Saturday, 28 May 2016 09:19

ዎዶሮ ሚዙ ባቁልያ ቢን ቢፃለ ሚዛራ ያደስ (ገመድ የምትበላው በቅሎዬ ብትሔድ፤ ልጓም (ብረት) የምትበላዋ መጣች) የጋሞች ተረትና ምሳሌ

Written by 
Rate this item
(30 votes)

አንድ ተኩላ አንዲት የበግ ግልገል፣ ከዕለታት አንድ ቀን አግኝቶ በጣም አስጐመዠችው፡፡ እንዲሁ
እንይበላት ምክንያት ያስፈልጋል ብሎ አሰበ፡፡ ስለዚህ አንዳንድ ጥያቄና ወቀሳ መሰንዘር ጀመረ፡፡
“አንቺ’ኮ ባለፈው ዓመት ሰድበሽኛል፤ ታስታውሻለሽ?”
ግልገሊትም፤
“ኧረ በጭራሽ ጌታ ተኩላ፤ እኔ አምና አልተወለድኩም”
ጌታ ተኩላ፤
“አንቺ ቀጣፊ! እንዲያውም በኔ መስክ ላይ እየተዘዋወርሽ ትግጪ ነበረ፡፡”
ግልገሊት፤
“ኧረ እኔ ገና ሣር ለመብላት ያልደረስኩኝ ጨቅላ ነኝ፡፡ ጥርሴም አልጠነከረም’ኮ!”
ጌታ ተኩላ፤ ድምፁ እየሻከረና ቁጣ ቁጣ እያለው መጣ፡-
“እንግዲያው ውነቱን ልንገርሽ፣ አዲስ ከፈለቀው ኩሬዬ ውሃ ስትጠጪ ታይተሻል፡፡ ጥግብ ብለሽም
በአካባቢው ፈንጭተሻል!”
ግልገሊትም፤
“ጌታ ተኩላ፤ እኔ ፈፅሞ ውሃ ጠጥቼ አላውቅም፡፡ ገና የእናቴን ጡት ጠጥቼ ያልጠገብኩ አንድ ፍሬ
ግልገል ነኝ!”
ጌታ ተኩላም፤
“ልታጭበረብሪኝ አትሞክሪ! እኔ ደጋ ወጥቼ፣ ቆላ ወርጄ ያጠራቀምኩትን ሥጋ በልተሽብኛል!”
ግልገል፤
“ጌታ ተኩላ! እንዴት መግባባት እንዳቃተን አልገባኝም፡፡ እኔ’ኮ በግ ነኝ፡፡ በግ ሥጋ አይበላም፡፡
ደሞም ከአንተ መኖሪያ ዋሻ ገብቼም አላውቅም፡፡ በቅጡ ተረዳኝ እንጂ እንግባባ”
ጌታ ተኩላም በጣም ተቆጥቶ፤
ያ “ለመግባባታችን ዋና ምክንያትማ የእኔ ረሀብ ነው”
ግልገልም፤
“እኛ ውይይት ውስጥ ያንተን ረሃብ ምን አገባው?” ስትል በጥሞና ጠየቀችው፡፡
ጌታ ተኩላ፤
“አየሽ፣ ያንቺ ችግር ይሄ ነው፡፡ አርቀሽ አታስተውይም፡፡ እኔ ተኩላ፤ ሰማይ ዝቅ መሬት ከፍ ቢል
እራቴን ሳልበላ ማደር የለብኝም!”
ግልገሊትም፤
“እሱ ልክ ነው፡፡ ግን ዕቅድህን ሳታሳውቅ (ፕሮፖዛል ሳታቀርብ)…” ብላ ሃሳቧን ተናግራ
ሳትጨርስ፣ ጌታ ተኩላ እንደ ጉድ ተስፈንጥሮ ግልገሊት ላይ ሰፈረባት፡፡
አንዲትም አጥንት ሳትቀረው ቆረጣጥሞ እራቱን በላ!
(እነሆ ግልገሊት፤ “ሳታመሃኝ ብላኝ” የተሰኘውን ምርጥ የአማርኛ ተረት ባለማወቋ፣ ጉዳዬን
አስረዳለሁ ብላ ስትዳክር ተበላችና አረፈችው!”)
    ***
ችግርን በአግባቡ በውይይት መፍታት የሠለጠነ መንገድ ነው፡፡ ሆኖም ይህ ሊሆን የሚችለው ሁለቱም ተወያይ ወገኖች ከጀርባ የተደበቀ ዓላማ (አጀንዳ) የሌላቸው እንደሆነ ነው፡፡ በአብዛኛው የአገራችን ሰው፣ ቡድን ወይም ፓርቲ የተደበቀ አጀንዳ በሆዱ ይዞ በመወያየቱ ምክንያት ውይይቶች ችግርን የመፍታት አቅም የላቸውም፡፡ ተወያዮቹ የመቀራረቢያ ምክንያት ፍለጋ ሳይሆን የመበላላት ሰበብ ፍለጋ ነው የሚሄዱት፡፡ If you are in the business of duck – hunting, you go where the ducks are. (God
is back: Exporting America’s God ከሚለው መጽሐፍ) ይላሉ ፈረንጆቹ፡፡ ወደምታድነው
እንስሳ ሂድ ነው ነገሩ፡፡ ዳክዬ አዳኝ ከሆንክ ዳክዬ ወዳለበት ሂድ እንደማለት ነው፡፡
ለጉዳይህ መፍትሔ የምታገኘው ጉዳይህ ወዳለበት በመሄድ ነው ማለትም ነው፡፡ አደን ሄደህ
