Monday, 04 April 2016 08:25

ፈራን…ፉክክር ፈራን….ውድድር ፈራን…ፈጠራ ፈራን!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(16 votes)

• የኪነ-ጥበብ ማህበራት በ“ቃና” ቴሌቪዥን ለምን ተሸበሩ?
• “የጋዜጠኞች ክብ ጠረጴዛ”---- ክብ አለመሆኑን ጠረጠርኩኝ!
• የመኢአድን ጉዳይ ከጠ/ሚኒስትሩ ውጭ ማንም አይፈታውም ተባለ!

    ብዕሬን ከወረቀት ለማዋደድ እየተጋሁ ሳለ፣ የወዳጄ የገጣሚ ነቢይ መኮንን አንድ ግጥሙ ትዝ አለኝ - “አንዳንድ ቀን አለ እሾህ የበዛበት---” እያለ የሚቀጥል ነው፡፡ እኔም በተራዬ ታዲያ “አንዳንድ ሳምንት አለ ---” ብዬ ለመቀኘት ሁሉ ዳድቶኝ ነበር። (ያለ መክሊቴ ብዬ ተውኩት እንጂ!) በሳምንቱ ውስጥ በተከታታይ የሰማኋቸው ነገሮች፣ የሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህንን ግጥም አስታወሰኝ - “ፈራን ---- ፍቅር ---- ፈራን ----- ህብረት ፈራን…” የሚለውን፡፡  (እኛ ነን ፍቅርን የምንፈራው ወይስ ፍቅር ነው እኛን የሚፈራን?) ብቻ እንደምንፈራራ እርግጥ ነው - እኛና ፍቅር!!
 የሳምንቱን ፖለቲካዊ ወጋችንን ጀምረናል። እኔ የምላችሁ ---- ኢትዮ ቴሌኮም ሰሞኑን መሸለሙን ሰማችሁ? በነገራችን ላይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮ ቴሌኮም የሚያገኛቸው  ሽልማቶች በዓይነትም በብዛትም እየጨመሩ ስለመጡ ቢደናገረን አይፈረድብንም፡፡ (በየጊዜው ሰርፕራይዝ እያደረገን እኮ ነው!) አንድ ጥያቄ ግን አለኝ --- ቴሌ የሚሸለመው ለእኛ በሰጠን አገልግሎት ነው ወይስ ለጐረቤት አገራት? አሁን ኢትዮ ቴሌኮም በአገር ውስጥ ይሸለም ቢባል በምን ዘርፍ እንደሚሸለም ታውቃላችሁ? ለኛ በሚልክልን የቴክስት ሜሴጅ ብዛት! (የደንበኞች የታጋሽነት ሽልማትም ቢኖር ሸጋ ነበር!)
እናላችሁ ከግራ ቀኝ ተፎካካሪ እየበዛበት የመጣው ኢቢሲ ባለፈው ቅዳሜ እንደዘገበው፤ ኢትዮ ቴሌኮም በእንግሊዝ ለንደን ከ60 በላይ አገራት በተሳተፉበት ውድድር በሁለት ዘርፎች ተሸላሚ ሆኗል፡፡ የመጀመሪያው ሽልማት ዓለም አቀፍ ግንኙነትን በማጠናከር፣ በዓለም አቀፍ መድረኮች ፍሬያማ ተሳትፎ በማድረግ፣ ማህበራዊ ፕሮጀክቶችን በማከናወን፣ ክፍለ አህጉርን በማስተዋወቅና ውጤታማ ዓለም አቀፋዊ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በማድረግ የተሻለ ሥራ ለሰራ የተሰጠ ነው ተብሏል፡፡ (ለዓለም አቀፍ አስተዋጽኦ እንጂ ለሎካል አይደለም!) ኢትዮ ቴሌኮም ያገኘው ሁለተኛው ሽልማት ስሙ ያስደምማል - “ዓለም አቀፍ የሶቅራጦስ ሽልማት” ይሰኛል፡፡ (ቴሌና ሶቅራጦስ ምን አገናኛቸው?) እንደ ኢቢሲ ዘገባ፣ ይኼኛው ደግሞ የተቋማት አመራሮች በተሰማሩባቸው የስራ ዘርፎች የማህበረሰቡ አዕምሮ እንዲጐለብትና ለ21ኛው ክፍለዘመን ብቁ እንዲሆን ላበረከቱት አስተዋጽኦ የሚሰጥ የዕውቅና ሽልማት ነው ተብሏል፡፡ (በኢትዮ ቴሌኮም አዕምሮዬ የጎለበተበትን ጊዜ ባስብ አልመጣ አለኝ!)
