Saturday, 25 February 2012 14:44

ለስብሃት ስብሃት ይገባዋል

Written by  ተስፋዬ ገሠሠ
Rate this item
(0 votes)

ጓደኝነታችሁ እንዴት ተጀመረ?

ከስብሃት ጋር ጓደኝነታችን የጀመረው ሁለታችንም ገና ልጆች ሳለን ነበር፡፡ አሜሪካን አገር እኔ በምማርበት ጊዜ ድንገት አንድ ቀን ነው ቤቴ ዲብ ያለው፡፡ ውቂያኖስ አቋርጦ ጓደኛ ፍለጋ መምጣትና ካንተ ጋር ልቀመጥ ማለት መቼም ትንሽ ነገር አይደለም፡፡ ይህንን እኔ ትልቅ ዋጋ የምሰጠው ጉዳይ ነው፡፡

ስብሃት እንደ ጓደኛ እንዴት ዓይነት ሰው ነበር?

ጥሩ ሰው መሆኑን ነው የማውቀው፡፡ ከጓደኛ ውዳሴ ቢቀርብ ተገቢ ባይሆንም ስብሃት ጥሩ ሰው ነበር፡፡ አብረን እንዞራለን፡፡ አራዳ ለአራዳ እየዞርን ትንንሽ መጠጥ ቤቶች ሁሉ እየገባን ጠላ፣ ቁንዲፍቱ፣ ጅን ሁሉ እንጠጣለን፡፡ እኔ ጫት አልበላም፡፡ በዚህች እንለያይ እንደሁ እንጂ በሌላው ነገር ሁሉ አብረን ነበርን፡፡ ማንኛውም ወጣት የሚፈነድቀውን ዓይነት ፍንደቃ አብረን ፈንድቀናል፡፡ ስብሃት ለጓደኝነት የሚመች ሰው ነበር፡፡

እንደስነፅሁፍ ምሁርነትዎ ስብሃት በኢትዮጵያ ሥነጽሑፍ ውስጥ ያለውን ቦታ እንዴት ይገልፁታል?

በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ስብሃትን እንደ አንድ ደራሲ በህይወት ዘመኑ በሥነጽሑፍ ውስጥ እዚህ ቦታ ነው የሚገኘው ብሎ መወሰን በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ስብሃት እንደአጋጣሚ ዕድሜው ከገፋ በኋላ ነው ህትመት ላይ የወጣው፡፡ ግን ወዲያው ዕውቅናን ለማግኘት የቻለ ሰው ነው፡፡ አዲስ ፈር ቀዳዱ ከሚባሉ ሰዎች መሃልም ይጠቀሳል፡፡ “Naturalism” የሚባለውን የአፃፃፍ ስልት ያቀረበ ደራሲ ነው፡፡ ስብሃትን ያነበበ ሰው ሁሉ እሱ ማን እንደሆነ ይገነዘበዋል፡፡

የ”Naturalism” አፃፃፍ ስልቱ ወይንም ተፈጥሮን እንደወረደ የመፃፍ ስታይሉ የስብሃት ስራዎች በህብረተሰቡ ውስጥ በይፋ እንዳይነገሩ ወይንም እንዳይወሩ አድርጓቸዋል ብለው ያምናሉ?

ዘመን ነው ይህንን የሚወስነው፡፡ አሁን እኛ የማናየውን እፀፅ የወደፊቱ ትውልድ ሊያየው ይችላል፡፡ እኛ አብይ ነው ብለን የምንገምተውንና ቦታ የምንሰጠውን ጉዳይ ደግሞ ዞር ብሎም ላያየው ይችላል፡፡ ስለዚህ ጊዜ ይሰጠው ነው የምለው፡፡ ስብሃት በዚህ የአፃፃፍ ስታይሉ የሠራቸው ሥራዎቹ አሁን ያላቸውን ደረጃ ይዘው ለቀጣዮቹ አስርት ዓመታት ከቆዩ እንደተባለው በኢትዮጵያ የሥነ ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ አንጋፋ ቦታ ይዞ ይቆያል፡፡ ያለበለዚያ ግን ሊወድቅም ይችላል፡፡ ከእሱ የበለጡ አሁንም ደግሞ ያሉ ያልታወቁ ፀሐፍት የሚያንፀባርቁበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ እንግዲህ የእሱ የአፃፃፍ ስታይል ተፈጥሮን እንደወረደ መፃፍ መሆኑ ምናልባትም ያልሽውን አይነት ችግር አስከትለው ይሆናል፡፡

ስብሃት ለበርካታ ወጣቶች አርአያ ሆኗል፡፡ ብዙ ወጣት ፀሐፍት መነሻቸው አድርገውታል፡፡ ይህ ጉዳይ ከምን የተነሳ ይመስሎዎታል?

ስብሃት በሥነጽሑፍ ዘርፍ ተስፋ ያላቸውን ሰዎች ማበረታታት ባህርይው ነው፡፡ ለዚህም ነው ብዙ ደቀ መዛሙርቶች ያሉት፡፡ ይህ ሁኔታ የስብሃት ጓደኞች ማህበር የሚል እስከመቋቋም አድርሷል፡፡ ይህንን ያደረገ ሌላ ደራሲ የለም፡፡ አንዳንድ ሰው ደራሲ ብቻውን መሆን አለበት ብሎ ያምናል፡፡ ከራሱ ጋር ብቻ የሚቀመጥ አለ፡፡ ሌላው ደግሞ እንደስብሃት፡፡ ስብሃት እንደኔ ፎርማል በሆነ መንገድ በክፍል ውስጥ አይደለም ዕውቀቱን ሲያካፍል የኖረው፡፡ በቤቱና በልዩ ልዩ ማህበራዊ ግንኙነቶች ላይ በመገኘት ነው፡፡ በዚህ ምክንያት በወጣቱ በኩል ከፍተኛ ተወዳጅነትን አትርፏል፡፡

ስብሃትን በአጭሩ እንዴት ይገልፁታል?

በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ስብሃት ትልቅ ተሰጥኦ የነበረው ደራሲ ነው፡፡ ከጀርባው የማናውቃቸው ብዙ ነገሮች አሉት፡፡ ከዚህ የበለጠ ሊያወጣልን ይችል የነበረ፣ ለሌሎች አርአያ ሆኖ ተስፋ የሰጠ ሰው ነው፡፡ ለስብሃት ስብሃት ይገባዋል፡፡

 

 

Read 2813 times Last modified on Saturday, 25 February 2012 15:55