Monday, 03 October 2016 00:00

የምትበላውን አጥታ የከሳች፣ እኔ ቀጭኗ ልጅ፣ ብላ ፎከረች!

Written by 
Rate this item
(17 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን የሩሲያ መሪ የነበረው ስታሊን፣አንድ አዳራሽ ውስጥ ጋዜጣዊ መግለጫ ሊሰጥ እየተዘጋጀ ነበር፤ አሉ፡፡
‹‹ጓድ ስታሊን መግለጫውን ለመስጠት ዝግጁ ነዎት?›› አለ ጋዜጠኛው፡፡
‹‹አዎን መቀጠል እንችላለን›› ሲል መለሰ ስታሊን፡፡
‹‹ጓድ ስታሊን፤ ግምገማን በተመለከተ በከተማችን የሚወራ አንድ ነገር አለ፡፡ ይኸውም አንድ የአገራችን ባለሥልጣን ሶስት ሰራተኞችን ሥራ ያዛል፡፡ ሥራውም፤ አንደኛው ሰራተኛ ጉድጓድ ይቆፍራል፡፡ ሁለተኛው የዛፍ ችግኝ ይተክላል፡፡ ሶስተኛው አፈር ይሞላል፡፡ አሁን ሥራ ሲሰሩ የሚታዩት ግን ሁለት ብቻ ናቸው፡፡ ቆፋሪውና አፈር ሞይው፡፡ ‹‹ምንም ሥራ እየሠራችሁ እኮ አይደለም፡፡” ብሎ አንድ መንገደኛ ሀሳብ ሰጣቸው፡፡ ‹‹እኛ ምን እናድርግ፤ ዛፍ ተካዩ ታምሜ ነው ብሎ ቀረ!” አሉና መለሱ፡፡
“ጓድ ስታሊን፤ስለዚህ ሁኔታ ምን ይላሉ?››
ጓድ ስታሊንም፤ ‹‹ሁለቱ ሠራተኞች ትክክል ናቸው፡፡ እነሱ ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል›› አለ፡፡
‹‹ግን’ኮ ምንም ዛፍ አልተተከለም?›› አለ ጋዜጠኛው፡፡
‹‹መጥቶ ዛፍ ያልተከለ ሰው በኋላ ይገመገማታል፡፡ ቆፋሪውና ደፋኙ ግን በሚገባ ሥራቸውን ተወጥተዋል፡፡ እንዲያውም መሾም አለባቸው!›› ብሎ ወሰነ፤ስታሊን፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ ጋዜጣዊ መግለጫው የሚሰማበት አዳራሽ ውስጥ አንድ ሰው አስነጠሰ፡፡ ስታሊን ማስታወሻ ማንበቡን ትቶ፤ ቀና አለና፡- ‹‹አሁን ያስነጠሰው ማን ነው?›› ሲል ጠየቀ፡፡ ማንም መልስ አልሰጠም፡፡ ፀጥ ፀጥ ሆነ፡፡
‹‹ማነው ያስነጠሰው ተናገሩ?››
አሁንም መልስ የለም፡፡
ስታሊን ወደ ግል ጠባቂዎቹ ዞሮ፤
‹‹ከአዳራሹ የመጨረሻ ረድፍ የተቀመጡትን ሰዎች አስወጡና ረሽኑልኝ!›› አለ፡፡
ጠባቂዎቹ የታዘዙትን ፈፀሙ፡፡
