Saturday, 10 March 2012 10:48

መፈንቅለ ስብሐት”

Written by  ዳዊት ስዩም
Rate this item
(1 Vote)

ሰሞኑን የታዋቂው ደራሲና ፈላስፋ ስብሐት ገ/እግዚአብሔርን ሕልፈተ ሕይወት ተከትሎ (ነፍስ ይማር ብያለሁ) ሚዲያው ሁሉ ስለ ሕይወት ታሪኩ፤ ስለስራዎቹና ስለፈላስፋው እያወራና እየጻፈ ባለበት በአሁኑ ሰሞን የሁኔታዎች መገጣጠም የሰመረለት አንድ ፊልም የመዲናዋ ሲኒማ ቤቶችን የተቆጣጠረ ይመስላል፡፡ “መፈንቅለ ሴቶች” ደራሲውና ሌሎች ታዋቂ ኮሜዲያን የተሳተፉበት ፊልም ሲሆን የፊልሙን ፖስተር የተመለከተ ማንኛውም ሰው፣ ልቡ ፍርስ እስኪል ድረስ ለመሳቅ ራሱን አዘጋጅቶ ወደ ሲኒማ ቤት እንደሚገባ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ምክንያቱስ? የፊልሙ ዘውጉ ኮሜዲ ነዋ! በዚያ ላይ ታዋቂ ኮሜዲያን የተሳተፉበት ነው፡፡ ርዕሱ በራሱ ደግሞ አዲስ ሃሳብና የሳቅ ፍንጭ ያመላክታል ተብሎ ስለሚታሰብ ወዘተ

እኔም ወደ ፊልም ቤቱ ስገባ ራሴን “በደንብ ዘና በል እንግዲህ” እያልኩ ለሳቅና ከተገኘም ለቁም ነገር ተዘጋጅቼ ነበር፡፡ ታዲያ ምን ያደርጋል…. እንደተሸወድኩኝ የገባኝ ፊልሙ ተጀምሮ አስር ደቂቃ እንኳን ሳይሞላ ነበር፡፡ ለምን? ማለት ደግ ነው፡፡ ይሄውላችሁ እንግዲህ “መፈንቅለ ሴቶች” ዋና ሐሳቡ የሚያጠነጥነው ሴቶች በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በጉልበትም ጭምር የበላይነቱን ተቆጣጥረው ይዘው፣ ወንዶች የቤት ውስጥ ሥራ፡- ልጅ ማሳደግ፣ ምግብ ማብሰል ወዘተ … ላይ ብቻ ተወስነው ጭቆናና በደል ስለደረሰባቸው፣ የሚደርስባቸውን ጭቆናና በደል ከላያቸው ላይ ለማውረድ የሚያደርጉትን ትግል የሚያሳይ ነው፡፡ በጣም ጥሩ ነው፤ እንደ ፊልሙ መነሻ ሃሳብ፡፡ በነገራችን ላይ የፊልም ርዕስ መያዝ አይሆንልኝም እንጂ ከዚህ ፊልም ጋር አንድ አይነት ጭብጥ ያለው የውጭ ሃገር ፊልም ማየቴን እርግጠኛ ነኝ፡፡ ለማንኛውም እሱ አያስጨንቀኝም፡፡ ኩረጃና መገልበጥ እንደሆነ ሀገራችን ውስጥ በሁሉም ዘርፍ እንደ ልብ ሆኖ የለ! ከኮረጁ አይቀር ጥሩ አድርጎ መኮረጅ ነው እንጂ ያቃተን ንግባእኬ ኃበ ጥንተ ነገር” እንዳለው ግዕዙ፣ ወደ ቀደመ ጉዳዬ ስገባ “መፈንቅለ ሴቶች” የፊልሙ መነሻ ሃሳብ ጥሩ ሆኖ እያለ፣ መሠረታዊ ተጠይቆችን ግን የሚመልስ አይደለም፡፡ ለምሳሌ እንዴት?  (How) የሚለውን አይመልሰም፡፡ አሁን ያለንበት ዘመን ወንዶች በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና በማህበራዊ ኑሮ የበላይነት የያዙበት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ሴቶች እንዴት አድርገው ነው ይሄን የበላይነት ሙሉ በሙሉ ወስደው ለራሳቸው ጥቅም ያዋሉት? ፊልሙ የሚመልሰው ነገር የለም፡፡ መቼት የት? (When and Where) ለሚለው መልስ የለውም-ፊልሙ፡፡ መቼ ነው ይሄ ነገር የተፈጠረው? ወደ ፊት ነው ወደ ኋላ? ወይስ አሁን ባለንበት ዘመን? ተዋናዮቹ አማርኛ ስለሚናገሩ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው ብለን ልንገምት እንችላለን እንጂ ቦታን የሚገልጽ ምንም ነገር ፊልሙ ላይ አናገኝም፡፡ ሌላው «መፈንቅለ ሴቶች» ላይ ያየሁት ትልቅ ድክመት የታሪክ አወቃቀር፣ ሴራና ልብ ሰቀላ የሚባል ነገር ከነጭራሹ አለመኖሩ ሲሆን ይሄ ደግሞ ፊልሙን የማያልቅ ተረት አስመስሎታል፡፡

