Saturday, 16 April 2016 10:26

እወድሃለሁ እያለ የሚጠላ፣ እፆማለሁ እያለ የሚበላ፣ እሰጣለሁ እያለ የሚነሳ፣ እነዚህን አምላክ ይጠላ (የትግሪኛ ተረት)

Written by 
Rate this item
(20 votes)

አንድ አርሶ አደር በአጥር ግቢው ውስጥ አንድ የፍሬ ዛፍ ነበረው፡፡ ሆኖም ይሄ ዛፍ ፍሬ አላፈራም፡፡ ስለዚህም አርሶ አደሩ፣
“አንተ ዛፍ፤ስንት ዓመት ሙሉ ደጃፌ ቆመህ አንዲት ፍሬ እንኳን ሰጥተኸኝ አታውቅም፡፡ አሁን መቆረጫህ ሰዓት ደርሷል - ተዘጋጅ!” አለው፡፡
በዛፉ ላይ በየቅርንጫፉ ውስጥ የሚኖሩና በጥላው የሚጠቀሙ ድንቢጥ ወፎችና አንበጣዎች አሉ፡፡ እነሱ ማረፊያቸው ሊፈርስባቸው ስለሆነ፤
“እባክህ ይሄንን ዛፍ አትቁረጥብን፡፡ መጠጊያ ታሳጣናለህ፡፡ ዛፉ የኛ መኖሪያ ከመሆኑም በተጨማሪ ለአካባቢው ጥላ ይሆናል፡፡ ነፋሻ አየርም ያመጣል” እያሉ ለመኑት፡፡
አርሶ አደሩ ግን “ምንም የማያፈራ ዛፍ ተሸክሜ አልኖርም” ብሎ መጥረቢያ ሊፈልግ ሄደ፡፡ ከልቡ ሊቆርጠው ወስኗል፡፡ መጥረቢያውን አግኝቶ መጣ፡፡ አንበጦቹና ድንቢጦቹ ደግመው ለመኑት፤
“እባክህ አያ አርሶ አደር፣ ዛፉን በመቁረጥ ምንም አትጠቀምም፡፡ ይልቁንም አያሌ ነብሳት ማደሪያ ያጣሉ፡፡ በጠዋት የሚዘምሩ ወፎች አትክልትህን ስትኮተኩት እያጀቡ ህይወትህን ያለመልሙልሃል” ሲሉ አወጉት፡፡
አጅሬ አንደኛውን ጨክኗልና ምክራቸውን አልሰማ አለ፡፡ የዛፉን ግንድም በመጥረቢያው ይመታው ጀመር፡፡ ደግሞ፣ ሰልሶ ሃይ - በል ካለው በኋላ፣ የዛፉ ውስጡ ይታይ ጀመር፡፡ በራሱ ባዶ ነው፡፡ ቀፎ ነው፡፡ ሆኖም ውስጡ ግን የንብ መንጋ ይኖር ኖሯል፡፡ በንቦቹ ዙሪያ ከባድ የማር ክምችት አለ፡፡ የዚያ ዛፍ ሆድ ዕቃ ለካ ከባድ የማር መጋዘን ኖሯል፡፡ አርሶ አደሩ በደስታ መጥረቢያውን ጥሎ ማሩን ተመለከተ፡፡ ነገር ግን ወዲያው ሀዘን ገባው፡፡
“ወይኔ! ወይኔ!” አለ፡፡ “ይህን ግንድ በህይወት ማቆየት ነበረብኝ፡፡ ውስጡ ምን እንዳለ ሳላውቅ፣ ለስንት ዘመን ማር የሚያጠራቅምልኝን ዛፍ ቆረጥኩት፡፡ ትልቅ ሀብት አፈረስኩኝ!” አለ፡፡
*        *          *
ታላላቅ ያገር ይዞታዎችን፣ የጥንት ታሪካዊ ቅርሶችን፣ በችኮላ ካፈረስን ለከባድ ፀፀት ሊዳርገን ይችላል፡፡ ውስጡ ያለውን እንመርምር፡፡ ብዙ ቅርሶቻችን የዘመናት ፍሬዎቻችን ናቸው፡፡ አንድ ነባር ዋርካ ሲወድቅ፣ በዙሪያው ያሉ የንፍቀ ክበቡ ነዋሪዎች ጥቅም ጭምር ይወድቃል፡፡ ሳናውቀው የብዙ ማህበረሰብም ኑሮ ሊናጋ ይችላል፡፡ ግንባታን ስናስብ ፍርሳታውን፣ አልፎም ልማታዊ ግቡን አበክረን ካላየን ጉዳቱ ሊበዛ ይችላል፡፡ በጥናት፣ በብልህነትና በጥንቃቄ መሰራት ያለባቸውን ነገሮች አስተውሎ ማየት ዋና ነገር ነው፡፡ ሌላው መሰረታዊ ነገር የቅርሶች አጠባበቅ ነው፡፡ ከዚሁ ጋር አስጊው ነገር