Sunday, 13 November 2016 00:00

“ሪፐብሊካኖች በታሪካቸው ለኢትዮጵያ መልካም ናቸው”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(8 votes)

ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ሚኒስትር

  ዶናልድ ትራምፕ እንደሚያሸንፉ ጠብቀው ነበር?
በመጀመሪያ ደረጃ የማቀርበው አስተያየት መንግስትን ወክዬ ሳይሆን በግሌ ነው፡፡ እንደ ማንኛውም ሰው፣ የአስተያየት ድምፅ የሚያሳየውን አሃዝ እከታተል ነበር፡፡ የቅድመ ምርጫ የህዝብ አስተያየት ሂላሪ እንደምታሸንፍ ነበር የሚያሳየው። ከዚህ አንጻር እኔም እንደ ብዙዎቹ ትራምፕ ያሸንፋል ብዬ አልጠበኩም ነበር፡፡ ግን አሸነፈ፡፡ ዲሞክራሲያዊ አካሄድን የተከተለ በመሆኑ፤ ‹‹እንኳን ደስ ያለህ›› ነው የምለው፡፡ በበጎ ነው የምቀበለው። ምክንያቱም ውሳኔው የአሜሪካ ህዝብ ነው እንጂ የሌላ ሀገር አይደለም፡፡ አሜሪካውያን የመረጡት ይጠቅመናል ብለው ስለሆነ ሁላችንም የምንቀበለው መሆን አለበት፡፡
የትራምፕ መመረጥ ምን በመላው ዓለም ላይ ምን አይነት ለውጥ ያመጣል ብለው ይገምታሉ?
አሜሪካ ስታስነጥስ ዓለምን ጉንፋን ይይዘዋል ይባላል፡፡ ይሄ እውነትም አለው፡፡ ከዚህ አንፃር በምርጫ ቅስቀሳ ጊዜ ትራምፕ የሚጠቀሙባቸው ቃላቶች፣ አንዳንድ ሰዎች ላይ ስጋት ፈጥሮባቸው ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን እኔ እንደሚገባኝ፣ በምርጫ ጊዜ ሲናገሩት የነበረው በአብዛኛው ምርጫውን ለማሸነፍ ተብሎ የተደረገ ስለሚመስለኝ የትራምፕ መመረጥ ብዙም ለዓለም ስጋት ነው ብዬ አላምንም፡፡ ምክንያቱም ፕሬዚዳንት ቢሆንም ሀገርን ነው ወክሎ የሚሰራው፡፡ ሀገርን ወክሎ ሲሰራ ደግሞ አንድ ሰው ብቻ አይደለም የሚወስነው የአሜሪካ የሌላው ዓለም ግንኙነት በነበረበት ይቀጥላል ብዬ ነው የማስበው፡፡ ምክንያቱም አሜሪካ ተጎጂ እንድትሆን አይፈልጉም። እንደሚታወቀው በዓለም ላይ ትልቅ የዲፕሎማሲ ኔትወርክ ያላት ሃገር ናት፡፡ ያ በምንም መልኩ ይጎዳል ብዬ አልጠብቅም፡፡ ትራምፕ ያኔ ሲናገሩ የነበረው ለምርጫ ግብአት እንዲሆን እንጂ አሁን ያንን ይተገብራሉ ብዬ አላምንም፡፡
አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ከመፍጠርዎ አንፃር የመንግስት ለውጡ ምን ተፅዕኖ ሊያሳድር ይችላል?
ከኢትዮጵያ ጋር የተሻለ ግንኙነት ይኖራል እንጂ ኢትዮጵያን የሚጎዳ ነገር ይመጣል ብዬ አልጠብቅም። ምክንያቱም ሪፐብሊካኖች በታሪካቸው ለኢትዮጵያ መልካም ናቸው፡፡ ዲሞክራቶችም እንደዚያው ናቸው፡፡ እንደሚታወቀው ባራክ ኦባማ ታሪካዊ ጉብኝት አድርገዋል፡፡ ያ የሃገሪቱን ታሪካዊ ግንኙነት ያሣያል፡፡ እንደሚታወቀው ሁለቱ ሃገራት ስትራቴጂክ ግነኙነት ያላቸው እንደመሆናቸው፤ ኢትዮጵያም ለአሜሪካ፣ አሜሪካም ለኢትዮጵያ በጣም አስፈላጊ ናቸው፡፡ ይሄ ግንኙነት በዚሁ እንደሚቀጥል ነው ተስፋ የማደርገው፡፡

Read 5032 times