Sunday, 13 November 2016 00:00

ፖለቲከኞች ስለ ትራምፕ ምን ይላሉ?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(9 votes)

‹‹ትራምፕ በዘረኝነቱ ነው ድምፅ ያገኘው››
ዶ/ር በዛብህ ደምሴ (የመኢአድ ፕሬዚዳንት)
   የአሜሪካን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ተከታትለውታል?
ምርጫው በንግድ አለምና በፖለቲካ አለም ባሉ ሰዎች መካከል የተካሄደ ነው፡፡ ሰውየው ጠንካራ ነጋዴ ነው፡፡ ሂላሪ ደግሞ በአሜሪካ ፖለቲካ ውስጥ የምትታወቅ ጠንካራ ፖለቲከኛ ነች፡፡ እሷና ኦባማ ዲሞክራትን ወክለው ለእጩነት ሲወዳደሩ፣ እኔ አሜሪካ ስለነበርኩ በትኩረት  እከታተል ነበር፡፡ ሴትየዋ ከፍተኛ ፉክክር ነበር የምታደርገው፡፡ ብዙ ትታገላለች፡፡ ዶናልድ ትራምፕ ምንም የፖለቲካ እውቀት የለውም፡፡ የሁለቱ የፖለቲካ እውቀት የሠማይና የምድር ያህል የተራራቀ ነው፡፡ የእሷ እውቀት ከፍተኛ ነው፡፡
ግን ምርጫውን ዶናልድ ትራምፕ አሸነፈ-----
ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ ክርክር ላይ ሲናገር የነበረው የአሜሪካውያን ነጮችን ልብ የሚነካ ነበር። “ከአፍሪካ፣ ከኤዥያ፣ ከላቲን አሜሪካ የሚመጡ ስደተኞች የእናንተን ስራ እየወሰዱባችሁ ነው፣ ጠላቶቻችሁ ናቸው፤ እነሱ ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ አደርጋለሁ” ይል ነበር፡፡ አሜሪካንን ወደ ታላቁ ቦታዋ እመልሳታለሁ የሚል ትልቅ ፕሮፓጋንዳ ሰርቶ ነው ያሸነፈው፡፡ ሰውዬው ዘረኛ ቢጤ ነው፡፡ በዚህ ምርጫ  ድምፅ የሠጡት ደግሞ በዝቅተኛ ደረጃ ያሉ ነጭ አሜሪካውያን ናቸው፤ ስለዚህ ይሄ ሰውዬ ልባቸውን ነክቶታል፡፡ በዘረኝነቱ ነው ድምፅ ያገኘው፡፡
 ትራምፕ ያሸንፋል ብለው ጠብቀው ነበር?
ፈፅሞ! ግን እጠራጠር ነበር፡፡ ሂላሪ ታሸንፋለች የሚል ግምት ነበረኝ፡፡ ትራምፕ ያሸንፋል ብዬ  አላሰብኩ፡፡ ምርጫው 3 ቀን ሲቀረው ይሄ ሰውዬ ሊያሸንፍ ይችላል ብዬ መጠራጠር ጀመርኩ፡፡ ሰውዬው በአነጋገሩ የነጭ አሜሪካውያንን ቀልብ ይስብ ነበር፡፡
የትራምፕ ማሸነፍ በኢትዮጵያ ላይ ምን ተፅዕኖ ይኖረዋል ብለው ይገምታሉ?
ለኢትዮጵያውያን ዲሞክራትም ሆነ ሪፐብሊካን ልዩነት የላቸውም፡፡ እንደኔ ሂላሪ ክሊንተን ለኛ ትጠቅመናለች የሚል እምነት የለኝም፡፡ ሁለቱም ለኛ ልዩነት የላቸውም፡፡ ከትራምፕ በኋላ ምን ይፈጠራል የሚለውን መገመት ያዳግታል፡፡ ሪፐብሊካኖች ከዲሞክራቶች የተሻለ ያስባሉ ብዬ መገመት አልችልም። ጆርጅ ቡሽ ሪፐብሊካን ነበር፡፡ ኢትዮጵያንም በጣም ይረዳ የነበረ ሰው ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ነጋዴ ነው፤ ገና አላየነውም፡፡ በሂደት ብናየው የተሻለ ነው፡፡
================================

“አሜሪካንን የሚመራው ሲስተሙ ነው”
አቶ ልደቱ አያሌው (ፖለቲከኛ)

ዶናልድ ትራምፕ ፕሬዚዳንት ይሆናሉ ብለው ጠብቀው ነበር?
