Saturday, 09 July 2016 09:53

የተቃዋሚ አመራሩ አቶ አብርሃ ደስታ ከእስር ተፈቱ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(13 votes)

     በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው በእስር ላይ የነበሩት የአረና ትግራይ ለዲሞክራሲና ሉአላዊነት ፓርቲ አመራር አቶ አብርሃም ደስታ ትናንት ከእስር ተለቀቁ፡፡ አቶ አብርሃ ደስታ ከሁለት አመት በፊት ሐምሌ 1 ቀን 2006 ዓ.ም ከሰማያዊና ከአንድነት ፓርቲ አመራሮቹ አቶ ሃብታሙ አያሌው፣ የሺዋስ አሰፋና ዳንኤል ሺበሺ ጋር በሽብር ተጠርጥረው በእስር ላይ ለሁለት አመት የቆዩ ሲሆን ከቀረበባቸው ክስ በከፍተኛው ፍ/ቤት በነፃ የተሰናበቱ ቢሆንም አቃቤ ህግ ለጠቅላይ ፍ/ቤት ባቀረበው ይግባኝ መሰረት ጉዳያቸው መቋጫ አለማግኘቱ ይታወሳል፡፡
በአቶ አብርሃና ሌሎች የፖለቲካ አመራሮች ላይ የቀረበው የሽብር ክስ፤ በኢትዮጵያ መንግሥት አሸባሪ ተብለው ከተፈረጁ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት በመፍጠርና አባል በመሆን በማንኛውም የሽብር ድርጊት ተሳታፊ መሆን የሚል ሲሆን ጉዳዩን ሲከታተል የነበረው የከፍተኛው ፍ/ቤት 19ኛ ወ/ችሎት፤ መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ እንዲሰናበቱና ከእስር እንዲለቀቁ ማዘዙ ይታወሳል፡፡
ይሁን እንጂ አቶ አብርሃ በነበረባቸው የዲሲፒሊን ቅጣት ምክንያት በእስር ላይ ቆይተው በትናንትናው እለት ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ተለቀዋል፡፡

Read 3945 times