Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 10 March 2012 09:35

የእናቴ ሙዳይ ነሽ!

Written by 
Rate this item
(10 votes)

ነ.መ

እናቴ እንደአገር ናት

ሁሉን ትሰጣለች እናቴ ስትያት…

የእናቴ ሙዳይ ነሽ

ጅል - ቀን ያልገለጠሽ!

መቃብር ፈልፍሎ፣ ልቤ እናቴን ሲሻ

ቃሏ ያፍነኛል፣ የአደራዋ ግርሻ!

ስጦታዋን ሳልከፍት፣ ያውም የእምዬን እጅ

ይጨንቃል መክረሜ፣ ፍቅርሽን ሳላውጅ፡፡

ዳተኛ ልቤ ውስጥ፣ ያላገኘሽ ቦታ

ልግመኛ አንጀቴ ውስጥ፣ ያላገኘሽ ቦታ

አደራ - በል ሆኜ፣ ያልሰጠሁሽ አፍታ

የእናቴ ሙዳይ ነሽ፣ የፍቅር ስጦታ

የእሳት ዘመን እሳት፣ ሆንኩኝና ሱታ

መክሊቴን ሳልገልጥሽ፣ የእናቴን ውለታ

አንቺን አጣሁ ሳልል

እኔን አጣሽ ሳልል

ወላጄን ሳስባት፣ ቃሏን ሳሰላስል

አደራዋን ጠቅሳ፣ “ምን አረካት?” ስትል

ዛሬም ሰማታለሁ

አዳምጣታለሁ - “እሷን አግባ” ስትል፤

ህመም ይሰማኛል፣ ቂም - ያዘለች ያህል

በተስፋ ተስለሽ

በገሃድ ያልተያዝሽ

ሆድ ውስጥ ተወልደሽ

እሆድ ውስጥ የቀረሽ

ያዩሽ የማይበሉሽ፣ ‘ማትበይ ፍሬ

መሆንሽን እያየሁ፣ አለሁ እስከዛሬ!

የእናቴ አደራ ነሽ፣ የምኞቷ አዝመራ

በቀን ያላፈስኩሽ፣ በእኔ ልግም ሥራ!!

የእምዬን ስጦታ፣ ሳላይሽ ከፍቼ

በእሳት - ቀን ዘመኔ፣ ቃሏን አንቺን ትቼ፤

እንደተበላ ዕቁብ

እንደፈሰሰ ውሃ

እንዳፈረሰ ቄስ

እንደተሳተ ጐል

ማለፉን ሳስበው

“ምን ነካኝ?” እላለሁ፤ ሲጨንቀኝ አደራው

ዓለምም አላፊ

መልክም ረጋፊ

ፎቶግራፍ ቀሪ

ነው ቢባልም እንኳ፤

ሳልቀዝፈው ቀርቼ፣ ያደራዋን ታንኳ

ፍቅር በመስጠሙ… ውስጤን ይጨንቀኛል

“የሰጠሁህ ሙዳይ፣ ከፍተህ ያላየሃት

ምን ሆነች” ስትለኝ፣ ህመም ይሰማኛል

ይከነክነኛል፡፡

እናቴ አንቺን ሰጥታኝ

ስጦታህ ነች ብላኝ

ከአንቺ አለመሆኔ፣ ከእኔ አለመሆንሽ

እያለን አንድ ላይ

ከኪሴ እንደወጣ፣ እንዳጣሁት ንዋይ

አርጌ ቆጥሬሽ፣ አንች የእናቴን ሙዳይ

ህመም ይሰማኛል፣ ጤና መሆኔን ሳይ

ህመም ይሰማኛል፣ ጤና መሆንሽን ሳይ!

አንች የእናቴ ሙዳይ

ያልፈከትኩሽ ሚስጥር

አንች ልጉም - አገልግል፣ የእማማ አዋይ ሲሣይ

ቀን ነው ያራራቀን፣ የዕጣ ፈንታ ጉዳይ

ስንገናኝ ውለን፣ ቀረን ሳንተያይ

የእናቴን ውለታ ሳልከፍለው መቅረቴ

ያንገበግበኛል፤

በአንቺ ተተምኖ፣ እያለ እንደሌለ መሆኑ ያመኛል፡፡

አደራ እንደበላ፣ እንቅልፍ ይነሳኛል

ዛሬም ሆነ ነገ - ያመኛል - ያመኛል

የእናቴ ሙዳይ ነሽ

ጅል ቀን ያልገለጠሽ፡፡

የካቲት 2004 ዓ.ም

(እየተያዩ ላልተገናኙ፡፡ ቀን እያላቸው፣ ቀን ለጠፋባቸው)

 

 

Read 6013 times Last modified on Saturday, 10 March 2012 09:41