እኔ ከመጀመሪያውም እንደሚያሸንፍ ጠብቄዋለሁ፡፡ አሁን ሳይሆን የማሸነፍ እድላቸው 1 በመቶ ነው በተባለበት ወቅት እንኳ የኔ ግምት ከዚያ የተለየ ነበር፡፡ ሰውዬው በጣም አደገኛና  የማሸነፍ እድል እንዳላቸው ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እገምት ነበር። ከብዙ ወዳጆቼ ጋርም ተከራክሬበታለሁ፡፡ ስለዚህ ትራምፕ ማሸነፋቸው አልገረመኝም፡፡ የጠበቅሁት ነው የሆነው፡፡
እንዴት ያሸንፋሉ ብለው ሊገምቱ ቻሉ?
አራት ነገሮች ናቸው እንድገምት ያደረጉኝ። ሰውየው አራት ወሳኝ ጥያቄዎች ነው ይዘው የመጡት፡፡ አንደኛ፤ ከቻይና እና ከሌሎች አለማት ጋር ያለውን የንግድ ትስስር በሚመለከት፣ “ስራችንን እየቀሙት ነው፤ ሀገር ቤት ያለውን ኢንዱስትሪ እየገደሉት ነው” የሚለው ቀላል ገዥ አስተሳሰብ አይደለም፡፡ የአሜሪካ ሱፐር ማርኬቶች “made in china” በሚሉ እቃዎች ነው የተሞሉት፤ በዚህ ረገድ ህብረተሰቡ ውስጥ የነበረው ቁጭት ቀላል አይደለም፡፡
ሁለተኛው፤ ከኒውዮርክ የአሸባሪዎች ጥቃት በኋላ የአሜሪካ ህዝብ የፀጥታ ዋስትና ችግር ውስጥ ወድቋል፡፡ ህይወታቸው በሙሉ ስጋት የተሞላ ሆኗል፡፡ ከእስልምና አክራሪነት ጋር በተያያዘ ውስጥ ውስጡን ከፍተኛ የሆነ ፍርሃትና ጭንቀት አለ፡፡ ሶስተኛ፤ ከስደተኞች ጋር በተያያዘ ሀገሪቱ የበርካታ ስደተኞች መዳረሻ ነች፡፡ በዚያ ምክንያት ሀገር ውስጥ ያለው ሲስተም ችግር ውስጥ የገባበትና ህብረተሰቡም በጣም የተማረረበት ሁኔታ ተፈጥሯል። በአንፃሩ እነዚህን ነገሮች ወደ አደባባይ አውጥቶ መተቸት እንደ ፖለቲካ ስህተት ተደርጎ ስለሚቆጠር ፖለቲከኞች ደፍረው አያነሷቸውም፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ነገሮች ከዘረኝነትና ከጥላቻ ጋር ተያይዘው ስለሚታዩ፣ ደፍሮ
የሚያነሳቸው ፖለቲከኛ አይኖርም፡፡ ህዝቡ ውስጥ ግን በጣም ሲብላሉ የነበሩ ቁልፍ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ትራምፕ ይዘዋቸው የመጡት እነዚህን ነው። እነዚህን ነገሮች ይዘው ሲመጡ በደንብ አስበውበት እንደሆነ ለኔ ግልፅ ነበር። በአራተኛ ደረጃ ከዋሽንግተን ፖለቲካ ውጭ በመሆናቸው ነው፡፡ የአሜሪካ ህዝብ የተወሳሰበና የረቀቀ ፖለቲካ የሚያወራ ሰው አይፈልግም፡፡ ‹‹ፖለቲከኞች የሚናገሩትና የሚሰሩት የተለያየ ነው፤ አናምናቸውም›› የሚል ከረዥም ጊዜ ጀምሮ ሥር የሰደደ አመለካከት አለ፡፡ ስለዚህ ዶናልድ ትራምፕ አፋቸው ያመጣላቸውን ሁሉ በቀጥታ መናገራቸው እንደ ችግር ሳይሆን እንደ በጎ ነው የታየላቸው፡፡
እሳቸውም ይሄን የህብረተሰብ አስተሳሰብ አጥንተው፤ ይዘውት የመጡት አዲስ አቀራረብ ነው። አንዳንድ ጊዜ ለሰዎች ሞኝ መስለው የሚታዩት ሞኝ ስለሆኑ ሳይሆን መምሰል ስለፈለጉ ነው፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች ነበር ያሸንፋሉ የሚል ግምት የነበረኝ፡፡
የኛን ሀገር ጨምሮ በሌሎች ሀገራት ላይ የትራምፕ መመረጥ ሊያሳድር የሚችለው ተፅዕኖ ምን ያህል ነው?
