Monday, 10 October 2016 06:43

‹‹ከአያያዝ ይቀደዳል!›› የአበው ብሂል

Written by 
Rate this item
(10 votes)

    ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ታላቅ ንጉሥ ሰፊ ግዛት እያስተዳደረ ይኖር ነበር፡፡ ዕድሜው እየገፋ  ሲሄድ ሶስቱን ልጆች በተራ ወደ አልጋው እየጠራ፣ አንድ ጥያቄ ይጠይቃቸዋል፡፡ በመጀመሪያ  ትልቁንና ጉልበተኛውን ልጁን ጠርቶ፤  ‹‹ልጄ፤ አሁን እኔ ህመምተኛ እየሆንኩ መጥቻለሁ፡፡ ስለዚህም አልጋዬን ለእናንተ መተው አለብኝ፡፡
ለመሆኑ ግዛቴን ለማስተዳደር ትችላለህ? ዝግጁ ነህ?››
ትልቁ ልጅም፤
‹‹መጠርጠሩስ! በደምብ እችላለሁ››
ንጉሡ፤
‹‹በምን ተማምነህ እንዲህ አልክ?››
ትልቁ ልጅ፤
‹‹በራሴ ስለምተማመን፡፡ ደግሞምኮ እንኳን እኔ ጎልማሳው፣ አንተም ሽማግሌው ስታስተዳድር
ነበር!›› ሲል መለሰ፡፡
‹‹እሺ ሂድ፡፡ መካከለኛውን ወንድምህን ጥራው››
መካከለኛው ወንድም ተጠርቶ መጣ፡፡
ንጉሡ፤
‹‹እንኳን ደህና መጣህ፡፡ ልጄ፤ አሁን እኔ እያረጀሁና ህመምተኛ እየሆንኩ መጥቻለሁ፡፡ ስለዚህም አልጋዬን ለናንተ ማውረስ አለብኝ፡፡ ለመሆኑ ግዛቴን ለማስተዳደር ዝግጁ ነህ?›› መካከለኛው ልጅ፤
‹‹እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ግን ካወረስከኝ ወንድሞቼን እያማከርኩ ለማስተዳደር እሞክራለሁ››
ንጉሥ፤
‹‹እሺ ሂድ፡፡ ታናሽ ወንድምህን ጥራው›› አለና ሸኘው፡፡
በመጨረሻ ታናሽየው ተጠርቶ ንጉሡ ፊት ቀረበ፡፡
ንጉሥ፤
‹‹ እንኳን ደህና መጣህ፡፡ ያስጠራሁህ አንድ ችግር ገጥሞኝ ነው፡፡ አየህ ልጄ፤ አሁን እኔ እያረጀሁና
ህመምተኛ እየሆንኩ መጥቻለሁ፡፡ ስለዚህም አልጋዬን ለናንተ ማውረስ አለብኝ፡፡ ለመሆኑ ግዛቴን
ለማስተዳደር ዝግጁ ነህ?›› ሲል ጠየቀው፡፡
ታናሽ ወንድምም፤
‹‹ማስተዳደር የምችል ይመስለኛል››
ንጉሥ፤
‹‹በምን ተማምነህ እንዲህ ልትል ደፈርክ?›› አለው፡፡
ታናሽ ወንድምም፤
‹‹ሦስት ዓይነት አቅም እንዳለኝ እተማመናለሁ፡፡
1ኛ/ የአንተን ምክር አዳምጣለሁ
2ኛ/ ከወንድሞቼ ጋር እመካከራለሁ
3ኛ ከአገሬው ጋር እወያያለሁ፡፡ የአገር ሽማግሌዎችን ጠርቼ ‹‹ምን ይበጃል?›› ብዬ እጠይቃለሁ፡፡
ሲል መለሰለት፡፡
ንጉሡ በጣም ተደሰተና፤
‹‹አገርና ሥልጣን የገባህ አንተ ነህ፡፡ ስለሆነም ግዛተ-መንግሥቴን መውረስ ያለብህ አንተ ነህ፡፡
ወንድሞችህን ጥራቸው›› አለው፡፡
ወንድሞቹን ሄዶ ጠራቸውና ሶስቱም ንጉሡ ፊት ቆሙ፡፡
ንጉሡም፤
