Monday, 05 March 2012 14:04

ኃይሌን የኦሎምፒክ ማራቶን አጣው ወይንስ አመለጠው ?

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

ከ8 ዓመት በፊት ኦሎምፒክን ለማዘጋጀት የስፔኗ ባርሴሎና፤ የጣሊያኗ ሮም እና የእንግሊዟ ለንደን ሲፎካከሩ ኃይሌ ገብረስላሴ ከሶስቱ ከተሞች ለየትኛው ድጋፍ ትሰጣለህ ተብሎ ከአዲስ አድማስ ተጠይቆ ነበር፡፡ ምላሹን የሰጠው ኦሎምፒክ ለለንደን ይገባታል ብሎ ነበር፡፡ እነሆ የለንደን ከተማ 30ኛው ኦሎምፒያድን የማስተናገድ እድል አግኝታ ታላቁ የስፖርት መድረክ ሊጀመር ሩብ ዓመት ቀርቶታል፡፡ ካለፈው አንድ ዓመት ወዲህ ኃይሌ ገብረስላሴ በለንደን ኦሎምፒክ ትሳተፋለህ በሚል በተደጋጋሚ ይጠየቅ ነበር፡፡ በለንደን የኦሎምፒክ ማራቶንን ለመሳተፍ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው በየምላሹ ሲገልፅ ቆየ፡፡ አስፈላጊ ሚኒማውን ለማምጣት ሁለት የማራቶን ውድድሮችን አነጣጥሮ ነበር፡፡ ጎን ለጎን ግን በለንደን ኦሎምፒክ የኢትዮጵያ የማራቶን ቡድን ለመካተት ከወጣት አትሌቶች ከባድ ፉክክር እንደሚገጥመውም ይናገር ነበር፡፡ የመጀመርያው እድል በ2012 መግቢያ ላይ ተካሂዶ በነበረው የዱባይ ማራቶን ቢሆንም ሳይሮጥ ቀረ፡፡

ባለፈው ሳምንት ግን ከፍተኛ ዝግጅት አድርጎ  የቶክዮ ማራቶንን ተሳተፈ፡፡  በኦሎምፒክ ማራቶን ለወንድ አትሌቶች የተቀመጠው የመግቢያ ሚኒማ 2 ሰዓት ከ15 ደቂቃዎች ነው፡፡ ኃይሌ ባለፈው ሳምንት በቶክዮ ማራቶን ሲወዳደር  አራተኛ ደረጃ አግኝቶ ጨረሰ፡፡ ርቀቱን የሸፈነበት ሰዓት ደግሞ 2 ሰዓት ከ8 ደቂቃ ከ17 ሰኮንዶች ነበር፡፡ በውድድሩ እስከ 35ኛው ኪሎሜትር መሪ ሆኖ ሲሮጥ የነበረው አትሌቱ ማራቶኑን በ2 ሰዓት ከ5 ደቂቃ በሆነ ጊዜ የመጨረስ ተስፋ ነበረው፡፡ ይሁንና በልምምድ ወቅት ወድቆ በጉልበቱ ላይ ያጋጠመው  መለስተኛ ጉዳት 7 ያህል ኪሎሜትሮች ሲቀሩ አገረሸበት በቶክዮ ማራቶን ሊያሳካ የነበረውን ሚኒማ የሚያሟላበት ብቃቱም እንከን አጋጠመው፡፡ ኃይሌ በቶኪዮ ማራቶን አራተኛ ደረጃ ይዞ ሲጨርስ ርቀቱን የሸፈነበት ጊዜ የኦሎምፒክ  ሚኒማን ቢያሟላም በለንደን ኢትዮጵያን ወክለው ለሚሮጡ 3 ማራቶኒስቶች ባለው ኮታ ለመግባት የሚበቃ አልሆነም፡፡ ምክንያቱም እሱ ባልተሳተፈበት የዱባይ ማራቶን ብቻ ከ1 እስከ 3 የገቡ አትሌቶች 2 ሰዓት ከ5 ደቂቃ ያለውን ጊዜ አስመዝግበዋል፡፡ የዱባይ ማራቶንን ያሸነፉት ብቻ አይደሉም በቤጂንግ ኦሎምፒክ የነሐስ ሜዳልያ ያለው ፀጋዬ ከበደ፤ በ2010 የኒውዮርክ ማራቶንን ያሸነፈውና ባለፈው ዓመት በቦስተን ማራቶን 2 ሰዓት ከ04 ደቂቃ ከ53 ሰኮንዶች ያስመዘገበው ገብረእግዚአብሄር ገብረማርያም እንዲሁም በዳጉ የዓለም ሻምፒዮና የነሀስ ሜዳልያ ሲወስድ 2 ሰዓት ከ05 ደቂቃ ከ23 ሰኮንዶች የያዘው ፈይሳ ሌሊሳ  በኃይሌ ተቀናቃኝነት የሚጠቀሱ ማራቶኒስቶች ናቸው፡፡

