Print this page
Monday, 05 March 2012 14:37

የታፈኑ የቢሮ ድምፆች

Written by  ቢኒያም ሐብታሙ
Rate this item
(0 votes)

እንዴት ናችሁ? ኑሮስ? ስራ ምናምን? እንደ ጐበዝ ተማሪ ጥያቄ አበዛው አይደል! አበው መጠየቅ የማወቅ በር ነው ሲሉ ሰምቼ ጉድ ሆኜላችኋለሁ፡፡ “እንዴት?” አትሉኝም፤ በቃ ከድሮ ጀምሮ ተማሪ እያለሁ መጠየቅ እወዳለሁ፤ የማልጠይቀው ነገር የለም፣ አደግ ስል እንደውም መጠየቅን ሁላ መጠየቅ ጀመርኩ (ፍልስፍና ጀመርኩ ማለቴ ነው፡፡)በተለምዶ “መጠየቅ ሀጢያት አይደለም” ሲባልም ስለሰማሁ ይሆናል አንዳንዴ ከልክ ያለፉ ጥያቄዎችን ሁላ እጠይቃለሁ፤ መልስ ባገኝም ባላገኝም፤ በቃ…መጠየቅ በራሱ ለኔ አንዳንዴ መልስ ነው፤ /እንዴት ብላችሁ ደግሞ እንዳትጠይቁኝ/ ባይሆን የሆነች ቀልድ ትዝ አለችኝ፡፡

ልጁ የኔ ቢጤ ነው፣ ማለቴ…መጠየቅ ይወዳል፤ እንጂ ተመጽዋች ነው ለማለት ፈልጌ አይደለም፤ ለነገሩ የኔ ቢጤ/ተመጽዋች/ እራሱ መጠየቅ አይደለም ስራው፡፡ አይ ጭንቅላት! ከየት ከየት አገናኘኋት ባካችሁ? አሁን ይሄ ጭንቅላት ፓርላማ አያስገባም? ለማንኛውም ወደ ቀልዱ ልመለስ፡፡ እናላችሁ ይሄ መጠየቅ የሚወድ ልጅ ከት/ቤት ሲመለስ ሁልጊዜ አባቱን ቤት ውስጥ በጥያቄ ያጣድፈዋል፡፡ አባትም ለአብዛኛው ጥያቄ መልሳቸው “ልጄ ይሄን አላውቀውም” የሚል ነው፡፡ ታዲያ ልጁ መች መጠየቅ ያቆማል፡፡ አሁንም ሌላ ጥያቄ…ይሄን ጊዜ የልጁ እናት “ኧረ ተው አንተ ልጅ! አባትህን ዝም ብለህ በጥያቄ አታድርቀው” ይሉታል፣ አባትም መልሰው “ተይው እንጂ ይጠይቅ፤ ካልጠየቀ እንዴት ያውቃል!” በማለት መለሱ እላችኋለሁ፡፡ እውነታቸውን እኮ ነው፤ አንዳንድ ጊዜ መጠየቅ እራሱ ለመልስ እሩብ ጉዳይ ነው፤ ወይንም በራሱ መለስ ነው፡፡ “መጠየቅ መጠየቅ አሁንም መጠየቅ” አይደለም ያለው ሌኒን/መቼም ሌኒን ያላለው ነገር የለም ብዬ ነው/

 

እስቲ አሁን ደግሞ ወደ ራሴ ጨዋታ ልመልሳችሁና አንድ የተማሪነት ገጠመኜን ላውጋችሁ፡፡ የኤለመንተሪ ተማሪ እያለሁ ጓደኞቼ ሲያሾፉብኝ፣ እገሌ እኮ ለሊቱን በሙሉ ሲያጠና ስለሚያድር ጠዋት ክፍል ውስጥ ገብተን ስንማር እንቅልፍ ሲያሸልበው በእንቅልፍ ልቡ ሁሉ እጁን ወጣል ይሉኝ ነበር - መጠየቅ መውደዴን ሲያጋንኑት፡፡ እርግጥ ስሆን አልጋ ላይ እንደተኛ ሰው ሙሉ ለሙሉ በእንቅልፍ - ልብ ውስጥ ስለማልሆንና ይልቁንም በክፍል - ልብ ውስጥ ሆኜ ስለምተኛ ነው፡፡ በሌላ አማርኛ ነቃ ብዬ ስለምተኛ ነው፡፡ ታላቅ ወንድሜ ደግሞ ሁልጊዜ ለጥናት ብዬ ቡና ስጠጣ “ነቃ ብለህ ለመኛት ነው አይደል?” እያለ ያሾፍብኝ ነበር፤ ምክንያቱም ለጥናት ብዬ ቡና ጠጥቼ ግማሽ ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እንቅልፍ ስለሚያዳፋኝ ነው፡፡ ታዲያ ልክ እንቅልፍ ሲያዳፋኝ እናቴ ታየኝና “አንተ ፈንዳሳ ቡናዬን በከንቱ ታከስራለህ አይደል!” ብላ በተራዋ በጥፊ ስለምታዳፋኝ ከቡናው ከቡናው ይልቅ ጥፊውን እያሰብኩ ነቃ ብዬ እተኛ ነበር፡፡ አይ ጥፊ! እንቅልፍን እስከነመፈጠሩ የሚያስጠላ ጥፊ! ደግሞ ሰዓቱ ነው የሚያናድደው፡፡ ልክ እንቅልፍ ሊወስድ ሲል ያለችው ጊዜ እኮ ናት!  ያቺ በመብረርና በመንሳፈፍ፣ በመዋኘትና በመቅዘፍ መካከል ያለችው ልዩ ውብ ሰዓት…እዛች ሰዓት ላይ አይደለም በጥፊ ጆሮ ግንድህ እስኪጮህ ተወልውለህ…

