Sunday, 13 November 2016 00:00

ትረምፕ በዋይት ሀውስ ይፈተናሉ!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(16 votes)

   ትውልድ የሚያፈራርቀው የዋይት ሀውስ ቅጥር ግቢ፣ በየአራትና ስምንት ዓመቱ የሀገሪቱን ምርጦች እየተቀበለና እየሸኘ ሲዘልቅ፣ ከፊሉ እንደ ገነት አንዳንዱ ደግሞ እንደ እስር ቤት ሲቆጥረው ዛሬም ድረስ አለ፡፡ በአዲሱ የፈረንጆች ዓመት በጥር 2017፣ የፕሬዚዳንትነት ዘመናቸውን አጠናቀው ከዋይት ሀውስ የሚሰናበቱት ባራክ ኦባማና ቤተሰባቸው ምን እንደሚሉ ባይታወቅም፣ ከዚያ ቀደም የነበሩት ግን የተለያዩ ስሜቶችን አንጸባርቀዋል፡፡
የጆርጅ ቡሽ ባለቤት ባርባራ ቡሽ፤ “ዋይት ሀውስ ውስጥ ገብቶ ደስተኛ ያልሆነ ሰው የትም ቢሄድ ደስተኛ ሊሆን አይችልም” በማለት የደስታቸውን ፅንፍ ባንድ ዓረፍተ ነገር ቋጭተዋል፡፡ ለዚህ ምክንያታቸው ደግሞ፡- “በሙዚየም ደረጃ የሚታዩ የቤት ቁሳቁሶች፣ ምርጥ የግቢው ሰራተኞችና ሼፎች እንዲሁም ሌሎች በርካታ የቅንጦት ህይወት ማሟያዎች ያሉበት ሥፍራ ነው” የሚል ነበር፡፡
የጄነራል ግራንት ባለቤት ጁሊያ ግራንትም ተመሳሳይ ስሜት ያንጸባርቃሉ፡- “ዋይት ሀውስ ያሳለፍኳቸው ስምንት ዓመታት በህይወቴ በጣም ደስተኛ የሆንኩባቸው ጊዜያት ነበሩ” በማለት፡፡ ፕሬዚዳንት ቴዎዶሮ ሩዝቬልት ለልጃቸው በፃፉት ደብዳቤ ብለዋል፡- “I don’t think any two people ever got any more enjoyment from the white house than mother and I.”
እውነት ነው፤ ዋይት ሀውስ ብዙ ወግ ማዕረግ ያዩ ደስተኛ ቤተሰቦች አሉ፤ የዚያኑ ያህል ደግሞ በእንባ የታጠቡ፣ በለቅሶ የተለዩም አልጠፉም፡፡ የደስታውን እንቀጥልና የጄኔራል ግራንት ብርቅዬ ሴት ልጅ ኒሌ፤ እንግሊዛዊውን ወጣት ወድዳ ስትዳር፣ አባትዋ ቅር ቢላቸውም “አሸወይና” ተብሎላታል፡፡ ለዚያውም የመወድስ ግጥሞችዋን የፃፈላት የ19ኛው ምዕተ ዓመት አሜሪካዊ ገጣሚ ዋልት ዊትማን ነበር። “ኦ - ሸጋዋ ሙሽራ!” በማለት፡፡ ስጦታ እንደ ጉድ ጎርፎላታል፡፡ ድል ያለ ድግስም ተደግሶላታል፡፡   
ዋይት ሀውስ ውስጥ እንደ አላይስ የቀበጠና የዘነጠ የለም፡፡ ሀገር በፍቅር የጣለች፣ እንደ ልቧ የሆነች ነበረች፡፡ ዋሽንግተንን ቀውጢ አድርጋለች። ለዚያ ነው ፀሐፊው፡- “The country fell in love with her!” ያላት፡፡ አባትዋ ቴዎዶሮ ሩዝቬልት ይቆጣጠሯት ዘንድ ተመክረዋል፤ ተዘክረዋል። እሳቸው ግን፡- “እኔ ሀገር መምራትና የሷን ጭራ መከተል አልችልም፡፡” ብለው ነበር፡፡ ታዲያ በበጋው መዝናኛ ወቅት ቤተሰቡ በሙሉ ለመዝናናት የሄደበት ቦታ፣ አንድ ወጣት መኪና እየነዳ መጣና ድንገት በሩን ከፍቶ ገባ፡፡ ሩዝቬልት ሽጉጣቸውን መዘዙ፡፡ ምላጭ ሊስቡ ሲሉ የመጣበትን ምክንያት ተናገረ፡፡ … በአላይስ ፍቅር ከንፏል፡፡ ሽጉጣቸውን መለሱ፡፡
ሰርጓ ዋይት ሀውስን ክንፍ አስነቀላት፤ ምስራቃዊ ክፍል በሚባለውና ብዙ ድግሶች በተካሄዱበት አዳራሽ 680 እንግዶች ታድመው፣ 145 ሰረገላዎች ግቢውን አጥለቅልቀው፣ ከግቢው ጥበቃዎች ሌላ በር ከፋች ፖሊሶች ተጨምረው ሰርጉ ጦፈ፡፡ ሥጦታው አይነገርም፡፡ ከመላው ዓለም መሪዎች ተጠርተው ነበር፤ ከቻይና ሳይቀር!
