ሁለቱም ክለቦች ሀገራችንን በመወከል በአፍሪካ የክለቦች ውድድሮች የሚሳተፉ በመሆኑ መላ የስፖርት ቤተሰቡ በመልሱ ጨዋታ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ክለቦቹ የሚያደርጉትን ጥረት ማበረታታት እንደሚገባ ፌዴሬሽኑ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡
በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ቅድመ ማጣርያ የመጀመርያ ግጥሚያውን ወደ ኮሞሮስ በመጓዝ ከኪዮን ኖርድ የተጋጠመው ኢትዮጵያ ቡና 1-0 በሆነ ጠባብ ውጤት ተሸንፏል፡፡ በሌላ በኩል በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ቅዱስ ጊዮርጊስ የጋቦኑን ያንጋ ስፖርት 1-0 አሸንፏል፡፡ለቅዱስ ጊዮርጊስ የአሸናፊነት ጎሉን ያስቆጠረው አዳነ ግርማ ነው፡፡ሁለቱ ቡድኖች በቅድመ ማጣርያው የመጀመርያ ጨዋታቸው ቡና 1ለ0 በሆነ ጠባብ ውጤት በመሸነፉና ጊዮርጊስ ከሜዳው ውጭ 1ለ0 ተጋጣሚውን በመርታቱ በሜዳቸው በሚያደርጓቸው የመልስ ጨዋታዎች አሸንፈው ወደ ቀጣዩ የመጀመርያ ዙር የማጣርያ ምእራፍ ለማለፍ ሰፊ እድል ይኖራቸዋል፡፡ በሌላ በኩል ቤኒን ከሳምንት በፊት ቀድሞ የፈረንሳይ አጥቂ ተጨዋች የነበሩትን የ50 ዓመቱን ማኑዌል አሞሮስ ለ2 ዓመት ብሄራዊ ቡድኑን እንዲያሰለጥኑ ሾሟል፡፡ የ34 ዓመቱ አሰልጣኝ ከፈረንሳይ ብሄራዊ ቡድን ጋር በ1984 እኤአ ላይ የአውሮፓ ዋንጫን ያገኙ ሲሆን በሁለት የዓለም ዋንጫዎች ተሳታፊ የነበሩ ናቸው፡፡
አሞሮስ ከቤኒን ሃላፊነታቸው 2 ዓመት በፊት የኮሞሮስ ብሄራዊ ቡድንን ያሰለጠኑ ሲሆን የመጀመርያ ጨዋታቸውን እዚህ አዲስ አበባ ከኢትዮጵያ ጋር በሚደረግ ጨዋታ ይጀምራሉ፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ አህጉራዊ ፉክከሩን በብሄራዊ ቡድን ከቤኒን ጋር በክለቦች ደግሞ ከአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጇ ጋቦንና ከኮሞሮስ ተወካይ ክለብ ጋር ተፋጥጧል፡፡ ከአራቱ አገራት በፊፋ የእግር ኳስ ደረጃ በ28ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ከፍተኛ መሻሻል ያሳየችው ጋቦን እጅግ ርቃ ሄዳለች፡፡ ደካማዋ ኮሞሮስ ናት፡፡ ቤኒን ደረጃዋ ከኢትዮጵያ ቀጥሎ ነው፡፡ ይህም ከተጋሚዎች ከባዱ ግጥሚያ ለጊዮርጊስ ያደርገዋል፡፡ ጊዮርጊስ ከሜዳው ውጭ አሸንፎ የመጣው ክለብ የጋቦም መሆኑ የክለቡ ጥንካሬና ተጨዋቾቹ ምን ያህል ለብሄራዊ ቡድኑ እንደሚያስፈልጉ ያሳያል፡፡
በፊፋ መረጃ
ኢትዮጵያና ቤኒን
የተጨዋቾች ብዛት 3,474,245 ፤320600
የተመዘገቡ 56,245 ፤ 7800
ክለቦች 1,004 ፤ 110
ባለሙያዎች 310,600 ፤ 1700
በፊፋ ያለፈው አንድ አመት አማካይና ወቅታዊ ደረጃ
ኢትዮጵያ 132.846፤ 137
ቤኒን 100.769 ፤ 136
ጋቦን 65.462፤ 45
ኮሞሮስ 183 ፤ 188