Saturday, 10 March 2012 10:57

ማሞ ውድነህ - በደራሲያንና በሃያሲያን ዓይን

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(1 Vote)

በብርቅ ጊዜ የነበሩ ብርቅ ደራሲ ናቸው - ደራሲ መስፍን ወልደማርያም

የስለላ ታሪኮችን ለአገራችን ያደረሰ ሰው ነው - ደራሲ ሲሳይ ንጉሱ

ብዙዎቹ የእሱ ትርጉሞች የቋንቋ መረዳት ችግር አለባቸው - ሃያሲ አስፋው ዳምጤ

የአገራችንን አንጋፋ ደራሲ ስብሃት ገ/እግዚአብሔር ባጣን በሳምንት ጊዜ ውስጥ ሌላውን ታላቅ የሥነጽሑፍ ባለሙያና ተርጓሚ ማሞ ውድነህ በተመሳሳይ ሁኔታ በሞት አጥተናል - በ82 ዓመታቸው ባደረባቸው ህመም ህክምና ሲከታተሉ ቆይተው ህይወታቸው አልፏል፡፡በተለይ የስለላ ታሪኮችን በመተርጐም የሚታወቁት አንጋፋው ፀሐፊ ማሞ ውድነህ ሕይወታቸው አስከአለፈበት ጊዜ ድረስ ከ60 በላይ መፃሕፍትን አዘጋጅተዋል፡፡ “ምጽአተ እስራኤል”፣ “የኦዴሣ ማህበር”፣ “90 ደቂቃ በኢንተቤ”፣ “ድግሪ ያሳበደው”፣ “ካርቱም ሄዶ ቀረ” ከትርጉም ሥራዎቻቸው የሚጠቀሱ ሲሆን “እድርተኞቹ” ፣ “እቁብተኞቹ” እና፣ “ማህበርተኞቹ” የተባሉ ልብወለዶችንም ጽፈዋል፡፡ ማሞ ውድነህ በአብዛኞቹ የሥነጽሑፍ ባለሙያዎች ዘንድ በትጉህነታቸውና በታታሪነታቸው ይታወቃሉ፡፡

ከ40 ዓመታት በላይ የዘለቀ ትውውቅ እንዳላቸው የገለፀው ደራሲና ወግ ፀሐፊው መስፍን ሀብተማርያም፤ ስለደራሲ ማሞ ውድነህ ሲናገር “ጋሽ ማሞ በብርቅ ጊዜ የነበሩ ብርቅ ደራሲ ናቸው፡፡ የጥረት ምሣሌ ናቸው፡፡ ሃሳባቸውን በቀላሉና በግልጽ የማስቀመጥ ብቃት አላቸው፡፡ እድርተኞቹ፣ እቁብተኞቹና ማህበርተኞቹ በተባሉት መጽሐፋቸው ማህበራዊ ችግሮችን ለማሳየት ሞክረዋል፡፡ ትርጉም ቀላል ነገር አይደለም ራሱን የቻለ ት/ቤት ነው፡፡ እናም ከትርጉም ብዙ ተምረዋል፡፡ ለስብሃት ገብረእግዚአብሔር ንባብ ህይወቱ እንደሆነ ሁሉ፣ ለእሣቸው ሥነጽሑፍ ህይወታቸው ነበር፡፡ ለሌሎች ጉዳዮች ጊዜ ያላቸውም አይመስለኝም፡፡” ብሏል፡፡

የማሞ ውድነህ ሥራዎች ለኢትዮጵያ የንባብ ባህል መዳበር ያደረጉት አስተዋጽኦ የማይናቅ እንደሆነም ደራሲ መስፍን ተናግሯል፡፡ በግል ባህርያቸው አገር ወዳድ እንደነበሩና ለህዝብ ጉዳይ ጆሮ እንደሚሰጡ የገለፀው ደራሲው፤ ደከመኝ አመመኝ ሳይሉ የሚሰሩ ትጉህ የስነጽሑፍ ባለሙያ ነበሩ ብሏል፡፡

“ሰመመን” በተሰኘ የበኸር ሥራው ይበልጥ የሚታወቀው ደራሲ ሲሳይ ንጉሱ፤ ማሞ ውድነህን የሃይስኩል ተማሪ ሆኖ እንደሚያውቃቸው ይናገራል፡፡ ማሞ ውድነህ የደራሲያን ማህበር ፕሬዚዳንት፣ እሱ ፀሐፊ በነበረበት ወቅት ትውውቃቸው መጠንከሩን ያስታወሰው ሲሳይ ንጉሱ፤ አስገራሚ የሥራ ዲሲፒሊን ያላቸው ሰው እንደነበሩ ይመሰክራል፡፡   “በጋሽ ማሞ ወጥ ሥራዎች ላይ ብዙ ማለት አልችልም፤ የትርጉም ሥራዎቹ ግን ብዙ ናቸው፡፡ ሥራዎቹ ሊተቹ ይችሉ ይሆናል፡፡ ግን የእሱን ያህል የፃፈ ሰው የለም፡፡ በአብዛኛው ጥልቀት ያላቸው ስራዎች አይደሉም፡፡

