Saturday, 21 May 2016 16:26

የ25 ዓመታት ትርፍና ኪሳራችንን እንተሳሰብ!!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(30 votes)

*መልካም አስተዳደር? የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት? የዜጎች ስደት? ኪራይ ሰብሳቢነት?
•     “ታላቁ የህዳሴ ግድብ ውስጤ ነው!!”
የግንቦት 20፣ሃያ አምስተኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ ክብረ በዓል ዋዜማ ላይ ነን፡፡ እንኳን ለዋዜማው አደረሳችሁ፡፡ የማይመለከታችሁ እንደተለመደው ልትዘሉት ትችላላችሁ፡፡ በነገራችሁ ላይ የዘንድሮው ድርብ በዓል ነው፡፡ ግንቦት 20 እና የ25ኛ ዓመት በዓል፡፡ እኔ የምለው --- አሁንም ግንቦት 20፣ ደርግ የተገረሰሰበት ዕለት በሚል ነው እንዴ የሚከበረው? (እኔማ የነጻነት ቀን ወይም የድል በዓል ቢባል አይሻልም ነበር ብዬ እኮ ነው!)
እናላችሁ ----- ሁሉም የመንግስት መ/ቤቶች ሰሞኑን በበዓል ዝግጅቶች መጠመዳቸው አይቀርም፡፡ የመ/ቤቱን ሃላፊ ለቃለ-ምልልስ ብትፈልጉት እንኳን ከጸሃፊዋ የሚገኘው መልስ “በግንቦት 20 ጉዳይ ተወጥረዋል” የሚል ይሆናል፡፡ (ዳተኝነት ላይ ካድሬነት ሲጨመርበት ውጤቱን አስቡት!)  ለነገሩ እንኳን በግንቦት 20 በዓል በቀድሞው ጠ/ሚኒስትር (ነፍሳቸውን ይማረውና!) ሙት ዓመት መታሰቢያ ሰበብ ስንቱ ከሥራው እንደሚፎርፍ የምናውቅ እናውቀዋለን፡፡ አንድ ሰው መለስን ሰማይ ቤት አግኝቶ ቢነግራቸው፤ ምን እንደሚሉ ታውቃላችሁ? “የምን ግርግር ነው? ሥራችሁን አርፋችሁ ሥሩ እንጂ!; አሁንማ የመለስን ሌጋሴ እናስፈጽማለን --- ምናምን ጨዋታ ቀርታለች፡፡ (ሁሉም የራሱን ሌጋሴ በማስፈጸም ተጠምዷል!)
 እኔ የምለው ግን ----- እያንዳንዱ የመንግስት መ/ቤት በነፍስ ወከፍ በግንቦት 20 በዓል ድግስ ላይ ከሚጠመድ (ድግስ ስላችሁ----ስብሰባውን፣ ዎርክሾፑን፣ ግምገማውን፣ ፕሮፓጋንዳውን፣ ፍረጃውን፣ ፉከራውን፣ ሽለላውን፣ ወዘተ-----ሁሉ ማለቴ ነው!) ለምንድን ነው የበዓል አስተባባሪ ኮሚቴ ተቋቁሞ ቅልጥፍጥፍ ብሎ የማይዘጋጀው?
ወዳጆቼ፤እቺ አገር ብዙም ድሎት ላይ ያለች አይመስለኝም፡፡ ድርቁ ያስከተለው ችግር፣የአየር መዛባቱ የሚፈጥረው ድንገተኛ የተፈጥሮ አደጋ፣ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት፣የመልካም አስተዳደር ጉድለቶች፣እዚህም እዚያም ብልጭ የሚለው ተቃውሞና ግጭት፣ ወዘተ---- በብዙ ችግሮች ነው የተከበብነው፡፡ በአጭሩ ለፌሽታ የሚሆን የተትረፈረፈ ጊዜ የለንም ለማለት ነው፡፡ ነገር ግን የ25 ዓመታት የግንቦት 20ን ትርፎችና ኪሳራዎችን ለመተሳሰብ የምትሆን ጊዜ ግን አናጣም፡፡ (የሥራው ዋና አካል እኮ ነው!)  