በስርዓት እንኳን ሰው ሲቀሰቅስህ እንዴት እንደምትናደድ ስለኸዋል?/ስዕል አልችልም እንዳትለኝ/

አይ የኔ ነገር፡ ዋናውን ርዕሰ ጉዳይ ትቼ ሌላ ሌላ ነገር እቀባጥራለሁ አይደል? አሁን ታዲያ ለኔ ጥፊ ያንሰኛል? ለማንኛውም ወደ ጉዳዬ…ነገሩ የተፈጠረው በቅርቡ ነው፤ “የት?” አትሉኝም፤ ጠይቁ እንጂ፤ ጉዳዩ እኔው የምሰራበት ቢሮ ነው የተከሰተው፤ የመጠየቅ መዘዙ የተመዘዘው፡፡

ቢሯችን እየከሰረ ነው፣ ኧረ እንደውም ሊዘጋ ነው የሚል ሩም ሩምታና ጉም ጉምታ በሰፊው እየተናፈሰ ነበር፡፡ ታዲያ ይህንን ሀሜታ የሰማነው ደሞዝ ከተሰጠን ወር ከአስራ አምስት ቀን በሆነን ጊዜ በመሆኑ “ምንድነው ነገሩ” ብለን ግራ ቀኙን ስንጠያይቅ ነበር፡፡ እናም ምክክር ያዝን፡፡ እንደ መፍትሔ ሃሳብ ምን መደረግ አለበት ስንል የቢሮ ባልደረቦች በምሳ እረፍታችን መከርን፤ ዘከርን፤ ፎከርን፤ አሴርን፡፡ የምሳ እረፍታችንን ለምክክር የተጠቀምንበት ሌላ የመመካከሪያ ጊዜ አጥተን አይደለም፤ ይልቁኑም ምሳን በምሳሌ፣ እራትን በተረት የሚያስብል ደሞዝ ተከፋዮች በመሆናችን ነው፡፡ ደሞዙስ ቁጥሩ ሲጠራ ሞገስ ነበረው፡፡ የዛሬን አያድርገውና! ግን፤ ያው ዘንድሮ ብሩ በረሮ ሆነ እንጂ፡፡

እናም ምክክራችን ጦፎ አንኳር ጉዳዮችን በጥልቅ የርሃብ ስሜት ውስጥ ሆነን ከተወያየን በኋላ የመፍትሔ ሃሳብ ጥቆማ ተጀመረ፡፡ አንዱ ባልደረባችን “ለምን ሰላማዊ ሰልፍ አንወጣም?” አለ፤ ሌላኛው አከለ “ሰላማዊ ሰልፉ እንዳለ ሆኖ እንደሚታወቀው የምሳ መብያም ስለሌለን በዛውም ለምን የረሃብ አድማ አንመታም?” ሲል በረሃብ ስሜት ብቻውን መቆም ባለመቻሉ የባልደረባው ሃሳብ ላይ ተደገፈ፤ እኔ ግን ምንም ነገር ባልዋጠው አንጀቴ ያቀረቡት ሃሳብ ያልተዋጠልኝ በመሆኑና በባዶ ሆድ ከመሰለፍ ወደሚቀጥለው ሃሳብ ማለፍ ያዋጣል ብዬ በማሰብ፣ የሌላኛውን ባልደረባችንን ሃሳብ እና የሆዳችንን ጩኸት መስማት ጀመርን፡፡ “እኔ የምለው ግን አለቆቻችንን በማያስቆጣ መልኩ ለየት ያለ የአጠያየቅ መንገድ ብናስብስ?” በማለት ወዲያው ንግግሩን ባጭሩ አቋርጦ እራቱን ማሰብ ጀመረ፤ /መሰለኝ/፡፡ በዚሁ ውይይታችን ለሻይ ቡና እረፍት ክፍት ሆነ፤ ወጉ አይቅር ተብሎ፡፡

