Saturday, 25 February 2012 14:00

በመዲናዋ ሰማይ የሚታየው ባሉን ምሥጢር

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

ለፈው ሰሞን አየር ጤና አካባቢ ነበር ያደርኩት፡፡ ጧት 1፡30 ገደማ ላይ የእህቴ ልጅ ስሜን ጠርታ፤ “ተነስ! ተነስ! ሰማይ ላይ ትልቅ ባሉን እየተንሳፈፈ ነው” ብላ ቀሰቀሰችን፡፡ ፈጥኜ ስወጣ፣ ቤተሰቡ በሙሉ በሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ ወደ ላይ አንጋጦ፣ “ምን ጉድ ነው? ደግሞ’ኮ የዘመን ባንክ አርማ ነው የለበሰው” ሲሉ ሰማሁ፡፡ ስለጉዳዩ አውቅ ስለነበር፣ ምን እንደሆነ ነግሬአቸው ወደቤት ተመለስኩ፡፡

ረፋድ ላይ ለኢንጂነር አሃዱ በዛ ደውዬ፣ “ባሉናችሁን አየሁት” አልኩት፡፡ እሱም፣ “አዎ! ዛሬ ከሳር ቤት ተነስተን በአምቦ (በኮልፌ) መስመር በርረን አንድ እርሻ ውስጥ አርፈናል፤ ያው ሁልጊዜ ማረፊያችን እርሻ ውስጥ ነው” አለኝ፡፡ የመጀመሪያ በረራቸውን እሁድ (የካቲት 4 ቀን) ከጃንሜዳ ተነስተው እንደሚያደርጉ አውቅ ስለነበር ለማረጋገጥ “እሁድ በረራችሁ እንዴ?” ስል ጠየኩ፡፡ “አይ፤ አየሩ ጥሩ ስላልነበር ተሰረዘ” አሉ፡፡ “የዛሬው የመጀመሪያችሁ ነዋ”! “የመጀመሪያውን በረራ ከትላንት በስቲያ ማክሰኞ ነው ያደረግነው” አለኝ፡፡

እናንተም ሰሞኑን የዘመን ባንክ አርማ ያለው ባሉን (ፊኛ) በአዲስ አበባ ሰማይ ጧት -ጧት ሲንሳፈፍ አይታችሁ ይሆናል፡፡ ምን መሰላችሁ? ሆት ኤር ባሉኒግ ይባላል፡፡ በሙቅ አየር የተሞላ በራሪ ባሉን (ፊኛ) እንደማለት ነው፡፡ “አቢሲኒያ ባሉኒግ” የተባለ ድርጅት በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ያካሄደው የመዝናኛና የማስጐብኛ ሲስተም ነው፡፡

ድሮ፣ ልጅ ሳላችሁ ወፎችና አሞራዎች በአየር ላይ ሲበርሩ ወይም ቢራቢሮዎችና ንቦች፣ ከአንዱ አበባ ወደ ሌላው እየበረሩ የማር ወለላ ሲቀስሙ አይተውና ተገርመው ይሆናል፡፡ ምናልባትም “ምነው እኔም እንደነሱ መብረር በቻልኩ!” ወይም “በወፎቹና በአሞራዎቹ ላይ ተቀምጬ እየበረርኩ ከዳመናው ጋር በተጫወትኩ፣ …” በማለት ተመኝተው ይሆናል፡፡

እነሆ ዛሬ፣ አቢሲኒያ ባሉኒግ፣ ልጅም ሆነ ታዳጊ፣ ወጣትም ሆነ ጐልማሳ፣ ሙሉ ሰው፣ አረጋዊ፣ … ፆታ ሳይለይ ቁመቱ ከ1.20 ሜ በላይ የሆነ ሰው ሁሉ ምኞቱ ሕልም ሆኖ እንዳይቀር የመሬት ስበት (ግራቪቲ) ሳይገድ፣ የዚችን ዓለም ጣጣ ሁሉ ረስተው፣ በልጅነት አዕምሮዎ ከፈጠሩት ሐሴት ጋር የሚመሳሰል ደስታ እንዲያጣጥሙ አቢሲኒያ ባሉኒግ፣ በሞቃት አየር የተሞላ የባሉን በረራ ይዞላችሁ ብቅ ብሏል፡፡