  እስቲ ጠጠር ወዳሉት የግንቦት 20 አጀንዳዎች ከማለፋችን በፊት ምርጫ ባለው ጥያቄ .. ዘና ፈታ…ላድርጋችሁ፡፡ በነገራችን ላይ ጥያቄው ፖለቲካዊም ኢኮኖሚያዊም አይደለም፡፡ (ለፍረጃ የማይመች ነው!) እነሆ ጥያቄው፡-
ከሚከተሉት ምርጫዎች መካከል “ውስጤ ነው” የምትሉትን ምረጡ፡-  
ሀ) ህገ መንግስቱ ለ) ታላቁ የህዳሴ ግድብ ሐ) የሊዝ አዋጅ መ) የፀረ -ሽብር ህጉ ሠ) ሀ እና ለ መልስ ናቸው ረ) መልሱ አልተሰጠም
 ያሻችሁትን የመምረጥ መብታችሁ የግንቦት 20 ትሩፋት በሆነው በህገ-መንግስቱ ተረጋግጧል፡፡ ይሄን የምለው ግን ህገ-መንግስቱን በተጽዕኖ “ውስጤ ነው” ብላችሁ እንድትመርጡ  አይደለም፡፡ “ህገ-መንግስቱ ውስጤ ነው” ብትሉም ባትሉም ከህገመንግስቱ ጋር አትቀያየሙም፡፡ ህገ መንግስታዊ መብት ማለት እኮ የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ መብቶች ማስከበሪያ ህግ ነው፡፡ ህገ-መንግስት የሰው ልጅ የአዕምሮ ውጤት እንደመሆኑ መጠንም ሊሻሻል፤ ሊበለፅግ፤ሊታደስ ሊቀነስና ሊጨመር እንደሚችል --- የታወቀ ነው፡፡ የየግል ምርጫችን እንደተጠበቀ ሆኖ ህገ-መንግስቱ ከግንቦት 20 ትሩፋቶች ወይም ትርፎች በዋናነት የሚጠቀስ እሴት ነው፡፡ (ልብ አድርጉ! ትሩፋት ያልነው ሰነዱን ነው!) ከላይ ላቀረብኩት ጥያቄ የእኔን መልስ ነግሬአችሁ ልለፍ፡፡ እናላችሁ----ለእኔ “ታላቁ የህዳሴ ግድብ ውስጤ ነው!!!” (ታዲያ ያለ ሙስናና የህዝብ ሃብት ብክነት ከተጠናቀቀ ብቻ ነው!)
ባለፈው ሳምንት እንዳልኩት የዘንድሮው የግንቦት 20 በዓል 25ኛ ዓመት የሚከበረው ቢያንስ ያንን ስልችት ያደረገንን ያለፈውን የደርግ ሥርዓት በመርገምና በመኮነን አለመሆኑን ከመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት መስማታችን ትልቅ የምስራች ነው፡፡ (የድል በዓል በማውገዝና በመኮነን የሚከበርባት ብቸኛዋ አገር ጦቢያ ትመስለኛለች!) እኔማ የአሁኖቹን የኢህአዴግ አመራሮች፤እግዜር ይስጣቸው አልኩኝ፡፡ ለምን መሰላችሁ? ከጥቂት ዓመታት በፊት አንጋፋው የኢህአዴግ ታጋይ ስብሃት ነጋ (አቦይ ስብሃት) ከአንድ መፅሄት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ የደርግ ጨፍጫፊነት ለ100 ዓመታት ሳይቋረጥ ለትውልዱ መነገር አለበት ብለው አስደንግጠውኝ ነበር፡፡ ትንሽ Creative በሆነ መንገድ ቢሆን ደግሞ ይመቻል፡፡  በታሪክ ሰንዶ ለመጪው ትውልድ ማኖርም የአባት ነው፡፡ ግንቦት 20 በመጣ ቁጥር ደረቅ ፕሮፓጋንዳ መንዛት ግን ትክት ይላል፡፡ (ህዝቡ የደርግን ጨፍጫፊነት ይረሳዋል ብሎ የሚሰጋ ያለ እኮ ነው የሚመስለው!) በዚያ ላይ ሥልጣን ላይ ያለው መንግስት፤“ደርግ ደርግ” ሲል የራሱን ህፀፆች ይዘነጋውና ያርፈዋል፡፡ አንዳንዴ የራሱንም ጥፋት በደርግ ሳያላክክ አይቀርም፡፡ (አውቆ ሳይሆን ሳይውቅ!)
የዛሬ ዓመት ይሁን ሁለት ዓመት ገደማ ኢቴቪ ያቀረበው ዘገባ አይረሳኝም፡፡ (ቃል በቃል ሳይሆን ሃሳቡን ነው ታዲያ!) “በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ካለፈው ሥርዓት የተወረሱ ችግሮች መሆናቸው ተገለፀ” የሚል ነበር፡፡ (አጃኢብ ነው!) እኔ በበኩሌ ይህን ዘገባ በአጭሩ ግለፀው ብባል፤“የደርግ ሥርዓት ናፋቂ” ነበር የምለው፡፡ (ኢቴቪ በዚህ ጉዳይ ላይ ግለ ሂስ አድርጓል እንዴ?)