ደሞ መዘረፋቸው ነው፡፡ ዘረፋ ደግሞ ባህል ሆኗል፡፡ “የአባትህ ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ” የሚለው የድሮ ተረት፣ ዛሬ የዕለት - ሰርክ ጉዳይ ሆኗል፡፡ ጥንቃቄ የሚሻው ይህ ጉዳይ ነው፡፡ ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል! የአየር ጠባይ መለዋወጡን አለመዘንጋት እጅግ ብልህነት ነው፡፡ ትላልቅ እርሻዎቻችንን መጪው የአየር ንብረት ለውጥ ምን አደጋ ላይ እንደሚጥላቸው ከወዲሁ በንሥር - ዐይን ማየት ይጠበቅብናል፡፡ ለሁሉም ነገር በሁሉም አቅጣጫ “መረጃም ማስረጃም ይኑረን” የተባለው እጅግ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ ሁሉም ፍሬ ነገር በእጃችን ያለ እየመሰለ በአፍታ ከእጃችን ያመልጣል፡፡ ተቋሞቻችን የማይናዱ ግንቦች ይመስሉንና ውስጣቸው እየተሸረሸረ አንድ ቀን ባዶ ሆነው ይገኛሉ፡፡ ዲሞክራሲ ጠንካራ ተቋማት ላይ ካልቆመ አብሮ ፈራሽ ነው፡፡ እንኳን እንደኛ አገር በአዲሱ ወለል ላይ መሰረት የሚቸክል ቀርቶ የበለፀጉትም አገሮች ስንቴ ወድቀው ስንቴ ተነስተው፣ ልብ - አድርስ የሚባል የዲሞክራሲ ዋንጫ አልጨበጡም፡፡ እነሱም ጋ ዛሬም ሙስና አለ፡፡ እነሱም ጋ ዘረኝነት አለ፡፡ እነሱም ጋ የኢኮኖሚ ድቀት (Economic Crisis) አለ፡፡ ይሄ የሚያሳየን የእኛን ዲሞክራሲና ኢኮኖሚ በቀላል ሊወድቅ መቻል ብቻ ሳይሆን፤ የእነሱንም ትኩሱን እፍ - እፍ ሳንል እንዳናጋብስና መሸፈኛውን ገልጠን እንድናይ ነው፡፡
የጥንት ታዋቂ ፖለቲከኞች፤ “ፖለቲካ የኢኮኖሚው ጥርቅም መገለጫ ነው” ይላሉና እያንዳንዷን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ አጥርተን ካላየን፣ በፖለቲካ መልክ ብቅ ስትል ማህበራዊ ቀውስን ጭምር አመላካች ትሆናለች፡፡ ለህዝብ የምንገባውን ቃል ተጠንቅቀን ካልሆነ ያስተዛዝባል፡፡ አገርን በሰላም መምራት “እራሱን ያልገዛ፣ አገር አይገዛ” ከሚለው ብሂል ጋር በእጅጉ የተሳሰረ በመሆኑ የራስን ጥንካሬ በየጊዜው መመርመር የግድ ያስፈልጋል፡፡
“ቃል የእምነት ዕዳ” ነው ይላልና ገጣሚው ቃላችንን እንጠብቅ፡፡ የህግ የበላይነት ካልን ከሱ በላይ ምንም እንደሌለ እናረጋግጥ፡፡ በወገን አንሰራም ካልን ዘር፣ ሃይማኖት፣ አብሮ አደግ አናፈላልግ፡፡ የትግሪኛው ተረትና ምሳሌ ይሄንን በአፅንዖት ይገልፀዋል፡፡ እንዲህ ሲል፡-
“እወድሃለሁ እያለ የሚጠላ፣
እፆማለሁ እያለ የሚበላ፣
እሰጣለሁ እያለ የሚነሳ፣
እነዚህን አምላክ ይጠላ”፡፡
በአደባባይ ቃል መግባት በአደባባይ መጠየቅን ነው የሚያመለክት፡፡ በየሚዲያው ለውዳሴም ሆነ ለቅዳሴ ብለን የምንገባውን ቃልና ኋላም አፈፃፀም በጥንቃቄ እናስተውል፡፡

Read 6519 times