Saturday, 16 July 2016 12:40

“ከአንበሳና ከዝሆን ማን ያሸንፋል?” ቢለው፤ “ከሁሉም አሳ ሙልጭልጭ ነው” አለው

Written by 
Rate this item
(15 votes)

    ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ሰው በጠና ታመመና አልጋ ላይ ዋለ፡፡ በየጊዜው እየሄደ ዶክተሮች ያነጋግራል፡፡
1ኛው ሐኪም - “አይዞህ ቀላል ነው፡፡ ለክፉ አይሰጥህም” አለው፡፡
ህመምተኛው - “ዕውን ሐኪም በዚህ ተፅናንቼ ልቀመጥ?”
1ኛው ሐኪም - “እርግጡን ነው የነገርኩህ”
ህመምተኛው - “እንዳፍዎ ያድርግልኝ!”
ግን አያርፍም ህመምተኛው - ወደ ሁለተኛው ዶክተር ይሄዳል፡፡  
ሁለተኛው ሐኪም - “ምንም ችግር የለብህም፤ አሁን የያዘህ በሽታ በረዥም ጊዜ የሚድን ስለሆነ ብቻ ነው አልጋ መያዝ ያስፈለገህ”
ህመምተኛው - “ቃልዎትን አምኜ ዝም ብዬ ልተኛ ሐኪም?”
ሁለተኛው ሀኪም - “እቺን ታክል አትጠራጠር!”
ህመምተኛው - “እንዳፍዎ ያድርግልኝ!”
ወደ ሶስተኛው ሀኪም በሚቀጥለው ቀን ይሄዳል፡፡
ሶስተኛው ሐኪም - ከሁሉም የተለየ ነገር ነው የነገረው፡፡
“ወዳጄ የያዘህ በሽታ ፈፅሞ ጊዜ የሚሰጥ አይደለም፡፡ እንዲያውም ሀያ አራት ሰዓት ለመቆየት መቻልህን እጠራጠራለሁ፡፡ ስለዚህ ምንም አላደርግልህም”
ህመምተኛው አመስግኖ ሄደ፡፡
ሁኔታው ሶስተኛው ሐኪም እንዳለው ሳይሆን ቀረ፡፡ ሰውየው ከቀን ቀን እየተሻለው መጣና በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ካልጋው ተላቆ ቆሞ መሄድ ቻለ፡፡ በእርግጥ ግን ህመሙ ብዙ ስጋውን ስለበላው በአፅሙ የሚሄድ ይመስላል፡፡
አንድ ቀን መንገድ ላይ ሶስተኛውን ሐኪም አገኘው፡፡ ሐኪሙ በጭራሽ ያየውን ማመን አልቻለምና፤
“የወዲያኛውን ዓለም አይተህ ተመልሰህ መጥተህ መሆን አለበት፡፡ ለዚህ ጥርጥር የለኝም፡፡ ከዚህ ቀደም ተለይተውን ወደ ሰማይ ቤት የሄዱት ወዳጆቻችን እንዴት ናቸው ባክህ?”
ህመምተኛውም - “እጅግ በጣም ተመችቷቸው፣ ደልቷቸው ነው የሚኖሩት፡፡ ዘለዓለማዊውን ውሃ ጠጥተውና የዓለም ችግር ሁሉ ረስተው፤ በጣም ተመችቷቸው ይኖራሉ፡፡ በነገራችን ላይ እኔ ከዛ ለቅቄ እየመጣሁ ሳለሁ ምድር ላይ ባሉ ዶክተሮች ላይ ፍርድ ለመስጠት እየተዘጋጁ ነበር፡፡ ያስቀመጡት ምክንያት ህመምተኛ ሰዎች በተፈጥሮአዊ መንገድ እንዳይሞቱ ጥበብ እየተጠቀሙ በህይወት እንዲቆዩ በማድረጋቸው ነው፡፡ አንተንም ከሌሎቹ ጋር እንደሚቀጡህ ሲያስቡ ነበር፡፡ እኔ ግን እሱን ተዉት፤ ምክንያቱም እሱ አባይ ጠንቋይ እንጂ ዶክተር አይደለም አልኳቸው!”
*              *           *
ውሸተኛ ዐባይ ጠንቋዮች እየበዙ፣ ዕውነተኛ ዶክተሮች እየሳሱ ከመጡ አገራችን አደጋ ላይ ናት! ዐባይ መምህራን እየበዙ ዕውነተኛ መምህራን ከተመናመኑ የትምህርት ነገር አዲዮስ! የሚባል ይሆናል! ዐባይ ጠበቆችና ዐባይ ዳኞች ከተበራከቱና ዕውነተኛ ዳኞችና ሀቀኛ ጠበቆች ከጠፉ “O! Justice thy has flown to beasts!!” (ፍትሕ ሆይ! ወደ አራዊት በረርሽን!) እንዳለው ሼክስፒር ይሆናል፡፡ ግልፅነትና ተጠያቂነት ለአፍ አመል ብቻ እየተስፋፉ በተግባር ግን ሁሉ ድብቅ፣ ሁሉ የአዋቂ አጥፊ እየሆነ የሚገኝ ከሆነ፤ የለበጣ ዲሞክራሲ እንጂ ሌላ የለም፤ ሃሳዊ መብት እንጂ ለዕድገት የቆመ ሀቀኛ ሥርዓት