በነገራችን ላይ መንግስትም ሆነ “አውራው ፓርቲ” የግንቦት 20ን የ25ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ በዓል በሩብ ክ/ዘመን የተገኙ ስኬቶችንና ክሽፈቶች በመገምገም ሲያከብር፣ ግምገማው ባይቀሸብ ይመረጣል፡፡ (ፕሮፓጋንዳ ባይቀላቀልበት ለማለት ነው!) አንዳንዴ አህአዴግ ከህዝብ ጋር ሳይግባባ የሚቀረው እውነታውንና ፕሮፓጋንዳውን ማመጣጠን እያቃተው ሳይሆን አይቀርም፡፡ የመንግስት ባለሥልጣናት “የተለጠጠ ዕቅድ” ምናምን ሲሉ ቶሎ ወደ አዕምሮዬ የሚመጣው ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? “ፕሮፓጋንዳ የተቀላቀለበት ዕቅድ” የሚል ሃሳብ ነው!! አንድ ወዳጄ ግን አረመኝ፡፡ “የተለጠጠ ዕቅድ” ማለት ኪሳራና የሃብት ብክነት ነው በማለት፡፡ በምሳሌ ሲያስረዳኝም፤10 የስኳር ፋብሪካዎች ግንባታን ለአንድ የመንግስት ተቋም (ሜቴክ) መስጠት ማለፈያ “የተለጠጠ ዕቅድ” ማሳያ ነው፡፡ ውጤቱም ኪሳራና የሃብት ብክነት ሆኗል፡፡ ከዕዳ ተራራ ጋር መፋጠጥ! መንግስት በራሱ ገንዘብ ይቀልዳል እንዴ? (ይቅርታ በህዝብ ገንዘብ ማለቴ ነው!)  
በነገራችን ላይ መንግስት ያልተሳኩለትን ዕቅዶች “ለጥጠን አቅደነው ነው ችንጂ--” ምናምን እያለ  እኛንም ራሱንም ሊሸነግል ቢሞክርም በዚህ መልኩ የታለፉት ሁሉ ከግንቦት 20 ኪሳራዎች የሚመደቡ ናቸው (በምን ተዓምር ስኬት ይሆናሉ?)
ባለፉት 25 ዓመታት ቢባል ቢባል ያልተሳካ ሌላው ነገር ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? የዜጎች ስደት! ኢትዮጵያውያን ያልተሰደዱበት አገር እኮ የለም፡፡ (ስደትና ተንቀሳቅሶ የመስራት መብት ለየቅል ነው!) ለነገሩ መሰደድም ራሱ መብት መሆኑ አልጠፋኝም፡፡ ዋናው ነገር ግን ኢትዮጵያውያን የሚሰደዱት ህገ መንግስታዊ መብታቸውን ለመጠቀም ብለው አይደለም፡፡ ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ከድህነት ለማላቀቅ እንጂ! አገር ውስጥ ሰርቶ ለመለወጥ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መኖሩን ለሚደሰኩረው ኢህአዴግ፤የዜጎች ስደት በሃዘኔታ ዓይን የሚታይ አይመስልም፡፡ በ100ሺ ብር ሰው አገር ከመሰደድ ለምን በአገራቸው ላይ ሰርተው አይከብሩም ባይ ነው (እንደ አፍ አይቀልም አሉ!) ግን ራሱ ኢህአዴግስ ያሰራል እንዴ? ለመሆኑ የኢህአዴግ አባል ሳይሆኑ ከጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት የገንዘብ ብድር ማግኘት ይቻላል? የመስሪያ ቦታስ ይሰጣል? አይሞከርም ይላሉ - ውስጥ አዋቂ ምንጮች፡፡ ይሄም ከግንቦት 20 ኪሳራዎች የሚመደብ ነው፡፡
የሚያሳዝነው ደግሞ የወገኖቻችን ስደት ሁሉ በመከራና በስቃይ የተሞላ መሆኑ ነው፡፡ (ማነው ስደት ሁሉ መከራ ነው ያለው?) ግን ኢትዮጵያውን ስደተኞች በሱዳን ወህኒ ቤት እስከ 20 ዓመት እስር ተፈርዶባቸው መከራቸውን ይበላሉ፡፡ በየመን ወደ አረብ አገራት እንሻገራለን ብለው የተፋፋመ ጦርነት ውስጥ ገብተው ይማገዳሉ፡፡ በአረብ አገራት ሴት እህቶቻችን የስቃይ ህይወት ይገፋሉ፡፡ ሌሎች ኢትዮጵያውያን  አውሮፓን ለመሻገር አልመው የባህር ሲሳይ ይሆናሉ፡፡ በየመንገዱና በየበረሃው የሚቀሩትን ቤቱ ይቁጠራቸው፡፡ ወዳጆቼ፤ስደት…ልንቀርፈው ያልቻልነው ብሔራዊ ውርደታችን ነው፡፡