“ትርጉሞቹ የስለላ ታሪኮች ናቸው፡፡ የስለላ ታሪኮችን ለአገራችን ያደረሰ ሰው ነው፡፡ ወጣቶች ሆነን በአማርኛ የተተረጐሙትን ሥራዎች ነው ያነበብነው፡፡ ይህ ደግሞ ለንባብ ባህል መዳበር አስተዋጽኦ አለው፡፡ ከጋሽ ማሞ የማደንቀው ነገር ቢኖር የሥራ ጥንካሬውን ነው፤ እስከመጨረሻው ህይወቱ ድረስ ሲጽፍ የኖረ ሰው ነው” ብሏል - ሲሳይ፡፡

በግል ባህርይው ሰዎችን መርዳት ይወዳል ያለው ሲሳይ፤ ወደ አስመራ ለሥራ በሄደበት ጊዜ እዛ ያሉ ሰዎችን በማስተዋወቅ እንደረዱት ያስታውሳል፡፡ አንጋፋው ደራሲና ሃያሲ አስፋው ዳምጤ በበኩላቸው፤ ደራሲ ማሞ ውድነህን በትርጉም ሥራዎቻቸው ቀደም ሲል ያውቋቸው እንደነበር ገልፀው፤ በአካል የተገናኙት ግን በ1971 ዓ.ም በወዳጃቸው አማካኝነት መሆኑንና በዚህ ወቅትም “ድግሪ ያሳበደው” እና “ካርቱም ሄዶ ቀረ” የተባሉ ሥራዎቻቸውን እንደሰጧቸው አስታውሰዋል፡፡ በማሞ ውድነህ የትርጉም ሥራዎች ላይ ያዩአቸውን እንከኖች በማንሳት ነዋሪ ሊሆኑ የሚችሉ ሥራዎችን እንዲሠሩ መምከራቸውንና መወያየታቸውን ያወሱት አስፋው ዳምጤ፤ ያለበለዚያ ግን ሥራዎቻቸው በኢትዮጵያ ሥነጽሑፍ ውስጥ ብዙ ጠቀሜታ ሊኖራቸው እንደማይችል በግልጽ እንደነገሯቸው ይገልፃሉ፡፡ “እቁብተኞቹ”፣ “እድርተኞቹ” እና “ማህበርተኞቹ” የተባሉት የማሞ ውድነህ ሦስት ወጥ ሥራዎችም የዚህ ውይይት ውጤቶች እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡

“አቶ ማሞ በባህርይው ስህተቶችን የመቀበልና ነገሮችን አብስሎ የመሥራት ፍላጐትና ትዕግስት የለውም፡፡ ነገሮችን በቁምነገር የመያዝ ሳይሆን ቶሎ ቶሎ ለገበያ የማድረስ ሥራ ላይ ተጠምዶ ነበር፡፡ ከ1950ዎቹ ጀምሮ በየዓመቱ ቢያንስ አንድ መጽሐፍ ያወጣ ነበር፡፡ ይህም ቢያንስ አንባቢያን ሊያነቡት የሚችሉት ነገር በማቅረብ ለማለማመድ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከቱን ያሳያል፡፡ የሚተረጐሙትን መጽሐፍት ምንጫቸውን አብዛኛው ሰው አያነበውም፡፡ ትርጉሙ ቢዛባ እንኳን አንባቢው ታሪኩ ልክ ነው አይደለም ብሎ ሳይጨቃጨቅ በተሰጠው ብቻ ይረካል፡፡ ብዙዎቹ የተረጐማቸው መጽሐፍት የስለላ ናቸው፤ አንባቢው እየተደሰተ እንዲያነብ አድርጓል፡፡

