Saturday, 10 March 2012 10:55

የእሳቶች ቀጠሮ

Written by  አለማየሁ ንጉሴ
Rate this item
(0 votes)

ዛሬ ከሚስቴ ጋር ፍቅር ለመስራት ቀጠሮ አለን፡፡ ከባህላችን ያፈነገጠ የፈረንጅ ፊልም ይዘናል፡፡ እንደውም የቪዲዮ ማጫወቻው ውስጥ ከተነዋል፡፡ የመኸር ዝናብ እንዳላረሰረሰው ደረቅ መሬት አፏ ኩበት እስኪመስል ድረስ በስሜት ነዷል፡፡ የገዛ ሙቀቴ አትንኖ፣ … ሰማይ አውጥቶ …ከገላዋ ላይ እስኪያዘንበኝ እኔንም አንዘፍዝፎኛል፡፡

… አለንጋ ያልሆኑ ግና የሰአሊ ብሩሽ የመሰሉ ሹል ጣቶቿ ይታዩኛል፡፡ በገጠር …  በፋንታ ጠርሙስ እስከ አፉ ድረስ ዘይት የተሞላ ላምባ አይነት አይኗ ትነቴን አፋጥኗል፡፡ … የኔስ መዘግየት ስለምነው? ጭኖቿን አጋልጣ ከአልጋዋና ከአልጋችን እየጠበቀችኝ እኮ ነው!፡፡ የወረዛ ግንባሯን ማራገቢያ አይሉት … ነገር ማባባሻ በልስልስ መዳፏ ስትሞዥቀው አየኋት እኮ!፡፡

አልጋውም ዝም ብላ ያለሥራ ተወዝታበት ብትከብደው እንዲህ ሲላት ሰማሁ፡፡ “ፍቅርን ይዞ በናፍቆትም ቆሞ መጠባበቅ ይከብዳል … ካልተውረገረጉበት፡፡ … ፍቅርን በአንቀልባ ተሸክሞም … እረብ እረብ ሲሉት ይቀላል …” ፍቺው አልገባኝም፡፡

የአልጋን ቋንቋ በቀላሉ አልረዳም፤ ግን የፈረንጅ አልጋ ቋንቋ ስለሆነ እንጂ … የኛው የጠፍሩ ሆኖ ቢሆን

አለች እረብ እረብ ወገቧ ሊሰበር

ገበያ ሲገዙኝ … ሽቦዬ ደህና ነበር! ሲለኝ በገባኝ፡፡

ጭቅጭቁ ሰለቸኝ፡፡ የልቤ፡፡ መንቻካ አተካሮ ውስጥ ከተተኝ፡፡ … ሂድላት … ሂድላት … ሂድላት … ሂድላት …፡፡ መሄዴ የሷ ብቻ፣ ደሞ መሄዴ የኔ ብቻ ጥቅም ይመስል፡፡ እንሂድ የሚል የደቦ ጩኸት ስሰማ ከተወዘትኩበት ሶፋ ላይ ስሮጥ እሄዳለሁ፡፡

ምን ይሄ ብቻ! በዛው ፍጥነት የመኝታ ቤታችንን በር እ.በ.ረ.ግ.ደ.ዋ.ለ.ሁ፡፡ ትንሽ ፍጥነቴን ቀንሼ ሁለት እግሮቿ መሃል … እገኛለሁ፡፡

ድምጹ መጣ … እነሆ የምስራች ለአለሙ ሁሉ፡፡ በእንቢልታ ያይደለ በእልልታ … በሆታ ያይደለ … እንሂድ! እንሂድ! እንሂድ! አለኝ፡፡

ቅድም ተጋልጧል ያልኩት ጭን አሁን ጭርሱኑስ መች ጨርቅ በላዩ አለ? የት ሄደ? … አቤት! ያኔ ይህች ሚስቴ ከወላጆቿ ቤት እያለች እንዲህ አጭር ቀሚስ፣ እንዲያ ደግሞ ከላይ ትንሽ ጥብቆ ተላብሳ ስትወጣ ከደጃፍ ስንዴ የሚያበጥሩ እናቷ …

“ተይ! ተይ…! እንደምታድጊ ሁኚ! ተይ

አንቺ ልጅ፡፡” ይሏት ነበር፡፡

እኔስ? እኔ ደግሞ ተንደርድሬ ሄጄ የበረገድኩትን የመኝታ ቤት በር ተደግፌ እንዲህ ልበላት …

“በይ! … በይ! እንደምታሰክሪ ሁኚ … በይ አንቺ ሴት … ያለመለኪያ … ሳትሰፈሪ የበዛሽ የወይን ጠጅ ሁኚ!”

እንዲህ እንደ እሳትራት ሄድ መለስ ስል … እንደተወዘትሁ ቆየሁ፡፡ በገዛ ሚስቴ ማን ከልክሎኝ ነው ግን? እኔ አደግድጌ እርሷንም ማስደግደጌ … ደጀ ማጥናቴ፡፡ በመሀልዬ ዘሰሎሞን ውዳሴ፣ በአድናቆት ወ ሔዋን መወድስ ቅዳሴ … ጐንበስ ቀና ሳልል ድርግም የማልልባት?