ዋይት ሀውስ ለብዙዎች ገነት የሆነችውን ያህል እንደ ሲኦል የቆጠሯትም አልጠፉም፡፡ ፕሬዚዳንት ሃሪ ትሩማን ይጠቀሳሉ፡፡ “… እዚህ አሮጌ ቤት ተጎልቼ … ስራ እሰራለሁ፡፡ … የምሰማው ሁሉ የዱካክ ኮቴ ነው፤ ሲወጣ … ሲወርድ፡፡ … ይሄ ነጭ ወህኒ ቤት፣ ለብቻ የሚኮንበት ሲዖል ነው፡፡” የቅርቡ ቢል ክሊንተን ደግሞ፡- “… ዋይት ሀውስ የፌደራል ማረሚያ ቤት ስርአትን በአልማዝ  ያንቆጠቆጠ ዘውድ ነው!” ብለውታል፡፡
የፕሬዚዳንት ሊንደን ቢ. ጆንሰን ባለቤትም ልክ እንደ ሃሪ ትሩማን ለዋይት ሀውስ የነበራት ጥላቻ ልክ የለሽ ነው፡፡ “የወጣትነት ህይወቴን በዋይት ሀውስ ተሰርቄያለሁ!” ነው ያለችው፡፡ ፕሬዚዳንት ታፍት ደግሞ በዋይት ሀውስ ያሳለፏቸውን ዓመታት ፍርድ ቤት በዳኝነት ቢያሳልፉ ለሀገራቸው የተሻለ ነገር ይሰሩ እንደነበር በቁጭት ተናግረዋል፡፡ ለሳቸው የፕሬዚዳንትነቱ ዘመን ጊዜ ማባከን ነው፡፡ ለዚያውም የሥልጣን ጊዜያቸውን ያጠናቀቁት ፕሬዚዳንት መሆናቸውን ልብ ሳይሉት ነበር፡፡
ዋይት ሀውስን በፌሽታ ጮቤ ያስረገጡትና በሰራተኞች ዘንድ በመወደድ አቻ የማይገኝላቸው  የፕሬዚዳንት ኤሊኖር ሩዝቬልት ቤተሰቦች ነበሩ። ታዲያ ሩዝቬልት ወደ ዋይት ሀውስ እንደገቡ ለግቢው ሰራተኞች፡- “You will find us a noisy family” ብለው ነበር፡፡ እውነትም ከዚያን ቀን ጀምሮ ዋይት ሀውስ በቀልድ፣ በሳቅ፣ በፌሽታ ጨርቁን ጣለ። ቀድመዋቸው የነበሩትን የታፍት ቤተሰቦች ፍቅር የጎደለው ህይወት ካሣ ሆነው ገቡ ተብሎላቸዋል። “ሩዝቬልት ዋይት ሀውስን ፕሬዚደንት የሌለበት ቤተ መንግስት አስመስለውት ነበር፡፡ አያስፈሩም፣ ለሰው ቅርብ ናቸው፡፡” ሲል ታሪካቸውን የጻፈላቸው ደራሲ ከትቧል፡፡  
ፕሬዚዳንት ታፍት ግን ቀዝቃዛ፣ ሰው የማይቀርቡ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን ደስ የማያሰኝ ብዙ ልማድና ጠባይ ነበራቸው ይሏቸዋል - የዋይት ሀውስ ሰዎች። ለምሳሌ ትልቅ የቀብር ስነ ስርአት ለመሳተፍ ሄደው በድንገት እንቅልፍ ይዟቸው ይሄዳል፡፡ ይሄ አብሯቸው የሄደው ሰው ይሳቀቃል፡፡ ሰውየው ሲናገር፤ “ወዲያው እንቅልፍ እንደወሰዳቸው ማንኳረፍ ይጀምራሉ! .. ያኔ መሬት ተከፍታ ብትውጠኝ እወዳለሁ” ይላል፡፡
ፕሬዚዳንት ታፍትና ቴዎዶሮ ሩዝቬልት ሲነፃፀሩ፤ ቴዎዶሮ ሩዝቬልት በሰርግም ሆነ ለቅሶ እንኳን ሊያንኮራፉ ቀርቶ አያስነጥሱም ብለው ያደንቋቸዋል። የእሳቸው ችግር ሰው ሁሉ ትኩረት እንዲሰጣቸው ይፈልጋሉ፤ ያንን ካጡ ያብጣሉ፡፡ የገዛ ልጃቸው አላይስ እንዲህ ትላለች፡- “የኔ አባት በሰው ሰርግ ሙሽራ፣ በየለቅሶውና ቀብሩ ላይ ሬሳ ልሁን ይላል፡፡”