መሰረታዊ የሚባልና የሀገሩን አጠቃላይ ሥርዓት የሚያፋልስ ነገር ይዘው ይመጣሉ ብዬ አላስብም። ይሄ በአሜሪካ ምርጫ የተለመደ ነው። ባራክ ኦባማ ሲመጡ እንደሳቸው ስለ ለውጥ ያወራ የለም። ስልጣን ላይ ከወጡ በኋላ ግን ያመጡት ለውጥ እዚህ ግባ የሚባል አልሆነም። የዶናልድ ትራምፕም ከዚያ የተለየ ይሆናል ብዬ አላምንም፡፡ ሲስተሙ በጣም ጠንካራ ነው፡፡ የራሳቸውን አስተሳሰብ ብቻ በፈለጉት መንገድ ለመፈፀም የሚፈቅድ አይደለም። ስለዚህ አንዳንድ በፕሬዚዳንት ደረጃ ሊወሰኑ የሚችሉ ለውጦችን ሊያመጡ ይችላሉ፡፡ ከዚያ ባለፈ ግን አይደለም የሌላውን አለም የአሜሪካንን ሁኔታ ሊቀይር የሚችል ለውጥ ያመጣሉ የሚል እምነት የለኝም፡፡ ገና ኋይት ሃውስ ሲገቡ ማብራሪያ ይሰጣቸዋል፡፡ ሀገሩን የሚመራው ሲስተሙ ነው የሚሆነው፡፡
የመሪዎቹ ሚና በምርጫው እንደምናየው፣ ያን ያህል አስፈሪ ነው ብዬ አላምንም። መሰረታዊ ለውጥም ያመጣሉ ብዬ አላስብም፡፡ በውጭ ፖሊሲያቸውም አንዳንድ ለውጥ ሊያመጡ ይችሉ ይሆናል፡፡ ግን በተለይ ከኛ ጋር በተያያዘ ያን ያህል መሰረታዊ ለውጥ ሊያመጡ ይችላሉ የሚል ስጋትም ተስፋም የለኝም፡፡
ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በርካታ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው የተለያዩ አገራት ስደተኞች በአሜሪካ ይኖራሉ፡፡ ትራምፕ በመመረጣቸው ስደተኞች ወደ የአገራቸው የመባረር ዕጣ ፋንታ ይገጥማቸዋል ይላሉ?
ትልቁ ችግራችን እኛ የአሜሪካንን ፖለቲካ የምንመዝነው በስደተኛ አይን ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ግን ለፕሬዚዳንትነት የሚወዳደሩት ለስደተኛ አይደለም፤ ለዜጋው ለሀገሩ ነው፡፡ ምርጫውን ስንገመግምም ራሳችንን በአሜሪካውያን ቦታ አስቀምጠን መሆን አለበት፡፡ አሁን ለምሳሌ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የዲሞክራቶች ደጋፊ ነው። ዲሞክራቶች ለስደተኞች የተሻሉ ናቸው ተብሎ ስለሚታመን ነው፡፡ ግን መሪዎቹ የሚጠበቅባቸው የስደተኛውን ችግር ሳይሆን የአሜሪካውያንን ችግር መፍታት ነው፡፡ መዳኘትም ያለባቸው ከዚያ አንፃር ነው፡፡ ዶናልድ ትራምፕ ለሀገራቸው ህዝብ ቃል ገብተዋል።
በዚህ መሰረት በመጠኑም ቢሆን ህገ ወጥ ስደተኞችን ሊያባርሩ (ዲፖርት) በስደተኞች ላይም ጠንካራ ቁጥጥር ሊደረግ ይችላል፡፡ ዞሮ ዞሮ እርምጃው ለአሜሪካኖች ከጠቀመ ስህተት ነው ሊባል አይችልም፤ እኛንም ቢጎዳ እንኳ፡፡

=================================

“የትራምፕ መመረጥ ለዓለም ስጋት ነው”
ኢ/ር ይልቃል ጌትነት (የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር

የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ፉክክር እንዴት ነበር?
