Print this page
Monday, 04 April 2016 08:02

እንዳንዘፍነው ዘፈንህ ሆነብን፤ እንዳንተወው ጣመን

Written by 
Rate this item
(24 votes)

ከኤዞፕ ተረቶች አንዱ እንዲህ ይላል፡-
ከዕለታት አንድ ቀን በአንድ ትልቅ በረት ውስጥ አንድ አውራ ዶሮና አህያ ይኖሩ ነበረ። አህያው ለአውራ ዶሮው፤
“ስማ አያ አውራዶሮ፤ መቼም እኔና አንተ የረዥም ጊዜ ወዳጆች ነን፡፡ ምንም ዓይነት ችግር ቢገጥመን እንዳንከዳዳ”
አውራ ዶሮም፤
“ይሄንን ነገር ማንሳትህ ራሱ በጣም አሳዝኖኛል፡፡ ስንት ዓመት ሙሉ ለጌታችን እየታዘዝን በአንድ ጣራ ስር ኖረናል፡፡ አንተም ሸክምህን ተሸክመህ፤ አንዴ በቀርበታ ውሃ ተሞልቶ ከወንዝ እዚህ ድረስ ስታመላልስ፣ አንዴ እህል ተጭነህ ወፍጮ ቤት ድረስ ስታመላልስ፣ አንዴ እንጨት ሲጭኑብህ ብዙ ስትንገላታ በዐይኔ በብረቱ አይቻለሁ፡፡ ስለዚህ ምንም ዓይነት ችግርና መከራ ቢደርስብህ ባለኝ አቅም ሁሉ እረዳሃለሁ፡፡ ሸክሙንም ቢሆን ቢቻለኝ አግዝህ ነበር” አለው፡፡
አህያም በጣም ተደሰተና፤
    “እንግዲያው ሆዴን ቀብትቶኛል፤ አንድ ጊዜ ላናፋ” አለው፡፡
አውራ ዶሮም፤
    “ማናፋት አውሬ ይጠራብናል፡፡ ጌታችንንም ያስቆጣል ይቅርብህ” አለው፡፡
አህያ ፤ “እባክህ አንዴ ብቻ” አለና ለመነው፡፡
ፈቀደለትና አንዴ ጮክ ብሎ “ሃ! ሃ! ሃ!” አለ፡፡ ከዚያ ተኙ፡፡
ጥቂት ቆይቶ አሁንም አህያ፤
    “ሆዴን ነፋኝ ቀበተተኝ፤ አንድ ጊዜ ላናፋ” ሲል ጠየቀው፡፡
አውራ ዶሮ፤
“ተው አያ አህያ፤ የቅድሙ የት እንዳለን ማሳያ፣ የአሁኑ ማቅረቢያ እንዳይሆን” ሲል አስጠነቀቀው።
አህያ፤
“ማንም የት እንዳለን ደኑ ውስጥ ሆኖ አያውቅም፡፡ ግዴለህም አንዴ ላናፋና ይውጣልኝ፡፡ በዚያ ላይ በረታችን የተከበረ በረት ነው፡፡ ማንም እዚህ ለመግባት አይደፍርም፡፡” አለና ማናፋቱን ቀጠለ፡፡
ለጥቂት ጊዜ እፎይ ብለው ተኙ፡፡ ሆኖም ከተወሰነ ሰዓት በኋላ አህያ፤
    “ስማ አያ አውራ ዶሮ፤ አንተ’ኮ በየሌሊቱ ትጮሃለህ ታድለሃል፤ እኔ ግን አይፈቀድልኝም”
አውራ ዶሮም፤
“የእኔ ጩኸት የዜማ ስልት ያለውና የሰው ልጆችን ለሥራ ስቀሰቅስ እንድኖር በተፈጥሮ የተሰጠኝ ግዴታ ነው፡፡ ያንተ ግን ስትጠግብና ሆድህ ከልኩ በላይ ሲሞላ ብቻ የምታናፋው ጩኸት ነው። ወዳጅንም ጠላትንም የሚጣራና የሚረብሽ ነው” አለና አስረዳው፡፡
