Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 25 February 2012 14:49

የስብሃት ገብረ እግዚአብሔር የሕይወት ታሪክ

Written by 
Rate this item
(17 votes)


ኢትዮጵያ አንድ ትልቅ ሰው ጠፋባት፤ በስራዎቹ ውስጥ አፀደ መንፈሱ ይኖራልና እንጽናናለን፡፡

ስብሃትን በማድነቅ የሚከተሉት ሁሉ በሱ እጅ ጽሑፍ የሚከተበውን ስብሃትለአብ የሚለውን ስሙን አንብበዋል፡፡ ገና በልጅነቱ አዲስ አበባ ሲመጣ ስሙን ቢያሳጥረውም አባቱ መምሬ ገብረእግዚአብሔር ገብረዮሐንስ እና እናቱ ወይዘሮ መዓዛ ተወልደመድህን ያወጡለት ስም ስብሃትለአብ ገብረእግዚአብሔር የሚል ነው፡፡ ስብሃት ለአብ “ወለላይ” የሚላቸው እናቱ እና አባቱ አቦይ ገብረእግዚአብሔር ከበፊት ትዳሮቻቸው ያፈሯቸውን ጨምሮ በአጠቃላይ 13 ልጆች ወልደዋል፡፡

በወለላይ እና አቦይ እማወራነትና አባወራነት በአንድ ጐጆ ይኖሩ የነበሩት ልጆቻቸው ግን ስብሃትለአብን ጨምሮ አምስት ነበሩ፡፡ ቤተሰብ ከጐረቤት እሳት እየተጫጫረ እቃ እየተዋዋሰ ይኖርባት የነበረችው መንደር በወቅቱ አጠራር ትግሪይ ጠቅላይ ግዛት አድዋ አውራጃ የምትገኘው ሩባገረድ ነች፡፡ ስብሐት ስለ ትውልዱ ሲናገር:- አረንጓዴውን መስክ፣ ሸንተረሩን የባላገሩን ጐጆ በምናባችሁ ሳሉት፡፡ የአዕዋፍን ዝማሬ፣ የከብቶቹን ጩኸት፣ ከመሬት ጋር ያለመታከት የሚታገለውን አርሶአደር ሕይወት በልቦናችሁ አብሰልስሉት፡፡ በዚህ ባላገር ውስጥ ሚያዝያ 27 ቀን 1928 ነው የተወለድኩት” ብሎ ነበር፡፡ የስብሃት የደራሲነት ስንቅ መቋጠር የያዘው ከዚህ ከሩባገረድ የቤተሰቡ ሕይወት አንስቶ ነው፡፡

ስብሃትለአብ ገብረእግዚብሔር የሥራ ልምድ ሲፃፍ ከ1935 -1939 የነበረው የእረኝነት ዘመኑ ቢቀድምም በእናቱ በወለላይ መዓዛ ተወልደመድህን አሳሳቢነት የአድዋን የገጠር ሕይወት ተሰናብቶ ገና በልጅነቱ ወደ አዲስ አበባ መጥቶ ዘመድ ጋ ማደግ የጀመረባቸውንና በዘመናዊ ትምህርት እየተቀረፀ ያለፈባቸው ጊዜያት ብዙ ላበረከተባቸውና ለታወቀባቸው ሙያዎቹ በቂ ሆነውታል፡፡ ስብሃት ሽሮሜዳ አካባቢ ይገኝ ወደነበረው የስዊዲሽ ሚሽን ትምህርት ቤት ነበር መጀመሪያ የተላከው፡፡

በኋላም አሳዳጊውን የጋሽ ሃጐስን የኢትዮጵያ መንግስት አማካሪ ሆኖ ወደ ግሪክ ሀገር መሄድን ተከትሎ በጃንሆይ ፈቃድ ትምህርቱን በተፈሪ መኮንን ከ1940-1948 ተከታትሏል፡፡ “ከልጅነቴ አኳያ አዲስ አበባ ውቅያኖስ ሆነችብኝ፣ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ደግሞ ባህር ሆነ፣ ትንሽዬ ኢትዮጵያን ፈጠረ፡፡” በማለት ይናገር የነበረው ስብሃት ገብረእግዚአብሔር፤ የመኖርያ አድማሱ በሰፋ ቁጥር ከብዙ ኢትዮጵያውያንና ከሌላ ዓለም ዜጐችና ሀገራት ጋር የአስተሳሰብ አድማሱም እየሰፋ መጣ፡፡ ስብሃት ከ1946 -1947 ድረስ በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት The TMS የተሰኘ መጽሔት በማዘጋጀት የጽሑፍ ሥራውን መስመር ጀምሮ ነበር፡፡