ለኔ በዲሞክራቶችና በሪፐብሊካኖች መካከል ብዙ ልዩነት አይታየኝም፡፡ ነገር ግን በሪፐብሊካኖች በኩል የያዙትን ነገር ጨከን አድርገው የመግፋት ነገር ሲኖር፣ በዲሞክራቶቹ በኩል ደግሞ የማባበልና ጊዜ የመግዛት ነገር አላቸው፡፡ ለኢህአዴግ አይነት መንግስት፣ የዲሞክራቶች ጠባይ የበለጠ ይስማማዋል፡፡ ሁለተኛው የኦባማ ቡድን የነበሩት፣ እነ ዊንዲ ሼርማን ጨምሮ በዙሪያው የተሰበሰቡ ሴቶች፣ የኢህአዴግ ደጋፊዎች እስኪመስሉ ድረስ ወዳጅነት አላቸው፡፡ ስለዚህ ሂላሪ ብትመረጥ ኖሮ፣ በኢትዮጵያ ፖለቲካ የተሰለቹት የኢህአዴግ ወዳጆች ተመልሰው ሊመጡ ይችሉ ነበር፡፡ አሁን ትራምፕ ስለተመረጡ ምናልባት የተለዩ ሰዎች ይመጡ ይሆናል፤ የተለየ እይታም ሊኖር ይችላል፡፡ ምንም እንኳ “ከዝንጀሮ ቆንጆ---” ቢሆንም፡፡  
በአጠቃላይ በምርጫው የሆነውና አጠቃላይ በአለማቀፍ አሰላለፍ አንፃር ስንመዝነው በጣም አደገኛ ስጋት ነው ያለው፡፡ አሁን የምናየው ነገር ፀረ-ፖለቲካ አስተሳሰብ ወደ መድረኩ እየመጣ መሆኑን ነው፡፡ ለምሳሌ የእንግሊዝ ከአውሮፓ ህብረት መውጣት ሲታይ፣ ከፖለተካ ይልቅ ኢኮኖሚ ሁሉንም ነገር እየቀደመ ያለበት ሁኔታ መምጣቱን መገንዘብ ያስችላል፡፡ ግለኝነትና ስስት ዋናው የካፒታሊዝም ባህርይ እየሆነ መምጣቱንና ከአብሮነት ይልቅ ልዩነትን የሚያስፋፉ አመለካከቶች መዳበራቸውን ያመላክታል፡፡
የትራምፕም አስተሳሰብ አግላይ ነው፡፡ ከተመረጠ በኋላ በሀገሪቱ የተደረገው ሰልፍም ለዚህ አግላይነት የተሰጠ ምላሽ ነው፡፡ ሰውየው የምንም ነገር እውቀት የሌለው፣ ዝም ብሎ ታዋቂነቱን ተጠቅሞ ወደፊት የመጣ ሰው ነው። መራጮቹም በእድሜ የገፉ፣ ነጮች፣ እምብዛም ያልተማሩ ሰዎች ናቸው፡፡ አሜሪካ ደግሞ የተለያየ ማህበረሰብ ያለበት ሀገር ነው፤ ነገር ግን እሱ ያንን አግልሎ መራጮቹ ነጮች እንዲሆኑ አድርጓል፡፡ 85 በመቶ መራጮቹ ነጮች ናቸው፡፡ 62 በመቶዎቹ የገጠር ሰዎች ናቸው።
አብዛኞቹ የሰራተኛው መደብ የሚባሉና ያልተማሩ ናቸው፡፡ በእንዲህ ያለ መንገድ የመጣ ሰው ለአለም ስጋት መሆኑ አይቀርም፡፡ ስለ አለም ያው ግንዛቤና እውቀትም አናሳ ነው ብቻ ሳይሆን ዜሮ ነው፡፡ ፖሊሲውንም ስንመለከተው ደጋግሞ፤ “አሜሪካን ዳግም ታላቅ ማድረግ” ይላል፡፡ ዝም ብሎ ስሜትን በማራገብ፣ አግላይ አመለካከት ያላቸውን ሰዎች ቀስቅሶና ዘረኝነትን አራግቦ ነው ወደ ስልጣን የመጣው፡፡ በዚህ መንገድ የመጣ ሰው ለአለም ስጋት ነው፡፡ እኔም የማየው እንደ ስጋት ነው።
ዶናልድ ትራምፕ ያሸንፋሉ ብለው ገምተው ነበር?