የዋይት ሀውስ ሰው ዓመሉ እንደ መልኩ ሺህ ነው። ፕሬዚዳንቶቹ ባልተጠበቀ ሁኔታ ጠባያቸው ወርዶ የሚገኝበት ጊዜም አለ፡፡ ደረጃቸውንና ስልጣናቸውን የሚተካከል ስርአት ያላቸውም ገብተው ወጥተዋል፡፡
የጠባይ ነገር ከተነሳ ብዙ ነገር ያወሳሉ፤ የዋይት ሀውስ ሰራተኞቹ፡፡ አንድ የግቢው ኃላፊ ሲናገር፤ ፕሬዚዳንት ጆንሰን መጀመሪያ ዋይት ሀውስ እንደመጡ፣ መታጠቢያ ቤቱን አይተው ተበሳጩ፤ “ይህንን የመታጠቢያ ክፍል አሁን ካላስተካከልከው፣ ወደ ቀድሞ መኖሪያዬ እመለሳለሁ!” በማለት የቂል ማስፈራሪያ ሰጡኝ፡፡” ብሏል፡፡ እርሱም አላቅማማም፡፡ የውሃ ታንከር አስመጥቶ፣ ዕቃ ለውጦ ለማስተካከል ሞከረ፡፡ በኋላ ብዙ ሺህ ዶላሮች ፈሰሱ፤ ሁኔታው ተስተካከለ። ታዲያ ኃላፊው ዌስት ስለ ጆንሰን የገረመው ነገር እኒሁ ፕሬዚዳንት የሀገር ሀብት እንዳይባክን ማታ ማታ አምፖሎች ያለ አገልግሎት መብራት የለባቸውም፤ በማለት ቤተሰቦቻቸውን መብራት እንዲያጠፉ ያዝዙ ነበር፡፡
ከጆንሰን ቀጥሎ የመጡት ፕሬዚዳንት ኒክሰን ደግሞ መታጠቢያ ክፍሉን አይተው፤ “ይህንን ቅራቅንቦ አሥወግዱልኝ” አሉና አረፉት። ሚስታቸው ቀዳማዊ እመቤትም፤ መታጠቢያ ክፍሎቹ በጌጠኛ መብራቶች እንዲያቆጠቁጡ አዘዙና እንደዚያው ተደረገ፡፡ ኒክሰን የእሳት ፍቅር የተጣባቸው ነበሩ፡፡ በጋ ሆነ ክረምት፤ ቅዝቃዜ ሆነ ሙቀት፤ ከማቀጣጠያው ላይ ፍልጦች እንዲጠፉ አይፈልጉም፡፡ የሊንከን የጥናት ክፍል ውስጥ ሁሌ እሣት አይጠፋም፡፡
ይህን ሁሉ ታዲያ እምቢ ማለት አይታሰብም። ሁሉንም እሺ ነው፡፡ ‹‹Whatever a president wants, the White house delivers; no questions, only action, a ‹‹yes sir!›› service...››
ትልቁ ጆርጅ ቡሽ በዋይት ሃውስ “የአበባ ጎመን አልይ” ብለው ሲያስነቅሉ፤ በምትካቸው የመጡት ቢል ክሊንተን ደግሞ “የአበባ ጎመኑን መልሳችሁ ትከሉ” ብለው ነበር፡፡…
የቀዳማዊ እመቤቶቹ ፀባይ ደግሞ  የጉድ ነው። የታፍት ባለቤት ነገረኛና ጠበኛ የሆኑትን ያህል፣ የሩዝቬልት ደግሞ ፍልቅልቅና ልበ ቅርብ ነበሩ እያሉ ያወሣሉ፤ የግቢው ሰዎች፡፡ ግቢው ውስጥ ያልተለመደና የማይረሣ አጋጣሚ ከገጠሟቸው ሰዎች መካከል አንዱ ፍራንሲ ቢ. ስይር የተባለው ወጣት ነው፡፡ ይህ ወጣት ምሁር የፕሬዚደንት ውድሮ ዊልሰንን ልጅ አጭቶ፣ ሙሽሪት ሰርጉ ቀላል ባለ ሁኔታ እንዲደረግ አስባ ስለነበር፣ በዋይት ሃውስ ጠበብ ያለ ክፍል (ሰማያዊው ክፍል) ውስጥ እንዲሆን መረጠች፡፡ ያለ ብዙ ግርግር እንዲጠናቀቅ ተወስኖ ነበር፡፡ በሠርጉ ቀን ሙሽራው ሽክ ብሎ ሲመጣ፣ ዋይት ሀውስ መግቢያ ላይ በጠባቂዎች ተያዘ፡፡ ሙሽራ የግብዣውን ካርድ ባለመያዙ አምባጓሮ ተፈጠረ፤ ቆፍጠን ያለው የፖሊስ አዛዥ አላስገባም አለው፡፡ ሙሽሪት ያለ ሙሽራው ብቻዋን ቀረች፡፡ ከዚያም አደባባይ እንዳይወጣ የፈለገችው ምስጢር በማግስቱ፣ “ዋሽንግተን ፖስት” ጋዜጣ የመጀመሪያው ገፅ ላይ ወጣ፡፡ “ሙሽራው የቀረባት ሙሽሪት” በሚል፡፡  