ስብሃት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ከ1948-1952 ዓ.ም በተከታተለው የትምህርት ሙያ (Education) የመጀመሪያ ዲግሪውን ተቀብሏል፡፡ በነዚያ የኮሌጅ ቀናቱ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ትያትር ቤት በተካሄደው የክርክር መድረክ ላይ ትምህርት ክፍሉን ወክሎ ያቀረበው የመከራከርያ ሃሳብ ንጉሱን አስደምሞ በትምህርት ምክትል ሚኒስትሩ በከበደ ሚካኤል አቅራቢነት በቤተመንግስት ተገኝቶ የወርቅ ሰዓት እንዲሸለም አብቅቶታል፡፡

በ1953 ዓ.ም ለተጨማሪ ትምህርት ወደ አሜሪካ ዌስተርን ሚቺጋን ዩኒቨርሲቲ አቅንቶ የላይብረሪ ሳይንስ ትምህርቱንም መከታተል ጀምሮ ነበር፡፡ ነገር ግን በዋናነት የሚሰጠው ትምህርት የሀገሬውን ዜጐች እንጂ ስብሃትንና ኢትዮጵያን የሚጠቅም ሆኖ ሊያገኘው ስላልቻለ ሀገሬን የምጠቅምበትን እውቀት ስጡኝ አሊያም ወደ መጣሁበት እመለሳለሁ ብሎ የጠየቀው ባለመፈፀሙ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ መጥቷል፡፡ በ1956 ዓ.ም የፍልስፍና መምህሩ የነበሩት ፕሮፌሰር ክላውድ ረዳት ሆኖ ያገለግል ዘንድ ወደ ፈረንሳይ ሀገር ዩኒቨርስቲ ማርሴ የተላከ ሲሆን እሱም በተማረበት መስክ በቂ እውቀት እንደጨበጠ፣ የትምህርቱን ፍሬና በኋላም በሕትመት ያገኘነውን “ሰባተኛው መልአክ” የተሰኘውን ልቦለድን ወደ ሀገሩ ይዞ ተመልሷል፡፡ አሻራውን ያተመባቸው ሙያዎች እንደሚመሰክሩት ስብሃት ገብረእግዚብሔር የመጀመሪያ ሥራውን ካዛንቺስ አካባቢ በሚገኘው አስፋወሰን

ትምህርት ቤት በእንግሊዝኛ መምህርነት ነበር የጀመረው፡፡  እዚያም ለሦስት ዓመታት አገልግሏል፤ ከ1953-1956 ዓ.ም ስብሃት ገብረእግዚብሔር በአሰፋወሰን ትምህርት ቤት ከርእሰመምህሩ እስከ መምህራን እና ተማሪዎቹ በሁሉም የተከበረ፣ ለለውጥ ይሰራ የነበረ፣ መምህርነትን የሚያከብር ባለሙያ ነበር፡፡” የመምህርነት ሙያ ሽኩቻ፣ ጥድፊያ ከማወቅና ካለማወቅ ጋር ነው፣ የምትመቀኘው ሌላን ሳይሆን ድንቁርናን ነው፣ የሚያስደስትህ ደግሞ የዘራኸው አድጐ ሲያፈራ ማየትህ ነው፡፡” ይል ነበር መምህሩ ስብሃት፡፡

ከ1958-1960 ዓ.ም በትምህርት ሚኒስቴር ስኮላርሺፕ ክፍልና የሕዝብ ግንኙነት ባልደረባ ሆኖ ያገለገለ ሲሆን በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታትም የኢትዮጵያ ጀግኖች ማህበር የእንግሊዝኛው መጽሔት አዘጋጅ ነበር፡፡ ከ1962 -1967 ዓ.ም የሕዝብ ግንኙነትና አማካሪ እና ሥራ አስኪያጅ ሆኖ ከመምራቱ ባሻገር በተጓዳኝ ከ1965-1966 የመነን መጽሔት ሥራ አስኪያጅ በመሆን አገልግሏል፡፡

