Sunday, 27 November 2016 00:00

ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ!

Written by 
Rate this item
(17 votes)

አንድ የቻይና ተረት የሚከተለውን ይላል፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ንጉሥ ልጆቻቸውን ሰብስበው፣
“ልጆቼ፤ እስከዛሬ መቼም በክፉም በደግም መንበሬ ላይ ሆኜ ሳስተዳድር ታውቁኛላችሁ፡፡ አሁን እርጅናም እየመጣ ነው፤ ሆኖም ለአንዳችሁ መንግሥቴን እንዳወርሳችሁ፤ በማስተዳድር ጊዜ የሰራሁት ጥፋት ካለ ንገሩኝ፡፡ ከእናንተ መካከል ለማን ማውረስ እንዳለብኝ እንዳመዛዝን ይጠቅመኛል” አሉ፡፡
ልጆቹ እርስ በርሳቸው መተያየት ጀመሩ፡፡ ሀሳባቸው ተከፋፈለ፡፡ ከፊሎቹ ንጉሱን በማወደስ ወንበሩን ለማግኘት ቋመጡ፡፡ ከፊሎቹ ደግሞ ዕውነቱን ተናግረን ያሉትን ይበሉ አሉና ሀሳባቸውን ሰነዘሩ፡፡
1ኛው/ “ንጉሥ” ሆይ! እንደርሶ ያለ መሪ በዓለም ታይቶ አይታወቅም፡፡ ሁሉን እኩል ያያሉ። ለሁሉም ፍትሐዊ ነዎት፡፡ ሰብዓዊ መብት እንዳይረገጥ ሌት ከቀን ሲለፉ ኖረዋል፡፡ ከላይ እግዚአብሔርን ከታችም እርስዎን የሚፈራ ህዝብ ፈጥረዋል፡፡ እኛ ልጆችዎ በእርስዎ እንድንወጣ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ እንደኖሩ ማንም አይጠራጠርም፡፡ አምላክ ዕድሜዎን ያርዝምልን እንጂ ውርሱ አይጠቅመንም” አለ፡፡
2ኛ/ “እርሶን የመሰለ ንጉሥ ፈፅሞ እግር እስኪነቃ ቢኬድ አይገኝም፡፡ በተለይ ከጎረቤት አገሮች ጋር ባለዎት የዲፕሎማሲ ግንኙነት አንፃር ወደር የለዎትም” አለ፡፡
3ኛ/ “በጤና፣ በትምህርት፣ በመንገድ ሥራ፣ ያመጡልን የዕድገት ውጤት ከአህጉራችን አንደኛ እንድንሆን አድርጎናል፡፡ ፀሎታችን እድሜዎትን እንዲያረዝምልን ነው” አለ፡፡
በዚህ ዓይነት ስድስቱ ልጆቻቸው የንጉሡን ደግነትና ርህራሄ፣ በህዝብ ያላቸውን ተወዳጅነት እያሞገሱ ብዙ ተናገሩ፡፡ በመጨረሻ ግን ሰባተኛው ልጃቸው ተነስቶ መናገር ጀመረ፡-
“በበኩሌ ስልጣን አልፈልግም፡፡ ስለዚህ እውነትን መናገር እመርጣለሁ፡፡ ንጉሥ ሆይ! በመጀመሪያው የግዛት ዘመንዎ ደህና አስተዳደር ነበረዎ፡፡ ትዕግሥት ነበረዎ፡፡ ወገናዊነት አልተፈታተነዎትም ባይባልም፤ ከሞላ ጎደል ዲሞክራሲያዊና ለሰው አሳቢ ነበሩ፡፡ ፍርድ ቤቶቹም ቀናና ለተበደለ ፍትህን የሚሰጡ ነበሩ፡፡ መብቶች እንደሚከበሩና ሀብት በአግባቡ እንደሚዳረስም ቃል ገብተው ነበር፡፡ በመካከለኛው ዘመንዎ ሁሉም ነገር ፈሩን እየሳተ መጣ፡፡ በመጨረሻውና አሁን በደረስንበት የግዛት ወይም የግዝት ዘመንዎ ግን ነገሩ ሁሉ ተገለባበጠ፡፡ ሙስናና ጉቦ የዕለት ሁኔታ ሆነ፡፡ ቁጥጥር ጠፋ፡፡ እንዲያውም አመራሮችም ሳይቀሩ ተዘፈቁበት፡፡ “የአሣ ግማቱ ከጭንቅላቱ” የሚለው ምሳሌ በዐይን ታየ፡፡ እርሶም እጅዎን ሰብስበው ተቀመጡ፡፡ የአስተዳደር ብልግና የማያስጠይቅ መሰለ፡፡ ሹም ሽር ቢያካሂዱም ቦታ መለዋወጥ እንጂ ሥርዓትዎ ስላልተለወጠ ከድጡ ወደ ማጡ መኬድ ቀጠለ፡፡ እንደ እርሶ ዕድሜ ማርጀት ሁሉ ሥርዓቱም እያረጀ ነው፡፡ “አዲስ ወይን በአሮጌ ጋን” ከመሆኑ በስተቀር ለውጥ አልተጠመቀም፡፡ አልታየም፡፡ አሁንም ሳንዋሽ ዕውነቱን አውጥተን ካልተነጋገርን መሸፋፈኑ አይጠቅመንም፤ ንጉስ ሆይ!” አለ፡፡
