ አስቸጋሪ አቧራማ ጉዞ … እንዲህ የሚረብሹ ሃሳቦች እየተመላለሱብኝ በጭንቀት መናወዜ አልቀረም፡፡ አጥፍቶ ጠፊ በቀበረው ፈንጂ መኪናችን ወደ ሰማይ ተተኩሳ ስትቃጠል .... ወይም አንዱ ሽፍታ በሞርታር ከርቀት ሲያጋየን …  በእዝነ ህሊና ማሰብ ይሰቀጥጣል፡፡  
ታዲያ ስሜቴ አንዱን ሀሳብ ሳይቋጭ፣ ወደ ሌላው ፈተና እየከተተኝ እንደ ፔንዱለም በሃሳብ ስወዛወዝ፣ “አለቃ ምነው ትካዜ አበዛህ”? የሚል ድምፅ አባነነኝ፡፡ አንዱ ባልደረባችን ነው፡፡ “አይ … መቼም የሚታሰብ አይጠፋ” ብዬ መለስኩ፡፡ ረጅም መንገድ፣ ያለጨዋታ አይገፋምና፣ አንዴ ሞቅ አንዴ ቀዝቀዝ እያልን ወደጨዋታ መግባታችን አልቀረም። ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ፣ ስፖርት፣ ፊልም፣ የቲቪ ወይም የሬድዮ ቻናል እያነሳን እናወራለን። ጭውውታችን ታዲያ፣ ስለእያንዳንዳችን ተፈጥሮአዊ ዝንባሌ፣ ፍላጎት፣ የፖለቲካ አቋም አንዳንዴም የእውቀት መጠን ለማወቅ የሚያስችል ሁናቴ መፈጠር ጀምሯል፡፡
የስምጥ ሸለቆ ሙቀት እና ወበቁ እየበረታ ሲመጣ፣ ሸሚዝ መክፈት፣ ቀበቶ መፍታት መቁነጥነጥ አብዝተናል፡፡ መተሃራ ከተማ ላይ፣ ቡና ጠጣንና አንዳንዶቹም በርጫቸውን ይዘው፣ በዱአ እና በዝየራ ጉዞአችንን ገፋነው፡፡ ወለንጪቲ፣ አዋሽ 7፣ ሜኤሶ፣ እና ሌሎች  ሞቅ ደብዘዝ የሚሉ ከተሞችን ተሻግረን፣ ጭሮ (በጥንት መጠሪያዋ አሰበ ተፈሪ) ደረስን፡፡ የምሳ እረፍት አድርገን እንደገና “በጠመዝማዛው …  ሽቅብ ቁልቁለት”... በምእራብ ሃረርጌ ዘወርዋራ መንገድ መጋለብ ጀመርን - ትናንሽ የሃረርጌ ከተሞችን እየገመስን፡፡
ከዚያ ሁሉ የተራራ ሰንሰለት በኋላ፣ ሜዳማ የሶማሌ በረሃዎች ይከሰታሉ ብሎ ማሰብ መቼም አስቸጋሪ ነው፡፡ አየሩና ምድሩ፣ ከቅዝቃዜ ወደ ግለት፣ ከአረንጓዴ ወደ አፈርማ ይቀየራል፡፡
ጅግጅጋ ከተማ የደረስነው በማግስቱ ረፋድ ላይ ነው፡፡ ከሶስት ዓመት በፊት የማውቃት ጅግጅጋ፣ እጅጉን ተቀይራለች፡፡ የከተማዋ እድገት ተፋጥኗል። መንገዶች እየተስፋፉ፣ ህንጻዎች እየተገነቡ ነው፡፡ የንግድ እንቅስቃሴው አጃኢብ ያስብላል፡፡ ስራችንን ለመጀመር ወደ ዞን እና ወረዳዎች ከመግባታችን በፊት ታዲያ፣ ከክልሉ መንግስት የትብብር ደብዳቤ መውሰድ ግዴታችን ስለሆነ ወደ ክልሉ ቢሮ ጎራ አልን፡፡ እንደተመኘነው አልቀናንም፡፡
“የቢሮ ሃላፊዋ አስቸኳይ ስብሰባ ላይ ናት” አለችን ጸሃፊዋ፡፡
“ምክትሏስ?” ብለን ስንጠይቅ
“እሱማ፣ አባቱ ሞተው ሃዘን ላይ ነው” ተባልን፡፡
ፍርሃትም ተስፋም ሰንቀን አዳራችንን፣ ወደ አንዱ ባልደረባችን ወዳጅ ደውለን፣ ወደ ቤት ጎራ ብንልስ ብለን ጠየቅነው፡፡ አብዱልአዚዝ ይባላል፡፡ ፈታ የማለት ባህሪ ይታይበታል፡፡
ያለንበት ድረስ መጣ፡፡ “እንዴት ናችሁ አቦ? አማን ናችሁ? … ያ የተኮራረፈ የሚመስለው የአዲስ አበባ ሰው እንዴት ነው አቦ? … ሰው በታክሲ እየሄደ አያወራ፣ አይናገር፣ የሆነ ዝጋታም እኮ ነው። እኔ ይጨንቀኛል፡፡ ሰው ሰው ሆኖ ተፍጥሮ እንዴት አያወራም? ከብት እንኳን በሽታ ሰላም ይባባላል እኮ።”
“እኔ የምልህ አብዱልአዚዝ ሚስት አገባህ አይደል?” ጠየቀ አብሮ አደጉ፡፡
“አዎ! አይሻ ነው ስሟ፡፡ ስታትስቲክስ ነው የጨረሰችው፡፡ ማስተርሷን ደግሞ በዴቨሎፕመንት ኢኮኖሚክስ ከጅግጅጋ ዩንቨርሲቲ አግኝታለች፡፡”
”አሃ ያቺ ባለፈው ስመጣ አብራህ የነበረችው ነች እንዴ?”