እንዴት ነው ይህ በረራ የሚናወነው? ወይም ሞተር በሌለው ባሉን መብረር የሚቻልበት ዘዴ እንዴት ነው? … የሚል ጥያቄ ሊሰነዘር ይችላል፡፡ ዘዴው ቀላል ነው፡፡ ባሉኑ መጀመሪያ በቀዝቃዛ አየር ይሞላል፡፡ ከዚያም የጋዝ ምድጃ ይለኮስና ባሉኑ ውስጥ ያለው አየር እንዲሞቅ ይደረጋል፡፡ ቀጥሎ ያለው የፊዚክስ ሥራ ነው - ቀዝቃዛ አየር ከሞቃት አየር የበለጠ ይከብዳል ወይም ክብደት አለው፡፡ ስለዚህ፤ ባሉኑ ውስጥ ያለው አየር ቀላል ስለሆነ በአየር ግፊትና ፍጥነት ብቻ እየተመራ በአየር ውስጥ ይንሳፈፋል - ይኼው ነው ምስጢሩ፡፡

ለመሆኑ ይህ ቴክኖሎጂ እንዴት በአገራችን ሊጀመር ቻለ? የዛሬው ኢንጂነር የያኔው አቶ አሃዱ በዛ ከሀገሩ ወጥቶ ሆላንድ መኖር የጀመረው በ1984 ዓ.ም ነበር፡፡ እዚያ ተምሮ የኮምፒዩተር ኢንጂነር ሆኗል፤ ትዳር መሥርቶ ልጆች አፍርቷል፡፡ በተማረው እውቀት በተለያዩ መ/ቤቶች እንደሠራ የሚናገረው ኢ/ር አሃዱ፣ ጓዙን ጠቅልሎ ወደ አገሩ ከመመለሱ በፊት ይሠራ የነበረው “ኮምፒዩተር ሰርቪስስ ኮርፖሬሽን” ለተባለ የአሜሪካ ድርጅት ነበር፡፡

ኢ/ር አሃዱ የተወለደው እነሞር ሲሆን በልጅነቱ መጥቶ ያደገውና የተማረው አዲስ አበባ ነው፡፡ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን ዳግማዊ ምንሊክ ት/ቤት ተምሮ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገባ፡፡ ትምህርቱን አቋርጦ መብራት ኃይል ማሠልጠኛ ተቋም ውስጥ  ሠልጥኖ ሥራ ጀመረ፡፡ ትምህርቱን ዘመቻ መምሪያ፣ በመጨረሻ ደግሞ የታክሲ ባለንብረቶች ማኀበር ሲቋቋም ዋና ጸሐፊ ሆኖ ታክሲ ያሽከረክር ነበር፡፡ ከ15 ዓመት የውጭ አገር ቆይታ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲመለስ አገሩን እንዴት አገኛት ይሆን?

“ያየሁት ነገር ከማምነው በላይ ነው የሆነብኝ፡፡ ብዙ ነገር ተለውጧል፤ የታክሲ

ሾፌር ስለነበርኩ የአዲስ አበባን መንገዶች አውቃለሁ እል ነበር፡፡ ነገር ግን አሁን ስመጣ ሁሉም ነገር ተለዋውጧል፡፡ በየት ወጥቶ በየት እንደሚገባ ግራ ገባኝ፡፡ አገራችን እያደገች መሆኑን ተገነዘብኩ፡፡ እዚህ መኖር፣ እዚህ መሥራት ይቻላል፡፡ … እንዴት ነው በዚያ አገር ደረጃ መኖር፣ ልጆቼን ማስተማር፣ … የምችለው እያልኩ ማሰብ ጀመርኩ፡፡ ድሮ፣ እንዴት ከአገሬ ልውጣ? እየተባለ ነበር የሚታሰበው፡፡ አሁን ደግም እንዴት ወደ አገሬ ልመለስ? ሆነ ጥያቄው፡፡

“እዚህ ተመልሶ ቢዝነስ መሥራት ይቻላል የሚል እምነት አደረብን፡፡ ቢዝነስ ከተሠራ ደግሞ እዚህ ያለውን ዓይነት ሌላ ዳቦ ቤት ሳይሆን፣ አዲስ የፈጠራ ውጤት መሆን አለበት ብዬ ወሰንኩ፡፡ ብዙ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ አዲስ ነገር መጀመር ብዙ ሪስክ (ችግር) አለው (ሊያከስር ይችላል) ተብሎ ስለሚሰጋ፣ የተለመደውን ዓይነት ቢዝነስ ካልሆነ በስተቀር፣ ፈታኝ የሆነ ነገር አይደፈርም፡፡ እኔ ግን ከሙያዬም ውጭ ቢሆን አዲስ ነገር ልጀምር ታግዬ፣ ውጤታማ አደርገዋለሁ ብዬ ወሰንኩ፡፡

