Sunday, 20 November 2016 00:00

የአዲሱ ካቢኔ ተስፋዎችና ፈተናዎች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(11 votes)

ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በግንቦት 200ገ ምርጫ ማግስት ራሳቸው ያቋቋሙትን የሚኒስትሮች ካቢኔ በመበተን፣ ከወትሮው በተለየ መንገድ በምሁራን የተዋቀረ አዲስ ካቢኔ መመስረታቸው አይዘነጋም፡፡ ሹመቱ የተከናወነው በዋናነት የትምህርት ዝግጅትና ብቃትን መሰረት አድርጎ
መሆኑን የገለጹት ጠ/ሚኒስትሩ፤ አዳዲሶቹ ሚኒስትሮች የህዝብን ጥያቄ ለመመለስ አቅሙና ብቃቱ ያላቸው እንደሆኑ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ፖለቲከኞችና የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችስ ምን ይላሉ? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ በአዲሱ ካቢኔ ዙሪያ የአንጋፋ ፖለቲከኞችን
አስተያየት እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡

“ኢህአዴግ በሩን በደንብ ከፍቶ መነጋገር አለበት”

አህመድ መሃመድ ሣኒ ሚሬ
(የአ.አ.ዩ 4ኛ ዓመት ኢንጂነሪንግ ተማሪ)

በኦሮሚያ ክልል ዋነኛ ጥያቄዎቹ የመሬት ጉዳይ፣ ስራ አጥነትና በፊንፌኔ ዙሪያ ላይ ናቸው፡፡ የስራ አጥነቱ ጥያቄ ሰፊውን ቦታ ይይዛል፡፡ የመሬትና የፊንፊኔ ጥያቄ ደግሞ የማንነት ጥያቄ መሰረት ያላቸው ናቸው፡፡ የማንነት ጥያቄ ስንል፣ የኦሮሞ ህዝብ የኢትዮጵያ ግንድ ነው፡፡ ከሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች ጋር ይዋሰናል፡፡ ስለዚህ ነው የኦሮሚኛ ቋንቋ ከአማርኛ ጋር የፌደራል ቋንቋ ይሁን የሚለው፡፡ ኦሮሚያ ለሀገሪቱ ከሚያመርተው የሰው ኃይል አንፃር ነው ከአማርኛ ጋር የስራ ቋንቋ ቢሆን የሚለው ጥያቄ የሚነሳው፡፡ ይሄ ደግሞ መልካም ጎን እንጂ መጥፎ ጎን የለውም፡፡ ጥያቄዎቹ በነዚህ ዙሪያ የሚሽከረከሩ ናቸው፡፡
በወቅቱ በጠባብነትና በትምክህተኛነት ከመፈረጅ ይልቅ፣ “ህዝቡን አወያዩ” የሚል ጥያቄ ለመንግስት ሲቀርብ ነበር፡፡ በ2008 መጀመሪያ አካባቢ በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በተዘጋጀ ስልጠና ላይ በዚህ ዙሪያ በሰፊው ተወያይተናል፡፡ እኔ በግሌ የአዲስ አበባ መስተዳድር ከንቲባ ጽ/ቤት ድረስ ሄጄ በማስተር ፕላኑ ላይ እውቀት ያላቸው፣ ሊያብራሩና ህዝቡን ሊያሳምኑ የሚችሉ ሰዎች ህዝቡን እንዲያወያዩ ሶስት ጊዜ ተመላልሼ ለመጠየቅ ሞክሬ አልተሳካልኝም፡፡ ያኔ ማንንም ሳልወክል በራሴ ተነሳሽነት ነበር የጣርኩት፡፡ ችግሩ በውይይት እንዲፈታ በነበረኝ  ፍላጎት ያደረግሁት ነው፡፡ በጊዜው በውይይት መፍታት የሚቻል ነገር ነው በኋላ ሰፍቶ የሰዎችን ህይወት የቀጠፈው፡፡
አሁን መንግስት እየወሰደ ያለው እርምጃም በእርግጥ መፍትሄ የሚያመጣ ከሆነ ጥሩ ነው፡፡ በእርግጥም የህዝቡ ጥያቄ የስልጣን ከነበረ፣ አሁን የተደረገው ሹም ሽር ምላሽ ሊሆን ይችላል፡፡ እኔ ግን ጥያቄው የስልጣን አይመስለኝም፡፡ ኦሮሞዎች በፊት በነበሩ መንግስታትም ውስጥ’ኮ ትልልቅ የስልጣን እርከኖች ላይ ነበሩ፡፡ ጥያቄው እገሌ የተባለ ባለስልጣን ይነሳልኝ፣ ኦሮሞ ይሹምልኝ አይመስለኝም፡፡ የህዝቡ ጥያቄ በትክክል መታወቅ አለበት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንግዲህ ለሀገሪቱ የሚጠቅም አዲስ ሃሳብ ይዘን እንመጣለን ብለዋል፡፡ ስር ነቀል ለውጥ የሚመጣ ከሆነም አብረን የምናየው ይሆናል፡፡
 ስልጣን ላይ ያለ መንግስት ወደ ህዝቡ የበለጠ መቅረብ አለበት፡፡ ኢህአዴግ እንደ ገዥ ፓርቲነቱ መስዋዕትነት ከፍሎ፣ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሁሉ መነጋገር አለበት፡፡ ምሁራኑም ዝም ብለው ውጪ ተቀምጠው የፈረንጅ ዜጎችን እያመረቱ፣ ”ኢህአዴግ እንዲህ ነው፤ ህዝቡ እንዲያ ነው” ማለታቸውን ትተው ይህቺን ሀገር ማዳን አለባቸው። እርግጥ ነው ተቃዋሚዎቹ ከኢህአዴግ የተሻለ ፕሮግራም ይዘው መጥተው፣ ህዝቡን በዙሪያቸው ማሰባሰብ የቻሉ አይደሉም፡፡ ኢህአዴግም ከማይችሉ ሰዎች ጋር ለመጫወት ወደ ሜዳ ይገባል፤ ህዝቡም ባይፈልገውም እንኳ እሱን ይመርጣል፡፡ ተቃዋሚዎች ከዚህ አዙሪት መውጣት አለባቸው፡፡ ኢህአዴግም በሩን በደንብ ከፍቶ በሚገባ መነጋገር አለበት፡፡

