Sunday, 04 September 2016 00:00

አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ!

Written by 
Rate this item
(29 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ቀበሮ ጉሮሮው ውስጥ አጥን ተቀርቅሮበት በጣም ሲሰቃይ ዋለ፡፡ ወደማታ ላይ አንዲት ረዝም ኩምቢ ያላት ወፍ አገኘና እንዲህ አላት፡-
“ወፊት ሆይ”
“አቤት” አለች ባለ ኩምቢዋ ወፍ፡፡
“አንድ ነገር ልለምንሽ?”
“የምችለው ከሆነ ምን ቸገረኝ”
“የምትችይው ነገር ነው፡፡ በዚያ ላይ ለውለታሽ ዋጋሽን እከፍላለሁ”
“ምን ትከፍለኛለህ?”
“የፈለግሺውን፡፡ ብቻ ከአቅሜ በላይ አይሁን”
“እሺ፡፡ እንግዲያው እኔን የሚያሳድዱኝ ጠላቶች አሉኝ፡፡ እነሱን አሳደህ ታጠቃልኛለህ?”
“ይሄማ በጣም ቀላል ነው፡፡ ብቻ አንቺ የምጠይቅሽን ፈፅሚልኝ”
“ምንድን ነው እንዳረግልህ የፈለግኸው?” ብላ ጠየቀችው፡፡
“ጉሮሮዬ ውስጥ አጥንት ተቀርቅሮ እያሰቃየኝ ነው፡፡ ስለዚህ ኩምቢሽን አፌ ውስጥ አስገብተሸ እንደ ምንም ብለሽ አውጪልኝ” አላት፡፡
“ይሄ ለእኔ ቀላል ነው፡፡ ፊትህን ወደ ብርሃን መልስና አፍህን በደምብ ክፈተው” አለችው፡፡
ወፊቱ ኩምቢዋን እጉሮሮው ድረስ አስገብታ አጥንቱን ጎትታ አወጣችለት፡፡ እፎይ አለ ቀበሮው፡፡
ከዚያም ወፊቱ፤ “በል እንደተዋዋልነውና ቃል እንደገባህልኝ ወደ ጠላቶቼ ልውሰድህና ተበቀልልኝ” አለችው፡፡ ቀበሮም ቃሉን አጠፈና፤
“ቀበሮ አፍ ውስጥ ገብቼ በሰላም ወጥቻለሁ፤ ብለሽ በኩራት መናገርሽ ይበቃሻል፡፡ ከፊቴ ጥፊ!” አለና አባረራት፡፡ ወፊቱም አቅራቢያዋ ወዳለው ዛፍ ላይ ወጣችና፤
“ሌላ አጥንት ጉሮሮህ ላይ የማይቀረቀር እንዳይመስልህ፡፡ ያኔ ምን እንደሚውጥህ እናያለን” አለችው፡፡ ከአካባቢው በርራ ጠፋች፡፡
*             *          *
በአንድ አገር ሶሺዮ-ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሂደት ውስጥ አንዱ ትልቅ ቁምነገር ለህዝብ ቃል መግባት ነው፡፡ ይህን ቁምነገር የሚያረክሰው ደግሞ የገቡትን ቃል ማጠፍ ነው፡፡ የገቡትን ቃል ማጠፍ ዕምነትን ያጠፋል፡፡ ዕምነተ-ጎዶሎ አመራር ደግሞ በጄ ብሎ መንግሥትን አምኖ የሚገዛ ህዝብ እንዳይኖር ያደርጋል፡፡ ሰላምን ያደፈርሳል፡፡ ጥርጣሬንና እየተገላመጡ መኖርን ያገዝፋል፡፡ መረጋጋት እንዳይኖር ያደርጋል፡፡ ከሀገር መሰደድን ያበዛል፡፡ ማንም ማንንም የማያምንበት፣ ነፃነቱን የሚጠራጠርበት፣ እኩልነቱን የማይቀበልበት፣ የሕግን የበላይነት በወጉ የማይረዳበት፣ ለምንም ነገር ብቃት እንዳለው የማይተማመንበት፣ አልፎ ተርፎም ኢትዮጵያዊነቱን ለጥያቄ የሚዳርግበት ሁኔታ ውስጥ እንዲገባ ሊገደድ የሚችልበት ደረጃ ሊደርስ ይችላል። ስለዚህም ልንፈፅም የምንችለውን ቃል ብቻ በአደባባይ መናገር ብልህነት ነው፡፡ መንገዶች ሁሉ ሁሌ አልጋ ባልጋ ላይሆኑ እንደሚችሉ እንገንዘብ፡፡ መንገዶች ሁሉ ሁሌ ወደ ሮማ አይወስዱም፡፡ ሁሌም “የአፈፃፀም ችግር ነው” እያልን እንደማንዘልቅ እናስብ፡፡ ይልቁንም እቅዳችንን እንፈትሽ፡፡ ራሳችንን ወደ ውስጥ እንይ። እርስ በርሳችን ምን ያህል እንተማመናለን፤ ብለን እንጠይቅ፡፡ ስንወሻሽ እንጠያየቅ፡፡ በችግር ላይ ችግር ለምን ይደራረብብናል? ብለን እንጠይቅ፡፡ ቀውስ በተፈጠረ ቁጥር ወደ ኃይል መሄድ ከትርፉ ኪሳራው የሚያመዝን ሁነት መሆኑን እንይ፡፡ ከቶውንም ኃይል ከቀውስ ወደቀ ውስ ሊከተን እንደሚችል ልብ እንበልና ልብ እንግዛ፡፡ “መካር የሌለው ንጉሥ፣ ያለ አንድ ቀን አይነግሥ” የሚለውን ተረት እናስታውስ። “እንደ ንጉሡ አጎንብሱ” የሚለው ተረትም ሁልጊዜ አያበላም፡፡ ጊዜው ያለፈበት ነውና፡፡ ይልቁንም ሐምሌት የሚለንን ከአንጀታችን እናዳምጥ፡-