ውይይት ምን ይፈይዳል? ማለትም ነው፡፡
ለየጉዳዩ ሰበብ ከጀርባ እየቋጠረች አገራችን ዛሬ እደረሰችበት ደርሳለች፡፡ በንጉሡ ዘመን፤ በደርግ
ዘመንና አሁንም መጠኑ ይለያይ እንጂ፤ ወይ በእጅ አዙር መነጋገር፣ ወይ በድብቅ አጀንዳ መተጋተግ አሊያም ተቀናቃኝን ጥርስ ውስጥ ማስገባት፤ ከልማድም አልፎ ባህል የማድረግን ሁኔታ ለዓመታት ስንታዘብ ኖረናል፡፡ ትዕግሥቱን ሰጥቶንና “ተመስገን ይሄንንም አታሳጣን!” እያልን እዚህ ደርሰናል፡፡
“ተመስገን ይለዋል፣ ሰው ባያሌው ታሞ
ካማረሩትማ ይጨምራል ደሞ!”
ይሏል ይሄው ነው፡፡ በበገናና ዘለሰኛ ሲሆን ይበልጥ በለሆሣሥ ይሰማል፡፡ ተመስገን ከማለት አልፈን፣ አዕምሮአችንን አንቅተን፣ ችግሮቻችንን አይተን፣ መፍትሔዎቻችንን ሸተን፣ አገራችንን አገር ለማድረግ አንዱ ቁልፍ ነገር በለውጥ ማመን ነው፡፡ ግትር አለመሆን ነው፡፡ እኔ ያልኩት ብቻ ነው ከሚል የአስተሳሰብ ጋግርት መላቀቅ ነው፡፡ ስለሠራነው ሥራ አለመኮፈስ ነው፡፡ ስለቀረንና፤ ድክመታችን ነው ወደምንለው፤ መሄድ ነው፡፡ እንደ አጭበርባሪ ነጋዴ “ባመጣሁበት ውሰደው” ማለትን መተው ነው፡፡ ስንጥቅ ማትረፋችን የታወቀ ነውና እንዳያስተዛዝበን ነው፡፡ ዛሬ የሃያ አምስት ዓመት ጉዟችንን ስናወሳ ለመሞጋገስ ብቻ መዘጋጀት የለብንም፡፡ ገጣሚ ፀጋዬ ገብረመድህን እንደሚለው፤
“ጅላጅል ምላስ ብቻ ናት፣
ማሞካሸት የማይደክማት
ቀን አዝላ ማታ እምታወርድ
ንፉግን ልመና እምትሰድ”
ከውዳሴው ባሻገር ራሳችንን መጠየቅ ያሻል፡፡ አንድ ፀሐፊ እንዳለው፤ “እስከዛሬ የሆነው ሁሉ ለዚህ
ቀን ዝግጅት ነበር፡፡ ይሄኛው ቀን ደግሞ ለነገው መዘጋጃ ነው” (all that has gone before was
a preparation to this day, and this, only a preparation to what is to come)
ዲሞክራሲ የት ደረሰ? የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ጠበበ ወይስ ሰፋ? የኢኮኖሚ ዕድገታችን ምን ውጤት አመጣ? ብዙዎች እየማቀቁ ጥቂቶች እየመጠቁ ያሉበት የሃብት ክፍፍል ነገ የት ያደርሰናል? የሕግ የበላይነት ዕውን ሆኗል? የሲቪክ ማህበረሰቦች ሚናቸውን እንዲወጡ ተገቢው ሁኔታ ተመቻችቶላቸዋልን? ከግንባር ወደ ፓርቲነትን የመቀየር ምኞታችን የት ደረሰ? ወደ ብሔራዊ መግባባት ለመድረስ ምን ያህል በቀናነት እየተጓዝን ነው? በዋናነነት ደግሞ ሙስናን የሙጥኝ ያለውን ሥርዓት እንዴት ልንገላገለው ነው? ከአመራር እስከ ምንዝር የተዘፈቀበት የሙስና አረንቋ፤ ዛሬ ሀ ብሎ እንቅፋቶቹን ማስወገድ የጀመረ ይመስላል፡፡ ዘግይቷል፡፡ ይሁን፡፡ ግን ገና ብዙ ይቀረዋል፡፡ በሥልጣን የባለጉትን አውርደን፤ ጨዋዎችን መተካት ነገ የሚጠብቀን ከባድ ተግባር ነው፡፡ የተመቻቸ የመቦጥቦጫ ክፍተት ዛሬም ሰፍቶ ተንሰራፍቶ እያለ፤ አዳዲስ ሹማምንት ብናስቀምጥ እዚያው ማጥ ውስጥ አዳዲስ ጥርስ እንደ መትከል ነው፡፡ ጓዳ ጐድጓዳው ተፈትሾ፣ ቀዳዳው ሁሉ መደፈን አለበት፡፡ አለበለዚያ ጋሞዎች እንደሚሉት፤ “ገመድ የምትበላው በቅሎዬ ብትሄድ፣ ልጓም (ብረት) የምትበላዋ መጣች” ይሆንና ለከፋ ብዝበዛ እንጋለጣለን!



Read 8460 times