ስታሊን፤‹‹አሁንስ አታወጡም?” አለ፡፡
 ሰው ፀጥ አለ፡፡ ስታሊን ወደ ጠባቂዎቹ ዞሮ፤
“ከኋለኛው መስመር አንድ ረድፍ አውጥታችሁ ረሽኑ›› አለና አዘዘ፡፡
 ትዕዛዙ ተፈፀመ፡፡
ለሶስተኛ ጊዜ፤“አሁንስ ያስነጠሰውን ሰው አታወጡም?” ሲል ጠየቀ፡፡
ይሄኔ አንድ ሰው እጁን አውጥቶ፤
“እኔ ነኝ ያስነጠስኩት” አለ፡፡
ስታሊንም፤ “ይማርህ!” አለ፡፡
ያስነጠሰውም ሰው “ያኑርህ!” አለው፡፡
*             *          *
መሪዎች አምባገነን ሲሆኑ ጭካኔያቸውም የዚያኑ ያህል ጣራ ይነካል፡፡ ማን አለብኝ ይላሉ፡፡ ለመሪዎች ፍላጎት ሲባል የብዙ ንጹህ ሰዎች ህይወት ይጠፋል፡፡ በ “ይማርህ” እና በ “ያኑርህ” መካከል ደም ሊፈስ ይችላል። ምንም ህይወት አላግባብ ሲያልፍ ሊቆጨን ሊያንገበግበን ይገባል፡፡ ተጠያቂነትም ሊኖር ግድ ነው፡፡ አያሌ ተድበስብሰው የቀሩና ተጠያቂም ያልተጠየቀባቸው፤ ከንቱ ሆነውም የቀሩ ጥያቄዎችና ነብሶች ነበሩ፡፡ ሳይመለሱ የቀሩ ጥያቄዎች ያመረቅዛሉ፡፡ አድረው ውለው ዳግመኛ ብቅ ይላሉ፡፡ ኦቴሎን እናስታውስ፡-
“ገንዘቤን የሰረቀኝ ሰው፣ ወሰደ እንበል ከንቱ ነገር
የእኔም፣ የእሱም፣ የዚያም ነበር
ግና ስሜን የሰረቀኝ
የማያከብረውን ወስዶ፣ እኔን በግልፅ አደኸየኝ!”
የሚለውን የሼክስፒርን አባባል ማስተዋል ይበጃል፡፡ ከሼክስፒር ስራዎች እጅግ ተደናቂ አባባል ተገኝቷል ከተባለ “መሆን ወይም አለመሆን” የሚለው ቀዳሚ ስፍራ ይይዛል፡፡ ቁጭትን፣ ፀፀትን፣ በቀልንና በተለይ የቁርጠኝነት ውሳኔ ላይ ለመድረስ የሚቀርብን የሞት - የሽረት ጥያቄ የሚያመላክት በመሆኑ፣ዝንተ ዓለም ችግር ባለበት አገር ውስጥ ሁሉ ሲጠቀስ ይኖራል፡፡ (እንደ ታሪኩ አካሄድ መሪው ገፀ ባህሪ ሐምሌት፤ አባቱ በአጎቱ ተገድሎበት፣ የአባቱ አልጋ ተወረሰ፡፡) የዚህ ቁጭት ነው የ“መሆን አለመሆን” መሰረት፡፡ ስለ አብነቱ ይጠቀስ። እነሆ፡-
“መሆን ወይስ አለመሆን፣ እዚሁ ላይ ነው ችግሩ
የዕድል የፈተና አለንጋ፣ ሲወናጨፍ ወስፈንጥሩ
በሀሳብ ግርፊያ መሰቅየቱን፣ ችሎ ታፍኖ ማደሩ
ወይስ የፈተናውን ማዕበል፣ ተጋፍጦ ጦሩን ከጦሩ
ተጋትሮ ወግቶ ድል መምታት፣ እስኪነቀል ከነሥሩ
የቱ ነው የሰው ልጅ ክብሩ ?….”