በቶክዮ ማራቶን ለኦሎምፒክ የሚያበቃውን ሚኒማ በበቂ ሁኔታ ማሟላት  ካልሆነለት በኋላ የእንግሊዝ ጋዜጦች ጉዳዩን መነጋገሪያ አድርገውታል፡፡ ኃይሌን የኦሎምፒክ ማራቶን አጣው ወይንስ አመለጠው በሚል በለንደን ጎዳናዎች የኦሎምፒክ ማራቶንን ኃይሌ ሲሮጥ ደጋፊዎቹ ላያዩት ነው በሚል ብዙዎቹ ቁጭት የተሞላ ዘገባቸውን ሰሞኑን አቅርበዋል፡፡ አንዳንድ መረጃዎች በ10ሺ ሜትር የኦሎምፒክ 2 የወርቅ ሜዳልያዎች፤ እንዲሁም በዓለም ሻምፒዮና 4 የወርቅ ሜዳልያዎች፤ የማራቶን ርቀትን ሪኮርድ ሁለቴ የሰበረ፤ ማራቶንን ከ2 ሰዓት ከ4 ደቂቃዎች በመግባት የመጀመርያው አትሌት ሊሆን የበቃውና 9 ትልልቅ የማራቶን ውድድሮችን ያሸነፈ ታላቅ አትሌት የለንደን ኦሎምፒክ ያጣዋል በሚልም ፅፈዋል፡፡ኃይሌ አሁንም ቢሆን በለንደን ኦሎምፒክ ሊያሳትፈው የሚበቃ ሚኒማ የሚያሟላበት እድል አልተሟጠጠም ያሉ መረጃዎችም ታይተዋል፡፡ ከ50 ቀናት በኋላ እዚያው ለንደን ከተማ በሚደረገው የቨርጂን ለንደን ማራቶን በመሳተፍ ሊያሳካው እንደሚችል ዘገባዎቹ እየጠቆሙ ናቸው፡፡ከቶክዮ በኋላ ኃይሌ ለኦሎምፒክ በቂ ሚኒማ በሚያገኝበት የማራቶን ውድድር ለመሳተፍ የማገገሚያና በቂ ዝግጅት የማድረጊያ 6 ሳምንታት ቢኖሩትም ለ38 ዓመቱ አትሌት ውጤታማነት ማስተማመኛ ጠፍቷል፡፡

ኃይሌ ከቶኪዮ ማራቶን ተሳትፎው በኋላ በሰጠው መግለጫ በሌላ ማራቶን ውድድር ከ2 ሳምንት በኋላ የመሳተፍ ብቃት እንዳለው በልበሙሉነት ተናግሯል፡፡ ይህን ለማሳካት ከኦሎምፒክ በፊት በለንደን ማራቶን ስለመሮጡ ግን የተናገረው የለም፡፡ኃይሌ በማራቶን የዓለም አቀፍ ውድድር ተሳትፎውን ከ6 ዓመት በፊት የጀመረው በለንደን ማራቶን ነበር፡፡ በወቅቱ 3ኛ ደረጃ አገኘ፡፡ ከዓመት በኋላ በተመሳሳይ ውድድር ሲሳተፍ ግን ከአተነፋፈስ ችግር ጋር በተያያዘ ውድድሩን አቋርጦ ለመውጣት ግድ ሆነበት፡፡ የለንደን ማራቶን የሚካሄደው በፀደይ ወቅት ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ኃይሌ በከተማው አበቦች ብናኝ  አለርጂክ መሆኑ ውድድሩን ላቋረጠበት ምክንያት ነበር፡፡ ዘንድሮም ከኦሎምፒክ በፊት በሚደረገው የለንደን ማራቶን ለመሮጥ ከፈለገ ይህ አይነቱ ችግር ሊያጋጥመው መሳተፉን አጠራጣሪ ያደርገዋል፡፡

 

 

Read 1967 times Last modified on Monday, 05 March 2012 14:06