‹‹አያችሁ ልጆቼ፤ ከሦስታችሁ ብልህ ሆኖ ያገኘሁት ትንሹን ወንድማችሁን ነው፡፡ የአገር አስተዳዳሪ  ብልህ መሆን አለበት፡፡ ይሄ ወንድማችሁ ብልህ በመሆኑ እኔንም አልተወ፤ እናንተንም አልተወ፤ ህዝቡንም አልተወ፡፡ እኔ ትላንት ነኝ፡፡ እናንተ ዛሬ ናችሁ፡፡ ህዝቡ ነገና ዘለዓለም ነው፡፡ ስለዚህም ሁላችንም በጊዜ ላይ ሠንሠለት ሰርተን አገርን አገር እናደርጋለን፡፡ ትንሹን ወንድማችሁን ውደዱት፡፡ ታዘዙት፡፡ ተግባብታችሁ ኑሩ!›› አላቸው፡፡
*  *  *
አገርን አገር ለማድረግ ሁላችንም መኖር አለብን፡፡ ታሪክን መርሳት የለብንም፡፡ ዛሬ ላይ ቆመንም  ነገን መገንባት እንዳለብን ማሰብ ይገባል፡፡ አገሬውን የያዘ አገርን በአግባቡ ይመራል፡፡ ከአገሬው የመከረ ከአገር መከረ ማለት ነው። ልባዊ መወያየትን መፍራት የለብንም፡፡ ሥነስርዓትን መፍራት የለብንም፡፡ አሮጌው ማለፉን አዲሱ ማሸነፉን (The new is invincible ይሏልና) ጭራሽ መዘንጋት የለብንም፡፡ መወራረስ መኖሩን፣ መለዋወጥ አይቀሬነቱን፣ ቋሚውና ቀሪ ህዝብን አገር መሆኑን ለአንድ አፍታም አለመርሳት እጅግ ይበጃል፡፡ ህዝብ ችግር ላይ ከወደቀ ሆድ እንደሚብሰው አለመዘንጋት ነው፡፡ ፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ፤ ‹‹በጎጃም በገንዘብ ወዳድነታቸው ብዙ ችግር ፈጥረዋል›› ያሏቸውን ራስ ኃይሉን የገለፁበት መንገድ ለእኛም ይጠቅመናል፡- (ከ‹‹ጎሬዛም ማሪያም እስከ አዲስ አበባ›› ከሚለው መጽሐፍ)
‹‹እንደሚወሳው፤ በጢስ የሚባል የግብር ሥነስርዓት ዘርግተዋል፡፡ ስለሆነም ጢስ የሚጤስበት ጎጆ ሁሉ ግብር እንዲጣልበት ተወሰነ፡፡ ገበሬው የተጣለበትን ግብር መክፈል ስላልቻለ፣ ብዙ ቤተሰቦች ቤቶቻቸውን እየለቀቁ፣ እየተዳበሉ፣ አንድ ጎጆ ውስጥ መኖር ጀመሩ፣ በዚህም ድርጊት ጢስ የሚጤስባቸው ጉጆዎች ቁጥር ቀነሰ፡፡ የተዳበሉ ቤተሰቦች፣ አንድ ቤት ቢኖሩም ቅሉ፤ ምግባቸውን የሚያበስሉ በተለያዩ ምድጃዎች ላይ ስለነበር፣ ራስ ኃይሉ ይህን ሲረዱ፣ በጉልቻ ቁጥር ላይ የተመሰረተ አዲስ ግብር ጣሉ፡፡ ባላገር ችግሩን ለማቃለል በወሰደው እርምጃ አንፃር፣ ራስ አዳዲስ ህግና ደንብ እያወጡ፤ አራሹ     ከችግሩ መላቀቅ ተሳነው፡፡
በዚህን ጊዜ አንድ አንጀቷ ያረረ፣ የተማረረች የሚከተለውን ገጠመች፡-
መሶቤን ወሰዱ፣
ድስቴንም ወሰዱ፤
ራስ የቀረዎ ትንሽ አማርኛ፣
ሆዴን በወሰዷት አርፌ እንድተኛ፡፡”
