Saturday, 25 February 2012 13:54

ከስብሐት ገ/እግዚአብሔር እረፍት ጀርባ “ሌላ ወግ“

Written by  ገዛኸኝ ፀ
Rate this item
(7 votes)

“...ሙሉ ደራሲ ነኝ አልልም፡፡ ድርሰት ሚስቴ አይደለችም፤ ውሽማዬ ናት”

“ለካ በደግ ዓይን ሲያዩኝ ይህንን እመስላለሁ?! ገርሞኝም አላባራ!”

“...እኔ ከማልኖር አለም ሁሉ ብትጠፋና እኔ ብኖር እመርጣለሁ! ቢቻል?’’

“...ሰው እያለ አጠገባችን

ቅንነቱን ማየት ሲያመን

ከኛ አብሮ በሕይወት ቆሞ፤ መልካሙን ስምን

መጥራት ሲያንቀን

“ሰው ካልሞተ ወይ ካልሄደ አይነሳም” እንላለን

እንዲህ እያልን፤

ስንቱን ጠቢብ እየሸኘን፤

አበባውን ቀጥፈን ጥለን፤ አበባ (እ) ናስቀምጣለን!!”

ይህ ግጥም የታዋቂው ዘመነኛ ገጣሚያችን የነቢይ መኮንን ስለመሆኑ ዘነበ ወላ “ማስታወሻ” በሚል ካሳተመው የስብሐት ታሪክ መፅሐፍ ላይ ነግሮናል፡፡ እኔም እንዳለች ነው የገለበጥኳት፤ “ማን ገልብጥ አለህ?” አትሉኝም? መልሴ አጭርና ግልጽ ነው - ማንም፡፡ ግን የጋሽ ስብሐትን መሞት ስሰማ፤ እስከዛሬ ያላነበብኩትን መፅሀፍ (“ማስታወሻ”) በብርሃን ፍጥነት ነው የገዛሁት - አንጀቴን አስሬ፡፡

እኛ ሃገር መቼም ለሞተ ሰው ያለን እንትን... ማለቴ ወግ የጉድ አይደል፡፡ በተለይ ደግሞ እንደ ጋሽ ስብሃት፤ በህይወት እያለ አለቃ ገብረሃናን ይመስል፤ ያለውን ያላለውን የሚወራበት የተረት ገፀባህሪ አይነት ሰው ሲሞት ብዙ ነው የሚወራለት፤ ሰሞኑን እንግዲህ የኢትዮጵያ ማስሚዲያ በሉ ሚኒሚዲያ ስራቸዉ ጋሽ ስብሃትን ማስታወስ ነው፤ በርግጥ በትህትና “ማስታወስ” አልኩ እንጂ ጉዳዩ እንኳን “ማማት” ነው ሊባልም ይችላል፡፡

ማስታወሻውን ከታቢው ዘነበ ወላ እህቱን “ሪፈረንስ” አድርጎ ጋሽ ስብሐት አዉቶብስ ላይ ያደረገዉን ለራሱ ለጋሽ ስብሐት አወጋው፡፡ ጋሽ ስብሃትም ሳቅ አለና ‘”በቃ በህይወት እያለሁ ተረት ልሆን ነው?” አለው፤ ዘነበም “አልቀረልህም!’ አይነት መልስ መልሶ ወጣቶች እንደሚወዱት፣ እንደሚገጥሙበት፣ እንደሚስሉበት፣  እንደሚያሳብቡበት፣ … ነገረው:: በርግጥ ጋሽ ስብሐት ባልንጀራዉ ደራሲ በአሉ ግርማ፣ አንድ አይሉ ሁለት ጊዜ ገፀባህሪ አድርጐ  በቃላት ፎቶ እንዳነሣው ይታወቃል - በኋላ ላይ ደግሞ ዘነበ ወላ ታሪኩን በግሩም ሁኔታ ከተበለት - ብራቮ ዘኔ፤ እንዳልከው ሞትን ቀድመሃል! እሡሥ ቢሆን፣ “ስናወራ … ስናወራ … ሳናስበው ይህ መጽሐፍ ብቅ ማለት ጀመረ፡፡ ተናገርኩ፣ መዘገበ፣ ፃፈ፡፡ በስድሳ አመት ዕድሜዬ ይህ ዘነበ በሚከተሉት ምዕራፎች እንደምታነቡት በቃላት ፎቶ አንስቶኝ አየሁ፡፡ ለካ በደግ አይን ሲያዩኝ ይህን እመስላለሁ?! ገርሞኝም አላባራ!” ማለቱ ለዚህም አይደል - በድጋሚ ብራቮ ዘነበ፤ ይህ መጽሐፍ ሣይፃፍ ቀድሞ ቢሆን፣ የአንድ ስብሐት ብቻ ሞት አይደለም - የሃገርም ሞት ይሆን ነበር!