በአንድ አይነት ሙያ ውስጥ በሕይወትህ እንዴት ገብተህ እንደምትሳተፍ አታውቀውም የሚለው ደራሲ እና ጋዜጠኛ ስብሃት ገብረእግዚአብሔር፤ ስለ ጋዜጠኝነት ሕይወቱ አጀማመር በአንድ ወቅት ሲናገር እንዲህ ብሎ ነበር፡፡ “እኔ በአንድ ወቅት በትምህርት ሚኒስቴር ስኮላርሺፕ ክፍል እየሰራሁ እያለ አንዱን ቀን በአሉ ግርማ እዚህ ዝም ብለህ ከቢሮክራሲ ጋር ጊዜህን አታባክን፡፡ አሁን በስኮላርሺፕ በሚሰራው ሥራ ሀገሪቱ ውስጥ በርካታ ሰዎች አሏት፡፡ ላንተ ተፈጥሮ የእኛ ሙያ ነው የሚስማማህ” ሲለኝ “እሺ እውነትህን ነው አልኩና መልቀቂያ እንዲሰጠኝ ላለሁበት የትምህርት ሚኒስቴር ማመልከቻ ፃፍኩ፡፡ ከበአሉ ጋር በማስታወቂያ ሚኒስቴር ሥር ሥራ ጀመርኩ፡፡” በማለት ይናገር እንጂ ከ1965 ዓ.ም በፊትም ከ1946-1947 “የተፈሪ መኮንን አላማ” የተባውን መፅሔት ላይ በአዘጋጅነት፣ በ1960-1962 የኢትዮጵያ ጀግኖች ማህበር የእንግሊዝኛውን መፅሔት በአዘጋጅነት፣ በተጨማሪም ጥቂት ለማይባሉ ዓመታት የካቲት መፅሔት መስራቱን የሕይወት ድርሳኑ ያመለክታል፡፡ በዚህ አጭር በሚመስለው የጋዜጠኝነት ቆይታው ቀላል ከማይባሉ ሙያው ከሚያማዝዛቸው መዘዞች ጋር ተጋፍጦ በእድል ሊተርፍ የቻለም ጋዜጠኛ ነበር፡፡

በጥበብ ሙያው ያለፈባቸውን ውጣ ውረዶች በገዛ ቃሉ ሲናገር “አንድ ቀን ቁራጭ ወረቀት ከሳንሱር ፅህፈት ቤት አካባቢ ተፃፈ፡፡ በዚያን ጊዜ የምፅፈው በአጋፋሪ እንደሻው ላይ ነው፡፡ የደረሰኝ ማስጠንቀቂያ የወዛደሩን ልዕልና የሚያሳይ ካልሆነ ቀልድ ክልክል ነው

ይላል፡፡ አጋፋሪ እንደሻው ደግሞ ወዛደር አይደሉ”… ብሏል፡፡ በዚህም የተነሳ ሥራውን ለቀቀ፡፡ አብረውት ይሰሩት ከነበሩት የሥራ ባልደረቦቹ አብዛኞቹ በወቅቱ የተገደሉ ሲሆን እሱ ግን ተረፈ፡፡ …ደራሲና ጋዜጠኛ ስብሃት ገብረእግዚአብሔር ልዩ የብዕር ዘርን ከዘራባቸው የጋዜጣና የመፅሔት ማሳያዎች መካከል “መነን” መፅሔት፣ “አዲስ ዘመን” ጋዜጣ፣ “አዲስ አድማስ” ጋዜጣ፣ “የዛሬይቱ ኢትዮጵያ”፣ “እፎይታ” መፅሔት፣ “ለዛ” መፅሔት፣ “ሪፖርተር” ጋዜጣና ሌሎችም ለቁጥር የሚያታክቱ አያሌ የፅነፅሑፍ ውጤቶች ያቀረበባቸው ይገኛሉ፡፡

ደራሲ ስብሃት ገብረእግዚአብሔር፣ ከበርካታ የፈጠራ ስራዎቹ በመፃሕፍ ከታተሙለት መካከል “አምስት ስድስት ሰባት” እና ከሌሎች አስር አጭር ልቦለዶች ጋር በ1981፣ “ትኩሳት” ረዥም ልቦለድ በ1990፣ “ሌቱም አይነጋልኝ” ረዥም ልቦለድ በ1992፣ “ሰባተኛው መላክ” ረዥም ልቦለድ በ1992 “እግረ መንገድ” ቁጥር ፩ ከ1985 እስከ 1990 በጋዜጣ ከተፃፉ ሥራዎች የተሰበሰበ፣ “እግረ መንገድ” ቁጥር ፪ ከ1985 እስከ 1990 በጋዜጣ ከተፃፉ ሥራዎች የተቀነጨበ፣ “እነሆ ጀግና” በ1997 እና “የፍቅር ሻማዎች” ሲሆኑ “ዛዚ” የትርጉም ሥራ ነው፡፡ ከስብሃት የድርሰት ሥራዎች ውስጥ “ሌቱም አይነጋልኝ” ወደ ፈረንሳይኛ ተተርጉሞ ለፈረንሳይኛ አንባቢዎች ሊቀርብ ችሏል፡፡