==================================

“የተሻሩ ባለስልጣናት ለምን እንደተሻሩ  መታወቅ አለበት”
አቶ አዳነ ጥላሁን (የመኢአድ ዋና ፀሐፊ

በዚህ አዲስ ካቢኔ ውስጥ በትምህርት ሻል ያለ ደረጃ ያላቸው ሰዎች መሰባሰባቸው አንድ ጥሩ ነገር ነው፡፡ ነገር ግን የሰዎች መለዋወጥ ምን ያህል ውጤት ያመጣል የሚለው በኔ እምነት ብዙም ለውጥ አያመጣም፡፡ በሌላ በኩል ተሽረዋል የተባሉት ሰዎች፣ ለምን እንደተሻሩ መታወቅ አለበት። የህዝብን ጥያቄ አከብራለሁ የሚል መንግስት፣ ይሄን ማሳወቅ አለበት፡፡ እነዚህ ሰዎች የተነሱት በምን ድክመት ነው? ድክመት ከሌለ ለምን ተነሱ? የሚለው ግልጽ ሊሆን ይገባል፡፡ ለምሳሌ የኦሮሚያ ፕሬዚዳንት ተሽረው በሌላ ተተክተዋል። ግን አሁንም በኦህዴድ ውስጥ ስራ አስፈፃሚ ናቸው፡፡ ስለዚህ የቀረባቸው አስተዳደርነቱ ነው፡፡ ይሄ እንዴት ሆነ? ግልፅ መደረግ አለበት፡፡ ኢህአዴግ ህዝብ ሳይጠላቸው አይቀርም የሚላቸውን ሹመኞች ያነሳል ግን የትም አያርቃቸውም፤ ስለዚህ ሹም ሽር ብቻውን በቂ አይሆንም፡፡ የፖለቲካ ምህዳሩ ይሰፋል፤ የምርጫ ስርአቱ ይስተካከላል ተብሏል። የተባለው ተሞክሮ መታየት አለበት፡፡ ችግርን በኃይል ከመፍታት በድርድርና በንግግር መፍታት ይቻላል የሚል አቋም አለን። በሆደ ሰፊነትና በመቻቻል ፖለቲካ እናምናለን። በዚህም መሰረት በድርጅታችን በመኢአድ በተደጋጋሚ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ደብዳቤ ፅፈናል። መፍትሄ የሚሆነው ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ መምጣት ነው፡፡ ለሃገሪቱ ችግሮች የመጨረሻው መፍትሄ ድርድር ነው፡፡ በድርድሩ ላይም የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች ሁሉ እንዲሳተፉ ማድረግ ይገባል፡፡  