ምንም ቢዘገይ---ከዕለታት አንድ ቀን ደግሞ ለደንበኞቹ በሚሰጠው ጥራት ያለው አገልግሎት እንደሚሸለም ተስፋ እናድርግ፡፡ እስከዚያው ግን የሽልማቱ ዓይነት ባይገባንም “ኮንግራ” ብለነዋል - ኢትዮ ቴሌኮምን!! ድንገት አንድ ኦሪጂናል አይዲያ ብልጭ አለችልኝ፡- ኢትዮ ቴሌኮም፤ “ለሽልማት የሚያስመርጡ 10 ብልሃቶች” በሚል ርዕስ ለምን መጽሃፍ አያዘጋጅም? (ሌሎች የመንግስት መ/ቤቶችም የእሱን አርአያ ተከትለው እንዲሸለሙ እኮ ነው!)
 ወደ ሌላ ወቅታዊ አጀንዳ ደግሞ እንለፍ፡፡ ከሳምንቱ አስገራሚ ሁነቶች በዓይነቱ ለየት ያለብኝ አንጋፋው መኢአድ ፓርቲ ለጠ/ሚኒስትሩ አቀረበ የተባለው አቤቱታ ነው፡፡ የተለመደው ዓይነት አቤቱታ እኮ አይደለም፡፡ እንግዲህ ላለፉት ጥቂት ወራት ፓርቲው የውስጥ ሰላም አልነበረውም። (ሰማያዊ ፓርቲን አልረሳሁትም!) የውዝግቡን መንስኤ እንፈትሸው ብለን ከተነሳን በጦቢያችን ተስፋ ስለምንቆርጥ ገብስ ገብሱን ብቻ እናውራ፡፡ እናላችሁ ---- ሁለት ቡድን ተፈጥሯል አሉ - በመኢአድ ፓርቲ ውስጥ፡፡ በማህተም ጉዳይ ፍርድ ቤት ሁሉ ተካሰው ዳኛው በብልሃት ውሳኔ ሰጥተዋል። (ተቃዋሚዎች ሲጣሉ ሮጠው ማህተም ላይ ነው!)  እናላችሁ---ምርጫ ቦርድን የፓርቲው መሪ ማን እንደሆነ አረጋግጥልኝ አለ ፍ/ቤት፡፡ ቦርዱ አረጋገጠለት። በቃ አለቀ፡፡ ፍ/ቤት ማህተሙ በማን እጅ መግባት እንዳለበት ወሰነ፡፡ የተረታው ወገን ነው አሁን የመኢአድን ጉዳይ ከጠ/ሚኒስትሩ ውጭ ማንም አይፈታውም ብሎ የተፈጠመው፡፡ ቆይ ግን ጠ/ሚኒስትሩ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ማሸማገል ከጀመሩ አገሪቱን ማን ሊመራት ነው? ገዢው ፓርቲ-ያውም ኢህአዴግ ነፍሴ --- ለሥልጣን የሚፎካከረውን ተቃዋሚ ውስጣዊ ችግር ከመቼ ወዲህ ነው መፍታት የጀመረው?! አንዱ ተቃዋሚ ፓርቲ ሌላው ተቃዋሚ በእርስ በእርስ ውዝግብ ሲናጥ፣ ጣልቃ ገብቶ ቢያስማማ ወደ ጠ/ሚኒስትሩ መሄድ ባልመጣ ነበር። ችግራችን ግን ምንድን ነው ? ሎሬት ጸጋዬ መልስ አለው - “ፈራን --- ህብረት ፈራን… ፍቅር ፈራን… መግባባት ----- መደማመጥ------ ፈራን …!”