አሁን ገባኝ … መዘግየቴ፡፡

የውበቷ ንግስት፣ የባለ ሰውነቷ ልእልት ጋር ቶሎ በነፍስ እንዳልደርስ የሆንኩት በሰውየው “የውቤ በረሃ” ንግርት ተመስጬ ነው፡፡ ምክንያቱ ቴሌቭዥኑ መከፈቱ ነው፡፡ ሁለትም በቴሌቪዥኑ ውስጥ የሚደሰኩረው ሰውዬ ነው፡፡ ሶስትም ሰውየው ስብሀት ገ/እግዚአብሔር በመሆኑ ነው፡፡ ነጃሳ ሽማግሌ … ውዴ ሶልያና እንድትበደል አገዘ፡፡

ጋዜጠኛ በርካታ መጽሀፍት አንብበሀል፣ መጀመሪያ ያነበብከውን መፅሀፍ ታስታውሳለህ?

ስብሀት ውቤ በረሀ ውስጥ እኮ ነው? ሁሉንም ሴት፣ ሁሉንም ልጃገረዶች እወዳዳቸዋለሁ፡፡ እዛ ያኔ የነበሩ ሰዎች ህይወት ነበራቸው … ልክ እንደሰው ነበር የምንዋደደው፣ ፍቅር ነበራቸው፣ ደስታ ነበራቸው፣ ሴተኛ አዳሪዎች እንዳይመስሉህ፡፡ ሴቶች፡፡

በቃ ሴቶች ናቸው፡፡

ስብሀት የቆዳ ጉዳይ ነው፡፡ ውስጥህ አያረጅም፡፡ ላይህ እንጂ፡፡ ጭንቅላትህን እንዳለ ነው፡፡ እርጅናም የራሱ የሆነ የሚደንቅ ነገር አለው፡፡ ውበት አለው፡፡ እወደዋለሁ፡፡ ግን ወጣት መሆን ነበር የምመርጠው፡፡

ጋዜጠኛ ጥልቅ ፍቅር ይዞህ ያውቃል?

ስብሃት አዎ!...ወድጃለሁ…ፍቅር ሰርቻለሁ፡፡ ተራብቻለሁ፡፡ ተራውን ለቅቄአለሁ አሁን፡፡

ጋዜጠኛ መጻፍ ስትጀምር በእንግሊዝኛ ነበር፡፡ አሁን በአማርኛ ነው የምትጽፈው፡፡

ስብሀት የዳኛቸው ወርቁን “አደፍርስ” እንዳነበብኩ በአማርኛ ለመጻፍ ማልኩ፡፡ ጻፍኩ፡፡ ራሴንም እሱንም አመሰግናቸዋለሁ፡፡

ጋዜጠኛ ትኩሳት እና ሌቱም አይነጋልኝ እንዴት ተጻፉ?

ስብሀት   ተጻፈ፡፡ ውቤ በረሃ ተጻፈ፡፡ ህይወት እንዳለች እንደነበረች፡፡ እኔ አንባቢዬን የማደርገው ያየሁትን እንዲያይልኝ ነው፡፡ ሲያመኝ እንዲያመው ነው፡፡ ማን ነኝ እኔ ተፈጥሮን የምጨምር የምቀንስ? ልክ ገበሬ ስለ ማረሻ ዕቃዎቹ እንደሚናገር እንደዛው፡፡

ጋዜጠኛ ሞትን ትፈራለህ?

ስብሀት   የሞት ፍርሃት የውሸት ፍርሃት ነው፡፡ እስካልታመምክ እስካልተራብክ ድረስ…ሞት ውሸት ነው፡፡ ከመብላትና ከመጠጣት በኋላ ያለው አስፈላጊው ነገር መራባት ነው፡፡ ትክክለኛውን ፍቅር በትክክለኛው ወቅት ሰርቻለሁ፡፡ ማድረግ የምፈልገውን አድርጊያለሁ፡፡ ቢሆንም ግን በመፈጠሬ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡

ጋዜጠኛ   ራስ ወዳድ ነህ?

ስብሀት አዎን፡፡ ነኝ እንጂ፡፡ እየዋሸሁም ቢሆን መኖር ነው የምፈልገው፡፡ እንደ ክርስቶስ ለእውነት ስል መሰቀል አልፈልግም፡፡ መኖር…እፈልጋለሁ፡፡ ግን ሞት አይቀርልኝም፡፡ ከመጣ ሞትን እኔ ራሴ ዘልዬ እገባበታለሁ፡፡

…እኔ ደሞ “ፍቅርን” ዘልዬ እገባበታለሁ፡፡ ማዕዱ እንደተሰናዳ ታግሶ ይቆየኝ ይሆን? አዎ የስሜቱን ዳና ሰምታለች፡፡ የአፍንጫዬን ስር ትኩሳት ስታነፈንፍ ጠብቃለች፡፡ በሩ ከስንት ፉከራና ያዙኝ ልቀቁኝ በኋላ ተከፈተ፡፡ ማን ፎከረ? እኔ፡፡ …እኔና እሷ እኮ ነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ ላይ ነን፡፡!

 

 

 

Read 2199 times Last modified on Saturday, 10 March 2012 10:59