Saturday, 25 February 2012 14:17

የማንችስተርና ለንደን ክለቦች ፍጥጫ ከአውሮፓ ውጭ ሆኗል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

የእንግሊዝ ክለቦች በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የነበራቸው የበላይነት በዘንድሮው የውድድር ዘመን እንዳበቃለት ተረጋግጧል፡፡ ማንችስተርን የወከሉት ሲቲ እና  ዩናይትድ ከአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ማጣርያ ውጭ ሁነዋል፡፡ በዩሮፓ ሊግ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቷቸው ሩብ ፍጻሜ ገብተዋል፡፡ ሰሞኑን ደግሞ በሻምፒዮንስ ሊጉ ሁለት የለንደን ክለቦች በጣሊያን ክለቦች ተንበርክከው ጥሎ ማለፉን በመውደቅ አደጋ ውስጥ ናቸው፡፡ የሰሜን ለንደኑ አርሰናል በኤሲሚላን 4ለ0 ሲሸነፍ የምዕራብ ለንደኑ ቼልሲ  ደግሞ በሌላው በናፖሊ 3ለ1 ተረትቷል፡፡ ሁለቱ የለንደን ክለቦች ከወደቁ እንደማንችስተሮቹ ክለቦች በቀጣይ ዓመት ወደ ዩሮፓ ሊግ መውረዳቸው አይቀርም፡፡

ሁለቱ የማንችስተር ከተማ ክለቦች በሻምፒዮንስ ሊጉ የምድብ ማጣርያ በመሰናበታቸው እያንዳንዳቸው ከ22 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ እንዳሳጣቸው ታውቋል፡፡ የለንደኖቹ ክለቦች አርሰናል እና ቼልሲም ከጥሎ ማለፉ ከተሰናበቱ በድምሩ እስከ 30 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ያመልጣቸል፡፡ ማን ዩናይትድና ማን  ወደ ዩሮፓ ሊግ ሩብ ፍፃሜ መግባታቸው በገቢ እጦት የደረሰባቸውን ኪሳራ ሊያክሱበት ይችላሉ፡፡ ማንችስተሮች ባላቸው ጥንካሬ ለዘንድሮው ዩሮፓ ሊግ የዋንጫ ጨዋታ ሊደርሱ እንደሚችሉ ከፍተኛ ግምት አለ፡፡ በሊግ ውድድርም የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፏቸውን ባረጋገጠ ደረጃ ሻምፒዮናነቱን እንደተናነቁበት ናቸው፡፡ በአንፃሩ ለንደኖቹ አርሰናልና ቼልሲ በሻምፒዮንስ ሊግ እና በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ከዋንጫ ተፎካካሪነት መራቃቸው ብቻ ሳይሆን የቀጣይ አመት ሻምፒዮንስ ሊግን ለመቀላቀል አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል፡፡ በማንችስተር ያሉት ክለቦች በአሰልጣኞቻቸው እምነት እንደያዙ ነው በለንደን ያሉ አሰልጣኞች ግን ቀጣይ ቆይታ ጥያቄ ውስጥ ይገኛል፡፡

 

የእንግሊዝ ክለቦች ባለፉት 5 ዓመታት በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ሩብ ፍፃሜ ለመግባት የነበራቸው የበላይነት  ዘንድሮ አሽቆልቁሏል፡፡ በ2007 እኤአ  ቼልሲ፣ ሊቨርፑልና ማን ዩናይትድ፤ በ2008 እኤአ እና በ2009 እኤአ አርሰናል፣ቼልሲ፤ ሊቨርፑልና ማን ዩናይትድ፤ በ2010 እኤአ አርሰናልና ማን ዩናይትድ እንዲሁም በ2011 ቼልሲ ማንዩናይድና ቶትንሃም ለሩብ ፍፃሜ መድረስ ችለው ነበር፡፡

