Sunday, 04 September 2016 00:00

ምናባዊ ቃለ ምልልስ - ከአውራው ፓርቲ ጋር!! (ቁ-2)

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(34 votes)

“ህዝቡ ድምጹን ለኛ ብቻ ሲሰጥ እኮ፣ ለአገሪቱ ችግሮች ሁሉ
መድሃኒቱ ኢህአዴግ ብቻ ነው ማለቱ ነው”
(በአገሪቱ ወቅታዊ የፖለቲካ ጉዳዮች ዙሪያ ከአውራው ፓርቲ ኢህአዴግ ጋር የተደረገውን ምናባዊ ቃለ-ምልልስ ሁለተኛ ክፍል፣ በጥሞና እንድትከታተሉ ተጋብዛችኋል፡፡ የገዢው ፓርቲ አመራሮች እንኳን ለእኔ ቃለ-ምልልስ የሚሰጡበት ጊዜ ቀርቶ መደበኛ ሥራቸውን የሚያከናውኑበት ጊዜም አጥሯቸዋል፡፡ (አንዳንዶቹ ሥልጣን ራስን ማበልጸጊያ ብቻ ሳይሆን የስጋት ምንጭም ሊሆን እንደሚችል የገባቸው ሰሞኑን ነው!) እናላችሁ በአንድ በኩል በፓርቲ ግምገማ (ያውም የ15 ዓመት)፣በሌላ በኩል የህዝብ ተቃውሞን ፈትሾ በየፈርጁ መተንተን፣(ቢያንስ ለፍረጃ እንዲመች!) ተወጥረዋል አሉ፡፡ (አዳሜ ነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ ላይ ነው!!)
ስለዚህ ከኢህአዴግ ሹመኞች አካባቢ ወቅታዊ መረጃ ማግኘት የሚታሰብ አይደለም፡፡ (እነሱም የሚሰጣቸው ቢያገኙ አይጠሉም!) እናም ባለፈው ሳምንት እንደጠቆምኩት ድንገት ብልጭ ባለልኝ የፈጠራ ሃሳብ መሰረት፣ ዛሬም ከገዢው ፓርቲ ጋር ምናባዊ ቃለ-ምልልሱ ይቀጥላል፡፡  በነገራችን ላይ ጠ/ሚኒስትሩ ሰሞኑን ያን ሁሉ የመንግስት ሚዲያ አሰልፈው መግለጫ ሲሰጡ፣ አንድ እንኳን የግል ሚዲያ አለመጋበዙ ያሳዝናል፡፡ ኢህአዴግ ራሱን ሲያድስ ኢ-ፍትሃዊው የመረጃ ክፍፍል ይሻሻላል ብዬ አምናለሁ፡፡ (በመግለጫው ላይ ባይካተትም!) የመልካም አስተዳደር ችግሮች እስኪፈቱና ሹመኞች ፋታ እስኪያገኙ ድረስ ግን ከመንግስት መ/ቤቶች፣ተቋማት፣ኮርፖሬሽኖች፣ ኤጀንሲዎች---ጋር ምናባዊ ቃለ-ምልልስ ማድረጌን እቀጥላለሁ (አንዳንዴ ከአመራሮቹም የተሻለ መረጃ ልናገኝ እንችላለን!) ወደ ቃለ-ምልልሱ ከመግባቴ በፊት አውራውን ፓርቲ (ኢህአዴግ)  በ“ሰፊው ህዝብ” ስም ላመሰግነው እወዳለሁ፡፡)ፖለቲካ በፈገግታ፡- ኢህአዴግ፤ ለአገሪቱ ችግሮች ሁሉ መፍትሄው እኔ ነኝ” ብሎ ተፈጥሟል የሚል ተደጋጋሚ ትችትና ወቀሳ ይቀርብበታል፡፡ ለምንድን ነው ለችግሮች ሁሉ መፍትሄው እኔ ብቻ ነኝ” የሚል ሌላውን አግላይ አቋም የያዛችሁት?