አይኖርም፡፡ የካብነው እየተናደ፣ አደግን ያልነው ቁልቁል እየሔደ፤ በየቀኑ በችግር ማጥ ውስጥ መላሸቃችን አሳዛኝ ነው! የግል ት/ቤቶች ዕውቅናና ፈቃድ አስቂኝ  ደረጃ ላይ ደርሷል! የት/ቤቶች ተቋማት ዕድሳት ዘወትር በማስጠንቀቂያና በማስፈራሪያ የሚታለፍ የመስፈራሪቾ (Scare-crow) ሂደት ሆኗል፡፡ ሥርአተ- ትምህርት አደረጃጀቱን ማጥራት እንዳቃተው ከረመ! የግብዓት አቅርቦትና አገልግሎት እንከን አልባ ለመሆን አልታደለም! የዝውውር ፖሊሲ እንደተሽመደመደ ነው፡፡ የመረጃ አያያዝ የተቆጣጣሪ ያለህ! እያሰኘ ነው፡፡ በት/ቤት ተቋማት ውስጥ ‹‹በአጋዥ መፃሕፍት› ሰበብ ያለንግድ ፈቃድ የችብቸባ ሥርዓት መፈጠር ዘግናኝ ዕውነት ነው፡፡ የወላጆች አቤቱታ የምድረ ባዳ ጩኸት ሆኗል (Crying in the Wilderness)፡፡ የዚህ ሁሉ ውጤት የሆነው የፈተና ብቃት አለ ወይ? ብለን ገና መልስ ሳናገኝ፤ የፈተና ስርቆሽ አደጋ አናታችን ላይ ያንዥብባል? ያውም ኢንተርኔት እስከማዘጋት የደረሰ የሌብነት መንግሥታዊ ሥጋት … ይህ ሁሉ ሲታይ እንዴት ሚሥጥራችን በሀገር ደረጃ ይጠበቃል? ብለን ዕምነት እንጣል፡፡ ዕምነት ማጣት ያለመረጋጋት እናት መሆኑን እንርሳ!
ችግሮችን የመፍታት መንገዳችን ወይ መንገድ አደለም፤ ወይ ወልጋዳ መንገድ ነው፡፡ ይህ ማለት ችግርን ለመፍታት ሌላ ችግር መንገድ ነው፡፡ ይህ ማለት ችግርን ለመፍታት ሌላ ችግር መቀፍቀፍ ነው፡፡ ችግር በችግር አይፈታም፡፡ ዘላቂ መፍትሔ በማይሆን መልኩ ጥገናዊ ማስታመሚያዎች ብንደረድር ቁስላችን ማመርቀዙ አይቀሬ ነው፡፡ ውስጣችን መፈተሽ አለበት፡፡ አንዱ ባንዱ ላይ በማላከክ ሳይሆን ዕውነተኛውን በሽታ ፈልቅቆ በማውጣት ነው ህክምናችን የተሳካ የሚሆነው፡፡ አለበለዚያ፤ አንደኛው ሀኪም ቀላል ነው፤ ሁለተኛው ሀኪም በረዥም ጊዜ የሚድን በሽታ ነው፤ ሦስተኛ ሀኪም- ሀያ አራት ሰዓት አትቆይም! አይነት መፍትሔ ይዘን እንደ አፍዎ ያርግልኝ እያልን በጥንቆላ የምንተዳደር ሊመስለን አይገባም፡፡ በሽታችን የሚወሳሰበው ጊዜ ወስደን በጥሞና ስለማንከታተለው ነው፡፡ የበሽታችንን መንስዔ ከስር መሰረቱ ለማወቅ፣ አካሚውም ታካሚውም ግልፅነት ስለሌለን ነው፡፡ በሽታውን የደበቀ መድሀኒት አይገኝለትም የሚለው ዕውነት እንዳለ ሆኖ፤ መድህን አያገኝም የሚለው ታክሎብናል፡፡ የመጨረሻው አሳሳቢ ነገር ደግሞ ትክክለኛውን መረጃ አለማግኘት ነው፡፡ ይህ እክል አንድም ከመረጃ ሰጪ ንፉግነት የሚመነጭ ነው፡፡ አንድም የመረጃ ሥርዓቱ ብቃት ማጣትና ይሆነኝ ተብሎ እንዲጥመለመል ማድረጉ ነው፡፡ አሊያም ጨርሶ ለመረጃ ፋይዳ ጥረት አለመስጠት ነው! ከሁሉም ይሠውረን፡፡ እጅግ አስከፊው ገፅታችን ግን፤ ‹‹ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ›› እንዲሆን ካደረግን ነው፡፡ ሆን ብለን መረጃ ካጣመምን ማለትም መረጃ ተቀባይ ትክክለኛውን መረጃ ሳይሆን የተሳሳተውን ወስዶ ሌሎችን እንሳስት አድርገን፤ እኛም መልሰን እሱን ከሳሽ ከሆንን የመርገምት ሁሉ መርገምት ይሆንብናል! እንዲህ ያለውን ሂደት መዋጋት የግድ ነው፡፡ መረጃ፤ መረጃ የሚሆነው ለሚመለከተው ጉዳይ በአግባቡ ሲውል ነው፡፡ አለበለዚያ፤ ‹‹ከአንበሳና ከዝሆን ማን ያሸንፋል?›› ቢለው፤ ‹‹ከሁሉም ከሁሉም አሳ ሙልጭልጭ ነው!›› የሚለውን ተረት ስናደምቅ መኖራችን ነው!

Read 7732 times