Saturday, 09 April 2016 09:58

“አባቴ፤ ብዙ መንገድ አለ በየቱ እንሂድ?” – “ባልተሄደበት እንሂድ” የህንዶች አባባል

Written by 
Rate this item
(20 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ አይጥና አንድ እንቁራሪት በቀጠሮ ይገናኛሉ፡፡
አይጥ፤
“እመት እንቁራሪት፤ አንዳንዴ ከውሃ ወጥተሽ መሬት ላይ ፀሐይ ስትሞቂ ሳይሽ ‘ምነው ከዚች ጋር ጓደኝነት ብንጀምር?’ እያልኩ ልቤ ስፍስፍ ይላል፡፡”
እንቁራሪትም፤
“ሆድ ለሆድ የመነጋገር ነገር ጠፍቶን ነው እንጂ እኔም እኮ ባየሁሽ ቁጥር ‘ምነው ጓደኛ በሆንን’ እያልኩ አስባለሁ፡፡”
አይጥ መልሳ፤
“አየሽ አንቺ ውሃም ውስጥ፣ መሬትም ላይ፣ ኗሪ ነሽ፡፡ እኔ ግን መሬት ላይ ብቻ ኗሪ ነኝ”
እንቁራሪት፤
“እንደሱ ብለሽ ራስሺን አታሳንሺ፡፡ ይልቁንም፤ ምንጊዜም እንዳንለያይ እንስማማ፡፡ እግራችንን በገመድ እንሠር” አለቻት፡፡
አይጥም፤
“እጅግ የብልህ ዘዴ አመጣሽ፡፡ በቃ ገመድ እኔ ከየትም ከየትም ብዬ አመጣለሁ” አለች፡፡
እንደተባለው እግሮቻቸውን አቆራኝተው በገመድ አስተሳሰሩ፡፡
መሬት ላይ ባሉ ጊዜ ሁሉ ወዳጅነታቸው ግሩም ድንቅ ሆኖ ቆየ፡፡ እንቁራሪት ወደ ውሃ ውስጥ ገብታ ዋና ስትጀምር ግን ጣጣ መጣ፡፡
አይጥ ወዴት እንደምትገባ መላው ጠፋት፡፡ አይጥ ከመስመጥ በቀር ምንም ምርጫ አልነበራትም፡፡ አይጥ ተንደፋድፋ ሰመጠች፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላም ሬሣዋ ውሃው ላይ ሲንሳፈፍ ታየ፡፡
ታሪኩ ግን በዚህ አላበቃም፡፡ አሞራ ከሰማይ የአይጥን ሬሣ ፍለጋ መጣ፡፡ አይጢቱን ላፍ አድርጐ ወደ አየር ሲምዝገዘግ፤ እግሯ አብሯት የታሠረውም እንቁራሪት ተንጠልጥላ ወደ ሰማይ ወጣች፡፡ “ከኑግ የተገኘህ ሰሊጥ አብረህ ተወቀጥ” ሆነ ነገሩ፡፡ ሁለቱም የአሞራ ራት ሆኑ!!
***
ጊዜን፣ ቦታን፣ ማንነትንና ተግባራዊ አንድነትን ያላገናዘበ መቀናጆ፤ መጨረሻው ክፉ ውድቀት ነው፡፡ ተያይዞ መንኮታኮት ነው፡፡ እንደ እንቁራሪት ውሃ ውስጥ፣ እንደ አይጥ መሬት ላይ የሚኖሩ፣ አንድ ዓይነት ነን ብሎ ማሰብ አጉል ህልም ነው፡፡ አስቀድሞ ነገር የወዳጅነቱ (የህብረቱ) ፋይዳ ምንድነው? ግቡስ ምን ነው? ምንስ ለመሥራት ነው? ሀገራዊ አንድነትን ስናስብ ሀገራዊ ፋይዳውን ማጤን፣ ለሁሉም ወገን ያለውን ፍሬ - ነገር ማሰላሰል፣ ተግባራዊ ሂደቱን መመርመርና ልብ ለልብ መነጋገር ቁልፍ ነገር ነው፡፡
የእንቁራሪትን የምድር - የውሃ ኑሮ በወጉ ማጥናት፤ አንዴ አይጥ አንዴ የሌሊት ወፍ ነኝ የምትለውንም አይጥ፤ ውስጧን ማመዛዘን እጅግ ወሳኝ መሆኑን አንዘንጋ፡፡ ከልዩ ልዩ መልካችንና ከልዩ ልዩ ይዞታችን ተነስተን ልንፈጥር የምንችለውን አገራዊ አንድነት ስናሰላው ልባዊ ግንኙነት ካላደረግን፤ ወይ “እባብ ለእባብ ይተያያል ካብ ለካብ”፣ “ወይ እርስ በእርሱ ሥጋን በኩበት ጠበሱ”፣ አሊያም “ድንጋይ በድንጋይ ላይ ቆሟል”፤ የከፋ መልክ ከያዘም ከታሪክ እንደምንማረው “ለምሣ ያሰቡንን ለቁርስ አረግናቸው” ዓይነት መበላለት ሊያስከትል የሚችል ሁኔታ ሊመጣ ይችላል፡፡ ከአድሮ ቃሪያ አካሄድ ይሰውረን፡፡
