Saturday, 07 May 2016 13:17

መብላት የለመደ ሲያይህ ያዛጋል

Written by 
Rate this item
(20 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ከዳር አገር ወደ ዋናው ከተማ የመጡ አዛውንት ለንጉሱ አቤቱታቸውን ለማቅረብ ከዙፋን ችሎቱ ዘንድ ተቀምጠው ተራቸውን ይጠብቃሉ፡፡
ባለሟሎች ስነ-ስርዓት እያስከበሩ ሁሉን በወግ በወግ ያስተናግዳሉ፡፡ አንዱ ሲጨርስ ሌላው ግባ ይባላል፡፡ በዚሁ ደንብ እኒያ የዳር-አገር መኳንንት ተራቸው ይደርስና ይቀርባሉ፡፡ ንጉሱ ገና ከሩቁ አውቀዋቸዋል፡፡ ጃንሆይ፤
“እህስ ምን ችግር ገጠመህና ከሩቅ አገር ድረስ ወደ እኛ መጣህ?”
አዛውንቱም፤
“ንጉሥ ሆይ! ከዚህ ከንጉሱ ከተማ እኛ ወዳለንበት ዳር-አገር ከሚመጡ ሹማምንት መካከል አንዱ ከብቶቹን በግፍ ነድተውብኛል … ያላግባብ ሰብሌን ወስደውብኛል፡፡ ሌላው ቀርቶ ለዘር ያወጣሁትን እህል እንኳ አልተውም፤ መዝብረውታል፡፡ እኔ ከላይም እግዚሃርን፣ ከታችም እርስዎን አምኜ የተቀመጥኩ አንድ ደሀዎ፣ በአገር አማን ይሄ ሁሉ በደል እንደምን ይደርስብኛል?”
ጃንሆይ፤
“ዕውን ይሄ ሁሉ በደል ደርሶብሃል? ለዚህ ዕማኝ አለህ?”
አዛውንቱ፤
“አዎን ጃንሆይ፤ አገር ይመሰክርልኛል፡፡ አገሩ ሁሉ ለእኔ ሲል አልቅሷል፡፡ “ነግ በኔ” እያለም ስጋት አድሮበታል፡፡
ጃንሆይ፤
“ይህ የሚለው ዕውነት ከሆነ በእርግጥ ተበዳይ ነውና ተጣርቶ ካሣ ይከፈለው፡፡ ግምቱ ተሰልቶ እህል ይሰጠው” አሉ፡፡
አዛውንቱ፤ ቀጠሮ ተሰጥቷቸው፣ እየተደሰቱ ወደ አገራቸው ተመለሱ፡፡ በቀጠሮአቸው መሰረት ወደ ንጉሱ አገር ተመለሱና ችሎት ቀረቡ፡፡ ባለሟሉ የአዛውንቱን የተጣራ ውጤት ለንጉሴ አቅርቧል፡፡
ጃንሆይ ተጣርቶ የቀረበላቸውን በጥንቃቄ ካዩ፣ ካስተዋሉ በኋላ፤
“ይህ ሰው በደል ደርሶበታል፡፡ ለመሆኑ ይሄን ያህል በደል ሲፈፀምብህ እስከዛሬ ለምን ዝም አልክ?” ሲሉ አዛውንቱን ጠየቁ፡፡
አዛውንቱም፤
“እኔማ ንጉሥ ሆይ! ‹ደንጊያና ቅል ተላግቶ፣ ዜጋና ሹም ተጣልቶ› አይሆንም ብዬ ነው፡፡ ሲብስብኝ በቀጥታ ወደ እርስዎ የመጣሁት፣ በየደረጃው መጎሳቆሉን ፈርቼ ነው፡፡ እርስዎ ባይደርሱበት ነው እንጂ ሹማምንቱን ያስደሰተ እየመሰለው እኛን ሱሪ ባንገት የሚያስወልቅ ስንት አዛዥ ናዛዥ አለ መሰለዎ?”