”አዎ...አዎ የዛን ቀን እኮ ነው ፍቅር የጀመርነው። ለካ ነበርክ? ወላሂ ጥሩ ሚስት አገኘሁ፡፡ አንተም ገደኛ ነህ አቦ!”
”ስንት ልጆች ወለድክ?”
”ሶስት ወልጃለሁ፡፡ ኢንሻላህ! አሁን ሶስተኛውን ልጃችንን በኦብራሲዮን ወልዳ ቆይ ላገግም አለቺኝ፡፡ ልጅ ኸይር ነው፡፡”(ሶማልኛ ቋንቋ ውስጥ “ፐ” ፊደል ያለ አይመስለኝም)
መኖሪያ ቤቱ፤ ጭናቅሰን መውጫ የሚባል አዲስ ሰፈር ላይ ነው፡፡ መኪና ውስጥ ገባንና ጉዞ ወደ ቤቱ ጀመርን፡፡ አልፎ አልፎ ሰፋፊ ቪላዎች ይታያሉ፡፡
”አየኸው ያን ነጭ ቪላ? የክልሉ ጸጥታ ሃላፊ የነበረ ያሰራው ቤት ነው፡፡”
”እውነትክን ነው?”
”አዎ!! ሞኝ ነው እንጂ፣ ሰው ከመንግስት ብር ሰርቆ፣ ጅግጅጋ ከተማ ላይ ቪላ ይሰራል? ወላሂ ይሄ ሰው አይደለም፡፡”
”ምን ሆነ አሁን?”
”አሁንማ አወረዱት እና አሰሩታ፡፡ ሱማሌ ሲፎግር ቤቱን “የህዝብ ክሊኒክ” ብሎታል፡፡ አታየውም? ክሊኒክ እኮ ነው የሚመስለው ”...ሳቅ
መኖሪያ ቤት ገባን፡፡ ቤት ውስጥ … ሶፋ፣ የሳሎን እቃ ጅኒ ቁልቋል ይኖራል ብላችሁ ካሰባችሁ ተሳስታችኋል፡፡ ዙሪያውን አረቢያን መጅሊስ የተነጠፈበት ሰፊ ሳሎን እና ፓወር ፖይንት ግድግዳው ላይ ተደግኗል፡፡ ከጎኑ ቴሌቪዥን ብቻ አለው፡፡ ፓወር ፖይንቱን ስመለከት፣ ዎርክ ሾፕ ወይም ስልጠና የሚሰጥበት አዳራሽ ነገር መሰለኝ፡፡
“ፓወር ፖይንቱን ምን ታደርግበታለህ?”
“እኔ ቴሌቪዥን የማየው በዚህ ነው፡፡”
ሳቅ...
“ምነው ትስቃለህ? እዛ ግብርና ቢሮ ስሰራ፣ የተሰጠኝ ነው፡፡ ወደ ሌላ ቢሮ ሲቀይሩኝ ለቤት ይሆናል ብዬ ይዤው መጣሁ፡፡ እኔ በዚህ  ማየት ለምጄ ቲሌቪዥን ይደብረኛል አቦ!! በተለይ እግር ኳስ ካለ  ይሄን ግድግዳው ላይ ቲለቃለህ፡፡ በቃ ስክሪን ነው፡፡” ... ሳቅ
”ትራስ አምጪ!” አዘዛት ትልቋን ልጁን፡፡
”አረፍ በሉ፡፡ ውሃ አምጡላቸው፡፡ ምሳ እንብላ?”
”እረ እኛ በልተን ነው የመጣነው፡፡”
”ወላሂ በሉ እስኪ?”
”ወላሂ፡፡”
”በቃ ቃሙ እናንተ እኔ ትንሽ ልብላ፡፡”
”ሃዬ!”
”እንዴት ነው ሶማሌ ክልል አሁን ሰላም ነው አይደል?” ሁሌም ስጋት የማይለየው ሾፌር ጠየቀ፡፡
”አሁንማ ምን አለ፡፡ አገር ተረጋግቷል፡፡ እኔ ከአምስት ዓመት በፊት፣ ምእራብ ጎዴ ስሰራ በቀኝ በኩል ወታደር፣ በግራ በኩል ሽፍታ እያጀበኝ ነበር የሰራሁት፡፡”
”እረ ባክህ፡፡ አሁንም ሽፍታ አለ?”
”የለም አቦ አቲፍራ፡፡ ወንድ ልጅ አይፈራም!!”
“እንደው ቤተሰብ ያለው ሰው ይጨነቃል ብዬ ነው፡፡” ሹፌሩ መለሰ፡፡
”ቆይ አንተ ስንት ልጆች አሉህ?”
አንድ ልጅ ነው ያለኝ፡፡”
”ሀይ!! አንድ ልጅ ወልደህ ነው ሃረካት የምታበዛው፡፡ አንድ ልጅ ብቻ ምን ያደርጋል፡፡ ጨምረህ ውለድ፡፡ ሚስትህን ውለጂ በላት፡፡ እምቢ ካለች ሌላ ሚስት አግባና ውለድ፡፡ ልጅ ኽይር ነው።” ሳቅ
(ይቀጥላል)
Read 4944 times