Monday, 05 March 2012 14:47

ጥበብና እውቀት ነፃ ያወጣቸው ወይዘሮ

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(0 votes)

“በቅሎሽ ተቃጠለብሽ ማለትን ሰማሁ፡፡ አንቺ ግን መቼም አትወጅም፡፡ በቅሎዬ ተቃጠለብኝ ብለሽ ሳትልኪብኝ ቀረሽ፡፡ የአፈ ንጉሥ ነሲቡ በቅሎም ተቃጥሏል የሚሄድበት በቅሎ አጥቶ እየታዘለ ቢመጣልኝ እወድ ነበር፡፡ አሁንም እርጥባን ማለፊያ በቅሎ ሰድጀልሻለሁ፡፡ ለአፈ ንጉሥ ነሲቡ ያዋስሽው እንደሆነ እንኳን በቅሎዋን አገርሽንም እነቅልሻለሁ፡፡ ኮርቻ ግን አለመጨመሬ ኮርቻ አልተቃጠለብሽም ብዬ ነው፡፡”

ይህ ደብዳቤ በጥር ወር 1898 ዓ.ም አፄ ምኒልክ ለወ/ሮ ደስታ ጣድየ የላኩት ነው፡፡ ወይዘሮዋ ለዚህ ደረጃ ከመድረሳቸው በፊት ግን የቤተ-መንግሥት አገልጋይ፣ በዘመኑ  ቋንቋ “አሽከር” ወይም “ባሪያ” ነበሩ፡፡ ከታች ተነስተው እላይ ለመድረስ ባለሙያና ለትምህርት ፍቅር የነበራቸው መሆኑ አግዞአቸዋል፡፡

በያዝነው ወር ለአንባቢያን የቀረበውን መፅሐፍ “ምርኮኛ መነኩሲት” ያዘጋጁት አቶ ገብረመድህን በርጋ ሲሆኑ መጽሐፉ የወ/ሮ ደስታ ጣድየ የሕይወት ጉዞን ያስቃኛል፡፡ ታሪኩ ከሸዋው ንጉሥ ሳህለሥላሴ ጀምሮ እስከ አፄ ምኒልክ ድረስ ጉራጌዎች ከነገሥታቱ ጋር የነበራቸውን የጦርነት፣ የጋብቻና የሥራ ሁኔታ ማዕከል አድርጐ የቀረበ ነው፡፡

በዘመነ መሳፍንት ጉራጌዎች ራሳቸውን በራሳቸው ያስተዳድሩ እንደነበር የሚገልጸው መፅሐፉ የሸዋው ንጉሥ ሳህለሥላሴ ወደ ሰሜን ጉራጌና በአካባቢው ወዳሉ የኦሮሞ ቀበሌዎች የወረራ ዘመቻ ቢያደርጉም ማስገበር አልቻሉም ነበር፡፡ በወረራው አጋጣሚ ለሚማርኳቸው በተለይ ለሴቶች ልዩ ትኩረት ይሰጡ የነበረ ሲሆን ለዚህም ምክንያቱ “ከጉራጌ ሴት የሚወለድ ልጅ ኢትዮጵያን ለረዥም ጊዜ በሰላም ይገዛል” የሚል ንግርት ስለነበር ነው፡፡

ንጉሥ ሳህለሥላሴ ጉራጌዎችን ለማስገበር ባደረጉት የመጀመሪያ ወረራ፣ በአንድ ቄስ ቤት በ”ግርድና/ባርነት” ያገለግሉ የነበሩት ወ/ሮ እጅጋየሁ ተማርከው ስለነበር ወደ ንጉሥ ሳህለሥላሴ ቤት ተወስደው ሲቀመጡ ከንጉሡ ልጅ ከኃይለመለኮት ምኒልክን ወለዱ፡፡ እንዲህም ሆኖ ትንቢቱ ወይም ንግርቱ ማን ላይ ተፈፃሚ እንደሚሆን እርግጡን ማወቅ ያስቸግር ስለነበር ከጉራጌ ሴት ለመውለድ ወታደሩም ቄሱም ይተጋ ነበር፡፡

የመሳፍንት አገዛዝ እንዲያከትም ንጉሥ አፄ ቴዎድሮስ ያደረጉት ጥረት መልክ እየያዘ መጥቶ አፄ ምኒልክ ከነገሱ በኋላም በማዕከላዊ መንግሥት ስር ያልነበሩ አካባቢዎችን ለማስገበር ሲንቀሳቀሱ፣ ከጉራጌዎች ጋር ለ15 ዓመታት ያህል መዋጋታቸውንና “ምኒልክ በጉራጌዎች ላይ ለምን ጨከኑ?” ያስባላቸውን ብዙ የኃይል እርምጃ እንደወሰዱ ጠቅሶ ምክንያቶቹን አስቀምጧል - መፅሐፉ፡፡