ወደ ሌላ አስገራሚ የሳምንቱ ሁነት ደግሞ ልውሰዳችሁ፡፡ ባለፈው ረቡዕ ነው፡፡ በሥራ ባልደረባዬ ጠቋሚነት የዛሚ ኤፍኤምን “የጋዜጠኞች ክብ ጠረጴዛ” ስኮመኩም ቆየሁና በመካያው የጠረጴዛውን “ክብነት” ተጠራጥሬ ቁጭ አልኩላችሁ፡፡ (አይቼው ስለማላውቅ አይፈረድብኝም!) በፕሮግራሙ ላይ ጋዜጠኛ ሚሚ ስብሃቱና ሌሎች ሁለት የ“ክብ ጠረጴዛው” ጋዜጠኞች ካነሷቸው ወቅታዊ ጉዳዮች፣ ትኩረቴን ይበልጥ የሳበውና ስሜቴን የኮረኮረው ሦስት አዳዲስ የግል ኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች፣ ፈቃድ ማግኘታቸውን በተመለከተ ያደረጉት ከ“ጠብ ጫሪነት” ያልተናነሰ ነቆራ ነበር፡፡ ፈቃድ ለተሰጣቸው የኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያ ባለቤቶች “ኮንግራ” ብሎ ስኬታማ የሥራ ዘመን መመኘትም ይቻል ነበር እኮ። (ግዴታ ነው አልወጣኝም!)
ምኞቱን ትተን ወደ እውነታው ስንመጣ፣የኤፍኤሞቹ መፈቀድ ገና ዜናነቱ እንኳን ሳያበቃ የክብ ጠረጴዛ ባልደረቦች፣ ለምን በነቀፋና በጥርጣሬ ሊቀበሏቸው እንደወደዱ ፈጽሞ አልገባኝም። በተለይ ደግሞ “One love” በተሰኘው የእነሠራዊት ፍቅሬ የሬዲዮ ጣቢያ ላይ እንደ ጉድ ነበር የወረዱበት፡፡ (የቆየ የግል ጠብ ይኖራቸው ይሆን?) እኔማ እነ ሠራዊት ከብሮድካስት ባለሥልጣን ገና ፈቃዳቸውን እንኳን ሳይወስዱ፣ምን ሰይጣን ገባባቸው ብዬ ክፉኛ አዝኜ ነበር፡፡ ገና “ከአራስ ቤት” ባልወጣ የሬዲዮ ጣቢያ ላይ ያ ሁሉ ውርጅብኝ አሁንም ድረስ ዓላማው  አልገባኝም፡፡ (ሳናውቀው---ሳንሰማው---ሳይጀምር----?!)
በተለይ ጋዜጠኛ መሰረት አታላይ፤የጣቢያውን ስያሜ ሁሉ አላስተረፈውም እኮ!! “One love” እንዴት ይባላል ---- ወረራው ከዚህ ይጀምራል --- በሚል አገር ይያዝልኝ ብሎ ነበር፡፡ እንዴት ካልጠፋ አገራዊ ስም (አማርኛ - ኦሮምኛ - ትግርኛ- ሶማሊኛ…) የእንግሊዝኛ ያወጣሉ ባይ ነው ጋዜጠኛው፡፡ (ሰሞኑን “የባህል ወረራ” የምትል ጨዋታ ተጀምራለች አሉ!) ግን እኮ እንኳንስ ገና ስራ ያልጀመረ የኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያ ቀርቶ፣ አብዛኞቹ የመንግስት መ/ቤቶችም በፈረንጅ አፍ እኮ ነው የሚጠሩት፡፡ (ትክክል ነው አልወጣኝም!)
እናላችሁ ----- ፈቃድ ካገኘ እንኳን ሳምንት ላልሞላው ጣቢያ፣ ያ ሁሉ ወቀሳና ነቀፋ ለእኔ “ያልተመጣጠነ ሃይል” እንደመጠቀም የሚቆጠር ነው። በነገራችን ላይ የጣቢያው ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ ሰራዊት ፍቅሬ ለአዲስ አድማስ እንደገለፀው፤ በስያሜው ላይ ገና የመጨረሻ ውሳኔ ላይ አልደረሱም። ጣቢያው ሥራ የሚጀምረውም ገና በመስከረም 2009  አዲስ ዓመት ላይ ነው። የአርጩሜው ጥድፊያ ግራ ያጋባል! (ፈራን ---- ፉክክር ፈራን---ውድድር ፈራን--ፈጠራ ፈራን ---- ያሰኛል!!)