ስለ ፊልሙ ጭብጥ ይሄን ያህል ካልን ወደ ትወና እንግባ እኔ እንደሚገባኝ በሁለት አይነት ዘዴ ሳቅ መፍጠር ይቻላል፡፡ በንግግርና በእንቅስቃሴ፡፡ እንደ እኔ «መፈንቅለ ሴቶች» በሁለቱም የተሳካለት አይደለም፡፡ ለምሳሌ ኮሜዲያን ደረጀ ኃይሌ የወንዶችን ችግር የሚፈታ ተመራማሪ ሆኖ በተቀረጸበት ገፅ ባህርይ ምንም አይነት የምሁር ወይም የተመራማሪ ቃልና ድርጊት የማያሳይ ሆኖ ነው ትውናውን የጨረሰው፡፡ “ሽንት ቤት ሄጄ ልመሰጥ” ከሚለው አባባል በስተቀር ሌላ ፈገግ እንኳን የሚያሳይ ንግግርም ድርጊትም አላየሁም፡፡ከሁሉም በላይ ግን ደራሲና ፈላስፋ የስነጽሑፍ ሰው ስብሐት ገ/እግዚአብሔር የተሰጠው ድርሻ /role/ ለመሳቅ የገባሁትን ሰው ከንፈሬን በንዴት እንድነክስና ብዕሬን እንድመዝ አድርጎኛል፡፡ ይኸውላችሁ በመፈንቅለ ሴቶች ላይ ደራሲ ስብሐት የስነ ልቦና ባለሙያ /ሳይካትሪስት/ የሆነ ገፅ ባህርይ የተሰጠው ቢሆንም ከአቀማመጡ ጀምሮ የመንደር ጠንቋይ ወይንም ጫት እየቃመ ያለ ሰው አሊያም የዮጋ አስተማሪ ነበር የሚመስለው፡፡ ዋናው አቀማመጡ አይደለም ትሉኝ ይሆናል፡፡ የሰው ችግር ሊፈታ የተቀመጠ ሳይካትሪስት ቢያንስ ችግሩን ማዳመጥ የመጀመሪያው መፍትሔ ሲሆን በመቀጠል ጥሩ አጽናኝና ተስፋ ሰጪ ነገር መናገር እንዳለበት ለማወቅ የስነ ልቡና ባለሙያ መሆንን አይጠይቅም፡፡ ከሁሉም ደግሙ  “እንጃልህ ውጣልኝ” ከሚሉ ተደጋጋሚ ንግግሮች በስተቀር ምን የሚናገረው አለመኖሩ ቆሽትን የሚያበግን ነው፡፡ ቢያንስ የፊልመን ጽሑፍ ድርሻ እራሱ እንዲፅፍና እንዲናገር ዕድል ቢሰጠው ወይ ከራሱ ፍልስፍና ወይም ካነበበው ታሪክ አንድ ነገር ሊለን ይችል ነበር ብዬ አሰብኩ፡፡ ምን ዋጋ አለው? ደራሲው ዕድሉን ስላልሰጠው ከዛ የመሰለ ንግግር፣ እራሱ ፍልስፍና ከመሰለ ደራሲ “እንጃ ልክ ውጣልኝ” ብቻ የሚል ቃል ሰምቼ ወጣሁ፡፡ ፊልሙን አይቼ ወደ ቤቴ እየሄድኩ ሳለ አርዕስቱ ምን ሃሳብ መጣልኝ መሰላችሁ? ይሄ ፊልም “መፈንቅለ ሴቶች” ሳይሆን መባል የነበረበት “መፈንቅለ ስብሐት” ነበር፡፡ ለምን ቢባል የሰውዬውን ክብርና ዕውቀት ያልመጠነ በመሆኑ፡፡ በመጨረሻ እንደኔ ለመሳቅ አሰፍስፎ ገብቶ አኩርፎ ከመውጣት ያድናችሁ እያልኩ ፅሑፌን አጠቃልላለሁ፡፡

 

 

Read 2966 times Last modified on Saturday, 10 March 2012 10:53