በአውሮፓ የቀዘቀዘው የእንግሊዝ ሁለት ከተሞች የእግር ኳስ ሃያልነት በሊግ ውድድር ከፍተኛ ትንቅንቅ በመብዛቱ ነው የሚል ምክንያት ይሰጣል፡፡ ይሁንና የለንደንና ማንችስተር ከተሞችን የወከሉ ክለቦች ጥንካሬ በፕሪሚዬር ሊጉ የ20 ዓመራሱን ሱፐር ሊግ ፈጥሯል በሚል ይታማል፡፡ መጀመርያ ሊቨርፑል ማን ዩናይትድ አርሰናል ነበሩ፡፡ ቀጥሎ ቼልሲ መጣ ከዚያም ቶትንሃምና  ማን ሲቲ በፉክክሩ ግልቢያ ተጨመሩ፡፡ የእነዚህ ክለቦች የፉክክር ደረጃ በመካከላቸው በገንዘብ አቅም እና በተደራጀ መዋቅር መቀራረብን ፈጥሮ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ከባድነትን አመጣ፡፡ ሊጉ ከሻምፒዮንስ ሊግ በለጠ፡፡የ5ቱ ክለቦች ጥንካሬ ከሌሎች አስራ ምናምን የሊጉ ተወዳዳሪ ክለቦች ርቆ ሄዷል፡፡ የእንግሊዝ ክለቦች በአውሮፓ ውድድሮች ላይ ካልተሳከላቸው በኋላ በሊጉም ለ4ኛ  ደረጃ ከ5 በላይ ክለቦች መያያዛቸው የሊጉ መክበድ የክለቦችን የአውሮፓ ተሳትፎ በአቋም መውረድ እንዲያንስ ምክንያት ሆኗል፡፡

የእንግሊዝ ክለቦች ባለፉት 7 የውድድር ዘመናት በስድስቱ ለፍፃሜ መቅረብ የቻሉ ነበሩ፡፡ ዘንድሮ ከጥሎ ማለፍ ለማምለጥም ዳግቷቸዋል፡፡ ይህን ታሪክ ካለወጡ ደግሞ የእንግሊዝ ክለብ የሌለበት የሻምፒዮንስሊግ ሩብ ፍፃሜ የሚያጋጥመው ከ16 የውድድር ዘመናት በሃላ ይሆናል፡፡አንዳንድ መረጃዎች የ62 ዓመቱ ቬንገር፤ የ70 ዓመቱ ፈርጉሰን የሚገኙበት ሊግ ባረጁና ብቁ ባልሆኑ አሰልጣኞች መካሄዱን ለድክመቱ ሰበብ ያደርጋሉ፡፡ በሊጉ የማንችስተሮቹ ክለቦች ለሻምፒዮናነት ሲተናነቁበት እና ለዩሮፓ ሊግ ድል ሲጠበቁ በቀውስ ያሉት ለንደኖች አርሰናል የያዘውን 4ኛ ደረጃ ለመንጠቅ 5ኛ ሆኖ የሚከተለው ቼልሲ ሆኖ ለሻምፒዮንስ ሊግ ህልውናቸው እንደተፋጠጡ ነው፡፡ ሌላው የለንደን ክለብ ቶትንሃም ሁለቱን ክለቦች በ10 ነጥብ ርቆ 3ኛ ደረጃን ይዞ ይገኛል፡፡ አርሰናልና ቼልሲ በቀጣዩ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ካልገቡ 45 ሚሊዮን ፓውንድ የገቢ ኪሳራ ይገጥማቸዋል፡፡በቼልሲ ያለው ችግር በሚወጣ ገንዘብ ልክ ውጤታማ ቡድን አለመስራት ሲሆን አርሰናል ደግሞ በወጭ እጥረት አቅመ ቢስ ስብስብ መያዙ ነው፡፡ አንድሬስ ቪያስ ቦአስ ሆነ አርሴን ቬንገር ከሻምፒዮንስ ሊጉ ጥሎ ማለፍ ከተሰናበቱ እና ቡድናቸውን ለቀጣዩ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የሚያበቃውን ደረጃ በሊጉ ይዘው ውድድር ዘመኑን ካልጨረሱ ሃላፊነታቸው ጥያቄ ውስጥ ይገባል፡፡ ቁማር አጫዋች ድርጅቶች  ከሚባረሩ አሰልጣኞች በመጀመርያ ደረጃ ያስቀመጡት የቼልሲውን ቪላስ ቦአስ ሲሆን ቬንገር የተሻለ ዋስትና  የተገመቱ ናቸው፡፡ የአርሰናል ባለድርሻ አካላት ክለቡ ለ6ኛ ተከታታይ የውድድር ዘመን በዋንጫ ድርቅ በመመታቱና በሻምፒዮንስ ሊግም ከቋሚ ተሰላፊነት ውጭ ለመሆን አጣብቂኝ በመግባቱ ቬንገርን ወደ መውጫው መግፋት ጀምረዋል፡፡ አሰልጣኙ የግዢ ፖሊሲያቸውን በመቀየር ትልልቅ ተጨዋቾችን በመሸጥ ሳይሆን በመግዛት ክለቡን እንዲያጠናክሩ  እቅድ መኖሩ ሰሞኑን ተሰምቷል፡፡ ቬንገር ተጨዋች በመግዛት ቡድኑን እንዲያጠናክሩ 100 ሚሊዮን ፓውንድ በጀት ለማድረግ ድጋፊዎቹ ግፊት ፈጥረው ተንቀሳቅሰዋል፡፡ ቬንገር ለቀጣዩ የውድድር ዘመን ቢያንስ 50 ሚሊዮን በማውጣት ክለቡን በምርጥ እና ብቁ ተጫዋች እንዲያጠናክሩ እድል ይኖራቸዋል፡፡

