Monday, 08 August 2016 05:52

የእርግዝና ትንሽ የለውም” ጆርጅ በርናርድ ሾው

Written by 
Rate this item
(16 votes)

   ከዕለታት አንድ ቀን፤ አንድ መንደር ውስጥ በርካታ የአይጥ መንጋ ይፈላና አካባቢውን ይወርረዋል፡፡ ይህን ችግር ለማስወገድ የሚቻለው ድመት ወዳለው ሰው ሄዶ ድመቱን ተውሶ አይጦቹን እንዲያስወግድ ማድረግ ነው፡፡
ስለዚህ የሰፈሩ ሰው መክሮ ተመካክሮ ድመት  ወዳለው ሰው ዘንድ ሄዶ፤
“ጌታ፤ እንደምታውቀው መንደራችን በአይጥ ተወሮ መድረሻ አሳጥቶናል፡፡ የአንተ ቤት ከዚህ ችግር ነፃ ነው፡፡ ድመት ስላለህ፡፡ የእኛ ግን አሁንም እንደተወረረ ነው፡፡ ስለዚህ፤ ድመትህን አውሰንና ሴት ድመቶችን አስወልዶ፡- አርብተን ከአይጥ ችግር ነፃ እንሁን?!” አለው፡፡
ባለ ድመቱም፤ ደግና አርቆ አሳቢ ሰው ኖሮ፤
“ዕውነት ነው፡፡ የእኔ ቤት ብቻ ከአይጥ ነፃ መሆን ችግሩን አያስወግደውም፡፡ ነገ የእናንተ ቤት አይጦች ወደ እኔ ቤት መምጣታቸው አይቀርም፡፡ ችግሩ ዙሪያ ገጠም (Vicious circle) ነው፡፡ ስለሆነም በሁሉም የሰፈሩ ሰው ቤት ያሉትን አይጦች ማስወገድ ነው የሚሻለው”፤ አለና ድመቱን አዋሳቸው፡፡
ድመቱ ስራውን ሰራ፤ ብዙ ድመት አስወለደ፡፡ አድገው አይጦቹን አሳደው በሉ፡፡ መንደሩ ከአይጥ ፀዳ! ሰላም ወረደ፡፡ ሜዳው ሁሉ ስጥ የሚሰጣበት እህል እንደ ልብ ፀሐይ እንዲመታው ሰሌን ላይ የሚዘረጋበት ወቅት ሆነ! ጥጋብ የአደባባይ ጉዳይ ሆነ!
ያም ድመት ቀን ወጣለት፡፡ እንደ ልቡ መብላት፣ መጠጣት፣ በየቤቱ ምግብ ማግኘት ዕድሉ ሆነ፡፡ ከሌላ ሰፈር ድመቶች ጋር ስሪያ፣ መዳራት፣ ማስረገዝ፣ ማስወለድ ሆነ ስራው፡፡ ምድር ሰማዩ በድመት ተሞላ!    
“ደሞ በድመት ብዛት ምሬት መጣ! “እነዚህ ድመቶች ወደ አጎራባች አገሮች በጉዲፈቻ እንስጣቸው!” ተባለ፡፡ ሁሉም ተስማማ፡፡ ሰፈሩ ከድመት ነፃ ሆነ፡፡ ዋናው ባለ ድመትም የራሱን ድመት ከእንግዲህ እንዳይወልድ አኮላሸው!
ለጥቂት አመታት ከአይጥ - ነፃ የሆነ ኑሮ ቀጠለ፡፡ ሆኖም አይጦቹ ጊዜ ጠብቀው መንደሩ በተዘናጋባት ሰዓት ከች አሉ፡፡ እህል ተበላ፡፡ ልብስ ተቀረጠፈ፡፡ መጽሀፍ ተከረተፈ፡፡ ችግር አጠጠ፡፡
እንደገና ህዝቡ ወደ ባለ ድመቱ መጣ፡፡
“እባክህ እንደ ካቻምናው ድመትህን አውሰን? ሴት ድመቶችን ያጥቃልን?” ሲሉ በትህትና ጠየቁት፡፡
“አዬ ወዳጆቼ! እኔስ ድመቱን በሰጠኋችሁ በፈቀድሁ፡፡ ግን አይጠቅማችሁም፡፡ ምክንያቱም፤ ዛሬ ድመቴ ተኮላሽቷል፡፡ አሁን አማካሪ (consultant) ሆኗል፡፡ የምክር አገልግሎት ብቻ ነው ሊሰጥ የሚችለው” አላቸው፡፡
*         *         *
ዛሬ ከስራ አስኪያጅነት ወደ አማካሪነት የሚመደቡ አያሌ ናቸው! በውሰት ችግርን ለመፍታት መሞከር ዘላቂ ሂደት አይሆንም፡፡ አንድ ጊዜ በዘመቻ የፈታነው ችግር መሰረታዊ መፍትሄ አገኘ ማለትም አይደለም፡፡ ሥር - ነቀል መፍትሄ ማግኘት ካስፈለገ፣ በቂ አቅም በገዛ ሀብት መፍጠር የግድ ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ ስራን በሙሉ ልብ የምንሰራበት ሁኔታ ማመቻቸት ግዴታ ይሆናል፡፡ ከዚህ ውስጥ አንዱ የተማረ ኃይልን በአመርቂ ሁኔታ ማሳተፍ ነው፡፡ አሳታፊ መድረክ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ምሁራን አድርባይ፣ ተጠራጣሪና ፈሪ ከሆኑ የስራ ሁኔታው የስጋት እንጂ የልበ - ሙሉነት አለመሆኑን ነው የሚያመላክተን፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ሙሉ  