ጃንሆይ፤
“መልካም፤ ባለፈው እንዳልኩት በደሉ ተገምቶ ተመጣጣኝ እህል ይዞ አገሩ ይግባ” ብለው ፈረዱላቸው፡፡
ይህ በሆነ በሁለተኛውም፣ በሶስተኛውም ሳምንት አዛውንቱ ምንም ያገኙት ነገር የለም፡፡ የተፈረደላቸው ፍርድ አልተፈፀመላቸውም፡፡ ይቀርባሉ፡፡
ጃንሆይ፤
“ዛሬስ ምን ሆነህ መጣህ?” ይሏቸዋል፡፡
አዛውንቱ፤
“ዛሬም አልተፈፀመልኝም ጃንሆይ”
ንጉሡ ደግመው ትዕዛዝ ይሰጣሉ፡፡
ታዛዦቹ ሹማምንት “እሺ ጃንሆይ እናስፈጽማለን” ይላሉ፡፡ በተግባር ግን ምንም አይታይም፡፡
አዛውንቱ በመጨረሻ ንጉሱ ዘንድ ይቀርባሉ፡፡

ጃንሆይ፤
“እህ ምን ችግር ገጠመህ?” አሏቸው፡፡
አዛውንቱም፤
“ንጉሥ ሆይ! ዛሬስ አጋሰስ ልጠይቅ ነው የመጣሁት፡፡ ሁሉ ቀርቶብኝ፤ አንድ አሥራ አምስት ያህል አጋሰሶች ይሰጡኝ!”
ጃንሆይ፤
“ለምንህ ነው አጋሰስ የፈለግኸው?”
አዛውንቱ፤
“የሸዋን መኳንንት “እሺታ” ልጭንበት!” አሉ፡፡
***
የሀገራችን የአፈፃፀም ችግር የጥንት የጠዋት ነው፡፡ ህግጋት ይደነገጋሉ፡፡ መመሪያዎች ይወጣሉ፡፡ ማዘዝ ቁልቁለት ነውና ትዕዛዛት ይፈስሳሉ፡፡ ግን በተግባር ሥራ ላይ ውለው አይገኙም፡፡ በየእርከኑ ያሉ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት፤ ወይ ነገሩን ከጉዳይ አይጥፉትም፤ ወይ በግላቸው እንዳይፈፀም ይሻሉ፤ አሊያም ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ምክንያቶች እየደረደሩ ባለጉዳይ ማጉላላታቸውን ይያያዙታል፡፡
ስብሰባዎች የኑሮ ዘዴ እስኪመስሉ ድረስ በተደጋጋሚ “ስብሰባ ላይ ናቸው”ን መስማት የተለመደ ሆኗል፡፡ ከአንድ ቢሮ ወደ ሌላ ቢሮ ጉዳይ የያዘ ፋይል ሲንፏቀቅ ይከርማል፡፡ ዳር የደረሰው ፋይል ደግሞ “ይሄ ይሄ አልተሟላም” ተብሎ ጉዳዩ መልሶ ጥሬ ይሆናል፡፡ የደከመው ባለጉዳይ እርም ብሎ ከነጭርሱ ነገሩን ይተወዋል፡፡ ያልታከተው ባለጉዳይ ሥራ ያቀላጥፍልኛል ወዳለው ሹም በአማላጅ ለመሄድ ይጥራል፡፡ ይሄ የባለጉዳይ መጉላላት እጅግ ሲደጋገም “ጉዳይ አስፈፃሚ” የሚል ታርጋ ያለው፤ በውል በ “ቢ ፒ አር” የማይታወቅ ማዕረግ ያነገበ፣ ሠራተኛ ፈጥሮ ቁጭ ይላል፡፡ ዛሬ በማናቸውም መሥሪያ ቤት ያለ ሥራ፣ ከተቋሙ ውጪ በሚኖር “ጉዳይ አስፈፃሚ” የሚተዳደር ይመስላል፡፡ የቢሮክራሲውን ቀይ ጥብጣብ (bureaucratic red tape) የሚበጥሱ ጉዳይ አስፈፃሚዎች” ናቸው፡፡ “ከእያንዳንዱ አሸናፊ ወንድ ጀርባ አንድ ሴት አለች” ይባል የነበረው፤ በዛሬው የአገራችን ሁኔታ፤ “ከእያንዳንዱ ስኬት ጀርባ አንድ ጉዳይ አስፈፃሚ አለ” የሚባልበት ወቅት ተፈጥሯል፡፡ አንዳንድ ውስጥ አዋቂዎች እንደሚሉት፤ በስሪያ ቤት ውስጥ ያሉ ሠራተኞች እርስ በርስ ሥራውን ለማሳካት “ጉዳይ አስፈፃሚ” ይፈልጋሉ ተብሏል፡፡