“በተለይ በ50ዎቹና በ60ዎቹ ብዙ አማራጭ ባልነበረበት ጊዜ እነዚህን ነገሮች ይዞ መቅረቡ ጥሩ ነው፡፡ ግን ትክክለኛ የሆነ የትርጉም ሥራ ሰርቷል አልልም፡፡ ብዙዎቹ ሥራዎቹ ከምንጮቻቸው ጋር ሲገናዘቡ የቋንቋ መረዳት ችግር አለባቸው፡፡ ትጋቱ ግን መደነቅ አለበት” ይላሉ አስፋው ዳምጤ፡፡ የማሞ ውድነህን የፈጠራ ሥራዎችንም የሚተቹት ሃያሲው፤ ሥራዎቹ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ያሉ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡ “መልዕክቱ በትክክል ተላልፏል ወይ ብለን ስንጠይቅ ችግር አለባቸው፡፡ እንደውም ሥራዎቹ የስለላ ታሪኮች በመሆናቸው ነው እንጂ የእነሼክስፒርን፣ ፣ የእነቶልስቶይ አይነት ክላሲክ ሥራዎች ቢሆኑ ኖሮ ችግሩ ጐልቶ ይወጣ ነበር፡፡ ከእኔም ጋር የማንጣጣምባቸው አንዳንድ ነገሮች ከዚሁ ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡” ብለዋል፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን ማሞ ውድነህ ምንም አልሰሩም ማለት እንዳልሆነ አስፋው ዳምጤ ይናገራሉ፡፡ “በአጠቃላይ ግን በቂ ደራሲያን በሌሉበት ወቅት አንባቢው የሚያነባቸው መፃሕፍት በማቅረብ የሰራው ሥራ የሚያስከብረው ነው” ሲሉ አድንቀዋል - ሃያሲው አስፋው ዳምጤ፡፡

=====================================================

ደራሲና ጋዜጠኛ ማሞ ውድነህ

በቀሞው የወሎ ክፍለ ሃገር ዋግ አውራጃ አምደወርቅ ከተማ ውስጥ በ1923 ዓ.ም ተወለዱ፡፡ ወላጅ እናታቸውን በሞት አባታቸውን ደግሞ በአርበኝነት ያጡት ደራሲና ጋዜጠኛ ማሞ ውድነህ፤ የልጅነት ህይወታቸውን ያሣለፉት እጅግ አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ነበር፡፡ በተወለዱ አካባቢ ትምህርት ቤት ባለመኖሩ ምክንያት ደሴ ከተማ ድረስ በመሄድ በወ/ሮ ስህን ት/ቤት የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተማሩ፡፡ ከዚያም በመቀጠል ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ኑሮአቸውን ለማሻሻልና ትምህርታቸውን ለመከታተል ጥረት አድርገዋል፡፡

አንጋፋው ደራሲና ጋዜጠኛ ማሞ ውድነህ፤ በጋዜጠኝነት ህይወታቸው “የፖሊስና እርምጃ” ሣምንታዊ ጋዜጣ ተባባሪ ዋጋ አዘጋጅ እስከመሆን የደረሱ ሲሆን በቀድሞው የኤርትራ ክፍለ አገር የማስታወቂያ ሚኒስቴር ተጠሪ ሆነው አገልግለዋል፡፡

በማስታወቂያ ሚኒስቴር ውስጥ በነበረው የአማርኛ ሥነ ፅሁፍ ክፍል የካቲት መፅሔት ላይ የሰሩ ሲሆን በመፃህፍት ትርጉም ወደ ሥነ ፅሁፍ ሥራ መግባታቸውም ታውቋል፡፡

ከ1985 – 1897 ዓ.ም ድረስ ለ12 ዓመታት የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ፕሬዚዳንት በመሆን ያገለገሉ ሲሆን በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ቀዳሚ ተባባሪ በመሆን ሰርተዋል፡፡ ከእነዚህ መካከልም የአክሱም ሃውልት አስመላሽ ኮሚቴ አባል እና የኢንተርፒስ ቢዩልዲንግ ኢንሼቲቭ መስራች አባል በመሆን ያገለገሉት ተጠቃሽ ነው፡፡ እኚህ አንጋፋ ደራሲና ጋዜጠኛ ከተረጐሞአቸው መፃህፍት መካከል “ምፅአተ እስራኤል”፣ “የኦዴሣ ማህደር”፡ “ዘጠና ደቂቃ በኢንተቤ፣” “ሾተላዩ ሰላይ”፣ “የ6ቱ ቀን ጦርነት”፣ የሚሉት የሚጠቀሱ ሲሆን በአጠቃላይ ወደ 60 የሚጠጉ መፃህፍትን አዘጋጅተዋል፡፡ ደራሲ ማሞ ውድነህ ስድስት ልጆችና 10 የልጅ ልጆችን አፍርተዋል፡፡

 

 

Read 3799 times Last modified on Saturday, 10 March 2012 11:00