የጋሽ ስብሐት እድሜ ሲነሣ፣ የእድሜው ስሌት፣ መዘበራረቁ ገረመኝ፤ አሁን ከሞተ በኋላ ማለቴ ነው፡፡ ጋሽ ስብሃት በሕይወት እያለ፣ አዘጋጁን ጌጡ ተመስገን ሆነ ኢቴቪን ያስመሰገነ “ሰው በምድር …” በተባለ ዝግጅት ላይ የተናገረው እድሜው ትዝ አለኝ፤ “አጋፋሪ እንደሻውና እኔ ሞትን አንፈልግም፤ እንፈራዋለን … እንደውም ለእናንተ ብዬ ነው እንጂ ስለሞት ማውራት አልፈልግም፤ አመስግኑኝ አሁንም፣ በጭብጨባ!” እያለ ለራሡ አጨብጭቦ አዘጋጁን ጌጡ ተመስገንንም ሆነ እኛን አስቆናል፡፡

በዚሁ ጊዜ ታዲያ፣ (መርሃ ግብሩ የተላለፈው ጥር 2002 ዓ.ም ነበር) ጋሽ ስብሐት ሞት ላይ ብዙ መፈላሰፉን በአንደበቱ ነገረን፤ “ይልቅ ሞት ብዙ ጊዜ ፊክሽን ነው … ተረት ነው፡፡ እኔ አሁን እየው ስንት ጊዜ ስለሞት ሣሥብ፣ ሥፅፍ 74 ዓመት ኑሬያለሁ፤ ውሸት ነበር ሞት እስከ አሁን … ስትሞት ብቻ ነው እውነት የሚሆነው … ከዚያ በኋላ ደግሞ አታውቅም፤ ከሞትክ በኋላ ምን እንዳለ?” አለን፡፡ እርግጥም ከሞት በኋላ ምን እንዳለ ማን ያውቃል? ንግግሩ ላይ ታዲያ 74 ዓመት እንደሞላው መመስከሩን ልብ በሉ፡፡ ከተናገረ ደግሞ ሁለት ዓመት አለፈው … ሥለዚህ ዛሬ ስብሐት የ76 ዓመት “ጐረምሣ” ነበር ማለት ይቻላል - “ጐረምሣ” ማለቴ ዛሬ በአካል እንደሆነ እንጂ በመንፈስ አላረጀም፤ ጐረምሣ፣ ወጣት ነበር፤ የዛሬ ሣምንትም በዚሁ ጋዜጣ ጽፎልን አልነበር?

ወደ እድሜ እንለፍ … የህይወት ታሪኩን ታዋቂው ተዋናይን ተፈሪ ዓለሙ ሲያነብልን 75 ዓመት የሚል የሰማሁ መሰለኝ? ማታ ላይ ደግሞ በአሜሪካ ድምጽ የአማርኛው ስርጭት ላይ 84 ዓመቱ እንደሆነ ተነገረ፡፡ “አይ የኛ ነገር?” የአንድ ታዋቂ ደራሲ እድሜ እንኳን በአንድ ቃል መናገር የማንችል የእውቀት  ድሆች ነን!” የምትል ሂስ ቢጤ ልሠነዝር ፈለግኩና “አንድ ሃገር ሙሉ ህዝብ የምተች እኔ ማን ነኝ?” ብዬ ተውኩት … በኋላ ላይ ግን ዘነበ ከከተበው ማስታወሻ ላይ ጋሽ ስብሐት ሚያዝያ 27 ቀን በ1928 ዓ.ም መወለዱን አነበብኩ፤ ፈንታሁን እንግዳ ከፃፉት “ታሪካዊ መዝገበ-ሰብ” መጽሐፍ ላይ ሚያዝያ 24 ቀን ይላል… መረጃዎች እየመረመርኩ በሄድኩ ቁጥር “ኢትዮጵያዊ መልኩን፣ ነብር ዥንጉርጉርነቱን” እንዳይለውጡ ፈርቼ ተውኩት፡፡