ስብሃት ገብረእግዚአብሔር በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ የካቲት 11 ለየካቲት 12 ቀን 2004 አጥቢያ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡ ስብሃት ለአብ ገብረእግዚአብሔር የሦስት ሴቶች የሁለት ወንዶች ልጆች አባትና የአምስት የልጅ ልጆች አያት መሆን መቻሉ የሥጋም የመንፈስም ፍሬዎችን መታደሉን ያሳያል፡፡ ስብሃት ለአብ ገብረእግዚአብሔር በልቦለድ እንደፃፋቸው አጋፋሪ እንደሻው ሞትን መፍራት እንዳለበት ቢናገርም ባለፉት ቀናት ግን ሞት ወደሱ መቅረቡን አውቆ ፈረስ አስጭኖ በሽሽት ሀገር ሳይለውጥ በጀግንነት ሞትን ግባ በሉት ብሎ ወደ ወዲያኛው ዓለም ሄዷል፡፡ ስብሃት የሌሎች ሞት አያገባኝም የማይል፣ በሰው ቁስል የሚታመም፣ በሰው ሃዘን የሚያለቅስ፣ በሰው ሞት የሚሞት ታላቅ መምህር፣ ጋዜጠኛ ደራሲና አርታዒ ነበር፡፡ በሕይወት እያለ ከሚወዳቸው ግጥሞች መካከል ይህ የጆን ዶን ሥራ ይገኝበታል፡፡

ማንም ሰው ከሴት አይደለም

የማንም ሰው ሞት እኔን ያጐድለኛል

የቀብር ደወል የሚደወለው ለማነው

ብለህ አትጠይቀኝ

የሚደወለው ላንተ ነው!

ለስብሃት ገብረእግዚአብሔር ቤተሰቦች፣ ወዳጆችና አድናቂዎች መፅናናትን እንመኛለን፡፡

(በቀብር ሥነ ስርዓቱ ላይ በአርቲስት ተፈሪ አለሙ የተነበበው የስብሃት ገ/እግዚአብሔር የህይወት ታሪክ)

===========================================

ወስብሃት ለፍጥረቱ

የፍጻሜው ዳር ድንበሩ

የአዙሪት ሽክርክሩ

ቆም አለና ለዘንድሮ

ጥይት ወጣ ተስፈንጥሮ

ክብ ቀለበት ህይወት አምሳል

የገጠመ መስመር ጥቅልል

ቀጣይ መስሎ ሩቅ ዑደቱ

ድንበሩን ጣሰ ጥይቱ

በስመአብ ብሎ ሩቅ ጀምሮ

ምስጢረ አለም ካብ በርብሮ

የአለም የሥጋ ዕቃ ዕቃ

ሳይገባው ኖሮ ሙዚቃ

ለራሱ አዳልቶ ቆርሶ

ሺዎች መግቦ አጉርሶ

ለራሱ ምሎ አስምሮ

ታሪኩን ስሎ አሳምሮ

ረስተን ሰንብተን ሞቱን

ድንገት አጠፋ መብራቱን

የዘመን ነጥብ ጥይቱ

የቃላት ፈርጡ ተረቱ

የስሜት ፍሙ ግለቱ

ዕድሜ ያልተፈታ አዛውንቱ

የታሪክ የመዝገብ ቤቱ

ፈረሰ ብዬ የማወራው

አይታመንም እውነቱ

በስመአብ ብሎ ጀምሮ

ሳንጠግብ ስብሀት ዘምሮ

ለምን ፈጠነ ፍታቱ

ራቀ ለምድር ጥይቱ?

 

ከኢሳያስ ከበደ

የካቲት 12 ቀን 2004 ዓ.ም

ለጋሽ ስብሃት እረፍት መታሰቢያ

 

 

Read 30609 times Last modified on Saturday, 25 February 2012 15:29