የኢኮኖሚ ችግሮች ሲያመረቅዙ ፖለቲካዊ ባህሪን ይወልዳሉና ሰብሰብ፣ ጠንቀቅ ብሎ ማየትን ይጠይቃል፡፡ (politics is the concentrated form of economics ይሏልና) የህዝብ ኢኮኖሚያዊ ምሬት ምላሽ እንደሚሻ ሁሉ በመድብለ ገፁ ፖለቲካዊ ቁጣ ሲሆንም አስቸኳይ ምላሽ መሻቱን ቢያንስ ዛሬ በይፋ አውቀናል፡፡ በይፋ ሰምተናል። ቁጣው ስርዓተ አልበኛነትን እንዳይወልድ በጊዜ የአስተዋይ መፍትሄ መስጠት ወሳኝ ነው፡፡ ከስሩ ያልተነቀለ ችግር ዳግም ማቆጥቆጡ አሌ አይባልም፡፡ የዛሬውን ተገላገልኩት ብሎ መተኛት መፍትሄ አይሆንም፡፡ ሰላም የራሱ ሂደት አለው፡፡ “ካያያዝ ይቀደዳል” የሚለውን ብሂል አንርሳ፡፡ ቀውጢ ቀውጢንና ጥላቻን እንጂ መረጋጋትን አይወልድምና ረጋ ብሎ “የረጋ ወተት ቅቤ ይወጣዋልን” ማሰብ ነው! ሁሉም
የህብረተሰብ ክፍል የነውጡ - ቀውስ ገፈት ቀማሽ ነው። ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የደረሰው ሀዘን ሀዘንተኛ ነው፡፡ ሁላችንም፣ ለአንዲት ነብስ ማለፍ የምንቆረቆር ሁሉ ሀዘንተኞች ነን!ዛሬ እንደድሮው ዘመን “… ወይ እረሱ፣ ወይ መንኩሱ፣ ወይ ተኩሱ” አይባል ነገር 21ኛው ክፍለ
ዘመን ነው፡፡ (አገር፤ አንድ አራሽ፣ አንድ ቀዳሽ፣ አንድ ተኳሽ ያስፈልጋታል እንዲል መጽሐፍ፡፡)
ይልቁንም ሰላምን ዓላማ ማድረግ ዋና ጉዳያችን ነው፡፡ የምናርሰውና የምንቀድሰው ሰላም ሲኖር ነው፡፡ ሁከት፣ ነውጥ፣ ትርምስ፣ ዓላማ ቢስ ዘረፋ፣ ሲቀጣጠል የብዙ ህይወት፣ የብዙ ንብረት፣ የብዙ ሞራል ጥፋት ሊያስከትል እንደሚችል ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ሁሉም “ከአያያዝ ይቀደዳል” ነው፤ መላ-ጨመቁ!
ከትውልዶች መወራረስና ከትውልድ ቅብብል የምናተርፈው፤ ካለፈው የምንማረው ምንም ይሁን
ምን አንዳች ነገር አይጠፋም፡፡ ፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ፤ “የቅብብሎሽ ሩጫ” በሚለው ግጥማቸው
ታላቅ ምክር ለግሰውናል፡- ከሰማን፡፡
አባቶቻችን እጅ፣ ትንታግ ተቀብለን፤
ርስ - በርስ ሽኩቻ፣ እሳቱን አዳፍነን፤
ጨለማ ውስጥ ነን፤
አትበሉ!
እጁን የዘረጋው፣ ይህ አዲሱ ትውልድ፣
ከከሰለ ችቦ፤ የቱን ብርሃን ሊወስድ፤
አትበሉ፤
መልካሙን ነው ማየት፣
ውቡን ነው መመኘት፣
ብርሃን ይከሰታል፣ ከተዳፈነ እሳት፡፡
ከአገሬው መምከር፣ ወደ ራስ ማየት፣ የሚነገረውን ማዳመጥ፣ ከአገር ሽማግሌዎች መማር፣ ልባዊ ውይይት ማድረግ፣ ጥፋትን በወግ በወጉ መዳኘት፣ ክስተቶች የምን ነፀብራቅ እንደሆኑ መመርመር፣ ብሶትን በአግባቡ መቀየድ፣ የግርግር ተጠቃሚዎችን ለይቶ ማየት፤ ደንብሮ አለማስደንበር፤ ሌላውን ለማይቀደዳል!”

Read 7062 times