አሁን እኔን እያሳሰበኝ ያለው፣ ከገድላችን ይልቅ፣ ከገድላችን ጀርባ የሚሰለቀው ወግ እየሳበኝ መምጣቱ ነው፡፡ ዶ/ር ፈቃደ አዘዘ እንደሚሉት፣ “በህዝባዊ ኢንተርኔቱ” የሚለቀቀው የእንደወረደ ወሬ እኮ የጉድ ነው… በነገራችን ላይ በስላሴ ካቴድራል በጋሽ ስብሃት ቀብር ላይ፣ ጋሽ ስብሃት ከወዳጁ ከደራሲ በዓሉ ግርማ ቮክስቫገን መኪና ውስጥ፣ የጠርሙስ አንገት ጨብጠው ከሚጨዋወቱ ከያን ጊዜው ባልንጀራዎቹ መካከል፣ ጋሽ አስፋው ዳምጤና ዶ/ር ፈቃደ አዘዘን አይቻቸዋለሁ… ከሞተ በኋላ ሥላለው ነገር ማን ያውቃል እንዳለው፣ አሁን በሄደበት የሞት መንደር፣ ከበዓሉ ግርማና ከያኔው ባልንጀራው ደበበ ሰይፉ ጋር ተገናኝቶ፣ ስለ ማርክሲስታዊ ሥነ ፅሁፍና ስለ አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ስነፅሁፍ ይወያዩ ይሆናል… ማን ያውቃል? ስለ “ልማታዊ ግጥሞች”፣ ስለ ብሔረሰቦች ሙዚቃ እድገትና ውድቀት ሁሉ የሰላ ሂስ ይሰነዝሩ ይሆናል፡፡ ጋሽ ስብሐት እስከ አሁን መቆየቱ፣ የኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያምን “ትግላችን” መፅሐፍ መታተሙን እንዲያይ አበቃው፤ ከበዓሉ ጋር ከተገናኙም፣ (በርግጥ ጋሽ ስብሐት በበዓሉ መሞት ላይ የሚጠራጠር ይመስላል) “ሰውየው እንኳን ሥለአንተ፣ አፄ ኃይለስላሴም እንዴት እንደሞቱና ከፅህፈት ቤታቸው ወንበር ሥር መቀበራቸውን እንደማያውቁ ተናገሩ!” በማለት ስለ ያኔው ቆራጡ አብዮታዊ መሪያቸው “ከሃዲነት” አጀንዳ ያሲዝ ይሆናል… እዚህ ላይ፣ በዓሉ “ዛሬም አብዮታዊ ደራሲዎች አሉ?” ብሎ ከጠየቀው ደግሞ “አይ አሁን ሁሉም ልማታዊ ደራሲዎች እየሆኑ ነው!” ይል ይሆናል… ማን ያውቃል…