ከታሪካችን ካየናቸው ችግሮች አንዱ የሒስ ባህል አለመኖር ነው፡፡ ማንም ስህተቱን መቀበል ቀርቶ፣ ስህተት ከናካቴው አልታየም በሚባልበት አገር፣ ግትርነት መንሰራፋቱ አይታበሌ ነው፡፡ አማካሪ ምክርን ሂሳዊ ቢያደርግ ብዙ መንገድ መጓዝ ይቻላል፡፡ “ተባባሪ ዋይታ” ችግር አይፈታም፡፡ ይልቁንም እዬዬን ያገር ባህል ያደርጋል!
አልፎ ተርፎም፤ ብሶት እስኪጠራቀም፣ አድሮም እስኪገነፍል፣ ሲሸፋፍኑ መኖር እንደ ፖለቲካ ዘይቤ ይያዛል፡፡ እንዲህ ያለ ዘይቤ ሀገርን ያቆረቁዛል፡፡ ነጋ ጠባ ያንኑ ሐተታ ከማነብነብ አንዳንዴ “እህ?” ብሎ ማዳመጥ፣ ስለ አካሄዴ ምክራችሁን ለግሱኝ፣ ያልተዋጠላችሁን ጠይቁኝ ማለት ያባት ነው፡፡ አሁን ይህ ባህል የተጀመረ ይመስላል፡፡ ዋናው ዘላቂነቱ ነው!
ዛሬ በህይወት የሌሉት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ፤ በ97 ዓ.ም ምርጫ ማግስት በነበሩት ችግሮች ላይ ሒስ ሲያቀርቡ፤
“ዋናውና መሠረታዊ ችግር ንቀት ነው፡፡ ተጠቃዋሚዎች በምርጫው አዲስ አበባን ሲያሸንፉ ገዢውን ፓርቲ ናቁ፡፡ ገዢው ፓርቲ ገና ከመነሻው ተቃዋሚዎች በምንም ረገድ አያሸንፉም የሚል ንቀት አድሮበት ነበር” ብለው ተናግረዋል ይባላል፡፡
በሁለቱም ወገን የታየው ንቀት ከፊውዳላዊ ተዓብዮ የመነጨ ነው፡፡ የመደብ መሠረታችን ይብዛም ይነስ በእያንዳንዱ የህይወት ዱካችን ላይ አሻራውን ማሳረፉ አይቀሬ ነው፡፡ ንቀት ካለን ለትግል ያለን ዝግጁነት ለቋሳ ይሆናል፡፡ ንቀት ካለን ወደ ማንጐላጀት እንጂ ወደ ንቁነት አንራመድም፡፡ ንቀት ካለን ጊዜን በአግባቡ አንጠቀምም፡፡ ንቀት ካለን የአገሩ ቁንጮ እኛ ብቻ ነን የሚል ዕብሪት ይጫነናል፡፡ ምንም አይነት ሒስ አንቀበልም፡፡ የተሠሩትን ስህተቶች ጨርሶ እንዳልነበሩ ስለምንቆጥር፣ ጥፋቶችን ከማየት ይልቅ ሌሎች ላይ ማላከክን ሥራዬ ብለን እንይዘዋለን፡፡
ይህ በፈንታው ሁሉን ኮናኝ፣ ሁሉን ረጋሚ ያደርገናል፡፡ ይሄኔ እንግዲህ ጨዋታው ሁሉ “Do damned don’t damned” የሚሉት ይሆናል ፈረንጆቹ! ሠራህም ትረገማለህ፣ አልሠራህም ትረገማለህ፡፡ ይሄኔ አገር ከሩጫ ወደ መራመድ፣ ከመራመድ ወደ መዳከር፣ ከመዳከር ዝሎ ወደ መቆም ትመጣለች፡፡ ፍትሐችን ልፍስፍስ፣ ዲሞክራሲያችን ወንካራ፣ መልካም አስተዳደሩ “አልሞትኩም ብዬ አልዋሽም” የሚል፣ ልማቱ ህልም እልም፣ ለውጡ አገም - ጠቀም፣ የህዝብ ቁጥር ከአፍ እስከገደፉ፣ የሥራ አጡ መጠን አበስኩ ገበርኩ ወዘተ. ይሆንና ነገን መፍራት ግድ ይሆናል፡፡ ነገን የሚሠራ ሰው ጥርጣሬ ፎቅ ይሠራበታል! ከዚህ ይሰውረን!
ጥርጣሬ የልብ ለልብ መነጋገር ጠር ነው፡፡ የብሔራዊ መግባባት ሃሳብ እስከዛሬ ሲብላላ ኖረ እንጂ ከልብ አልተሞከረም፡፡ የህግ የበላይነትን አምኖ፣ የዲሞክራሲን መላ በአግባቡ ተረድቶ፣ የዜጐች እኩል ተጠቃሚነትን ተማምኖ፣ ባህላዊ የመግባቢያ መንገዶችን ፈትሾ በቁርጠኝነት ከታጓዙ፣ ብሔራዊ መግባባትና ዕርቅ ላይ መድረስ ይቻላል፡፡ እስከዛሬ አልተሞከረም፤ እንሞክረው፡፡ “አባቴ፤ ብዙ መንገድ አለ፡፡ በየቱ እንሂድ? ባልተሄደበት” አሉ የሚባለው ለዚህ ነው፡፡  

Read 6599 times