የሞውሪንሆ ምትክ የተባሉት ፖርቱጋላዊው አንድሬስ ቪያስ ቦአስ በስታምፎርድ ብሪጅ እንደሚቆዩ ከአብራሞቪች ድጋፍ ቢያገኙም የመልበሻ ቤት ችግር እንዳለባቸው እየተወራ ነው፡፡ በቼልሲ አመራሮች ያለፈውን ሁለት የውድድር ዘምን ስራ ፈተው የቆዩትን የቀድሞውን የሊቨርፑል አሰልጣኝ ራፋ ቤኒተዝ የመቅጠር ፍላጎት መኖሩ ተሰምቷል፡፡አብራሞቪች በቼልሲ 300 ሚሊዮን ፓውንድ ለተጨዋች ብቻ አውጥተው ክለቡ ከ50 ዓመት በሃላ ለመጀመርያ ጊዜ የሊጉ ሻምፒዮን አድርገዋል፡፡ ይህን ስኬትም ደግመዋል፡፡ ማን ሲቲ በአቡዳቢው ባለሃብት ሼክ መንሱር ከ3 የውድድር ዘመናት በፊት ሲያዝ በ1 ቢሊዮን ፓውንድ ኢንቨስትመንት ነው፡፡ የመጀመርያውን ሁለት የውድድር ዘመናት ክለቡን ያሰለጠኑት ማርክ ሂውጅስ ለእያንዳንዱ ዓመት ለተጨዋቾች ግዚ ብቻ 250 ሚሊዮን ዶላር ተመድቦላቸዋል፡፡ አሁን ክለቡን የያዘው ማንቺኒ ደግሞ ቡድኑን ለማጠናከር እስከ 150 ሚሊዮን ፓውንድ በጀት ተደርጎለት እየሰራ ነው፡፡ በሁለቱ የማንችስተር ከተማ ክለቦች መካከል  ያለው ተቀናቃኝነት 128 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ የፕሪሚዬር ሊጉን ሻምፒዮን ይወስናል የተባለው የማንችስተር ደርቢ ግጥሚያ ከ2 ወራት በኋላ አስቀድሞ ከወጣው ፕሮግራም በሁለት ቀናት ተሸጋሽጎ ሰኞ እለት ሊደረግ ተውስኗል፡፡

በዓመታዊ ገቢ ማን ዩናይትድ 331.3 ሚሊዮን ፓውንድ በመሰብሰብ ብልጫ ሲኖረው ማን ሲቲ 125 ሚሊዮን ፓውንድ ያገኛል፡፡

የደሞዝ ወጪ ላይ  ማን ዩናይትድ 152.9 ሚሊዮን ፓውንድ በመክፈል ሲበልጥ ማን ሲቲ 133 ሚሊዮን ፓውንድ ያወጣል፡፡

ማን ዩናይትድ 110.9 ሚሊዮን ፓውንድ ትርፍ የሚያስመዝግብ ክለብ ሲሆን ማን ሲቲ ደግሞ በየውድድር ዘመኑ 121 ሚሊዮን ፓውንድ ኪሳራ ይመዘገብበታል፡፡

ማን ዩናይትድ 308.3ሚሊዮን ፓውንድ እዳ ሲኖረው ማን ሲቲ ምንም እዳ የለበትም፡፡

ሼክ መንሱር ከመጡ በኋላ የሁለቱ ክለቦች አጠቃላይ ከወጪ ቀሪ ሲወራረድ የማን ሲቲ 402.12 ሚሊዮን ፓውንድ ሲሆን የማን ዩናይትድ 15.58 ሚሊዮን ፓውንድ ብቻ ነው፡፡

ማን ዩናይትድ በሁሉም ውድድሮች ከ60 በላይ ዋንጫዎች ሲሰበስብ 19 የሊግ፤ 11 የኤፍኤ ካፕ 3 ደግሞ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎች ናቸው፡፡ ማን ሲቲ ደግሞ 13 ዋንጫዎች በሁሉም ውድድሮች ያገኘ ሲሆን ሁለቱ የሊግ አምሰቱ የኤፍኤካፕ ድሎች ናቸው፡፡

 

 

Read 2558 times Last modified on Saturday, 25 February 2012 14:20