አዎ! ጠብቄ ነበር፡፡ ሂደቱ ያሣይ የነበረው ይሄንኑ ነው፡፡ ከ9 ወር በፊት በፌስቡክ ገፄ፣ አንድ ሰው የፀረ-ፖለቲካ አመለካከት እየመጣ ነው ብለው የፃፉትን ሼር አድርጌው ነበር፡፡ በወቅቱ የብሪቴን ከአውሮፓ መውጣት፣ የትራምፕ የፖሊሲ ሰዎችን እየበለጡ መምጣት---- አንዳች ውጤት እንደሚያስመዘግብ ያስታውቅ ነበር፡፡ ስሜትን እያራገበ ብዙ ትኩረት ሲስብ እንደነበር ያየነው ጉዳይ ነው፡፡ ይሄ ሰውዬ ሀብት በማግኘቱና ታዋቂ ሰው በመሆኑ ያራገባቸው ስሜቶች ተቀባይነት አግኝተውለታል፡፡ እነ ሂላሪ በአንፃሩ የተሸነፉት በቅስቀሳ ስልታቸው ነው፡፡ እኔ በግሌ ትራምፕ እንዳይመረጥ እመኝ ነበር፡፡ እንዲህ አይነት አመለካከት ያለው ሠው፣ ወደ ፖለቲካ አለም እንዲመጣ በምንም አይነት አልፈልግም፡፡ ግን ስጋቴና ፍርሃቴ ትክክል ሆነ ማለት ነው፡፡
በአሜሪካ የሚገኙ ህጋዊ ወረቀት የሌላቸው ስደተኞች፣ በጭንቅና በፍርሃት ውስጥ እንደሚገኙ ይነገራል፡፡ ትረምፕ በስደተኞች ላይ እወስዳለሁ ያሉትን እርምጃ ይተገብሩታል?   
ምናልባት ህጋዊ ወረቀት የሌላቸውን ከአገር የማባረርና በስደተኞች ላይም ከቀድሞ የጠነከረ ቁጥጥር ማድረግ ሊጀምሩ ይችላሉ፡፡  
የትራምፕን መመረጥ የሚቃወሙ በተለይ ተማሪዎች Trump is not my president የሚሉ መፈክሮችን በመያዝ በተለያዩ ከተሞች ሰልፍ ሲያደርጉ ነው የሰነበቱት፡፡ ይሄ ምን ያሳያል?
እንግዲህ ይሄ ሰውዬ ገና ሲጀምር እንዲህ ያለው ተግዳሮት እየገጠመው ነው፡፡ ግን የተናገረውን ሁሉ ዝም ብሎ ያደርገዋል ማለት አይደለም፡፡ ወደድንም ጠላንም እርስ በእርሱ በተሳሰረ አለም ላይ ነው የምንኖረው፡፡ ግን እሱ ሜክሲኮአዊያን ስደተኞች እንዳይገቡ አጥር አጥራለሁ፣ ከሽብርተኛ ሀገር ሙስሊም ወደ አሜሪካ እንዳይገባ እቆጣጠራለሁ፣ የኢራን ኒውኩሌር ስምምነትን አጥፋለሁ፣ የኦባማን የጤና ኢንሹራንስ አስወግጄ በሌላ እተካለሁ ----- ብሏል፡፡ እነዚህን ሁሉ ተግባራዊ ማድረግ ግን ይከብደዋል፡፡ ማናናቅና ማጣጣል አንድ ነገር ነው። በተግባር መስራት ደግሞ ሌላ ነው፡፡ በምርጫው ወቅት የነበረው ፉከራ ሁሉ ወደ ተግባር ይለወጣል ማለት አይደለም፡፡ ግን አሜሪካ በዓለም ላይ የነበራትን ገፅታ አበላሽቷል፡፡  
በእኛ አገር ላይስ ምን ተፅዕኖ ይኖረዋል?
እኔ ከበፊቱ የተሻለ ነገር ይመጣል ብዬ ነው የማስበው፡፡ ዲሞክራቶቹ የማባበል ፀባይ ይታይባቸዋል፡፡ ችግሩን እያወቁት ማስታመም ይወዳሉ፡፡ ኦባማን የመሰለ የህግ ምሁር ኢትዮጵያ መጥቶ፤ “በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ መንግስት ነው” ብሏል፡፡ ይሄ የማባበል ፀባይ ነው፡፡ ሪፐብሊካኖች ግን የሀገራቸውን ፍላጎት የሚያስቀድሙ ቢሆንም የማስታመም ፀባይ የላቸውም፡፡ ስለዚህ ለኢትዮጵያ ጥሩ ነው ባይ ነኝ፡፡ የኢህአዴግ ወዳጅ የነበሩት ሴቶችም ከቦታው ገለል ይሉ ይሆናል፡፡ እኔ ይሄን እንደ መልካም አጋጣሚ ነው የማየው፡፡ ይሄን ስል ግን እኔ የዶናልድ ደጋፊ ነኝ ማለት አይደለም፡፡ የእሱ መመረጥ ለአለም ስጋት ነው፡፡

Read 7820 times