የእናታቸው ወገኖች አልተባበር ስላሏቸው በዚህ ተናደው ነው የሚለው ሰበብ ቀዳሚው ነው ሌላኛው አለቃ አፅሜ “በጉራጌ ጦርነት ያልተለቀሰበት የአማራ ቤት አልነበረም” እንዳሉት ዘመቻው ንጉሡን ብዙ ጀግኖች ስላሳጣቸው ሲሆን ሦስተኛው ምክንያት የጉራጌዎች ለንጉሡ አለመገበር፣ የተቀረው የደቡብ ሕዝብም እንዲያምፅ በር ስለሚከፍት ያንን ለማስቆም ነበር የሚሉ እንዳሉት ሁሉ በተቃራኒው ጥቃቱ ከንጉሡ የመነጨ ሳይሆን የምርኮ ቁጥራቸው እንዲበዛላቸው ከተመኙ ወታደሮች ፍላጐት የመነጨ ነበር በመፅሐፉ እንደሰፈረው፡፡

“ከጉራጌ ሴት የሚወለድ ልጅ ኢትዮጵያን ለረዥም ጊዜ በሰላም ይገዛል” የሚል የሸዋ ንግርት ስለበር ብቻ ሳይሆን የጉራጌዎች ጉዳይ በተለያየ ምክንያት የገዢ መደብ አባላቱን ይስብ እንደነበር ይገልፃል፡፡ አፄ ምኒልክ ከመንገሳቸው በፊት ለአፄ ዮሐንስ በሚገብሩበት ዘመን ከገንዘብና ቁሳቁስ ጋር “ባሪያም” ይልኩ ነበር፡፡ የሚላኩላቸው አገልጋዮች ብዙዎቹ ከጉራጌ የተማረኩ መሆኑን ያስተዋሉት አፄ ዮሐንስ “የጨቦና ጉራጌ ምርኮኛ የያዝህ በቶሎ ወደ እኔ አስገባ” ብለው አዋጅ በማስነገራቸው ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ጉራጌዎች ለቤተ መንግሥት ቅርብ ሆኑ፡፡

አፄ ዮሐንስ ምርኮኞቹን ነፃ ለማውጣት ያነሳሳቸውን ምክንያቶች መፅሐፉ ይዘረዝራል፡፡ በ13ኛው ክፍለ ዘመን አፄ አምደፅዮን ወደ ደቡብ ሲዘምቱ፣ ያልተመለሱትና በአካባቢው የቀሩት ሕዝቦች ምንጫቸው ሰሜን ነው የሚለው ቀዳሚው ሲሆን ሁለተኛው ምክንያት በዮዲት ጉዲት ዘመን፣ ታቦተ ፅዮን ከአደጋ ለመከላከል ወደ ደቡብ የሄዱት የሰሜን ሰዎች የአካባቢው ነዋሪ ሆነዋል የሚል ነበር፡፡

አፄ ምኒልክ ጉራጌን ለማስገበር ባደረጉት ዘመቻ ከአካባቢው የተማረኩ ሰዎች ወደ ቤተ-መንግሥት እየተወሰዱ በተለያየ ሙያ ማገልገል እንደጀመሩ የሚጠቁመው “ምርኮኛዋ መነኩሲት” ወ/ሮ ደስታ ጣድየም በአፄ ምኒልክ ቤተ-መንግሥት ከነበሩት ሰዎች አንዷ የሆኑት የአፄ ዮሐንስን አዋጅ መሰረት በማድረግ እንደነበር ያወሳል፡፡

“ወ/ሮ ደስታ በምኒልክ ቤተ-መንግሥት እጅግ ተወዳጅና ታዋቂ ሴት ሆኑ” የሚለው መፅሐፉ፤ ወይዘሮዋ ባለሙያ ስለነበሩ የቤተ መንግሥቱ “ሥራ ቤት (ማዕድ ቤት)” ኃላፊው ሆነው እንደተሾሙ ይጠቁማል፡፡ የ1888 ዓ.ም ለአድዋ ጦርነት ዝግጅት ለንጉሡ መጠለያ የሚሆን ድንኳን እንዲዘጋጅ ሲወሰን ኃላፊነቱን ወስደው ጥጥ ፈታይ ሴቶችን አሰባስበው ድንኳኑ ተሰርቶ ተጠናቀቀ፡፡ በ”ፈታይ ቤት” ኃላፊዋ በወ/ሮ ደስታ ሥም የተሰየመው ድንኳን አፄ ምኒልክ ለአድዋ ጦርነት፣ አፄ ኃይለሥላሴ ለማይጨው ጦርነት እንደተጠቀሙበት በኋላም ንጉሡ ወደ ለንደን ሲሄዱ እንደያዙት፤ ጣሊያን ከተባረረ በኋላም ወደ አገር ውስጥ ይዘውት እንደመጡ መፅሐፉ ዝርዝር ታሪኩን ያስነብባል፡፡