በጋሽ ስብሃት ቀብር ላይ የተለያዩ ወሬዎች ጦፈው ነበር፡፡ እኔ ምለው ግን…. እቺ አብዮታዊ ዲሞክራሲያችን የፈጠረችው ብሔር ተኮር ንቃተ ህሊናችን መቃብር ደጅ ላይ እንኳን ሆነን ትከታተለናለች… እናም እላችኋለሁ በቀብሩ እለት የጋሽ ስብሐትን ታዋቂነት ያህል ባይሆንም ብዙ ታዋቂ፣ ስመጥር ሰዎች ነበሩ፡፡ በየጋንታው እየተከፋፈለ ሰው ያወራል… በደንብ ያወራል… “ኧረ እንደ ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን እዚህ አይቀበርም ብለው ጉድ እንዳያፈሉ?” አንደኛው ታዋቂ ደራሲ ድምፁን ዝቅ አድርጐ ተናገረ፡፡ እኔም ያለ ደረጃዬ ከተራው ቀባሪ ፈንጠር ብዬ ከታዋቂ ሰዎች ጀርባ ቆሜያለሁ…. እንደተባለው እንደ ጋሽ ፀጋዬ ገብረመድህን የጋሽ ስብሐትም ቀብር ይስተጓጐል ይሆን ብዬ ጭንቅ ገባኝ….

እዚህ ላይ አሁን “ምን አግብቶህ ነው ጭንቅ የገባህ…. እንኳን አንተ ጋሽ ስብሐት እራሱም ከሞተበት ተነስቶ የቀብሩን ሁኔታ ቢያይ አይጨንቀውም! እንደውም ይገርመው ይሆናል?...” ልትሉኝ ትችላላችሁ፤ እርግጥ ነው ጋሽ ስብሃት የሃይማኖት ጉዳይ፣ የቀብር ጉዳይ፣ የሚያስጨንቀው እንዳልሆነ ይነገራል፡፡ ዘነበም በ”ማስታወሻ”ው ገፅ 21 ላይ “የጋሼ ስብሐት አባት፣ አያትና ቅድመ አያቱ… አሥራ አራት ትውልድ ድረስ ቀሳውስት ናቸው፡፡ እሱም በልጅነቱ የኦርቶዶክስ ኃይማኖት ተከታይ ነበር፡፡ አዲስ አበባ እንደመጣ የፕሮቴስታንት እምነት ተቀበለ፡፡ ይህ አጋጣሚ መፅሐፍ ቅዱስ እንዲያውቅ አድርጐታል፡፡ ከዚህ ታላቅ መፅሐፍ የገበየው እውቀት ለፈጠራ ሥራው በጥልቀት ጠቅሞታል፡፡ በአሁኑ ሰዓት በእምነት ደረጃ ከመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚቀበላቸውም፣ የማይቀበላቸውም ምዕራፎች አሉት፡፡ እግዚአብሔር የለምም፣ አለምም አይልም፡፡”

እናም እላችኋለሁ፣ የጋሽ ስብሃትን የቀድሞ ፕሮቴስታንትነት ጠይቀው፣ አርበኛ ሆኖ አልተዋጋም ብለው አሳብቀው፣ የሀገር ወግ ልማድ ምናምን መጠበቅ (“በሥነ ምግባር አርአያ አይደለም”) አይነት አጉል ሃሳብ አርቅቀው እንዳይቀበር ይላሉ ብዬ መስጋቴ ልክ መሰለኝ፤ ለነገሩ ሌሎችም ሲሰጉ ነበር፡፡

ኋላ ላይ ግን በጣም ተደሰትኩ፤ በተለይ በፓትሪያርኩ በአቡነ ጳውሎስ (ማዕረጋቸውን ሁሉ ያልገለፅኩት… በመርዘሙ ነውና ይቅርታ!) ፍታት ተደርጐለት ተቀበረ፡፡ እንደውም አቡነ ጳውሎስ እረጅም ንግግር ሲያደርጉ፣ ብዙ ሰዎች አቋርጠው መሄዳቸውን ሳይ ተናድጄ ነበር፡፡ ሰው ንግግራቸውን ጨርሶ ቢያደምጥ ምን አለበት?

አንዱ ታዋቂ ደራሲ (ስሙን መጥቀስ አልፈለግኩም) ባልንጀራው፣ የጳጳሱን ረጅም የማፅናኛ ንግግር አቋርጦ ሲሄድ፣ “ምነው ቆይ እንጂ!” ቢለው፣ “መቆም ደከመኝ! ፍታቱ ልማታዊ ሆነብኝ!” ማለቱን በጆሮዬ በብረቱ አድምጫለሁ፡፡ እንደውም የስብሐት መፅሐፍ መነበብ እንዳለበት የሰጡትን ምክር ሳይሰማ በመሄዱ ጓደኛው ሲበሰጫጭ ነበር፡፡ ለካ የሀገሬ ወግ የሚጣፍጠው፣ ዶ/ር ፈቃደ እንደሚሉት፤ “በህዝባዊው ኢንተርኔት” ታጥቦና ተቀሽሮ ሲቀርብ ነው….