================================

“ለፖለቲካዊ ጥያቄ ፖለቲካዊ መልስ ነው የሚሆነው”

አቶ ግርማ ሰይፉ (የቀድሞ የፓርላማ አባል)

እኔ በግሌ ኢህአዴግ ካቢኔውን “እንዲህ ያድርግ፣ እንዲያ ያድርግ” በሚለው ላይ የሚያገባን አይመስለኝም፡፡ የኢህአዴግን ፖሊሲ ሊያስፈፅምለት የሚችል የፈለገውን ካቢኔ የማዋቀር መብቱም ምርጫውም የሱ ነው፡፡ በእርግጥ ከስራው ጋር እውቀትና ልምድ ያላቸውን ሰዎች መልምሎ ስራውን ለመስራት ያስችላል በሚል ፍልስፍና ካቢኔ ማዋቀር በዓለም ላይ ያልተለመደ ነው፡፡ ካቢኔ ሚኒስትሮች የፖለቲካ ተሿሚዎች እንጂ ሙያተኞች አይደሉም። ካቢኔ ተሿሚዎች የሚያስፈልጋቸው የፖለቲካ አቅም ነው፡፡ እነዚህ ካቢኔዎች የህዝቡን ችግር ይፈቱ እንደሆን እንግዲህ በቀጣይ የምናየው ነው፡፡ ነገር ግን እንደኔ የህዝቡ ጥያቄ ይሄ አይመስለኝም፡፡ ካቢኔ ለውጡልን ብሎ ጥያቄ ያነሳ የለም፡፡ ጥያቄው የአንድ ፓርቲ አገዛዝ ይቁም ነው፡፡ ስለዚህ አሁን እየሆነ ያለው ያልጠፋበት ቦታ ሄዶ የጠፋ እቃን እንደመፈለግ ነው፡፡ ጥያቄው የነበረው የዲሞክራሲ እንጂ “እገሌ የተባለው ሚኒስትር ይነሳልኝ” የሚል አልነበረም፡፡ እኔ ከተሳሳትኩ እታረማለሁ፡፡
አዲሱ ካቢኔ “የኢትዮጵያ ህዝብ የፖለቲካ ሪፎርም ነው የጠየቀው፤ ሪፎም መደረግ አለበት” የሚል ጥያቄ የሚያቀርብ ከሆነ፣ እኔ ቆሜ ነው የማጨበጭበው፡፡ እንደሚመስለኝ ግን ይሄ ካቢኔ ተሰብስቦ ፖለቲካዊ ሳይሆን ቴክኒካዊ ነገሮችን ነው የሚገመግመው፡፡ ለፖለቲካዊ ጥያቄ ደግሞ ቴክኒካዊ መልስ አይሆንም፤ ለፖለቲካዊ ጥያቄ ፖለቲካዊ መልስ ነው የሚሆነው፡፡
የምርጫ ስርአቱ ይሻሻላል የሚለው ህገ መንግስታዊ ማሻሻያን የሚጠይቅ ነው፡፡ ይሄን ሳያገናዝቡ የምርጫ ስርአቱ ይሻሻላል ማለታቸው ግራ አጋቢ ነው፡፡ ሁለትና ሶስት ወንበር እየሰጡ “ተቃዋሚዎች በፓርላማው አሉ” ለማለት ይመስላል እንዲህ ሊያደርጉ ያሰቡት፡፡ መቀየር ያለበት ግን የራሳቸው የአውራ ፓርቲ ፍልስፍና ነው፡፡ አውራ ፓርቲነት በእድል ተቀባይነት ይኖረዋል፤ አውራ ፓርቲነት በሂሳብ ስሌት