Saturday, 21 May 2016 16:23

ከምትጠላው ጋር ገበታ ከመቅረብ፣ ከምትወደው ጋር መንገድ ጀምር

Written by 
Rate this item
(27 votes)

ከዝነኛው ኤዞፕ ተረቶች አንዱ እንዲህ ይላል፡-
ከዕለታት አንድ ቀን ተኩላዎች ወደ ውሾች መንደር መጡ ይባላል፡፡
“እንደምናችሁ ውሾች?”
ውሾችም፤
“እኛ ደህና ከርመናል፡፡ እናንተስ ተኩላዎች እንዴት ሰነበታችሁ?” አሉ፡፡
ተኩላዎችም፤
“እናንተ ውሾች በጣም ታሳዝኑናላችሁ”
“ለምን?”
“እስከዛሬ እኛና እናንተ ጠላት መሆናችን እጅግ ያሳዝናል፡፡ አለመተሳሰባችንና              አለመነጋገራችን ነው እንጂ ተስማምተን መኖር እንችል ነበር”
ውሾችም፤
“ኑሯችን ለየቅል ሆኖ እንዴት አብረን መኖር እንችላለን” አሉ፡፡
ተኩሎችም፤
“ዋናው ችግር በእርግጥ እሱ ነው፡፡ በመልክና በሁኔታችን በጣም እንመሳሰላለን፡፡ አፋችን፣
ጆሯችን፣ እግራችን ጭራችን …ሁሉ ነገራችን ተመሳሳይ ነው፡፡
ዋናው ልዩነታችን የሥልጠና ጉዳይ ነው፡፡
1ኛ) የምንኖረው በነፃነት ነው
2ኛ) እናንተ የሰው ልጅ ባሪያ ናችሁ፡፡ የሰው ልጅ እንደፈለገ ይቀጠቅጣችኋል፡፡
3ኛ) አንገታችሁ ላይ ሠንሠለት አስሮ ሣጥን ውስጥ ከቶ ያሳድራችኋል፡፡
4) የከብት መንጋ ያስጠብቃችኋል፡፡ ያለፍላጐታችሁ የሰው ከብት ስታዩ ትውላላችሁ፡፡
5ኛ) ለዚህ ሁሉ ልፋታችሁ የተጋጠ አጥንት ነው የሚወረውርላችሁ፡፡
ስለዚህ ከዚህ መከራ መገላገል አለባችሁ፡፡ ቢበቃችሁ ይሻላል፡፡” አሏቸው፡፡
ውሾችም፤
“የተናገራችሁት ዕውነት ነው፡፡ ነገር ግን ምን ማድረግ እንዳለብን አናውቅም” አሉ፡፡
ተኩላዎችም፤
“እኛ የመጣነው ዘዴውን ልንነግራችሁ ነው” አሉ፡፡
ውሻዎች በጥድፊያ፤
“ምንድነው ዘዴው?” አሉና ጠየቁ፡፡
ተኩላዎችም፤
“ዘዴውማ ከብቶቹን ለእኛ ስጡንና ወደ እኛ ጫካ ይዘናቸው ሄደን፣ የሰቡ የሰቡትን እየበላን፣
መጨፈርና መዝናናት ነው፡፡
እዚህ የሰው ልጅ ባሪያ ከመሆን ይሄ የነገርናችሁ ዘዴ አይሻልም?” አሏቸው፡፡  
ውሾች፤
“ሀሳቡን በደስታ እንቀበላለን፡፡ ድንቅ ሃሳብ ነው፡፡ ከብቶቹን እየነዳን አብረን እንሂድና
እንደሰት፡፡ ነፃ እንውጣ” አሉ፡፡ ተኩላዎችና ውሻዎች ተያይዘው፣ ከብቶቹን እየነዱ ወደ ዱር
ሄዱ፡፡
ተኩላዎቹ ግዛታቸው መድረሳቸውን ካረጋገጡ በኋላ ግን፤ ውሻዎቹን አንድም ሳያስቀሩ
ቦጫጭቀው ጨረሷቸው፡፡
