Saturday, 25 February 2012 14:41

ስብሃት ለእኔ መምህሬ ነው

Written by  ደራሲ ዘነበ ወላ
Rate this item
(0 votes)

ስብሃት ላንተ ምንድነው?

አሪፍ መምህር ነው፡፡ እርፍናውን በአንድ ነገር ልንገርሽ፡፡ ይህንን አድርጊው ብሎ አያዝሽም፡፡ ዝም ብሎ ይነግርሻል፡፡ ውስጥሽ መዝራት ሲፈልግና ልትሰሪው እንደምትችይ ሲያውቅ አሁን የምነግርሽን ታሪክ ወጣት ብሆን ኖሮ Hi Storical novel አድርጌው እጽፈው ነበር ይልሻል እና አሪፍ የፍቅር ታሪክ ይነግርሻል አትረሺውም፡፡ የገንዘብ አቅም፣ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ፈጽሞ ሳትጽፊው አትቀሪም፡፡ ለኔ የነገረኝ አንድ የፍቅር ታሪክ አለ፡፡ በዮሐንስ ዘመን መጨረሻ በሚኒሊክ ዘመን መጀመሪያ ላይ የተፈፀመ፡፡ ይህንን ታሪክ እጽፈዋለሁ፡፡ ትንሽ ጊዜ ወሎ፣ ትንሽ ጊዜ ጐንደር፣ ትንሽ ጊዜ ደግሞ ሱዳን መቀመጥን ይጠይቃል የባለታሪኮቹን ሥነልቡና ለመላበስ - ግን እጽፈዋለሁ፡፡ እና እንዲህ እያደረገ የሚሰጥሽ ነገር አለ፡፡ አያዝሽም ግን ይነግርሻል፡፡ መፃፍም ሪኮርድ ማድረግም አያስፈልግም፡፡ አንጐልሽ ላይ ልክ በድንጋይ እንደተወቀረ ነው የሚያደርገው፡፡ እና ስብሃት ለእኔ መምህሬ ነው፡፡

“ማስታወሻ”ን ስሰራ ከነድክመቴ ነበር የተወኝ፡፡ እንደዛ ማድረጉ ደራሲው እኔ መሆኔን ሊያሳየኝ ነው፡፡ አንባቢው መጽሐፉን ሲያነብ ስብሃት አላየውም እንዴ እያለ ነው ያነበበው፡፡ እሱ ግን ምክንያት ነበረው፡፡ ያ ሥራ የእኔ ሥራ እንዲሆን ይፈልጋል፡፡ እዛ ላይ ጠንካራ የአርትኦት ሥራ ቢሰራ ኖሮ ሥራው የስብአት ሥራ ነበር የሚሆነው፡፡ ደስ የሚለኝ ነገር እሱ ከማለፉ በፊት አርትኦት ችዬ አሳይቼው ነው ያለፈው፡፡ አሁንም እጄ ላይ ያሉ ሥራዎች አሉ፤ እነሱንና የቀሩኝን ሃሳቦች ጨማምሬ እንዲሁም እሱን ለማዳን የተደረጉ ሙከራዎችን ጨማምሬ “ማስታወሻ”ን ከሁለትና ከሶስት ወራት በኋላ እንደገና አሳትመዋለሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

ለስብሃት ቅርብ ከመሆንህ አንፃር የአኗኗር ሁኔታው ምን ይመስል ነበር?

በወግ ሊኖር የሚገባውን ያህል ኖሮ ያለፈ ሰው ነው፡፡ ከ10 ዓመታት በፊት ሐረር ሄደን ከዚህ በኋላ ምን ያህል ዓመት የምትኖር ይመስልሃል ብዬው ነበር፡፡

እስከ 80 ዓመቴ ድረስ እኖራለሁ ነው ያለኝ፡፡ ከተባባልነው 4 ዓመት ከ3 ወር ቀንሶ ነው የሞተው፡፡ እግዜአብሔር ይህንን ዕቅዱን ሳያሳካለት በመቅረቱ ቅሬታ አለኝ፡፡ ከዚህ በተረፈ ስብሃት በደንብ ኖሮ ያለፈ ሰው ነው ብዬ ነው የማስበው፡፡

የስብሃት የመጨረሻ ቀናት እንዴት ነበሩ?

በሽታው የጉሮሮ ካንሰር መሆኑ ከታወቀ በኋላ ውጭ አገር ወስዶ ለማሳከም በጣም ጥረት ተደርጐ ነበር፡፡ የሬዲዮ ፕሮግራም ሁሉ ሊሰራ ታቅዶ ነበር፡፡ ዶ/ር ወንድሙ ተወልደም በጣም ደክሟል፡፡ ግን ሁኔታው ተስፋ አስቆራጭ መሆኑን ካወቅን በኋላ የሠላም እረፍት እንዲያገኝ ዝም ብለን መንከባከብ ጀመርን፡፡ እኔ ለመጨረሻ ጊዜ ያየሁት ሐሙስ ዕለት ነው፡፡ እሱ የሚያሳድገው ደምሰው የሚባል ልጅ አለ - ሆስፒታል ውስጥ እየጠበቀው ነበር፡፡ እሱ እንደነገረኝ ከምሽቱ 5 ሰዓት ከምናምን ላይ ምግቡን በቲዩብ ሰጠው፡፡

ያንን ወሰደ፡፡ ትንሽ ጋደም ካልኩበት ስነቃ ስብሃት ለምግብ መውሰጃ የተሰራለትን ቱቦ (ቲዩብ) ነቃቅሎ ጣለው “ምነው?” ስለው “ከዚህ በላይ እየተሰቃየሁ መኖር አልፈልግም፡፡ በጣም የምወድህ ልጅ ነህ፤ የዛኑ ያህል እንድጠላህ እያደረከኝ ነው፡፡ ምክንያቱም መኖር አልፈልግም እያልኩህ በግድ እንድኖር እያስገደድከኝ ነው” አለኝ ብሎ ነገረኝ፡፡ ቃሉ እንደ ህግ እንዲከበርለት ፈልገናል፡፡

ሐሙስ ዕለት ተረኛው እኔ ነበርኩ፡፡ እየጠበኩት እያለ ቀን ላይ ብንን አለና በምልክት ወረቀት ስጠኝ አለኝ ሰጠሁት፡፡ በግራ እጁ “ተኛ” ብሎ ፃፈልኝ፡፡ እሺ አልኩት፡፡ በዛን ወቅት ጉሮሮው ላይ ኩርር የሚል ነገር እያስቸገረው ነበር፡፡

ለምን መሰለህ እንዲህ የሚያደርግህ? ምግብ ስለማትወስድ ነው የሚያሰቃይህ አልኩትና ቲዩቡ ተመልሶ እንዲገባልህ ትፈልጋለህ ወይ? አልኩት አዎ አለኝ፡፡

ከቤተሰቦቹ ጋር ሆነን ቱዩቡ እንደገና እንዲቀጠልለት ለማድረግ ስንሞክር የጉሮሮው እጢ አብጦ ቱዩቡን አላስገባ አለን፡፡ በቃ ያኔ ተስፋ ቆረጥኩ፡፡ የመጨረሻችንም ዕለት ያቺ ሆነች፡፡

 

 

Read 3001 times Last modified on Saturday, 25 February 2012 14:44