ጋሽ ስብሃት “ሃይማኖት የለውም!” ብለው እንዳይቀበር የፈለጉ አንዳንድ “ፀረ ልማት የቀብር ስርአት አስፈፃሚዎችን”፣ ፓትሪያሪኩ ኩም ሲያደርጓቸው ሳይ ደስ አለኝ፡፡ በርግጥ የአንደኛው ጋንታ መሪ፣ “ስብሐት አርበኛ አይደል? እንዴት እዚህ አስቀበሩት?” ሲል፣ ሌሎቹ በፈገግታ አጀቡት፡፡

ለቀብር የመጣው ሰው በየጋንታው ተደራጅቶ ወሬውን እንደሚሰልቅ የገባኝ ከቆምኩበት ቦታ ፈንጠር ብዬ ሌሎች ቡድኖች ጋ ስጠጋ ነው፡፡ ስለ ጋሽ ስብሐት የማይወራ አልነበረም…. በድረ ገፆች ላይ በስሙ ሲለቀቁ የነበሩ፣ ፀያፍ አባባሎችና ተረቶች ሁሉ ይሰለቃሉ…. “ኧረ ግብአተ መሬት እስኪፈፀም ዝም እንበል!” በማለት ከመካከላቸው የሚመክር ወጣት የተሰነዘረበት የመልስ ምት “ሌላ ወግ” ነው… ለማንኛውም ግን ፓትሪያሪኩ፣ የጋሽ ስብሐትን መፅሐፍ ለንባብ በመጋበዝ ጭምር፣ የቀብር ሥርዓቱን በወጉ እንዲሆን ላደረጉት መልካም ተግባር ምን አለበት ብናመሰግናቸው?

ለማንኛውም…. ጋሽ ስብሃት፣ “ሙሉ ደራሲ ነኝ አልልም፣ ድርሰት ሚስቴ አይደለችም፤ ውሽማዬ ናት!” ቢልም፣ እውቁ ደራሲ መቀበሩ ቁርጥ ሆኗል፡፡ ግብአተ መሬቱ ሲፈፀም፣ ከታዋቂው ጋዜጠኛ ጌጡ ተመስገን ጋር የተነጋገረው ነገር ውስጤን እንደነካኝ አልደብቃችሁም፤ “…መሞቴን እንጃ እንጂ…. እኔ ከማልኖር አለም ሁሉ ብትጠፋና እኔ ብኖር እመርጣለሁ! ቢቻል?” ብሎ ነበር… በመጨረሻው ሰአት ግን አልቻለም - ሰው ነውና!

ሌላውን ወጌን የምቋጨው ግን፣ ነገ ብዙ በሚያነጋግረን፣ በየጋዜጦቹ በየመፅሔቶቹ ላይ ለእንጀራው ሲል ሲፅፍ “እግረመንገዱን” ብዙ ሃገራዊ እውነቶቻችንን ባረቀቀልን ታላቅ ደራሲ (ከጋሽ ስብሐት) ሃገራዊ ፍልስፍና አንዲት ቅንጣት ቆንጥሬ በማስነበብ ነው….“ዘነበ፣ ያንተ ዘር ጋሞ ነው፡፡ የኔ ደግሞ ትግሬ፡፡ ምኒልክ መጣና የምንግባባበትን የአማርኛን ቋንቋ፤ ለዜግነታችን ደግሞ ኢትዮጵያዊነትን፤ ከዚያም በላይ ባንዲራን ሰጠን፡፡ የነጮች ባሪያ ከመሆን አዳነን፡፡ ምኒልክ ባይኖር ኖሮ በምን አይነት ቋንቋ እንግባባ ነበር?”

 

 

Read 21409 times Last modified on Saturday, 25 February 2012 15:21