አውራው ፓርቲ፡- በመጀመሪያ ደረጃ ይሄን አቋም የያዘው ማነው የሚለውን በቅጡ መለየት ይኖርብናል፡፡ ይሄንን አቋም ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ የገለጸው ኢህአዴግ ሳይሆን ራሱ ህዝቡ ነው፡፡
ስለዚህ ከተወቀሰም መወቀስ ያለበት ህዝቡ እንጂ እኛ አይደለንም፡፡ ፖለቲካ በፈገግታ፡-  መቼ ነው ደግሞ ህዝቡ ይሄን አቋም የያዘው?!አውራው ፓርቲ፡- መቶ በመቶ በሆነ ድምጽ እኛን ሲመርጥ ነዋ! ከ70 የሚበልጡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በተሳተፉበት ምርጫ፣ ድምጹን ለኛ ብቻ ሲሰጥ እኮ፣ ለአገሪቱ ችግሮች ሁሉ መድሃኒቱ
ኢህአዴግ ብቻ ነው ማለቱ ነው፡፡ ህዝብ ካለ ደግሞ አለ ነው!! መውቀስ የፈለገ ህዝቡን ተሳስተሃል ብሎ መውቀስ ይችላል፡፡ፖለቲካ በፈገግታ፡- ኢህአዴግ ለችግሮች ሁሉ መፍትሄው እኔ ብቻ ነኝ የሚለው የሥልጣን
ዕድሜውን ለማራዘም ሲል ነው ብለው የሚተቹት ወገኖች አሉ -----
አውራው ፓርቲ፡- ነገርኩህ እኮ ኢህአዴግ አይደለም፤ ለአገሪቱ ችግሮች መፍትሄው እኔ ብቻ ነኝ”
ያለው፡፡ ህዝቡ ነው፡፡ ለአመጽና ለተቃውሞ ሲሆን ብቻ ነው እንዴ ህዝቡ አይሳሳትም የሚባለው፡፡ ስለዚህ ሥልጣን ለማራዘም ምናምን የሚባለው ተራ አሉባልታ ነው፡፡ ኢህአዴግ፤ሥልጣን ሰጪውም ሆነ ነሺው ህዝብ መሆኑን አሳምሮ የሚያውቅ ድርጅት ነው፡፡ ፖለቲካ በፈገግታ፡- የፖለቲካ ተንታኞች፤ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ መዳከምና መጥፋት  ገዢውን ፓርቲ ተጠያቂ ያደርጋሉ፡፡ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያለመኖራቸው አሁን የሚታየውን ህዝባዊ አመጽም መሪ አልባ አድርጎታለ፡፡ ኢህአዴግ በዚህ ጉዳይ ላይ አቋሙ ምንድን ነው?አውራው ፓርቲ፡- ይሄ ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው ውንጀላ ነው፡፡ ኢህአዴግ በተቃዋሚ ፓርቲዎች መዳከምም በለው መጥፋት ላይ ቅንጣት ታህል ሚና የለውም፡፡ እንደውም በአገሪቱ ላይ ጠንካራና
ገዢውን ፓርቲ የማያፈናፍን ብርቱ  ተቃዋሚ ለመፍጠር መከራውን ሲያይ ነው የከረመው፡፡
አልተሳካለትም እንጂ፡፡ አብዛኞቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚፈለገውን መስዋዕትነት ለመክፈል
ፈቃደኛ ባለመሆናቸውና ሥልጣን በአቋራጭ ፈላጊዎች ስለሆኑ ነው የተዳከሙት ወይም የከሰሙት፡፡ ኢህአዴግ በዚህ ተጠያቂ ሊሆን አይችልም፡፡     ፖለቲካ በፈገግታ፡- የፖለቲካ ተንታኞች ግን የአገሪቱ ተቃዋሚዎች የተዳከሙት በገዢው ፓርቲ
በሚደርስባቸው ወከባ፣እስርና ግድያ ነው ይላሉ -----
አውራው ፓርቲ፡-  እውነቱ ግን ----- የተቃዋሚው ጎራ የተዳከመው መስዋዕትነት ለመክፈል ፈቃደኛና ዝግጁ ስላልነበረ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ተቃዋሚዎች አሁን የት ነው ያሉት? አፈናና እስር በዛብን ብለው ወደ ትጥቅ ትግል ገብተዋል፡፡ ህጋዊ እንቅስቃሴን ትተው ህገ-ወጥ ሆነዋል፡፡ ከፊሎቹስ? መስዋዕትነት ከመክፈል ስደትን መርጠው ማክዶናልድ እየገመጡ፣ተቃውሞውን በሳይበር ይመራሉ፡፡ ያለ መስዋዕትነት ደሞ ድል አይገኝም፡፡ የእኛ አገር ተቃዋሚዎች ምቾትና ድሎታቸው ሳይነካ ሥልጣን ላይ መውጣት የሚያልሙ የዋሆች ናቸው፡፡ ይሄ ደግሞ እንኳን በእኛ አገር በዲሞክራሲ ባህል የዳበረ ልምድ ባላት አሜሪካም የሚቻል አይደለም፡፡ የመስዋዕትነቱ መጠን ሊለያይ ይችላል እንጂ መስዋዕትነት መክፈል የግድ ነው፡፡ፖለቲካ በፈገግታ፡- ኢህአዴግ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን እንደ ጠላት ነው የሚያያቸው ይባላል፡፡  እውነት ወይስ ሃሰት?