ከመጣ ግን አይሆንም፡፡ ሚዲያ እንከፍታለን የመሳሰሉት ለኔ አይታየኝም። በአሁን ሰዓት 20 ጋዜጦች ቢኖሩ ምን ይዘግባሉ? ምንም አይዘግቡም፤ ምክንያቱም ምንም የፖለቲካ እንቅስቃሴ የለም፡፡ መጀመሪያ የፖለቲካ ምህዳሩ መስፋት አለበት፡፡  ይሄ ደግሞ ከባድ አይደለም፤ ማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት ትክክለኛ ነው ብሎ ያመነበትን ሃሳብ በነፃነት እንዲያንቀሳቅስ መፍቀድ ነው፡፡ አሜሪካ ለትራምፕ የሰጠችውን እድል በኢትዮጵያ የተሳሳተ አመለካከት ያለው ፓርቲ ቢቋቋምም እድል ሊሰጠው ይገባል፡፡ ህዝቡ የተሳሳተ ሀሳብ ከመረጠም ለዚያ እድል ተሰጥቶት፣ ስህተት መሆኑን ራሱ በተግባር ማረጋገጥ አለበት፡፡ በቃ ሜዳውን መክፈት አለባቸው፡፡ እኛ ኢህአዴግ ማሊያ እንዲገዛልን፣ እንዲያጠናክረን አይደለም፤ በሰላም እንድንንቀሳቀስ ካደረገን በቂ ነው፡፡
መንግስትና ፓርቲ መለያየት አለባቸው፡፡ እነዚህ ካልተለያዩ የመንግስትን ፖሊሲ ስትቃወም፣ ፖሊስ መጥቶ ይደበድባል፡፡ በዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ የፖለቲካ ምህዳር አስፍቶ መንቀሳቀስ አይቻልም። ፓርቲ ሳይሆን ስርአት የሚያዘው ፖሊስ ነው የሚያስፈልገው፡፡ ከፖሊስ ጣቢያዎች ላይም የአቶ መለስን ፎቶግራፍ ማንሳት አለባቸው። ሌላው ችግሩን የፈጠሩ ሰዎች ብቻቸውን ተሰብስበው ችግሩን ሊፈቱ አይችሉም፡፡
ጥያቄ ያነሳውን ህዝብ እያሰሩ፣ ጥያቄ ያላነሳውን ቀድሞም አብሯቸው የነበረን ህዝብ ሰብስቦ መወያየት ውጤት እንደማያመጣ እሙን ነው፡፡ አሁን መወያየት ያለባቸው ድሮ ከማያወያዩት ሰው ጋር ነው፡፡
በውይይት መድረኮች ላይ በትክክል የተከፋውን ህዝብ የሚወክል ሰው ነው መሳተፍ ያለበት፡፡ ውይይት ያስፈልጋል ስንል በራችሁን ዘግታችሁ ተወያዩ እያልን አይደለም፤ እንወያይ ማለታችን ነው፡

==============================================

“የግለሰቦች ለውጥ ብቻውን መልስ ሊሆን አይችልም”
አብርሃ ደስታ (ፖለቲከኛ እና የፍልስፍና ምሁር)