ንጉሡም፤
“በመጀመሪያ የተናገራችሁት ልጆቼ፤ ያሞገሳችሁኝንም፣ ዕድሜ የተመኛችሁልኝንም አመሰግናችኋለሁ፡፡ ከእናንተ ጋር በተሰበሰብን ጊዜ ሁሉ ስሰማው የኖርኩት ነው፡፡ የመጨረሻው ልጄ የተናገርከው ነገር ግን፤ ዕውነተኛው መልካችን ነው፡፡ ከፍተኛው ምሥጋናም የሚገባህ ላንተ ነው። መንግስቴንም የማወርሰው ላንተ ነው! ምክንያቱም አገር ለመለወጥ የምትችል አንተ ነህ!” ብለው አሰናበቷቸው፡፡
*      *     *
“ጅላጅል ምላስ ብቻ ናት
ማሞካሸት የማይደክማት
ቀን አዝላ ማታ እምታወርድ
ንፉግን ልመና እምትሰድ!”
ይለናል ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህን፡፡ አስመሳዮችና አድር ባዮችን ተማምነን፤ መልካም የሰራንና የተሻለ አቋም ላይ ያለን ከመሰለን፤ ስህተታችን ከዚያ ይጀምራል፡፡ ከቶም መልካም አስተዳደር በሙገሳ እንደማይገኝ ያለፉት አመታት በማያወላዳ ሁኔታ አረጋግጠውልናል፡፡ መሸነጋገል እንደማያዋጣም ተገንዝበናል፡፡ ዲሞክራሲ፣ ፍትህ፣ የተጠያቂነት ስርዓት፣ ግልፅነት፣ የማንነትና የባለቤትነት ጥያቄ፣ የሥራ ዕድል መፍጠር፣ የሲቪክ ማህበራት ማደራጀት፣ መመሪያዎችን በለበጣ ሳይሆን ከልብ የመተግበር አሰራር፣ ወዘተ ከአፍ አልፎ በስራ የሚገለጥበት፤ በተስፋና በዱቤ ሳይሆን “እጅ - በጅ ፍቅር እንዲደረጅ” የሚባልበት፣ እንዲሆን ከተፈለገ፤ ግምገማዎች ሀቅን የተንተራሱ፣ መሬት የነከሱ እንዲሆኑ፤ ከልብ ማመን ግድ ነው! መገናኛ ብዙኃን ተዓማኒ የሚሆኑት የመንግሥት ደጃፎች መረጃ ለመስጠት ክፍት ሲሆኑ ነው፡፡ የመንግስት ሚዲያዎች እንዳይደመጡና እንዳይነበቡ የሚሆኑት … የማጋነኛ መድረኮች ሲሆኑና ዕውነት - ጠለቅ ሳይሆኑ፣ “የጌታዬ ቃል የእኔ ቃል” በሚል መርህ ስለሚጓዙ ነው፤ ለማለት ይቻላል፡፡
“ለመቶ አምሳ ጌታ
ስታጠቅ ስፈታ
ነጠላዬ
አለቀ በላዬ”
ማለት የዱሮ ፈሊጥ ይምሰል እንጂ “የሆድ የሆዳችንን እንነጋገር” በሚለው ህዝብ፣ በምሁሩ፣ በነጋዴው፣ በተማሪው፣ በዜጋው ሁሉ የሚብሰለሰለው ሀሳብ ይሄንኑ ፈሊጥ የሚገልጥ ነው፡፡ ግምገማዎች ከመፈራራት፣ ከእከክልኝ ልከክልህ፣ ከአሞግሰኝ ላሞግስህ፣ ከሾሜሃለሁ ትሾመኛለህ/ትክሰኛለህ፣ ከ “ይሄን ተናግረህ ሰው አያረጉህም” አስተሳሰብ፣ ካልፀዱ ዋጋቸው አናሳ ነው፡፡ ወይም አክሳሪ ነው፡፡ በጥናትና በፅናት መካከል ገደል አከል ልዩነት አለ፡፡ አንዱ ዘዴ፣ አንዱ መስዋዕትነት ጠያቂ ነው፡፡ የህዝብ ብሶት አራምባ፣ የግምገማው መንፈስ ቆቦ ከሆነ ውጤቱ “ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ” ነው፡፡ ያልተዘራ አይታጨድምና እናስብበት፡፡ በየግምገማው አድርባዮች ዥዋዥዌያቸውን ከቀጠሉ፣ አመራሮች ከአንገት በላይ “ተሳስተን - ነበር” ማለቱን እንደ አዘቦት ሰላምታ ከለመዱት፣ የበታች ምንዝሩም “ይሄ ቃል ተገብቶልን አልተፈፀመልንም” ማለቱን የዕለት ፀሎት ያህል መደጋገሙን እንጂ ሰርንቆና ገትቶ ተግባራዊነቱን ካልተቆጣጠረ፣ ወጥሮም ካልታገለ፣ ከህዝብ እሮሮና በደል አንፃር ስናየው፣ “ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ” ይሆናል፡፡ እናስብበት፡፡ ግምገማዎች ወደ አደባባይ ተግባር ያምሩ እንጂ፤ የአዳራሽ ቴያትር ሆነው አይቅሩ!

Read 6690 times