የአገር ጉዳዮች እልህ መጋባት ድረስ ሲደርሱ፣ የአደጋ ቀይ መብራት መብራቱን መገንዘብ ያባት ነው። ኢትዮጵያ የአገር ሽማግሌ ትፈልጋለች፡፡ ችግራቸውን ራሳቸው የሚፈቱ፣ ቀናውን መንገድ የሚያዩ፣ እሾና አሜኬላውን ለይተው የሚያስወግዱ፤ ልባምና ሆደ ሰፊ ሰዎች ያሿታል፡፡ ከማንም የማይወግኑ፣ የማንም ተፅዕኖ የሌለባቸው፣ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ልጄ ነው የሚሉ፣ ችግሩ ችግሬ ነው የሚሉና አስተዋይ የአገር ሽማግሌዎች አገርን ከአገር ለማቀራረብ፣ “መልካም ምላስ ፍቅርንና ሰላምን ትወልዳለች” በማለት መላ የሚመቱ፤ ሀቀኛ ልጆች ያስፈልጋሉ፡፡ እኒህን ሽማግሌዎች ለማዳመጥ የሚያስፈልገው አንድ ነገር ብቻ ነው - ከቀድሞው አስተሳሰባችን መላቀቅ፤ መፋታት! (Breaking with old ideas) ይህ ደግሞ ከግትርነት፣ ከማን አለብኝነት፣ “እስከ ዛሬ የለፋሁት ምን ይሆናል?” ከማለት፣ ወንበርን እንደ ግል - ንብረት ከማየት አስተሳሰብ መላቀቅን በግድ ይጠይቃል፡፡ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ይህን ሁሉ የማደርገው ለሀገር አንድነት፣ ለሀገር እኩልነት፣ ለሀገር ሰላም ስል ነው፣ ማለትን ይጠይቃል፡፡
ያልተሄደበትን መንገድ (The road less travelled እንዲሉ) መሞከር በጎ ነው፡፡ የተለመደውን መዝሙርና ዘፈን ቢያንስ መቀነስ፣ ቀስ በቀስም መተው የወቅቱ ጥያቄ ነው (order of the day እንዲሉ፡፡) የአገር ሽማግሌዎች በተስኪያን ሳሚ፣ መስጊድ ፀላይ ናቸውና ለሰላም ቅርብ ናቸው፡፡ የራሳቸውን መፍትሄ ለመሻት ቅርብ ዘዴ አጥተው አያውቁም፡፡ ግብረ ገብነት እንጂ የጥናት መመሪያ አይፈልጉም፡፡ ባህልን የመጠበቅ ልማዳዊ አቅም አላቸው፡፡ የሀገራቸው ጣራም፣ ግድግዳም፣ ወለልም ራሳቸው ናቸው፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ እናቱም፣ አባቱም የሀገር ሽማግሌዎች ናቸው (“Civic society” እንደ ማለት ነው) የሀገር ሽማግሌዎች ወገን መቀያየሪያ አይደሉም፡፡
“ጓደኞቼ አሁን በያዝኩት አካሄድ ከቀጠልኩ ውጤቴ ውድቀት ነው አሉኝ፡፡ ስለዚህ አንድ ነገር ማድረግ እንዳለብኝ አሰብኩ፡፡ ከቤቴ ወጥቼ ሄድኩና አዲስ ጓደኛ ቀየርኩ፡፡ ይሄ ጓደኛ ትወድቃለህ አይለኝም፡፡”  
የሚለው የአበው ፖለቲከኞች አነጋገር፣ ከግብዝነት እንድንላቀቅ ትልቅ ትምህርት ይሰጠናል፡፡ መውደቃችን እየታወቀን “አይዞህ አትወድቅም” የሚለን ቲፎዞ ለመፈለግ መሯሯጥ ግብዝነት ነው፤ነው የሚለን ትምህርቱ፡፡ ከዚህ ይሰውረን! ትልቁ ጉዳይ ትራንስፎርሜሽን ሊኖር የሚገባው በየአንዳንዳችን ጭንቅላት ውስጥ መሆኑ ነው። ያ ደግሞ በየቅንነታችን መጠን እንጂ በግምገማ የሚለካ አይደለም - የባህል አብዮት ነውና! በሌለ ነገር መፎከር የቁርጡ ቀን ሲመጣ በአደባባይ እርቃናችንን ያወጣናል፡፡ “የምትበላውን አጥታ የከሳች፣ እኔ ቀጭኗ ልጅ፣ ብላ ፎከረች!” የሚለው ተረት፣የዚህን ውስጠ - ሚስጥር ይነግረናል፡፡ “ያመነ የተጠመቀ የዘላለም ህይወት አለው” ይለናል መጽሐፉ፡፡






Read 8290 times