በፕሮግራሙ ላይ ትችትና ነቀፋ ብቻ አልነበረም የተሰነዘረው፡፡ ቅሬታና ስሞታም ተስተጋብቷል።… አንዳንድ ኤፍ ኤሞች የዛሚን ፎርማት እንደሚኮርጁ፣(ዘረፋ በሚል የተገለጸ ይመስለኛል) ጣቢያዎቹ በአዲስ አበባ ብቻ መከማቸታቸው ተገቢ እንዳልሆነ (መልዕክቱ ለብሮድካስት ባለሥልጣን መሆን አለበት!) ኩረጃ ሲበዛ የሃሳብ ብዝሃነት እንደሚሳሳ ወዘተ ወዘተ ተዘርዝሯል፡፡ (ቃል በቃል ሳይሆን ሃሳቡን ነው ያሰፈርኩት!)
በእርግጥ አንዳንድ የጠቃቀሷቸውን ስጋቶች እኔም እጋራቸዋለሁ፡፡ (ቅዱስ ስጋቶች በመሆናቸው!) ኩረጃን በተመለከተ ጋዜጠኛ ሚሚ ስብሃቱ የጠቀሰችው ግን (እሱ ብቻ ከሆነ)  አፍ ሞልቶ “ፈጠራችንን ተሰረቅን” የሚያስብል አይመስለኝም (ከተሳሳትኩ እታረማለሁ!) “ዛሚ 24 ሰዓት” የሚለው “ብስራት 12 ሰዓት” ተብሎ ተኮርጆብናል ብላለች። (ሙሉ ስክሪፕት ተሰርቆ ፊልም በሚሰራበት ከተማ ላይ ነን!) በውይይቱ ላይ ከሰማኋቸው አስተያየቶች ወይም ትችቶች በእጅጉ ግራ ያጋባኝ ወይም ፈጽሞ ያልገባኝ የቱ መሰላችሁ? የጣቢያው ባለቤቶች የገንዘብ ምንጭን በተመለከተ የተነሳው ጥያቄ ነው። (በአሸባሪነት ስለሚጠረጠር የፖለቲካ ድርጅት የሚወራ እኮ ነው የሚመስለው!!) እናላችሁ---ሚሚና ጋዜጠኛ መሰረት አታላይ በተደጋጋሚ የገንዘብ ምንጫቸው መመርመር አለበት ሲሉ ነበር። እነማ? ምን? እንዴት? --ወሬው አምልጦኝ መሃል ላይ የደረስኩ ነበር የመሰለኝ። መሰለኝ እንጂ አንዳችም ያመለጠኝ ነገር የለም፡፡ በቃ መንግስት የገንዘብ ምንጫቸውን መመርመር አለበት ብለው ነው የተናገሩት፡፡  
እውነቱን ልንገራችሁ አይደል… መጀመሪያ ላይ የተረጋገጠ መረጃ ያላቸው መስሎኝ ነበር፡፡ ቆየት ብዬ ግን “ደንብ 5” በተሰኘው ድራማ ላይ እንዳለችው የኢንጂነር ባንጃው 6ኛ ሚስት (ውዴ)፤ “ጠርጥረው” መሆኑን ጠረጠርኩኝ፡፡ እንዴት አትሉም? ጋዜጠኛ መሰረት አታላይ “…በወሬ እንደምንሰማውም..” ብሎ ሲናገር ሰማሁት! ለነገሩ ከወሬ ያለፈ መረጃ ቢኖራቸውማ ለማን ያስቀምጡታል - ይነግሩን ነበር፡፡
ሌላው በዛሚ ውይይት የተነሳውና ሌሎች የኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች ላይ የተነጣጠረው ትችት፣ የሰለጠኑ ጋዜጠኞችን ያስኮበልላሉ የሚል ነው፡፡ እንደ አድማጭ፤ “ተመራጭና ተደማጭ” ከሆነ ጣቢያ እንዲህ ያለውን ውሃ የማያነሳ ቅሬታ ወይም ስሞታ ባንሰማ ይመረጥ ነበር (መብታችን ነው!) በዘመነ ካፒታሊዝም ሠራተኛ የተሻለ ክፍያ ወዳለበት እንደሚጐርፍ ሳይታለም የተፈታ ነው። ብቸኛው መፍትሔም ቅሬታና ክስ ሳይሆን ለሠራተኛ ጥሩ ደሞዝ መክፈል ብቻ ነው፡፡ (“ጋዜጠኛ ሃብታም ሆኖ አያውቅም” አያዋጣም!) እነ ጋዜጠኛ መሰረት አታላይ፤ ሌላው የዘነጉት ጉዳይ ምን መሰላችሁ? የመኮብለል ጉዳይ  የሠራተኛውም መብት ጭምር መሆኑን ነው፡፡ (ባይዘነጉት ኖሮማ እንደ አጀንዳ ባላነሱት ነበር!)