“በንጉሥ ፍርፋሪ የፋፋን ትል
አሣ አገኘችና፤ ቅርጥፍ
አሣ-አጥማጅ፣ እሷን ቅርጥፍ!
ሆድን ሞልቶ እንደስልቻ
በልቶ ለመበላት ብቻ!!”
ከሀገራችን የችግር ቁንጮዎች አንዱ አድር - ባይነት ነው፡፡ የጥንቱ የጧቱ ወዳጃችን ሌኒን፤ ‹‹The Pendulum of Opportunism never stops Oscillating›› ይላል፡፡ የአድር-ባይነት ፔንዱለም ዥዋዥዌውን አይተውም፤ እንደ ማለት ነው፡፡ አድር-ባይነት፣ ብቃት የጎደላቸው ሰዎች የኑሮ ዘዴ ነው። አጉል መካሪ ሀገር ያጠፋል፡፡ አድር - ባዮች አጉል መካሪ ናቸው፡፡ የራሳቸውን ጥቅም ለማካበት ሲሉ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለምና፡፡ ልታይ ልታይ ያበዛሉ፡፡ አደባባይ ይደፍራሉ፡፡ በአደባባይ ቃል መግባት አይፈሩም፡፡ ልሳናቸው ስል ነው፡ በሀገር ተቆቋሪነት ስም የማይዘላብዱት ነገር የለም! እንደ እስስት መልካቸውን ይለዋውጣሉ፡፡ በሠርግ ላይ ዘፈን አውጪ፣ በልቅሶ ቤት ሙሾ አውራጅ ናቸው! ሁሉንም የሚያደርጉት ለግል ጥቅማቸው ነው፡፡ ስለሆነም የሙስና ፈታውራሪ ናቸው፡፡ ሆኖም ደግሞ ሙሰኞችን ሲኮንኑ ይሰማሉ፡፡ የግምገማ መሪ ተዋንያን ናቸው፡፡ አልባሳት የመቀያየር ክህሎት አላቸው፡፡ ከነዚህ ያልተጠነቀቀ አመራር ወይም መሪ ለአደጋ የተጋለጠ ነው፡፡ ተንሸራታችና አንሸራታች ናቸውና፡፡ አፋቸው እንጂ ግብራቸው እኩይ ነውና!
‹‹አጓጉል ምላስ ብቻ ናት
ማሞካሸት የማይደክማት፤
ቀን አዝላ ማታ እምታወርድ
ንፉግን ልመና እምትሰድ!››
ይለናል ጋጣሚ ፀጋዬ ገብረመድህን፡፡ ይህን ልብ ማለት ይበጃል፡፡ ሌላው የሀገራችን ቁንጮ ችግር፤ ብሶትና ምሬትን ቸል ማለት ነው፡፡ ውስጥ ውስጡን የሚቀጣጠል እሳት አንድ ቀን የማይጠፋ ቋያ ይሆናል፡፡
‹‹ከጥንት ጀምሮ እኛ እንደምናውቀው
ሲነድ ሲቃጠል የሚስቅ እሳት ነው
ነገሩ አልሆን ብሎ ሁኔታው ሲጠጥር
ጠጣሩ እንዲላላ፣ የላላውን  ወጥር!››
ዛሬም ያው በረከተ-መርገም ነው! የህዝብን ብሶት እናዳምጥ፡፡ ችግርን ፊት ለፊት መጋፈጥና ተነጋግሮ፣ ተመካክሮ መፍታት እንጂ መሸፋፈኑ፤ ‹‹አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ›› የሚለውን የአበው ብሂል መዘንጋት ነው፡፡ ‹‹እንደ ድመት አሥራ ሶስት ነብስ ነው ያለን!›› ማለት አያዋጣም፡፡
‹‹እኛ አድገናል ሌሎች ችግር ገጥሟቸዋል›› ማለትም ብዙ አያራምድም፡፡ ያለው›› ‹‹አለባብሰው ቢያርሱ..›› ነው፡፡ ህዝብ እየተቃወም ነው ሲባል፤ ‹‹በእነ እገሌ ምክንያት ነው› ማለትም ያው ‹‹አለባብሰው ቢያርሱ…›› ነው፡፡ የተቃውሞዎች ሁሉ ማጠንጠኛ ‹‹የመልካም አስተዳደር ችግር ነው›› ማለትም ያነው ‹‹አለባብሰው ቢያርሱ…›› ነው፡፡ የአባዬን እከክ ወደ እምዬ ልክክ (Blame-shifting) ያው ‹‹አለባብሰው ቢያርሱ…›› ነው፡፡ የሕግ የበላይነት በአፍ ቀላል ቢሆንም፣ በተግባር ግን እየተፈፀመ አለመሆኑን አለማመንም ‹‹አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ›› ነው፡፡ ከሁሉም ይሰውረን! አዲሱ ዓመት አዲስ አድማስ ያሳየን! ልብና ልቦና ይስጠን!!

Read 8062 times