አቅማቸውን ለተፈለገው ግብ አያውለውም፣ አልፈው ተርፈውም እንቅፋት እስከመሆን ይደርሳሉ ማለት ነው። “መሳም ፈልገሽ፣ ጢም ጠልተሸ አይሆንም” የሚለውን ተረት አለመዘንጋት ብልህነት ነው። አሳታፊ መድረክ መፈጠር አለበት ሲባል፤ ዲሞክራሲያዊ መሆን አለበት፡፡ አሳታፊ መድረክ ይፈጠር ሲባል ፍትሐዊ፣ ኢ-ወገናዊ (non-nepotistic) ሁኔታ መኖር የለበትም ማለት ነው፡፡ አሳታፊ መድረክ ይኑር ሲባል፤ ስራ በብቃት፣ በጥራት፣ ጊዜን ቆጣቢ በሆነ መልኩ ያለብክነት የሚተገበርበት ሁኔታ ይፈጠር ማለት ነው፡፡ አሳታፊ መድረክ ይኑር ሲባል፤ ከታማኝነት አስቀድሞ የስራ ክህሎት መመዘኛ ይሁን ማለት ነው፡፡ አሳታፊ መድረክ ይኑር ሲባል፣ ግልፅነትና ተጠያቂነት፣ እገሌ ከእገሌ ሳይባል ሥራ ላይ ይዋል ማለት ነው፡፡ አሳታፊ መድረክ ይኑር ሲባል፣ ከሰራተኛው አማካሪው (consultant) አይብዛ ማለት ነው፡፡ ከሌላ ቦታ በድክመት የተነሳ፤ አማካሪ አይሁን ማለትም ነው፡፡ አሳታፊ መድረክ ይኑር ሲባል፤ የቅራኔና የእልህ መድረክ ሳይሆን ለሀገርና ለህዝብ ደህንነትና ዕድገት ሁሉም ፈትል ከቀስም ሆኖ በአንድነት የሚሰራበት መድረክ ይፈጠር ማለት ነው፡፡፡ አሳታፊ መድረክ ሲባል፣ ሙስና አልባ መድረክ መፍጠር ማለት ነው፡፡
ከቶውንም ዛሬ በሀገራችን ስራ በማንኪያ መብል በአካፋ የሆነበት ዘመን ነው፡፡ ይኸውም ባቋራጭ መክበርን እንደ ርዕዮተ ዓለም ይዞ የሚንቀሳቀስበት ዘመን ሆኗል፡፡ ዕድገት እየፋጠነ ነው እየተባለ የቦጥቧጩ፤ የሸርሻሪው ከአፍ እስከ ገደፍ መሆን፤ በግልም፣ በመንግስትም፣ መንግስታዊ ባልሆነ ድርጅትም ያለ ምህረት ምዝበራን ማካሄድ በአዋጅ የታዘዘ ይመስላል፡፡ እርግጥ አዋቂዎች፤ ዝመና (modernization) እና ሙስና ቁራኛ ናቸው ይላሉ፡፡ “ሙስና ከዝመና ጋር የሚመጡት የግለኝነትና የህዝብ ሀብት ልዩነት ውጤት ነው፡፡ አንድም ደግሞ ስኬታማ ያልሆነ የፖለቲካ ተቋማ አለመኖር ምልክት ነው፡፡ … ሙስና ህዝባዊ ሚናን ከግል ጥቅም ማምታታትንም ያሳያል፡፡ የህብረተሰቡ ባህል ንጉሱን እንደ ግለሰብ ሚናውን ካልለየና ንጉሱን እንደ ንጉስ ሚናውን ካልለየ፤ ንጉሱ የህዝብ ገንዘብ ለግል ጥቅማቸው አውለዋል ብሎ ሊከሳቸው አይቻለውም፡፡ የንጉሱ አካሄድ አግባብ ነው፣ አደለም ብሎ መፍረድም ያዳግተዋል!” በእኛ አገር አንፃር ሲታይ፤ ግልፅ ሌብነት ይፋ እየሆነ ከመጣ ውሎ አድሯል፡፡ እነ ናይጄሪያን ባንተካከልም በራሳችን የሚታይ፣ ያፈጠጠ፣ ያገጠጠ ሙስና አለን፡፡ ኤም.ጂ ስሚዝ የተባሉ ፀሐፊ፤ “ብሪታኒያው ሙስና የሚለውን፣ አውሳው ግፍ ይለዋል፡፡ ናይጄሪያዊው ፍላኒ ግን አስፈላጊና ባህላዊ ተግባር ነው ይለዋል” ይሉናል። ዞሮ ዞሮ እየዘመንን ስንመጣ፣ ሙስናችን ዳር ድንበሩን እደጣሰ ታዝበናል፡፡ አስከፊው ነገር ደግሞ ሃይ ባይና ተቆጪ ብሎም ቀጪ፤ አለመኖሩ ነው፡፡ ሁሉ ተነክሮበት ማ፣ ማንን ይቅጣ? “እኔ ትንሽ ብቻ ነው የወሰድት” የሚሉ ሹማምነት እንዳሉ ቢሰማም ጆርጅ በርናርድ ሾ እንዲህ ይመልስላቸዋል፡- There is no little pregnancy! - የእርግዝና ትንሽ የለውም ማለቱ ነው፡፡ የሙስናም ትንሽ የለውም፡፡ ኃጢያት ከኃጢያት ማወዳደር ሳይሆን ከኃጢያት መንፃት ነው ታላቁ ቁም ነገር! ማንም ከህግ በላይ አይደለም ካልን፤ “all men are equal but some men are more equal” “ሁሉም ሰው እኩል ነው፤ አንዳንድ ሰዎች ግን የበለጠ እኩል ናቸው” ማለትን ምን አመጣው?! ከዚህም እንንፃ!

Read 7111 times