Monday, 25 July 2016 07:15

“ጎርፍም ያለ እርከን፣ ምራቅም ያለ ከንፈር አይቆምም” - የላቲኖች አነጋገር

Written by 
Rate this item
(17 votes)

    ከዕለታት አንድ ቀን አንዲት መነኩሲት ጎኅ ሲቀድ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሊሄዱ ይነሳሉ፡፡ አንድ ዛፍ አጠገብ ሲደርሱ ተንበረከኩና ሁለት እጃቸውን በልመና መልክ ዘርግተው፤ ፀለዩ፡-
“አምላኬ ሆይ! መቼም አንተ የነገሩህን የማትረሳ፣ የለመኑህን የማትነሳ፣ ሰማይን ያለ ካስማ ያቆምክ፣ የማይዘሩ የማያጭዱትን ወፎች የእለት ምግባቸውን የምትሰጥ ነህ! አሁን እኔ የምለምንህ እጅግ ትንሽ ነገር ናት፡- አምላኬ ሆይ! አደራህን ዕድሜዬን ጨምርልኝ?” አሉት
ወደ ቤተ ክርስቲያን መንገድ ቀጠሉ፡፡ ወደ ቤት ተመልሰውም፣ ይሄንኑ ሲያብሰለስሉ አመሹ፡፡
በሚቀጥለው ቀን ማለዳ ጎኅ ሲቀድ፤ ተነስተው ወደዚያው ዛፍ ስር ሄደው፤ ምናልባት ፀሎቴን አሳንሼው ይሆናል በሚል፤
“አምላኬ ሆይ! ድንገት ከወትሮው ፀሎቴ አሳንሼብህ ይሆናል፡፡ የከዋክብት ብዛቱን፣ የውቂያኖስ ስፋቱን፣ የሙሴ በትሩን፣ የገብርኤል ተዓምሩን፣ የእመቤታችን አማላጅነቷን የምታውቅ፣ የምትሰጥ፤ የነገሩህን የማትረሳ፣ የለመኑህን የማትነሳ፣ ሰማይን ያለ ካስማ ያቆምክ፣ የማያርሱ የማይዘሩ ወፎችን የእለት ጉሮሮ የምትዘጋ፣ ምንም የማይሳንህ አምላክ ሆይ! ካንተ ልግስና አንፃር እጅግ ትንሽ ነገር ነው የምለምንህ፡- እባክህ ዕድሜዬን ጨምርልኝ?”
ለካ ይህን ፀሎታቸውን ሲያደርሱ፣ ሁሌ ቁጥቋጦ ውስጥ ተደብቆ የሚያዳምጣቸው አንድ ተንኮለኛ የቆሎ ተማሪ ኖሯል፡፡
በሚቀጥለው ማለዳ ጎኅ በቀደደ ሰዓት ያ የቆሎ ተማሪ፣ ቀደም ብሎ ዛፉ ላይ ወጥቶ ይጠብቃቸዋል። እሳቸው እንደልማዳቸው መጥተው ፀሎትና ልመናቸውን አሰሙ፡፡ በመጨረሻም፤ “ዕድሜዬን ጨምርልኝ፣አደራ!” አሉ፡፡
ይሄኔ፤ ያ የቆሎ ተማሪ፤
“አንቺ መነኩሲት! ምን ያህል ዕድሜ ልጨምርልሽ?” አለ ድምፁን ጎላ አድርጎ፡፡ መነኩሲቷ ደነገጡ። ፀሎታቸው ተሰማ! ሲያስቡት ሃያም ትንሽ ነው፡፡ አርባም ትንሽ ነው፡፡ መቶም ትንሽ ዕድሜ ነው። በመጨረሻ እንዲህ ሲሉ መለሱ፤ “አምላኬ ሆይ! አንድ ድሃህን ከነጭራሹስ እዚሁ ብትተወኝ፣ ምን እጎዳሃለሁ?!” አሉ፡፡
*             *           *