“ገንዘብ የደም ሥር ነው” የሚለው የጥንት አባባል፣ ዛሬ ዐይን ባወጣ መልኩ እንደ ዱላ ቅብብል ሥራ ማስኬጃ መሆኑ የአደባባይ ፀሐይ የሞቀው ጉዳይ ነወ፡፡
ከአንድ ቢሮ ጉዳይ ለማንቀሳቀስ ህጉ፣ ባለጉዳዩ የያዘው ገንዘብ ነው፡፡ ፀሐፊዋ ያለገንዘብ፣ ፋይል ለአለቃ አታቀርብም፡፡ በአንዳንድ አጋጣሚ በፈገግታ “ጉዳይህ ምንድነው” ለማለት ገንዘብ ትሻለች፡፡ አለቃዋ፤ አሉ የሉም፤ ለማለትም ገንዘብ ያስፈልጋታል፡፡ ጉዳይ ከተፈፀመ በኋላም ገንዘብ እንደማህተም የሚያገለግል የፋይሉ አካል ነው፡፡ ይሄን እንደምሳሌ ጠቀስን እንጂ ከተላላኪ እስከ ሥራ አስኪያጅ፣ ከዚያም እስከ ቦርድ ሰብሳቢ ድረስ፤ መላው ይሄ ሆኗል፡፡ እንግዲህ ይሄ አካሄድ “እየተሻሻለ መጥቷል” በተባለው የመልካም አስተዳደር ዘይቤ ውስጥ ያለ ነው፡፡ “ፍትሐዊ አሠራር እየሰፈነ ነው” በሚባልበት አገር ነው፡፡ “እጅህን እኩሬው ውስጥ ክተት፡፡ ወይ አሣ ታገኛለህ፤ ካልሆነም እጅህን ታጥበህ ትወጣለህ” ነው የትም ቦታ ያለው ሙስናዊ መርህ፡፡ አንዳንድ ሰፈር፤ “አለዛ (ያለገንዘብ) እንዴት ሥራ ይሠራል?” የሚለው አነጋገር የመጽሐፍ ቃል ይመስላል፡፡
አንድ ፀሐፊ እንዳለው፤ “የአፍሪቃ አማፂያን ድል ባደረጉ ማግስት ገንዘብ ማርባት ይጀምራሉ፡፡ ከዚያም ራሳቸው ይሰባሉ፡፡ በመጨረሻም ዕውነተኛው ግብ ራስን ማድለብ ይሆናል”፡፡ (At the end, the real goal becomes fattening oneself) ስለፈጣን ልማት እያወራን ፈጣን ስባት ውስጥ ከገባን፣ ልማቱን ወደ ፈጣን ጥፋት ለወጥነው ማለት ነው፡፡ በቪላዎች፣ በፎቆች፣ በመሬት ብዛት፣ በባንክ ደብተሮች ቁጥር ብዛት፣ በልጅ በዘመድ አዝማድ ውክልና ብዛት ወዘተ… በአጠቃላይ በግል ልማት፤ የአገርን ልማት ተክተን የምንንቀሳቀስ ከሆነ፤ ወሰን-የለሽ መንኮታኮት ገና ይጠብቀናል፡፡ እስር ቤቶች ያለጥርጥር ሞልተው ይትረፈረፋሉ፡፡ የሚገርመው፤ የሚሞሉት በጉቦ ተቀባይ ብቻ ሳይሆን በጉቦ-ሰጪም ነው፡፡ ዛሬ ዛሬ፤ ጉቦ-ተቀባዩ በምን መልክ መቀበል እንዳለበት ተጨንቆ ተጠቦ መላ የሚዘይድለት ራሱ ጉቦ-ሰጪው የሆነበት ደረጃ በመድረሱ ወደ ባህልነት ተሸጋግሯ፡፡ ጉዳይ አስፈፃሚው እንደ ህግ አማካሪ ማገልገሉም አይገርምም - የልምድ አዋላጅነት ፈጣን ገቢ የማከማቻ አቋራጭ ሆኗልና! በአቋራጭም ሆነ በረዥሙ መንገድ መንጋ በላተኛ ፈጥረናል፡፡ ደላሎቹ እንደሚሉት፤ “የሥራው ፀባይ ነው” ማለት በሙስናም ረገድ የማያሳፍር አባባል ነው፡፡ ትላልቅ ውሸቶች የጥቃቅንና አነስተኛ ውሸቶች መድብል ናቸው፡፡ አያሳፍሩም፡፡ ገንዘብህን የበላ፣ መሬትህን የበላ፣ ንብረትህን የበላ፤ አንተን ከመብላት ወደ ኋላ አይልም - “መብላት የለመደ ሲያይህ ያዛጋል” የሚባለው ለዚህ ነው!!

Read 4935 times