አህያ ግን በጄ አላለም፡፡ አንዴ ለሶስተኛ ጊዜ “ሃ! ሃ! ሃ!” ሲል አናፋ፡፡
አውራ ዶሮም፤
“የመጀመሪያው መጥሪያ፣ ሁለተኛው ማቅረቢያ፣ ይሄ ሦስተኛው መበያ ይሆናል ብዬ እሰጋለሁ” አለው፡፡
አውራ ዶሮ ተናግሮ ሳይጨርስ አንበሳ መጣ፡፡ አህያ የሚገባበት ቦታ ጠፋው፡፡
አውራ ዶሮው ብልህ ነውና ዘሎ ቆጡ ላይ ወጣና ክንፎቹን ደፍደፍደፍ አርጎ መትቶ አንዴ ኩኩሉ ብሎ ጮኸ፡፡ አንበሳ በዓለም ላይ የሚፈራው ነገር ቢኖር የአውራ ዶሮ ጩኸት ነው፡፡ ስለዚህ እግሬ አውጪኝ አለ፡፡ ወጥቶ ወደ ዱሩ መንገድ ቀጠለ፡፡
ይሄንን ያየው አህያም “አንበሳ እንደዚህ ፈሪ ነው ለካ! ተከትዬ እደቁሰዋለሁ!” ብሎ ከበረት ወጥቶ እየሮጠ ሊይዘው ሞከረ፡፡ አንበሳ ግን ፊቱን አዙሮ አህያን በክርኑ ደቁሶ ደቁሶ ከጥቅም ውጪ አደረገው፡፡
                                                            *   *   *
አቅምን አለማወቅ ለውድቀት መዳረጉ አይቀሬ ነው፡፡ የጥጋብና የቁንጣን ጩኸት የማታ ማታ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ምክር የማይሰማ፣ እያደር የሚደነቁር ፍፃሜው የሮማ አወዳደቅ ነው፡፡ ችግር ሲኖር መጮህ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም ስልት ያለው ጩኸት መሆን አለበት፡፡ ደግሞ ጊዜውን መጠበቅ አለበት፡፡ “ጊዜ የስልጣን እጅ ነው” ይለናል ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን፡፡ በሀገራችን በርካታ ስህተቶች በየጊዜው ሲሰሩ እንመለከታለን፡፡ የሚሰራ ይሳሳታልና አስገራሚ ላይሆን ይችላል፡፡ “የመላዕክት ስብስብ አይደለንም” ብለዋል የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ (ነፍሳቸውን ይማረውና!) ዋናው ስህተትን ማረም ነው፡፡ ስህተት ካልታረመ ወደ ክፉ ጥፋት ያድጋል፡፡ ውሎ አድሮም ወደ ካንሰር ይለወጣል፡፡ ለብዙ ዓይነት ውድቀቶች መንስኤም ይሆናል፡፡
በዕውቀትና በመግባባት ላይ ያልቆመ ብልፅግናና ኃጢያት (ጥፋት) በዛበት አገር የችግር መናኸሪያ ነው፡፡ አንጋራ ፈላስፋ (የፈላስፎች አነጋገር) የሚባለው፣ ሊቀ መዘምራን ሞገስ እቁበ ጊዮርጊስ ከግዕዝ ወደ አማርኛ የተረጎሙት መጽሀፍ ይሄን ይለናል፡- “በሀገር ላይ ኃጢያት የተደረገ፣ ክፋት የተገለጠ እንደሆነ፣ ጥበብ ከሀገር ወጥታ ትሸሻለች፡፡ ጥበብ ከሀገር ወጥታ የተለየችና የሸሸች እንደሆነ፣ ሕግ ትዋረዳለች፣ ትናቃለች፡፡ ሕግም የተዋረደችና የተናቀች እንደሆነ፣ የንጉሡ ግርማ (መታፈር፣ መፈራት) ይጠፋል፡፡ ልብሰ መንግሥቱ ይገፈፋል፡፡ ጠላቶቹ ይሰለጥኑበታል (ይደፍሩታል)”