በአድዋ ጦርነት በአፄ ምኒልክና በእቴጌ ጣይቱ ድንኳን አገልጋይ የነበሩት ወ/ሮ ደስታ ጣድየ፤ በቦታው ተገኝተው የተመለከቱትን የጦርነትና የድል ታሪክ ምስክርነት የሚያስነብበው መፅሐፍ፤ ከአድዋ ጦርነት በኋላ ወ/ሮ ደስታ እንዴት ለትልቅ ደረጃ እንደደረሱ ያስቃኛል፡፡

“ወ/ሮ ደስታ በነበረቻቸው ትርፍ ጊዜ በራሳቸው ጥረት የቄስ ትምህርት ተምረው ዳዊት ደገሙ፡፡ ይህንን እንዳጠናቀቁ ለግርማዊት እቴጌ ጣይቱ የምሥራች አሉ፡፡ እቴጌም ከመደሰታቸው የተነሳ ሳምዋቸው፡፡ ለግርማዊ ጃንሆይ አቀርብሻለሁና ተሰናጂ አሉዋቸው፡፡

የተባለውም አልቀረም፡፡ በእቴጌይቱ አቅራቢነት ከጃንሆይ እጅ ነሱ፡፡ እንኳን ደስ ያለሽ ብለውም እንደ ጥያቄያቸው የአባቴ እርስት ነው ያሉትን ዋቢ ወንዝ አካባቢ የሚገኝ መሬት እንዲሰጣቸው ተደረገ፡፡ አፄ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ ተመካክረውም ወ/ሮ ደስታና አፈንጉሥ ነሲቡ እንዲጋቡ ተወጥኖ ጋብቻቸው በቤተመንግሥት በተከናወነ ታላቅ ሥነ ሥርዓት ተፈፀመ፡፡ በእለቱ አፄ ምኒልክ ለወ/ሮ ደስታ በቅሎ ሸለሟቸው፡፡ የአፈንጉሥ ነሲቡ የከብቶች ጋጣ ሲቃጠል እንስሶቹም አብረው መቃጠላቸውን ሰምተው ነበር፡፡ አፄ ምኒልክ በመግቢያዬ ላይ የቀረበውን የማፅናኛ ደብዳቤ ለወ/ሮ ደስታ የላኩት፡፡ከአፈንጉሥ ነሲቡ በፊትም ትዳር መሥርተው የነበሩት ወ/ሮ ደስታ ጣደየ፤ ልጅ ስላልወለዱ የእህታቸውን ልጆች አሳድገው እየዳሩ ከተለያዩ መኳንንትና መሳፍንት ቤተሰብ ጋር ያላቸውን ዝምድና አጠናከሩ፡፡ ከዚያ በኋላ ምርኮኛዋ ደስታ ባላባትና ባለእርስት ሆነው ከገዢ መደብ አባላት አንዱ ሆኑ፡፡ ወይዘሮዋ የመጨረሻ እድሜያቸውን ኢየሩሳሌም በመሄድ በምንኩስና ኖሩ፡፡በአገራችን ኢትዮጵያ የሰው ልጆች “ባሪያ” ተብለው እንዳይሸጡ ቀዳሚውን ትልቅ ተግባር ያከናወኑት አፄ ቴዎድሮስ ናቸው የሚሉት የመፅሐፉ ደራሲ አቶ ገብረመድህን በርጋ፤ ከኋላ ቀርነት ጋር በተያያዘ ብዙዎችን የጐዳውን አጉል ልማድ ለማስቆም አፄ ዮሐንስና አፄ ምኒልክ ያከናወኑትንም ተግባር በመፅሐፋቸው ለማሳየት ሞክረዋል፡፡

የወ/ሮ ደስታ ጣድየን የሥራ ሰው መሆን፣ ታማኝነት፣ ጥበብ አዋቂና ትምህርት ፈላጊነት አይተው ለታላቅ ደረጃ ያበቋቸው አፄ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ፤ ጐጂውን ኋላ ቀር ሥርዓትና አስተሳሰብ ለማስወገድ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማድረጋቸውንም መፅሐፉ ያመለክታል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ተፅፈው እየቀረቡ እንዳሉት መፃህፍት ሁሉ “ምርኮኛዋ መነኩሲት”ም ለአንባቢያንና ለታሪክ ተመራማሪዎች ጠቃሚ ሰነድ ነው፡፡

 

 

 

Read 2939 times Last modified on Monday, 05 March 2012 14:50