ቢሮ ገብቼ በባዶ ሆዴ ለፈጠራ ብንጠራራም እንዲሁ በቀላሉ የሚመጣ አልሆነም፤ ወዲያውም አንድ ሀሳብ ብልጭ ብሎ ድርግም አለብኝ፤ እንደገና ብልጭ አለልኝ…አገራችን ውስጥ ብዙ የፈጠራ ሰዎች የሌሉት ለካ ስለሚራቡ ነው ብዬ “ሃንገር ቲዮሪ” አፈለቅሁ፡፡ አንድም የቲዮሪ ፈጣሪነት ችግራችንን በተወሰነ መልኩ ለመቅረፍ ሌላም ትሪ የናፈቀውን ወገኔን በቲዮሪ ለመካስ በማሰብ፡፡ ይህ በዚህ እንዳለ አንዲት ስርጉት የምትባል የቢሮ ባልደረባችን ብስኩት ገዝታ እየበላች ነበርና አንድ ብስኩት ፀደቀችብኝ፡፡

ብስኩቴን ከሽ እንዳደረኩ “ጨጉዌክስ” ለአእምሮዬ ሜሴጅ ላከለት መሰለኝ ደረጃ -3 ውስጥ ሊካተት የሚችል ምን የመሰለ ሃሳብ መጣልኝ፡፡ ሃሳብን በስዕል የመግለጽ ሃሳብ/መብት ልል ነበር ቸኩዬ፤ ሃሳብ ሁሉ መብት ቢሆን የት በደረሰን/፡፡ ለማንኛውም፣ ሃሳቡ የመጣልኝ በፌስ ቡክ ድረ-ገጽ በተደጋጋሚ ካየኋት ስዕል ነው፤ ስዕሏ “Salary, why do you take so long!” የምትል መግለጫ (caption)  አላት፡፡ እንግሊዝኛና ህልም እንደ ፈቺው ነው ይላል የለ! (ደሞዝ ሆይ ወዴት አለሽ?) እንደ ማለት ነው ትርጉሟ እናም ይችን ስዕል የኮምፒውተሬ ስክሪን ሴቨር ለማድረግ ወሰንኩ፡፡ ምክንያቱም አለቆቼ ከፊት ለፊቴ ስለሚቀመጡ ስዕሏ አንድም ሃሳቤን ትገልጥላቸዋለች፣ ሌላም ታዝናናቸዋለች፡፡ በዋናነነትም ጥያቄዬን ትጠይቅልኛለች በማለት - በየዋህነት፡፡ ታዲያ ያልጠረጠረ ተመነጠረ ነውና ይህንን ያየችው አለቃዬ እንኳን የስዕሌን ሃሳብ ተረድታ ልትዝናና እና ጥያቄዬን ልትመልስ ቀርቶ፣ “አገኘኋት እንደተመኘኋት” በሚል  “በስራ ኮምፒውተር ላይ ኢ-ስነምግባራዊ መልዕክት በመለጠፍ” የሚል የመጀመሪያ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ አሻረችኝ፡፡

አሁን እውነት እንነጋገር ከተባለ ደሞዝ በጊዜውና በአግባቡ አለመስጠት ነው ወይስ “ደሞዝ ሆይ ወዴት አለሽ?” ብሎ ሃሳብን በስዕል መግለጽ ኢ-ሥነምግባራዊ ተግባር? ለማንኛውም ይህንን ጉዳይ በቀላሉ የማየው አይሆንም፡፡ እስከ አለም አቀፉ የኢ-ሥነምግባር አጣሪ ኮሚሽን ድረስ ቢቻለኝ በጽሑፍ አልያም በስዕል ሃሳቤን አስረዳለሁ፡፡ ማን ይሙት ዲሞክራሲ በጽሑፍ ብቻ ሳይሆን በስዕል በሚገኝባት አገር ይህን አይነቱን ኢ…ተግባር ምን ይሉታል? ምናልባት የመጠየቅ ጠንቅ? እኔ እንጃ!

በሌላ የቢሮ ወሬ እንገናኝ፡፡ ሰላም!

 

 

 

 

Read 2494 times Last modified on Monday, 05 March 2012 14:39