***
“የባሰ አለ አገርክን አትልቀቅ” ይላል አበሻ ሲተርት፡፡ “ጠላ አገኛለሁ ብለህ፣ ውሃ ረግጠህ አትሂድ”ም ይላል፡፡ ያ ማለት ግን የታሠርክበትን ሠንሠለት ለመበጠስ አትሞክር፤ ዘላለም በባርነት ኑር ማለት አይደለም፡፡ ከበጠስክ በኋላ የት እንደምትደርስ በትክክል ዕወቅ፤ ቀጥለህም “ከዚያ በኋላስ?” ብለህ ጠይቅ ነው፡፡ አንድ ጥቁር አሜሪካዊ የትምህርት ሰው (academician) ስለ አፍሪካውያንና ስለ ነጮች ልዩነት ሲናገር፤ “አፍሪካውያን (ጥቁሮች) እጅግ ታታሪ ናቸው፡፡ ግባቸውንም ይመታሉ፡፡ ችግሩ የሚመጣው ከዚያ ቀጥሎ ነው፡፡ ይኸውም አንድ ግብ ሲመቱ “ቀጥሎ ምን መደረግ አለበት?” አይሉም፡፡ ነጮቹ ያንን መነሻ አድርገው ገና ወደ ላይ ይስፈነጠራሉ፡፡ አይ ፈረንጅ! ፈረንጅ የነካው ነገር እኮ ተዓምር ነው የሚፈጥረው” እንላለን፤ አለ፡፡ ይህንን በአበሽኛ ማሰብ ነው የሚጠበቅብን፡፡ ከሁሉም ያገኘነውና የተረፈን የስብሰባ ባህል ነው፡፡ ደራሲ በዓሉ ግርማ፤ “ህይወት ራሷ የተራዘመ ስብሰባ መሰለችኝ” እንዳለው ነው፡፡ ዛሬ ያውም ብሶ ተባብሶ ነው!! ሁኔታዎችን ተቆጣጣሪ ጠፋ፡፡ የትራፊክ አደጋ አንዱ ምሳሌ ነው፡፡ “ለመንገደኛ ቅድሚያ ባለመስጠት የተከሰተ ነው!” እየተባለ፤ “የሞኝ ለቅሶ መልሶ መልሶ” ሆነናል፡፡ ቢያንስ የዓለም ባንክ ሪፖርት የጠቀሰውን “የኢትዮጵያ የትራፊክ አደጋ ችግር፤ ትንሽ ያለማገናዘብ (Lack of commonsense) ችግር ነው” ያለውን ልብ ማለት ያባት ነው፡፡
 የኢኮኖሚ ችግራችንም ቢሆን እጅግ ቅጥ ያጣ ነው፡፡ የኢኮኖሚ ባለሙያዎቻችንም ነገር “ቄሱም ዝም ዳዊቱም ዝም” ነው! የስኳር ኮርፖሬሽን መቀመቅ መግባት አሰቃቂ ነው፡፡ ወይ በሰዓቱ ለህዝብ አልተነገረ፣ ወይ አስቀድሞ አደጋው በባለሙያዎቻችን አልተተነበየ፤ “አይመጣምን ትተሽ ይመጣልን ጨምሪበት” የሚለውን እንኳ ተረት አለማሰብ ከተማረ የማይጠበቅ ነው፡፡ ያን ካላሰብን፤ ቢያንስ “የተማረ ይግደለኝ!” ለማለት እንኳ አቅም ማጣታችን ነው! “የተማረ ይግደለኝ የምትል ከሆነ፤ ዩኒቨርሲቲ ደጃፍ ሄደህ ተንከባለል” የሚለውን ተረባዊ አባባል ተቀበል፤ የሚለውን ተግባራዊ ማድረግ ነው፡፡ ችግሩ ትምህርቱ ምሁር ሊፈጥር ባለመቻሉ ለሁሉም የዕቃ-ዕቃ ጨዋታ መሆኑ ነው! ጣጣችን ብዛቱ ይዘገንናል፡፡ መንገዶች ተሰሩ እንጂ ጠጋኝ የላቸውም! ኮንዶሚኒየሞች ከተሰሩ እና ከተሸጡ በኋላ ተከታታይ የላቸውም! ገበያዎች የሸማቹ ኪስ እስካለ ድረስ እንደፍጥርጥራቸው የሚባሉ ከሆኑ ውለው አድረዋል፡፡ አንድ የውጪ አገር ዜጋ እንደታዘበው፤ “የቢሮ ሰራተኞች እርስ በርስ ተቆላልፈዋል፡፡ በዚያው ሥራውም አብሮ ተቆልፏል” ብሎናል! የሀገራችንን ሁልቆ መሳፍርት የሌላቸው ችግሮች ለመፍታት የሚመሳሰሉ ሰዎች አንድ ላይ መሆናቸው ወሳኝ ነው! አፍና ልብ መገናኘታቸውም ዋና ነገር ነው፡፡ ዘይትና ውሃ ሆኖ ሥራ መስራት፣ ልማት ማልማት ብሎ ነገር እንዲያው ጨዋታ ነው! “ወመቴን ከአለሌ፣ ጨውን ከአሞሌ” መለየት ግድ ነው!” ከምትጣላው ጋር ገበታ ከመቅረብ፣ ከምትወደው ጋር መንገድ ጀምር! የሚባለው ለዚህ ነው!!

Read 8180 times