ሆት ባሉን በተለያየ ቀለምና ቅርፅ (የእንቁራሪት ቅር…) ጧትና ማታ በአውሮፓ አየር ላይ  ሲበርሩ ማየት በጣም ያስደስታል - በጣም ይገርማል፡፡ አፍሪካ ውስጥ የት እንዳለ ስፈልግ ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ግብፅ፣ … እንዳለ ተረዳሁ፡፡ ለምሳሌ በኬንያ ይህን አገልግሎት የሚሰጡ አራት ድርጅቶች አሉ፡፡ ኢትዮጵያስ ለምን አንድ አይኖራትም ብዬ ተነሳሁ” ይላል ኢ/ር አሃዱ፡፡

የቢዝነስ ሐሳቡን ይዞ ወደ ሆላንድ ተመለሰና እውቀቱና ልምዱ ባይኖረውም ቢዝነስ ፕላኑን መሥራት ጀመረ፡፡ ከዚያም በዓመቱ (2009) አገራችን ገብተን መሥራት እንፈልጋለን የሚሉ 11 ሰዎችን ጋር መጥቶ አገሪቷ ለቢዝነስ አመቺ መሆኗን የተለያዩ ድርጅቶችን፣ ባንኮችን፣ ቀደም ሲል ከሆላንድ መጥቶ መኪና መገጣጠም የጀመረውን ሆላንድ ካር፣ የአገሪቷን የቢዝነስ ሕጐች፤ የቢዝነስ ማበረታቻዎች፣ … ተመለከቱ፡፡ አብረውት የመጡት ሁለት ሳምንት ቆይተው ሲመሉሰ፤ እሱ አንድ ሳምንት ጨምሮ ጐብኝቶና ሐሳቡን አጠናክሮ ተመለሰ፡፡ ይሁን እንጂ ሁለት መሰናክሎች ገጠሙት፡፡ አንደኛው በዘርፉ እውቀትና ልምድ ያለመኖር ሲሆን፤ ሌላው ደግሞ የሚያስፈልገው የኢንቨስትመንት መጠን ትልቅነት ነበር፡፡ ስለዚህ፣ በሽርክና አብሮት የሚሠራ ሰው (ድርጅት) መፈለግ ጀመረ፡፡

አንድ ሰው ቢያገኝም፤ በአንዳንድ ነጥቦች ስላልተስማሙ እሱን ትቶ ሌላ መፈለግ ጀመረ፡፡ ከዚያም Virgin Balloans Benclux ከሚባል የ30 ዓመት ሰፊ ልምድ ያለውን ትልቅ ኩባንያ፣ ጥሩ ቢዝነስ ፕላን ስላለኝ አብረን እንሥራ አላቸው፡፡ ያነጋገረው የዛሬ ሸሪኩን Bram Van Loosbroek ነበር፡፡ ብራም በሐሳቡ ቢስማማም መጀመሪያ አገሪቷን ልይ አለው? ከዚያም ከጓደኛው ጋር መጥቶ አያትና በጣም ወደዳት፡፡ ቢዝነስ ፕላኑን አሻሽለው ወጪውንም ሆነ ትርፉን ለመካፈል፣ አቢሲኒያ ባሉኒግ ኃ.የተ.ማ. በ50 በመቶ እኩል ድርሻ አቋቋሙ፡፡   በሆላንድ ፕራይቬት ሴክተር ኢንቨስትመንት (PSI) የሚባል ፈንድ አለ፡፡ ይህ ፈንድ፣ ከታዳጊ አገሮች የሚቀርቡ አዳዲስ የቢዝነስ ፕላኖችን ያበረታታል፡፡ በዚሁ መሠረት ኢ/ር አሃዱና ሚ/ር ብራም በኢትዮጵያ ለመሥራት ያቀረቡት ቢዝነስ ፕላን ከ140 ፕሮፖዛሎች ውስጥ አንደኛ ሆኖ በመመረጡ የኢንቨስትመንቱን ግማሽ ካፒታል (50 በመቶ) ከሆላንድ መንግሥት ማግኘታቸውን ተናግሯል፡፡

የፕሮጀክቱ ካፒታል ምን ያህል ነው?

500ሺ ዩሮ ወይም ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ ግማሹን ከሆላንድ መንግሥት አግኝተናል፡፡

ባሉኑ መሪ አለው?