በተደጋጋሚ ያየናቸውና ያነሳናቸው ችግሮች እየተዋለዱ ለያዥ ለገራዥ አልመች ያሉ ሆነዋል፡፡ የችግሩን ሥር አግኝቶ ሥር ነቀል እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደሞ ንፁህ እጅ ያስፈልጋል፡፡ ንፁሃን መክረው ለመጓዝ መተማመንና ፍቅር ሊኖራቸው ያሻል፡፡ “ፀብ ክርክር ካለበት ጮማ ፍሪዳ፤ ፍቅር ያለበት ጎመን ይሻላል” ይባላልና ባለ ጮማና ባለ ፎቆቹን በዓይነ - ቁራኛ እያዩ፣ ባለ ጎመኖቹን አቅፎ መጓዝ የአባት ነው፡፡ “የበላን አብላላው፣ የለበሰን በረደውን”ም አለመዘንጋት ደግ ነው፡፡
የመሬት ነገር አንገብጋቢ መሆኑ መቼም ተወርቶ አልቋል፡፡ ጥያቄው የተረፈ ቦታ አለ ወይ? የአዲሳባ ደር ዳሩ ተነክቷል፡፡ አንዳንዶች እንደሚሉት፤ የተበላ ዕቁብ ነው፡፡ “ዳሩ ሲነካ መካከሉ ዳር ይሆናል” የሚለው አባባል እዚህ ጋ ትርጉም ያገኛል፡፡ አስገራሚው ነገር በዳሩም በማህሉም መጠየቅ ያለባቸው አካላት፣ ቡድኖችና ግለሰቦች መኖራቸው ፀሐይ የሞቀው ጉዳይ መሆኑና ብዙ ማስጠንቀቂያ ቢሰጥም ብዝበዛው አለመስከኑና ዛሬም የመሬት መዋዋሉ እንደቀጠለ አለመነገሩ ነው፡፡ ተራው ያልደረሰው ሙስናው ደጃፍ ላይ ተሰልፏል፡፡ የሚነገርለት መረብ አለመበጣጠሱና ድለላው ይብስ መጧጧፉ የመንግስት ድክመት፣ የባለስልጣናት ረጅም እጅ አሁንም መዘርጋቱ የሁለት ቢላዋ (የሁለት ቤት) ሰራተኞች መበርከት፣ በጊዜ ያልተቆጡትና ያልቀጡት የቤት ልጅ መብዛት፣ “ከመጠምጠም መማር ይቅደም” የማይባሉ ባለጊዜዎች መኖር፣ “ባለቤቱን ካልናዉ አጥሩን አይነቀንቁ” የሚለው ተረት የማይመለከታቸው ባለሀብቶች ከቤት ደጅ መትረፍረፋቸው፣ ወዘተ ሊሆን ይችላል ሰበቡ፡፡ ይሄ ሁሉ በወገንተኝነት ሲጠረነፍ እንግዲህ መጠንጠኛ ምህዋሩ፤ ባለጊዜው፣ ባለሥልጣኑና ባለእጁ ያሉበት ጨዋታ በመሆኑ በዙሪያው ያሉ ሁሉ ጮክ ብለው ለመናገር እያቃታቸው፣ ጥቅሙም እንዳይቀር እያሳሳቸው ማጨብጨባቸውን መቀጠላቸው ነው፡፡ “እንዳንዘፍነው ዘፈንህ ሆነብን፤ እንዳንተወው ጣመን” ማለት ይሄ ነው!

Read 6309 times
Administrator

Latest from Administrator