ውይይቱ ከመቋጨቱ በፊት የተነሳው የመጨረሻ አጀንዳ ግን ከእነመሰረት ጋር አስማምቶኛል፡፡  በማህበራዊ ድረገፆች የ “ቦይኮት” ዘመቻ የተጧጧፈበት የብርሃኔ ንጉሴ “ቤዛ” ፊልምን የተመለከተ ነበር፡፡ ጋዜጠኛ ሚሚ እንዳለችውም፤ነገሩን አስገራሚ የሚያደርገው የፌስቡክ አዝማቾቹ፣ፊልሙን አትመልከቱ (boycott አድርጉ!) የሚሉት ገና ይዘቱንና ምንነቱን ሳያውቁት ነው - በጭፍንነት! (የክብ ጠረጼዛ ጋዜጠኞችም፤ በአዲሶቹ የኤፍኤም ጣቢያዎች ላይ ያደረጉት ከዚህ የተለየ አይደለም!) የጣቢያዎቹን ይዘት ሳያውቁና ሳይሰሙ ነው የቅድሚያ ትችት የሰነዘሩት፡፡ (እንደ ኢንጂነር ሚስት “ጠርጥረው”!) ወደ “ቤዛ” ፊልም ልመልሳችሁ፡፡ ባይገርማችሁ----የፌስቡክ አዝማቾቹ፤“ባይኮት” አድርጉ የሚሉት ፊልሙን ብቻ ሳይሆን በፊልሙ ላይ መሪ ተዋናይ ሆና የሰራችውን (ተጋዳላይዋን) ሰላም ተስፋዬን ጭምር ነው፡፡ እንዴት ያለ ጉድ ነው!? “ቦይኮት በደሌ”---- “ቦይኮት ኮካ”----- “ቦይኮት ቤዛ”---- “ቦይኮት ሰላም ተስፋዬ” ----- የቦይኮት ዘመን ሆነ እኮ!! አንድ ቀን ተነስተው ደሞ ኑሮንም “ቦይኮት” አድርጉ እንዳይሉን!!
በነገራችን ላይ ጋዜጠኛ ሚሚ ስብሃቱ፤ በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ አዳዲሶቹ ኤፍ ኤሞች ከሌላ በመኮረጅ ሳይሆን የፈጠራ አቅማቸውን በመጠቀም፣ የራሳቸውን ፎርማትና ይዘት ፈጥረው ለአድማጩ አዲስ ነገር ይዘው እንደሚመጡ፣ የራሳቸውንም ጋዜጠኞች እንደሚያሰለጥኑ ተስፋ አድርጋለች። እኔ ደግሞ አዳዲሶቹ የኤፍኤም ጣቢያዎች መረጃ ሳይዙ እንደ ኢንጂነር 6ኛ ሚስት “ጠርጥሬ ነው” እያሉ እንደማያወሩልን ተስፋ አደርጋለሁ። ለነባሮቹም ለፍሬሾቹም የኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች ተወዳጅነትንና ስኬትን ተመኘሁላቸው!