ሆት ኤር ባሉን ለየት የሚያደርገው ነገር፣ ሞተር የለውም፣ መሪ የለውም፡፡ የሚጓዝበትን ፍጥነትና አቅጣጫ የሚወስነው የወቅቱ ነፋስ ነው፡፡ አብራሪው ወይም ፓይሌቱ የሚያደርገው ነገር ባሉኑን ወደ ላይ ማውጣትና ወደ ታች ማውረድ ብቻ ነው፡፡ ፓይለቱ ከምድር በላይ ያለውን ከፍታ መወሠን ይችላል፡፡

የባሉኑ መጠን ምን ያህል ነው?

ትልቅ ነው፡፡ 30 ሜ. ቁመትና 20 ሜ. ስፋት አለው፡፡ አንድ ፎቅ 3ሜ. ቁመት ቢኖረው የ10 ፎቅ ከፍታ አለው ማለት ነው፡፡

ባሉኑ ምን ያህል ሰዎች መያዝ (ማሳፈር) ይችላል?

አሁን ያመጣነው ከ10-12 ሰዎች መያዝ የሚችል ነው፡፡ ነገር ገን የተለያየ መጠን ያላቸው ባሉኖች አሉ - ሁለትና ሦስት ሰው እስከ 30 ሰው የሚይዙ ባሉኖች አሉ፡፡

ምን ያህል ባሉኖች አላችሁ?

አሁን ያለን አንድ ነው፡፡ ሁለት፣ ሦስት እያልን በ5 ዓመት ውስጥ 10 የማድረስ ዕቅድ አለን፡፡

ታሪፋችሁ (ዋጋችሁ) ምን ያህል ነው?

በየወቅቱ በየጊዜውና በየቀኑ የሚቀያየር ነው፡፡ የዕረፍት ቀንና የሥራ ቀን ታሪፍ አለን፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የውጭ ዜጐች (የቱሪስቶች) እና ለኢትዮጵያውያን የተለያየ ታሪፍ አለን፡

በአጠቃላይ ስንመለከተው ታሪፋችን ከ250 እስከ 450 ዶላር ይደርሳል፡፡ ከዚህም በላይና በታች ሊኖር ይችላል፡፡ ለልጆችና ለተማሪዎች የተለየ ታሪፍ ይኖረናል ብዬ እገምታለሁ፡

እንዴት ነው ታሪፉ አልበዛም? የኢትዮጵያዊውን አቅም ያገናዘበ ነው?

ብዙ ጥቅም ለማግኘት ብለን አይደለም እንዲህ ያደረግነው፤ ብዙ ወጪ ስላለው ነው፡፡ ባሉኑን የሚያበርሩት ፓይለቶች የሚመጡት ከውጭ አገር ነው፡፡ ትልቁ ወጪ የእነሱ ደሞዝ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ የባሉኑ ወጪ ነው፡፡ ይኼ ባሉን ከ100ሺ ዩሮ በላይ ነው የተገዛው፡፡ (2.2 ሚ.ብር ያህል ማለት ነው) ሌሎች ባሉኖችን መጨመር የምንችለው እንደዚህ ካስከፈልን ብቻ ነው፡፡ ሌሎች አገሮች ከዚህ በላይ ነው የሚያስከፍሉት፡፡ ለምሳሌ በኬንያ 500 ዶላር ነው፡፡ እኛ ዝቅ ያደረግነው ለማስለመድና የአገራችን ሰው አቅም የለውም ብለን ነው ሁለት ታሪፍ ያደረግነው፡፡

የከፍታ ፍርሃት ሮቢያ ያለበት ሰው በባሉን መሳፈር ይችላል?

ከፍ ካለ ፎቅ ላይ ወጥቼ ወደ ታች ማየት አልችልም የሚሉ ሰዎች ሊኖሩ ይችላል፡፡ የሚገርመው ነገር ግን አንድ ሰው ሆት ኤር ባሉን ላይ ወጥቶ የቱንም ያህል ከፍታ ቢወጣ የከፍታ ፍርሃት የሚባል ነገር አይኖርም፡፡ ለምን እንደማይኖር ታውቃለህ? ያለበትን ከፍታ የሚያነፃጽርበት ምንም ነገር የለም፡፡ የሚሄደው በነፋስ ፍጥነትና አቅጣጫ ነው፤ ሁለተኛ ግራቪቲ የለም፤ ወደፊት እንጂ ወደ ታች አያይም፡፡ ስለዚህ ቤት ውስጥ የቆመ ያህል ነው የሚሰማው፡፡ የእኔ ሸሪክ ብራም አባቱና ወንድሙ የከፍታ ፍርሃት (ፎቢያ) አለባቸው፡፡ የሚገርመው ነገር ሦስቱም የሆት ኤር ባሉን ፓይለቶች ናቸው፡፡

የሆት ኤር ባሉን አደጋ ምን ያህል ነው?