የዓለም ኢኮኖሚ ጉዳይ አንጋፋ ባለሙያ የሚባለው አዳም ስሚዝ፤ “የሰው ልጅ ፍላጎት ወሰን የለውም” ያለንን ከላየ ያየነው ተረት በአበሽኛ ሳይገለጥልን አልቀረም - Human wants are unlimited ማለት ይሄው ነው፡፡ ዛሬ መጠለያ ጠየቅን፡፡ ነገ ምግብ እንጠይቃለን፡፡ ከነገ ወዲያ መንቀሳቀሻ መኪና እንፈልጋለን። ከዚያ ወዲያ ሰፋ ያለ ግቢ እንዲኖረን እንጠይቃለን፤ ወዘተረፈ ችግሩ የሚመጣውና የሚስፋፋው መሰረታዊ ፍላቶታችን ከተሟላ በኋላ ነው፡፡ ወለሉ ግን መሰረታዊ ፍላጎት ነው፡፡ ኢኮኖሚያችን ከዚህ ወለል በታች ከሆነስ? “እዚሁ ላይ ነው ችግሩ” እንዳለው ነው ሼክስፒር፡፡ “መሆን ወይስ አለመሆን?” የሚባለው ጥያቄ፣ ማናቸውም ጉዳይ ለውሳኔ አሳሳቢ ደረጃ ሲደርስ የሚመጣ ነው፡፡ ውስጥን መፈተሽ አለመፈተሽ፣ እርምጃ መውሰድ አለመውሰድ? ነው ጉዱ! ምኞት ከአቅም በላይ መሆን እንደሌለበት ማንም ጅል አይስተውም። የፍላጎት አቅማችን እየኮሰሰ፣ ምኞታችንን ሲያጫጨው፤ የተስፋ መቁረጥ ጉድባ ውስጥ እንገባለን፡፡ ዜግነታችን ራሱ ያስጠላናል፡፡ የሀገር ፍቅራችን ይሟሽሻል፡፡ ሁሉን ነገር አሉታዊ እሳቤ ውስጥ እንከተዋለን። መንገድ ተሰራ ስንባል የሚሄዱበት እነሱ እንላለን፡፡ ፎቅ ተሰራ፤ ‹የማን ነውና!› ዘር ከዘር ታጋጨ፤ ‹ማን አመጣውና› ዕውነትም ውሸትም አለው ነገሩ፡፡ ህይወታችን የምንግዴ ህይወት ይሆናል፡፡
ሰብዓዊም ሆነ ቁሳዊ ዕሴት ያለን አይመስለንም፡፡ ይሄ የተስፋ ቆራጭነት ሁኔታ (desperado state) ለሀገርም፣ ለህዝብም አደገኛ ነው! አይበጅም! የኢኮኖሚ ችግር፣ የፖለቲካ ድንግዝግዝነትን (obscurantism) ብሎም ጠርዘኝነትንና ዕንፋዊ ጥላቻን ሲፈጥር፤ ‹የመጣው ይምጣ› አስተሳሰብ ይከሰታል፡፡ ማህበራዊ ቀውስ፣ ሥርዓተ-አልበኝነት፣ ምን ዳኝነት፣ ዘራፌነት፣ እኔ ምንተዳዬነት ወዘተ … ይነግሳሉ፡፡ አጠቃላይ ድቀት ይከተላል፡፡ ማንም ስለ ማንም መጨነቁን ይተዋል፡፡ ከዚህ ይሰውረን!!
ዛሬ በሀገራችን የአሳሳች መረጃዎችና ሰነዶች መብዛት ከአቅም በላይ የደረሰ ይመስላል፡፡ የወንጀለኛ መቅጫ ህጉ አለ፡፡ የተጭበረበሩ ሰነዶች ግን ከመፈጠር አላባሩም፡፡ ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ፣ በሀሰት የተፈበረከ (Forged) ፈቃድ… ለምሳሌ የህንፃ ፈቃድ፣ የቀበሌ መታወቂያ፣ የግንባታ ፈቃድ፣ የመንጃ ፈቃድ፣ የንግድ ፈቃድ፣ አልፎ ተርፎም የጋብቻ ሰርተፍኬት ሳይቀር በሙስና አዋላጅነት፣ በሽበሽ ሆነዋል! የቀረው የአመፅ ፈቃድ “በፎርጅድ” ማሰራት ብቻ ነው ተብሏል! እጅ ላይ ያለው ችግር በአግባቡ መፍትሄ ባለማግኘቱ፤ ከድጡ ወደ ማጡ መሄዳችን ግድ ሆኗል፡፡ ብዙ ነገር ካንሰር - አከል በሽታ ሆኖብናል። አሰቃቂው ነገር፤ የጉዳዩ ተወናዮች- አለቃውም ምንዝሩም፣ ህግ አውጪውም፣ አስፈፃሚውም፣ መሆናቸው ነው! እርምጃ ማን ይውሰድ? አሰኝቶናል፡፡ ህገ-መንግሥቱንም፣ ህዝቡንም የረሱ አያሌ ሹማምንት ለመኖራቸው ዛሬ ብዙ አያጠራጥርም! ህገ ወጥነት ጣራውጋ ሲደርስ ማጣፊው ያጥራል! “የንጉሡን ፊት አይተህ ፈገግ በል›› የሚለውን ተረት፤ በየደረጃው እንደመሪ መፈክር የያዙ በርካታ ናቸው። ሁኔታዎች ከቁጥጥር ውጪ የሆኑ ለታ ግን ሁሉን ጥፋት በክልል ከማላከክ አልፈን የራስ ተጠያቂነት አፍጦ ይመጣል፡ ‹‹ባሪያ ላግዝሽ ሲሏት መጇን ትደብቃለች›› የሚለው ተረትም በመንግስትና በባለሙያ መካከል ይታያል፡፡
እያደር ዕውን የሆነና የሚሆን ግጭት፣ ፍጭት፣ ወደ ዘረኝነት አቅጣጫ ለመሄድ እርሾው የሚታይና አብሲቱ የተጣለ የሚመስልበት ሁኔታ፣ ብዙው የፖለቲካ ጨዋታ ሲሟጠጥ እንደሚሆነው ሁሉ ወደ ጡንቻ የሚሄድ፣ የደም መፋሰስ ትርዒት ማየት፣ ስለ ብዙ ሰላም ለምታወራ አገር የሚያምር ቁም ነገር አይደለም፡፡ ያለመረጋጋት አስረጅ ይሆናልና ከወዲሁ መገደብና ሰላማዊ መፍትሔ መሻት አስፈላጊ ነው። ቁጣን በቁጣ መመለስ አባዜው ብዙ ነው! የተኙት ብዙዎች፣ የተናደዱትና የነቁት ጥቂቶች ሲሆን፤ የበሠለ አመራር በስሜታዊነት ይዋጣል፡፡ ቁጣ ቦታ የሚያገኘው ይሄኔ ነው፡፡ መጠንቀቅ ይገባል፡፡ ሆድ ሰፊ መንግሥት an eye for an eye (ዐይን ያወጣ ዐይኑ ይውጣ) ከሚል ጥንታዊ ‹ህግ› የተላቀቀ ሊሆን ይገባዋል፡፡ የሠለጠነ ህግ አለውና፡፡ ህግ እንዳለ ከረሳን ግን የአልዛይመር ምርመራ ማረግ ነው፡፡
አሁንም የውስጥ ምርመራ ያስፈልጋል- የከአንገት በላይ ምርመራው ብቻ በቂ አይሆንምና፡፡ ትንሽ ቁስል ሰፍታ ሰፍታ የአገር ህመም የምትሆን ከሆነ ጠቅላላ ምርመራ የግድ ነው፡፡ ክፍሎቻችን ሁሉ በቅጡ ይመርመሩ!!
የሚጠራቀሙ ጥቃቅን ብሶቶች፤ ልክ ጠብ ጠብ እንደሚሉ የውሃ ጠብታዎች ናቸው፡፡ ሲጠራቀሙና አቅም ሲያገኙ ጎርፍ ይሆናሉ፤ ይላሉ የጥንቱ የጠዋቱ የቻይናው ማዖ ዜዱንግ፤ ትግላቸውን ነብሱን ይማረውና፡፡ ጫማ ልክ አልሆን ሲል እግር የመቁረጥ ፖለቲካም አይሠራም ይላሉ፡፡ ጥቃቅንና አነስተኛ ችግሮች፤ ያለ አራሚ እንደሚያድጉ አረሞች ናቸው፡፡ እያደር ዙሪያ ገባውን ዳዋ እንዲውጠው ያደርጋሉና። ከዚያ ‹‹አይጥ በበላ ዳዋ ተመታ›› ነው ተከታዩ፡፡ ሀገራችን ከዚህ ‹‹ውጣ እምቢ፣ ግባ እምቢ›› አጣብቂኝ የሚያወጣት መላ መምታት አለባት፡፡ ቅርቃር ውስጥ ናት - በሰላምና በሰላም ማጣት ራስ-ምታት መካከል። ቅርቃሩ ጊዜያዊ ነው ወይስ አይደለም? መመርመር ነው!! አሁንም ጠብታዎች ጎርፍ፣ ጎርፎች ዥረቶች፣ ዥረቶች ወንዞች እንዳይሆኑ፤ ቅድመ ማስጠንቀቂያዎችን ማየት ደግ ነው፡፡ ላቲኖች፤ ‹‹ጎርፍም ያለ እርከን፤ ምራቅም ያለ ከንፈር አይቆምም›› ያሉት ልብ ማለት ይጠቅመናል፡፡


Read 8720 times