Saturday, 09 July 2016 09:51

በመሃል ከተማ የሚገነቡ ህንፃዎች ከ20 ፎቅ በላይ ይሆናሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(13 votes)

አዲስ አበባ 300 ሽንት ቤቶች ያስፈልጋታል ተባለ
   ለአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ቀርቦ ይፀድቃል ተብሎ የሚጠበቀውና ዝግጅቱ 4 ዓመታትን ፈጅቷል የተባለው የአዲስ አበባ ከተማ መሪ ፕላን በ10 ዓመት ውስጥ በከተማዋ 300 ሽንት ቤቶች እንዲገነቡ፤ ወንዞችን ይበክላሉ የተባሉ ፋብሪካዎች ከመዲናይቱ እንዲወጡ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ በአሁን ወቅት በአዲስ አበባ 1 መፀዳጃ ቤት ለ50 ሺህ ነዋሪዎች እያገለገለ ሲሆን ከ90 በመቶ በላይ በከተማዋ ያሉ ፋብሪካዎች ፍሳሻቸውን ሳያጣሩ ወደ ወንዞች ይለቃሉ ተብሏል፡፡ የከተማዋ ከ70 በመቶ በላይ ፍሳሽ ወደ ወንዝና መንገዶች እንደሚለቀቁ የጠቆመው የፕላኑ ጥናት፤ አብዛኞቹ መንገዶችም ወደ ውሃ መውረጃነት ተቀይረዋል ተብሏል፡፡
በአሁን ወቅት 17 የህዝብ ሽንት ቤቶች በመዲናዋ ቢኖሩም የተሟላ ዘመናዊ አገልግሎት አልሰጡም ያለው መሪ ፕላኑ በ10 ዓመት ጊዜ ውስጥ ቁጥሩ አሁን ካለበት 3.3 ሚሊዮን ወደ 5 ሚሊዮን ከፍ ለሚለው የመዲናዋ ነዋሪ 300 ሽንት ቤቶች በዋና ዋና የህዝብ መተላፊያዎች መገንባት እንዳለባቸው ያመላክታል፡፡ የሚገነቡት ሽንት ቤቶች ባለሁለት ፎቅ ህንፃ ሲሆኑ በሁለተኛው ወለል ላይ ሬስቶራንት ይኖራቸዋል ይላል - መሪ ፕላኑ፡፡
ለአረንጓዴ ቦታና ለመንገዶች ይበልጥ ትኩረት የሚሰጠው መሪ ፕላኑ፤ የመዲናዋ 30 በመቶ ቦታ በአረንጓዴ አካባቢ እንዲሸፈን እንዲሁም 30 በመቶ ደግሞ ለመንገድ ግንባታ፣ 40 በመቶ ብቻ  ለህንፃዎች ግንባታ እንዲውል ይጠቁማል፡፡
በአሁን ወቅት አማካይ የአረንጓዴ ቦታ ሽፋኑ 0.3 ካሬ ሜትር ሲሆን ፕላኑ ተግባራዊ የሚደረግ ከሆነ በአማካይ ወደ 9 ካሬ ሜትር ከፍ ይላል፡፡
አንዱ የመዲናዋ ችግር ሆኖ የተጠቀሰው የመዝናኛና የፓርክ እጥረት ሲሆን ይህን ችግር ለመቅረፍ በፕላኑ አሁን ያለው ግዮን ሆቴል ከፍል ውሃ ጋር ተያይዞ ሙሉ ለሙሉ ወደ ፓርክነት እንዲቀየር አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
ተመሳሳይ 10 የፓርክ ማዕከላት በከተማዋ እንደሚኖሩ የሚጠቅሰው መሪ ፕላኑ፤ ከብሄራዊ ቲያትር በኢትዮ-ኩባ ወዳጅነት አደባባይ እስከ ቸርችል ጎዳና ያለው አካባቢ ከተሽከርካሪ ነፃ የሆነ የህዝብ መዝናኛ ማዕከል ይሆናል ይላል፡፡
አሁን ያለው ኢዩቤልዩ ቤተ መንግስትና አምባሳደር አካባቢ የሚገኘው መከላከያ ሚኒስቴር ወደ ሙዚየምነት ይቀየራሉ፡፡
ከተማዋ ያላትን 54 ሺህ ሄክታር መሬት ተጠቅማ በመጨረሷ ከእንግዲህ ወደ ጎን የማስፋፊያ ቦታ እንደሌላት ያመለከተው መሪ ፕላኑ፣ እድገቷም ወደ ጎን ሳይሆን ወደላይ ይሆናል ይላል፡፡
አብዛኛው ህንፃም በመልሶ ማልማት የሚገነባ ሲሆን ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚገነቡ ህንፃዎች በላያቸው ላይ የመኖሪያ ቤቶች እንዲኖሩ መሪ ፕላኑ ያስገድደዋል፡፡ በመሃል ከተማዋ የሚገነቡ ህንፃዎች ከ20 ፎቅ በላይ መሆን ያለባቸው ሲሆን አብዛኞቹ ህንፃዎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሚኖሩባቸው ይሆናሉ፡፡ የሚገነቡ ህንፃዎች የደህንነት ካሜራዎችና አደጋ መከላከያ ዘዴዎች እንዲኖራቸውም በመሪ ፕላኑ ተመልክቷል፡፡ አዲስ አበባን ያዘምናል ለተባለው ለዚህ መሪፕላን ማስፈፀሚያ 290 ቢሊዮን ብር ይበቃል የተባለ ሲሆን ፕላኑን እየተከታተለ የሚያስፈፅም “የፕላን ኮሚሽን” ይቋቋማል ተብሏል፡፡ አዲስ አበባ እንዲህ ያለው ፕላን ሲዘጋጅላት የአሁኑ 10ኛው ነው፡፡   

Read 6761 times