ማንኛውም ነገር ሪስክ (አደጋ) አለው፤ ሆት ኤር ባሉን ግን በቂ ልምድና ችሎታ ባለው አብራሪ ከበረረ የለውም፡፡ የባሉን በረራ፣ የመኪና መንገድ የማቋረጥ ወይም መኪና የመንዳት ያህል እንኳ አደጋ የለውም፡፡

ለምሳሌ የእኛ ሸሪክ ድርጅት ከ25 ዓመት በላይ ሲሰሩ በርካታ ሺ በረራዎች አድርገዋል ነገር ግን አንድም ቀን አደጋ አልደረሰባቸውም፡፡ አውሮፕላን አደጋ ካጋጠመው ሰው ላይተርፍ ይችላል፡፡ ይኼኛው፤ ነፋስ ባይኖር እንኳ ቀጥ ብሎ ይቆማል እንጂ ምንም አይሆንም የሚበርበት ጋዝ ቢያልቅ ወይም ባይሰራ እንኳ፡፡ ባሉኑ ራሱ እንደ ፓራሹት ሆኖ ያወርዳል፡፡ ፕሮፌሽናል ፓይሌቶች ግን መኖር አለባቸው፡፡

ስለዚህ፣ የአገር ውስጥ ፓይሌቶች ቢሰለጥኑም በቂ ልምድ እስኪያካብቱ ድረስ ቶሎ ሥራ እንዲጀምሩ አናደርግም፡፡

ተሳፋሪውን የሚደግፍ ነገር አለ?

ሰዎችን የሚደግፍ ቅርጫት አለ፡፡ የቅርጫቱ ቁመት 1ሜ ከ20ሳ.ሜ ነው፡፡ ከወገብ በላይ ደረት አካባቢ ስለሚደርስ ይደግፋቸዋል ማለት ነው፡፡ መቀመጥ ግን የለም፤ ቆመው ነው የሚሄዱት፡፡

አብሯችሁ የሚሰራው ኩባንያ ማን ነው?

ቨርጂን ባሉን ቤነሉክስ ይባላል፡፡ ድርጅቱ አውሮፕላን፣ መጻሕፍት፣ ባሉኖች አለው፡፡ የዚህ ድርጅት ባለቤት፣ ሪቻርድ ብራንሰን በዓለም ላይ በጣም የታወቀ ነው፡፡ በቅርቡ ቱሪስቶችን ወደህዋ የሚያመጥቀውን መሳሪያ የሚሠራውም ይኼው ድርጅት ቨርጂን ነው፡፡ ቨርጂን፣ በዓለም የታወቀ ስም ስለሆነ፣ ቱሪስቶች ሲመጡ ምንም አይነት ስጋት አይገባቸው ማለት ነው፡፡ ለዚህ ነው ከእነሱ ጋር መሥራት የመረጥኩት፡፡

የባሉን በረራ/ወ ለምን ለምን ሊያገለግል ይችላል?

ለቱሪስት፣ ለጋብቻ (ሙሽሮችና ሚዜዎች) ለልደት፣ ለክብረ በዓላት፣ ለፍቅረኞች፣ ለተለያዩ በዓላት፣ ለተማሪዎች፣ ለተሰብሳቢዎች እንዲሁም ለማስታወቂያ ሊያገለግል ይችላል፡፡

ይህን የባሉን በረራ አገልግሎት የት የት ነው  ለመስጠት ያሰባችሁት?

በአዲስ አበባ፣ ሀዋሳ፣ ነጭ ሳር ፓርክ፣ በሰሜን ተራሮች፣ ጐንደር፣ ላሊበላ አክሱምና በሌሎች ታሪካዊ ስፍራዎችን ለመስጠት አቅደናል፡፡

የዘመን ባንክ አርማ የምትጠቀሙት ለምንድነው?

ዘመን ባንክ ስፖንሰር እንዲያደርገን ጠየቅነውና ፈቃደኛ ሆነ፡፡ ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት የዘመን ባንክን አርማ (ሎጐ) ይዞ በምድራችን ላይ እንዲበር ተስማምተናል፡፡

የወደፊት ዕቅዳችሁ ምንድነው?

የባሉኖችን ቁጥር መጨመርና በቀጣይ አስርና ሃያ ዓመታት መጠነኛ ገቢ ያለው ኢትዮጵያዊ ሁሉ በባሉን መንሳፈፍ የሚሰጠውን ደስታ እንዲያይ (ልምድ እንዲኖረው) ማድረግ ነው፡፡

 

 

Read 3229 times Last modified on Saturday, 25 February 2012 15:40