ያሳለፍነው ሳምንት አስገራሚ ሁነት አላበቃም፡፡ ጉደኛ ሳምንት ነው ብያችሁ የለ!! እናላችሁ --በዚያችው በፈረደባት ረቡዕ ዕለት --- በአንድ ላይ አይተናቸው የማናውቃቸው የኪነጥበብ ማህበራት በብሄራዊ ቴአትር ተሰይመው ነበር፡፡ ምድር የሚያናውጥ ወይም መሬት አንቀጥቅጥ የፈጠራ ሥራ ሊያስተዋውቁን እንዳይመስላችሁ፡፡ ዓላማቸው አንድና አንድ ነበር። በቅርቡ የተለያዩ የውጭ አገራት ፊልሞችን በአማርኛ በማስተርጎም ለተመልካች ለማቅረብ ዱብ ዱብ እያለ የሚገኘውን “ቃና” የቴሌቪዥን ጣቢያ ከተቻለ ለማዘጋት፣ካልተቻለ ይዘቱን እንዲቀይር ጫና ለማሳደር ነው፡፡ እናላችሁ ---- ያለሙት እንዲሳካ ብቻ “ቃና” የተሰኘው የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ ያለጠፉት ሃጢያት የለም፡፡ ጣቢያው ጭራቅ ነው ለማለት ምን ቀራቸው? “የውጭ አገር ፊልሞች ንግድ ተኮር በመሆናቸው፣ ምንም ዓይነት ትምህርታዊና ሞራላዊ ይዘት ስለሌላቸው፣የባህል ወረራን በማስፋፋት ትውልድን ከማጥፋታቸው በፊት መንግስት ህጋዊ እርምጃን እንዲወስድ ጠይቀዋል” - ማህበራቱ፡፡
አያችሁልኝ ጭፍን ነቀፋ! አያችሁልኝ ጭፍን ማጠቃለያ! አያችሁልኝ ጭፍን ውንጀላ! አያችሁልኝ ወደ ክልከላና ህጋዊ እርምጃ ለመሄድ እንዴት እንደምንጣደፍ! እኔ የምለው--- የውጭ አገር ፊልሞች በሙሉ ትምህርታዊና ሞራላዊ ይዘት የላቸውም ያለው ማነው? ጥናት አድርገው ነው እዚህ ማጠቃለያ ላይ የደረሱት? “ቃና” ቲቪ ሊያስተላልፍ ካሰናዳቸው የውጭ ፊልሞች ምን ያህሉን ተመልከተዋቸዋል? ሌላም ጥያቄ አለኝ፡- ማህበራቱ ከዚህ ቀደም የባህል ወረራ አሳስቧቸው እንዲህ በጋራ መግለጫ ሰጥተው ያውቃሉ? (ትዝ ስለማይለኝ ነው!) ልጆቻችን እስከ ዛሬ በዲሽ የቱርክ ፊልሞችን (አረብኛ ቋንቋ መልመድ እስኪችሉ ድረስ) ሲኮመኩሙ ትውልድ እንዳይጠፋ” የሚል ስጋታቸውን ገልጸው ነበር? እንኳን በአገር ደረጃ በግል ልጆቹን ከእነዚህ ፊልሞች የገደበ ብዙም አናገኝም፡፡ እናሳ ---- ይሄ ሁሉ ጫጫታ ከምን የመጣ ነው? እውነት ለኢትዮጵያ ሲኒማ እድገት ተቆርቁረው ነው? እውነት ለተመልካቹ አስበው ነው? ወይስ ከውጭ ፊልሞች ጋር መፎካከር አንችልም ብለው ሰግተው ነው?  ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ተመልካቹም ያሻውን፣ የወደደውን፣ የመረጠውን---የመመልከት መብት እንዳለው መዘንጋት የለብንም፡፡
ዝም ብዬ ሳስበው ---- የኪነጥበብ ማህበራቱ በተለይ የፊልም ጉዳይ የሚመለከታቸው ይሄኔ እንዲህ ብለው ያዜሙ ይሆናል - ፈራን…ፉክክር ፈራን….ውድድር ፈራን…ፈጠራ---ፈራን!
በመጨረሻም ከባለቅኔው ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን ግጥም ጥቂት አንብበን እንሰናበት፡፡ ልብ ይስጠን!
ፈራን ፍቅር ፈራን
ልጅነት የለገሰንን
የፍቅር ዓምላክ በጥበቡ
በረቂቅ ያለበሰንን
በመለኮት የቀባንን
ህብረት ፈራን… ፍቅር ፈራን… (መግባባት መደማመጥ ፈራን …)

Read 5469 times