ኤርትራውያንን ጨምሮ በመቶና ሁለት መቶ ሺዎች የሚገመቱ የጐረቤት አገራት ስደተኞችን ተቀብሎ በክብር በማስተናገድ መልካም ስም ያተረፈው “ልማታዊ መንግስታችን”፤ የራ]ሱን ዜጎች ከስደት መግታትም ሆነ ከአደጋ መከላከል ግን አልተቻለውም፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚ/ር በሱዳን እስር ቤት እስከ 20 ዓመት እስር ተፈርዶባቸው የመከራ ህይወት ስለሚገፉ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ሲጠየቅ መረጃው እንደሌለው ገልፆ በካርቱም የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሁኔታውን ይከታተላል ብሎ ተስፋ እንደሚያደርግ ተናግሮ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ግን ለ3 ዓመት በእስር ላይ ለቆዩት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ከባዶ ሽንገላ በቀር ምንም ያደረገላቸው ነገር እንደሌለ እስረኞቹ ገልፀዋል፡፡
መቼም ዜጐች አስገዳጅ የኑሮ ሁኔታ ካልገፋቸው በቀር መንግስት እንደሚለው፤ በህገ-ወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች ተታልለው ወይም ማልለው ብቻ ለስደት መከራ አይዳረጉም፡፡ አዲሱ የውጭ አገር የሥራ ቅጥርን የሚመለከተው አዋጅ በፍጥነት አለመተግበሩም ለህገ-ወጥ ስደቱ መባባስ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ እናላችሁ… የዜጐች የስደት ጉዳይ  ከጉልህ የግንቦት 20 ኪሳራዎች አንዱ ብለን ልንፈርጀው እንችላለን፡፡ (ፀሐይ የሞቀው፤ አደባባይ ያወቀው እውነት ነዋ!)
በቀድሞው ጠ/ሚኒስትር (መሬት ይቅለላቸውና) የሥልጣን ዘመን፣ኢህአዴግም ሆነ ልማታዊው መንግስት ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ የመፍጠር ጽኑ ምኞት እንዳላቸው ሲነገር እንሰማ ነበር፡፡ (የተለጠጠ ዕቅድ ሳይሆን አይቀርም!) በተጨባጭ ግን እንኳንስ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ ሊፈጠር፣የደካከሙትም እንኳን የሚኖሩበት የፖለቲካ ምህዳር መጥበቡን ባለቤቶቹ ከሚያሰሙት እሮሮና ይፋ መግለጫ መረዳት ይቻላል፡፡ ኢህአዴግም እንደ ቀድሞው ዘመን ለአፉ ያህል እንኳን “ጠንካራ ተቃዋሚ የመፍጠር ጽኑ ምኞት አለኝ” ማለቱንም እርም ብሎ ከተወ ብዙ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡
የግንቦት 20 ትሩፋት የሆነው ህገመንግስቱ፤ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ያጐናፀፋቸው የመሰብሰብና የተቃውሞ ሰልፍ የማድረግ መብትም ባልተፃፈ ህግ መታገዱን ይናገራሉ፤ተቃዋሚዎች፡፡ በአመራሮቻቸውና በአባላቶቻቸው ላይ የሚደርስባቸው ወከባና አፈና፣ እስርና ድብደባም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ መምጣቱን በመግለጫዎቻቸው ከማስታወቅ ችላ ያሉበት ጊዜ የለም፡፡ በ2007 የግንቦት ምርጫ የኢህአዴግ በመቶ ፐርሰንት ማሸነፍና ፓርላማው በ “አውራው ፓርቲ” አባላት ብቻ መሞላቱ የስኬት ሳይሆን የኪሳራ ምልክት መሆኑን የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ - የአገር ውስጥም የውጭዎችም፡፡ እናላችሁ … ይሄ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን የሚያዳክም፣ የማታ ማታም የሚገድል አካሄድ ሌላው የግንቦት 20 ኪሳራ ተብሎ ሊመዘገብ ይችላል፡፡ (ያውም ከህገ መንግስቱ ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት ያለው!)