በመጀመሪያ አዲስ የተቋቋመው ካቢኔ ምንም እንኳ ለውጥ ባያመጣም እንደ ሀሳብ ጥሩ ነው። ሁኔታውን ለመቀየር ጥረት እያደረግሁ ነው ለማለት እንደ ጅምር ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን ለውጥ የሚያመጣ ነገር አይደለም፡፡
ምክንያቱም አንደኛ የህዝቡ ጥያቄ የስርአት ለውጥ ጥያቄ እንጂ የግለሰብ ባለስልጣናት ጥያቄ አይደለም፡፡ ስለዚህ የግለሰብ ለውጥ ብቻውን መልስ ሊሆን አይችልም፡፡ ሌላው የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ናቸው መባሉን በተመለከተ መጀመሪያ ምሁራን ወደ ፖለቲካ እንዲገቡ ከተፈለገ መደረግ የነበረበት የመንግስት መዋቅርና ፓርቲን መለያየት ነው፡፡ ከዚያም ምሁራን በተለያየ አግባብ በመንግስት ተቋማት እንዲሰሩ በመፍቀድ የፖለቲካ ልምድና አቅም ማሳደግ የሚችሉበትን ሁኔታ መፍጠር ያስፈልግ ነበር፡፡
አሁን ዩኒቨርሲቲ ስላስተማሩና ሰርተፊኬት ስላላቸው ብቻ የፖለቲካ ስራ መስራት ይችላሉ፤ ፖለቲካ ያውቃሉ ማለት አይደለም፡፡ ከፖለቲካ ርቀው የነበሩ ሰዎችን በቀጥታ ወደ ፖለቲካ ማምጣት የራሱ ችግር ይኖረዋል፡፡ መፍትሄም አይሆንም፡፡
ሌላው እነዚህ ሰዎች ከኢህአዴግ ስርአት ነፃ ናቸው ማለት አይደለም፡፡ አብዛኞቹ አባላትና ደጋፊዎች ናቸው፤ ስለዚህ ከበፊቱ ብዙ የተለየ አሰራር ሊያመጡ አይችሉም፡፡ እነዚህ ሰዎች የፖለቲካ አቅም አላቸው እንኳ ቢባል ስርአቱ በነፃነት እንዲሰሩ ካልፈቀደላቸው የሚያመጡት ለውጥ አይኖርም፡፡ አንድን ሚኒስትር እኮ ታች ያለ 8ኛ ክፍልን ያላጠናቀቀ አንድ ተራ ካድሬ የሚያዝበት አሰራር ነው ያለው፡፡ በዚህ ሁኔታ ለውጥ ይመጣል ብዬ አልጠብቅም፡፡
ሌላው የምርጫ ስርአቱ ይሻሻላል ለሚባለው በመጀመሪያ ደረጃ መስተካከል ያለበት ነገር ስርአቱ ነው፤ ህዝብ የስልጣን ባለቤት እንዲሆን ከተፈለገ ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ መሆን አለበት፡፡ ለፓርቲዎች እውቅና መስጠትና ማፍረስ የምርጫ ቦርድ ስልጣን መሆን የለበትም፤ የፍርድ ቤት ነው መሆን ያለበት። ህግን የመተርጎም ጉዳይ የፌዴሬሽን ም/ቤት ሳይሆን የፍርድ ቤት ነው መሆን ያለበት፡፡ ፍ/ቤት ደግሞ ከሁሉም በላይ ነፃ መሆን አለበት፡፡ ፍ/ቤት ነፃ እስካልሆነ ድረስ ስለ ምርጫ ቢወራ ትርጉም የለውም፡፡
በሌላ በኩል ነፃ የግል ዜና አቅራቢ መገናኛ ብዙኃን መከፈት አለባቸው፡፡ ህዝብ አማራጭ ሚዲያዎችን ማግኘት አለበት፡፡ የሁሉንም ፓርቲዎች ሃሳብ የሚያስተናግዱ ሚዲያዎች መፈቀድ አለባቸው፡፡ ከእነዚህ ነው የሚጀምረው፡፡ ያለበለዚያ ምርጫው ተመጣጣኝ ሆነ አልሆነ፣ትክክለኛ አሰራር ከሌለና የህዝብ ድምፅ የማይከበር ከሆነ ትርጉም የለውም፡፡ መጀመሪያ ሜዳውን ክፍት ያደርጉት፤ከዚያ ህዝቡ የሚፈልገውን ይምረጥ፡፡ በአጠቃላይ ቃል የተገባውን ነገር ከፈፀሙ ትንሽ ለውጥ ሊኖር ይችላል፡፡

Read 5623 times