እንግዲህ እንዲህ ባለው የዋይት ሀውስ የሕይወት ዑደት ውስጥ መግባት ፈልገው ያልገቡም ነበሩ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንዷ የአንድሪው ጃክሰን ባለቤት ራሄል ነበረች፡፡ ይህች ሴት ባልዋ ለፕሬዚዳንትነት ተመርጦ ዋይት ሀውስ መግባቱ እውን ከሆነ በኋላ፣ ፕሬዚዳንታዊ ንግግሩን ለማድረግ ሁለት ወራት ሲቀሩ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ፡፡ ራሄልም፤ ‹‹ቀዳማዊ እመቤት›› የሚለውን ስያሜ ሳታገኘው ቀረች፡፡ ሌላኛዋ ያልተሣካላት ሴት፣ የፕሬዚዳንት ዊልያም ሔነሪ ሐሪሰን ባለቤት ናት፡፡ ይህቺም ሴት ባለቤትዋ ፕሬዚዳንታዊ ንግግሩን ባደረገ በወሩ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየና የጓጓችለትን የዋይት ሀውስ ሕይወት ሳታይ ተነጠቀች፡፡
አዎ ዋይት ሀውስ ዛሬም እንደ ሁልጊዜው ናት። የሣቅና የለቅሶ፣ የሀዘንና የደስታ፣ የድልና የሽንፈት መድረክ!...
ዛሬስ የፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ቤተሰብ ትዝታ ምን ይሆን?.. በሥልጣን ዘመናቸው ያሰቡትንና የተጠበቀባቸውን ያህል አልሠሩም!... በሚሏቸው ሰዎችና መገናኛ ብዙኃን ፊት ልባቸው ምን ይዘምር ይሆን?.... መሰናበቻቸው ላይ የዋይት ሀውስ  ሰራተኞች ቸልተኝነትስ የቤተሰባቸውን ልብ በሀዘን ይገርፈው ይሆን?.... ወይስ ኦሳማ ቢን ላደንን የሚያህል ቁንጮ ሽብርተኛ  ማስወገዳቸው ልባቸውን ጮቤ ያሥረግጠዋል?
 ዋይት ሀውስ የእሣት መድረክ ናት፤ትፈትናለች!... ዓመዱ በእንባ፣ ውስጡ በፈዛዛ ትዝታ ሲቀር፤ ወርቁ በታሪክ መድረክ ላይ ይንቀለቀላል፡፡… ሊንከን የዋይት ሀውስ ወርቅ፤ የአሜሪካ የታሪክ ጉልላት የሆነውም ለዚህ ነው፡፡ የአሁኑ ዶናልድ ትራምፕ፤ ዋይት ሀውስ ሲገቡ የግቢው ሰዎች እንዴት ባለ ስጋት ይቀበላቸው ይሆን? … ዘንባባ ዘንጥፈው፣ ወይስ ፊታቸውን ከስክሰው? እንግዲህ ትራምፕ እንደ ምርጫ ቅስቀሳ ንግግራቸው ከሆነ … ዋይት ሀውስ ጉድዋ ፈላ! … ትራምፕ በዋይት ሀውስ እሳት ነጥረው እንደ ወርቅ ወይም ነድደው እንደ አመድ ይቦንናሉ … “ይለያል ዘንድሮ!” ማለት ይሄኔ ነው።  

Read 4611 times