አውራው ፓርቲ፡- ሃሰት!! ምክንያቱም አንዳንዴ ከጠላትም ይብሳሉ፡፡ ፖለቲካ በፈገግታ፡- ኢህአዴግ አንድ ቀን ከሥልጣን ወርዶ ተቃዋሚ ፓርቲ ሊሆን እንደሚችል አስቦ ያውቃል?
አውራው ፓርቲ፡- በቅርቡ ባይሆንም አንድ ቀን ህዝቡ ተቃዋሚ ፓርቲ የመሆን ዕድል ይሰጠናል
ብለን እናስባለን፡፡ ግን ለቀረው ዓለም በአርአያነት የምንጠቀስ ልማታዊ ተቃዋሚዎች እንደምንሆን
የጸና እምነት አለን። የመላው ዓለም የተቃውሞ እንቅስቃሴም ትርጉም ባለው መልኩ እንደምንለውጠው አንጠራጠርም፡፡ በዚህም የአገሪቱን ስም በበጎ እንደምናስጠራ እናምናለን፡፡    ፖለቲካ በፈገግታ፡- የግሉን ሚዲያ ያቀጨጨው የመንግስት ጣልቃ ገብነት እንደሆነ በስፋት ይነገራል፡፡ ኢህአዴግ እንደ ኢህአዴግ የግል ሚዲያው የቀጨጨው በምን ምክንያት ነው ብሎ ያምናል? አውራው ፓርቲ፡- በመጀመሪያ ደረጃ የአገሪቱ የግል ሚዲያ ቀጭጯል ብለን አናምንም፡፡ የእኛ ግምገማ ከዚህ በተቃራኒው ነው፡፡ በዚህ ዓመት ብቻ ስንት የግል ቴሌቪዥኖች ተከፍተዋል? 10 ገደማ ደርሰዋል። መስከረም ላይ የሚከፈቱ 3 ተጨማሪ የኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች አሉ፡፡ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ 20 የሚደርሱ የግል ቴሌቪዥን ጣቢያዎችን ሊፈቅድ በዝግጅት ላይ ነው፡፡ ጥያቄው መሆን የነበረበት አገሪቱ እነዚህን ሁሉ የግል ሚዲያዎች የመሸከም አቅም አላት
ወይ የሚለው ነው?  ፖለቲካ በፈገግታ፡-  ኢቢሲና ሌሎች የመንግስት ሚዲያዎች፣የገዢው ፓርቲ ልሳን ከመሆን ተላቀው የተለያዩ ተቃራኒ ሃሳቦችና አመለካከቶች ማስተናገድ የሚጀምሩት  መቼ ነው?
አውራው ፓርቲ፡- ኢቢሲም ሆነ ሌሎች የመንግስት ሚዲያዎች እንደ ማንኛውም የአገሪቱ ተቋማት የመልካም አስተዳደር ክፍተቶችና የአቅም ማነስ እንዳለባቸው የሚካድ አይደለም፡፡ ነገር ግን ለምሳሌ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ውሃ የማያነሳ ስድብና ዘለፋቸውንም ቢሆን ለኢቢሲ ከመስጠት ይልቅ የአሸባሪ ድርጅት ልሳን ለሆነው ኢሳት ወይም ከሱ ለማይሻለው ቪኦኤ መስጠት ይቀናቸዋል። አስገድደን በኢቢሲ ስደቡን ማለት አንችልም፡፡ ሌላው ችግራቸው ላለፉት 25 ዓመታት በገዢው ፓርቲ ላይ የሚያወርዱትን ስድብና ዘለፋ እንኳን በአዲስ አለመቀየራቸው ነው፡፡ ያረጀ ያፈጀ ስድብና ዘለፋ በብሄራዊ ቴሌቪዥን ማስተላለፍ ደግሞ ፌር አይደለም፡፡ አዲስ የተሻለ ዘለፋና ውግዘት ከፈጠሩ ከማስተላለፍ ወደ ኋላ አንልም፡፡  በሌላ በኩል ግን በኢህአዴግ 10ኛ ጉባኤ ማጠናቀቂያ ላይ መንግስት አዝማሪ ሚዲያ አይፈልግም በማለት ኢቢሲና መሰል ሚዲያዎችን ገምግመናል፡፡  በቀጣይም ልማታዊና የህዝብ ወገንተኝነት ያለው ሚዲያ ለመፍጠር ተግተን
መስራታችንን እንቀጥላለን፡፡  






Read 6235 times