ኢህአዴግ በመንገድ ግንባታ ጨርሶ አይታማም፡፡ (በደህና ጊዜ ቻይናን ይዟል!) በባቡር ሃዲድ ዝርጋታም ተሳክቶለታል፡፡ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ እንዲሁ እስካሁን ችግር አልሰማንም፡፡ (አያምጣው ነው!) እናም እኒህ እኒህ ስኬቶች የግንቦት 20 ትሩፋቶች ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ በሌላ በኩል ኢህአዴግ ከ5 ዓመት በላይ ለዘለቀው የመዲናይቱ የትራንስፖርት ችግር መፍትሄ ማምጣት ተስኖት፣ (ማሰብ ተስኖት ማለት ይቀላል!) እስከ ዛሬ እጁን አጣጥፎ መቀመጡ የሩብ ክ/ዘመን አሳፋሪ ክሽፈት ነው፡፡ የከተማዋን የትራንስፖርት ጉዳይ እመራለሁ ብሎ የተቀመጠው ሃላፊ፣ ምን እየሰራ ደሞዝ እንደሚቆረጥለት ፈጣሪ ይወቀው፡፡ መ/ቤቱስ እንዴት እስከ ዛሬ ሳይፈርስ ተቀመጠ? ይሄም ከግንቦት 20 የኪሳራ ታሪኮች እንደ አንዱ የሚጠቀስ ነው፡፡ (ያውም እኮ የችግሩ ፈጣሪ ራሱ ሆኖ ነው!) ቅድም የጠቀስነው በስኳር ፋብሪካ ግንባታዎች ላይ የተከሰተው መጓተትና የህዝብ ሃብት ብክነት ግን የግንቦት 20 “ትልቁ ኪሳራ” ነው ሊባል ይችላል፡፡ ይታያችሁ ----- ከ6 ዓመታት በላይ ጊዜ ፈጅቷል:: ውጤቱ ግን ስኳር ሳይሆን ዕዳ ሆኗል፡፡  2 ቢ. ዶላር የውጭ ዕዳና ከ10 ቢ. ብር በላይ የአገር ውስጥ ዕዳ ይጠብቀናል፡፡
የ25 ዓመት የልማት ጉዞ ትርፍና ኪሳራችንን መተሳሰቡን እንቀጥላለን፡፡ በፖለቲካዊ ስላቅና በምጸታዊ ወጎቹ የሚታወቀ በኃይሉ ገ/እግዚአብሔር የ97ን ቀውጢ ወቅት ለማስታወስ በሚል በፌስቡኩ ያሰፈረው ጽሁፍ ስለተመቸኝ፣እግረመንገድም የግንቦት 20 ውጤት ስለመሰለኝ ለእናንተ ለውድ አንባቢያን ላጋራችሁ ወደድኩ፡፡ በነገራችሁ ላይ በኃይሉ “ኑሮና ፖለቲካ” የሚሉ መጽሐፍትን
ወቅቱ ያ መከረኛ ወቅት ነው፡፡ የአዲስ አበባ ሰው ሁሉ በየቤቱ በተከተተበት አስፈሪ ምሽት ጥንቅቅ ብሎ የሰከረ አንድ ጀብራሬ መሃሉን የመኪና መንገድ ይዞ እያቅራራ፣እያንጎራጎረ፣እየጮኸ፣ቆላና ደጋ እየረገጠ ሲሄድ ሁለት የከተማ ፖሊሶች አገኙት፡፡ እንኳን ሌሊት ሆኖ በቀንም ያለው እንቅስቃሴ የተገታበት ጊዜ ነበርና ፖሊሶቹ ተናደውበታል፡፡ ከተማዋ እንዲህ ባለ ጭንቅ ተይዛ፣እሱ ሰክሮ ለመለፋደዱ በግነዋል፡፡
“ና አንተ” ጠራው አንደኛው ፖሊስ
“አቤት” አለ ሰውየው፤ቀብረር ብሎ ስካር ያዝ ባደረገው አንደበት፡፡
“ለምንድን ነው አካባቢ የምትረብሸው? ጸጥ ብለህ አትሄድም?”
“ምን ጎደለብኝና ጸጥ እላለሁ” አለ ትከሻውን በትዕቢት እያማታ፡፡
“ነው!” አለና በጥፊ አጮለው፡፡
“አባል እኮ ነኝ” አለ መታወቂያውን ለማውጣት እጁን ወደ ኪሱ እየሰደደ፡፡
“የምን?;
“የፓርቲ ነዋ!”
“እና ብትሆንስ?” አለና ሁለተኛው ፖሊስ በጠረባ ዘረረው፡፡
ሰውየው መሬት ላይ ተነጥፎ ምን ቢል ጥሩ ነው? #አረ ጉድ ነው፤ሳንሰማ መንግስት ተቀየረ እንዴ?”



Read 6675 times